ብልጽግና ፓርቲ በሰጠው ጠንካራና ቅቡልነት ያለው አመራር የአገረ መንግሥት ግንባታን የሚያፋጥኑ ሥራዎችን ማከናወን መቻሉን የብልጽግና ፓርቲ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ለሁለት ቀናት ሲያካሂድ የቆየውን ስብሰባ ማጠናቀቁን ተከትሎ የፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ አደም ፋራህ ነግረውናል ::
አዎ! ፓርቲው ባለፉት ጊዜያት በሠራቸው ሥራዎች እንደ አገር የተመዘገቡ ውጤቶች የሉም የሚባል ክህደት የለንም:: በፖለቲካዊ፣ በማኅበራዊ፣ በኢኮኖሚያውና ዲፕሎማሲያዊ ዘርፍ የተሠሩ ሥራዎችም ስኬታማ አይደሉም አይባልም:: ከእነዚህ ሥራዎቹ ጎን ለጎንም በየደረጃው ያሉ አመራሮቹን ብቃት እየፈተሸ በየጊዜው የሚያደርገው ለውጥም የሚናቅ አይደለም::
ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ባካሄደው መደበኛ ስብሰባ በፖለቲካ፣ በኢኮኖሚ፣ በማኅበራዊና በዲፕሎማሲያዊ ዘርፎች የተመዘገቡ ውጤቶችን ገምግሞ የቀጣይ አቅጣጫዎችን አስቀምጧል፤ በፖለቲካው ዘርፍ የጋራ መግባባት ያልተደረሰባቸው መሠረታዊ አገራዊ ጉዳዮችን በምክክር ኮሚሽኑ አማካኝነት በዴሞክራሲያዊ መንገድ ለመፍታት የተጀመረው ጥረት መልካም ስለመሆኑ ምንም ጥርጥር የለም::
ፓርቲው በኢትዮጵያ የዴሞክራሲ ሥርዓትን ለማስፈን በፖሊሲ የሚለዩትን የተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ሳይቀር በመንግሥት መዋቅር ውስጥ በማሳተፍ የትብብር መንፈስ እንዲፈጠር ማድረጉም የሥራ አስፈጻሚው ብቻም ሳይሆን በሁላችንም ዘንድ ቅቡልነት ያለውና የሚደነቅ አካሄድ ስለመሆኑ መመስከር ይቻላል:: በሌላ በኩልም የትጥቅ ትግል ሲያካሂዱ ከነበሩ አካላት ጋር ዘመናዊና ባሕላዊ የግጭት አፈታት ዘዴዎችን ያጣመረ ውይይት በማካሄድ አንጻራዊ ሰላም እንዲሰፍን ጥረት መደረጉ በሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴው ብቻም ሳይሆን እንደ ሕዝብ በአዎንታዊነቱ የምንቀበለው ነው::
ይህም ሆኖ ግን የሕግ የበላይነትንና ሕገ መንግሥታዊነትን የተረጋገጠባት፣ የተሟላ ሰላምና ጸጥታ የሰፈነባት ሀገር በማጽናት ሂደት ውስጥ ያለው ክፍተት አሁንም የመንግሥትን ከፍተኛ ትኩረት የሚሻ ነው። ዜጎች በየትኛውም የሀገሪቱ ክፍሎች ያለስጋት ተንቀሳቅሰው የሚሠሩበትንና የሚኖሩበትን ሕገመንግሥታዊ መብት በማስጠበቅ ሆነ፤ ሕዝብን በሕዝብ ላይ ለማነሳሳት በሚጥሩ ጽንፈኛ ግለሰቦችንና ቡድኖችን አደብ በማስያዝ በኩልም ሕዝቡ ከመንግሥት ብዙ ይጠብቃል ። መጠበቅ ብቻ ሳይሆን ከመንግሥት ጎን ቆሞ ለመታገልም ዝግጁነቱም ሰፊ ነው።
ፍትሐዊ ልማትን ከማረጋገጥ አንጻር አካታች ኢኮኖሚ እየተገነባ መሆኑን በውይይቱ እንደተመላከተ ምክትል መሪው ነግረውናል። በተለይም በስንዴ ምርታማነት የታየውን ውጤት በትልቅ ስኬት ይነሳል፤ በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ የኢንዱስትሪ ዘርፉን ችግር በመፍታት፣ ምርታማነትን ለማሳደግና የገበያ ትስስር በመፍጠር አበረታች ውጤቶች መገኘቱም እንደዛው፤ በገበታ ለሀገር እና ሌሎች ፕሮጀክቶች የቱሪዝም ዘርፉን ለማነቃቃት መቻሉን እንዲሁም ከሥራ ዕድል ፈጠራ አኳያ በዘጠኝ ወራት ውስጥ ለበርካታ ሚሊዮን ዜጎች ሥራ ዕድል መፈጠሩንም ሰምተናል፤ እኛም ተጠናክሮ ይቀጥል ባዮች ነን::
የፓርቲው ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ የዋጋ ንረትን ለማረጋጋት፣ ኮንትሮባንድን ለመከላከል፣ በአምራችና ሸማቹ መካከል እሴት የማይጨምሩ የገበያ ሰንሰለቶችን ለመቀነስ ጠንካራ ርምጃዎች እንዲወሰዱ አቅጣጫ ማስቀመጡን ነግሮናል:: ጥሩ ቢሆንም እስከ አሁን የተሄደበት መንገድና የተመዘገበው ውጤት የተጠበቀውን ያህል አይደለም። በማኅበራዊ መስክ፤ በትምህርት ጥራት፣ በፍትሕና እና በእኩል ተጠቃሚነትን ዙሪያ፣ በሥነ ምግባር የታነጸ ሀገር ወዳድ ትውልድ በመገንባት በኩል የሚታየውን ክፍተት ለማጥበብ መንግሥት ብዙ የቤት ሥራዎች ይጠብቁታል::
እንደ አንድ ኃላፊነት እንደሚሰማው ሀገር ወዳድ ዜጋ በብልጽግና ፓርቲ በፖለቲካዊ፣ በማኅበራዊ፣ በኢኮኖሚያዊና በዲፕሎማሲያዊ መስክ የጀመራቸውን የለውጥ ሥራዎች አጠናክሮ መቀጠል ይጠበቅበታል፤ ለሕዝብ ቃል ከገባቸው ጉዳዮች አንጻር ከሠራቸው ገና ሊሠራቸው የሚገቡ ብዙ የቤት ሥራዎች ይጠብቁታል።
ፓርቲው ቀጣይ ሥራዎቹን የበለጠ በስኬት ለመወጣት በአመራሩ ዙሪያ የሚታየውን ክፍተት ማረም ይጠበቅበታል፤ አመራሩን ማጥራት፣ ማጠናከርና መገንባት ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ ጉዳይ ነው። ይህን ማድረጉ ሕዝብን ይዞ ረጅም ርቀት ለመሄድ ያስችለዋል::
መንግሥት ይህንን ሲወጣ እኛ ዜጎቹ ደግሞ ከጎኑ ልንቆም ግድ እንደሚለን መገንዘቡም ትልቅነት ነው፤ በተለይም በበሬ ወለደ ወሬ ሳንወሰድ፤ ጥፋታችንን እንጂ ልማታችንን የማይወዱ የውስጥም የውጭም ጠላቶቻችን የሚያደርሱትን ጫና ጆሮም ግዜም ሳንሰጠው በተሠማራንበት መስክ ሁሉ ጠንክሮ በመሥራት ይኖርብናል ።
በለውጥ ሂደት ውስጥ የሚያጋጥሙንን ተግዳሮቶች ፤ተግዳሮቶቹ ሊፈጥሯቸው የሚችሏቸውን ጥያቄዎቻችንንም በሕግና በሕግ አግባብ በማቅረብ እስኪመለሱም ትዕግስትን በማድረግ አገራችንን ከብተና ሕዝቡንም ከተባባሰ የኢኮኖሚ የማኅበራዊ ችግር ልንታደገው፤ ሀገርን ወደ ከፍታ ልናሸጋግር ይገባል ።
ይህንን ሳናደርግ አንዳችን በአንዳችን እያመኻኘን የምናጠፋት ሰዓት ደቂቃ ሁሉ አገራችንን ዋጋ የሚያስከፍል ነውና በተቻለ መጠን የተረጋጋ የሰከነ የሰለጠነ ዜጋ በመሆን ኃላፊነታችንን እንወጣ:: መንግሥትም በምርጫ ቅስቀሳ ወቅት የተገባልንን ቃል ተሳቢ በማድረግ ከፍ ባለ ተጨማሪ ቁርጠኝነት ሊንቀሳቀስ ይገባል። አበቃሁ
በእምነት
አዲስ ዘመን ግንቦት 26/2015