ኢትዮጵያና ቻይና ግማሽ ምዕተ-ዓመትን የተሻገረ ትብብርና ወዳጅነት አላቸው፡፡ የሀገሮቹ ትብብርና ወዳጅነት መሬት ላይ ካለው እውነታ አኳያ ሲታይ ደግሞ ትብብርና ወዳጅነቱ ከተጠቀሰው ቁጥርም በላይ ገዝፎ ይታያል፡፡ ትብብርና ወዳጅነቱ ታሪካዊ ብቻ አይደለም፤ ሁሌም እየታደሰ እዚህ የደረሰ ወቅታዊና ትኩስም ነው፡፡ የሃገሮቹ የንግድ፣ የኢንቨስትመንት፣ የትምህርት፣ የዲፕሎማሲና የሌሎች ዘርፎች ግንኙነት የደረሰበት ከፍተኛ ደረጃ ይህንኑ ያመለክታል፡፡
ቻይና በአሁኑ ወቅት ዋንኛዋ የኢትዮጵያ የኢንቨስትመንትና የንግድ አጋር ሆናለች፡፡ በርካታ የቻይና ኢንቨስትመንቶች በኢትዮጵያ ይገኛሉ፡፡ የሀገሪቱ ግዙፍ የግንባታ ተቋራጮች በርካታ የኢትዮጵያ የመንገድ ፕሮጀክቶችን እንዲሁም የባቡርና የኢንዱስትሪ ፓርክ መሠረተ ልማተ ልማቶችን ገንብተዋል፡፡ የመንግሥትንና የግሉን ዘርፍ ግዙፍ ህንጻዎችንም ገንብተዋል፤ እየገነቡም ናቸው፡፡
በተመሳሳይም በርካታ የቻይና ኩባንያዎች በተለያዩ የኢንቨስትመንት መስኮችም ተሰማርተዋል፡፡ የኢንዱስትሪ ፓርኮችን ጭምር በመገንባት ለተለያዩ ኢንቨስትመንቶች መሠረተ ልማቶችን አኑረዋል፡፡ የኢንቨስትመንቶቹ ወደ ኢትዮጵያ መምጣት ለሥራ ዕድል ፈጠራ፣ ለውጭ ምንዛሪ ግኝት፣ ለቴክኖሎጂና እውቀት ሽግግር ከፍተኛ አስተዋፅዖ እያበረከተ ይገኛል፡፡
የቻይናውያኑ በኢትዮጵያ የመሠረተ ልማት ግንባታ በዚህ ልክ መገኘት ለቴክኖሎጂና እውቀት ሽግግር የሚኖረው ሚና ከፍተኛ ነው፡፡ ግንባታ የሚያካሂዱባቸው ቴክኖሎጂዎችና የሚጠቀሙት እውቀት ሀገሪቱ በቀጣይ ለምታደርጋቸው ሰፋፊ የመሠረተ ልማትና ከተማ ልማት ግንባታዎች እንዲሁም ለግንባታው ዘርፍ ተዋንያን ትልቅ ትምህርት ቤት በመሆን ሊያገለግሉ ይችላሉ፡፡
በንግድ በኩልም ሲታይ ቻይና ዋንኛ ከሚባሉት የኢትዮጵያ የንግድ አጋሮች አንዷ ናት፡፡ በርካታ ኢትዮጵያውያን ከቻይና የኮንትስትራክሽን ግብዓቶች፣ አልባሳት፣ የኤሌክትሮኒክስና የቴሌኮም ቁሳቁስና ሌሎች ሸቀጣሸቀጦችን ወደ ኢትዮጵያ በስፋት ያስገባሉ፤ ምንም እንኳ የንግድ ሚዛኑ ለቻይና በከፍተኛ ደረጃ ያደላ ቢሆንም፤ ቻይና እንደ ሰሊጥ ያሉት የኢትዮጵያ የግብርና ምርቶች መዳረሻ በመሆን የኢትዮጵያ የገበያ መዳረሻ ናት፡፡
ቻይና የተለያዩ ድጋፎችን በማድረግም ትታወቃለች፡፡ መንገዶችንና የመንገድ ማሳለጫዎችን እንዲሁም ሆስፒታል በራሷ ወጪ ገንብታ በማስረከብ የኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን ባለውለታ ናት፤ ውቡ የወዳጅነት ፓርክም የኢትዮ-ቻይና ወዳጅነት ማሳያ ነው፡፡ ለአዲስ አበባ ከተማ ተጨማሪ ውበት ያጎናጸፉት ለአፍሪካውያን በራሷ ወጪ የገነባቻቸው የአፍሪካ ኅብረትና የአፍሪካ በሽታ መቆጣጠሪያ ዋና መሥሪያ ቤቶች ሕንጻዎች ለአፍሪካውያን የተገነቡ ብቻ ሳይሆኑ ለኢትዮጵያውያን የተበረከቱ ውብ ስጦታዎች ናቸው፡፡
የቻይናና የኢትዮጵያ ግንኙነት ከሁለትዮሽም ከባለብዙ ግንኙነትም በላይ በጅጉ ይሻገራል፡፡ ቻይና የኢትዮጵያ የክፉ ቀን ወዳጅ ናት፡፡ ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ጫና ውስጥ በነበረችባቸው ባለፉት ዓመታት ኢትዮጵያን በተለያዩ መልኮች ከታደጉ ሀገሮች ቻይና ትልቁን ስፍራ ትይዛለች፡፡ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት ስለኢትዮጵያ ቆማ ተሟግታለች፤ ሃገር ብድርና እርዳታ እንዳታገኝ ጫና በተፈጠረባት ወቅት አለኝታም ነበረች፤ የኢትዮጵያ የግብርና ምርቶች ከኮታ ነጻ ወደ አሜሪካ ገበያ እንዲገቡ የሚፈቅደው የአጎአ ስምምነትን አሜሪካ ስታግድ ቻይና ለኢትዮጵያ የግብርና ምርቶች ሌላ ከቀረጥ ነፃ እድል የከፈተች ታላቅ ባለውለታ ናት፡፡
በሁለቱ ሀገሮች ትብብርና ወዳጅነት የታዩ ለውጦች በሀገሮቹ መንግሥታት መካከል በተፈጠረ የሁለትዮሽና ባለ ዘርፈ ብዙ ግንኙነት ተሠርተው የመጡ ናቸው፡፡ በቀጣይም ብዙ ለውጦች እንደሚኖሩ ከግንኙነቶቹና ትብብሮቹ ፍሬዎችና አዝመራዎች መረዳት ይቻላል፡፡
ሰሞኑን የኢፌዴሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን በቻይና ያደረጉት ጉብኝት ደግሞ ትብብርና ወዳጅነቱን ይበልጥ የሚያጸና ሆኖ ተገኝቷል፡፡ ጉብኝቱን የኢትዮጵያና ቻይናን ትብብርና ወዳጅነት ያጸና ብቻ ሳይሆን ወደ ላቀ ስኬታማ ደረጃ ያሸጋገረ ሲል የኢፌዴሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርም ገልጾታል፡፡ በአፍሪካ ቀንድና አለም አቀፍ ጉዳዮች ላይም ሀገሮቹ ትብብራቸውን ከሚያጠናክር መግባባት ላይ የደረሱበት መሆኑንም አስታውቋል፡፡
የሁለቱን ሀገሮች ታሪካዊ የሁለትዮሽና የባለብዙ ወገን ግንኙነት የበለጠ ማጠናከር፣ የኢትዮጵያ የኢንቨስትመንት አመንጪ የሆነችው ቻይና ባለሀብቶች መዋዕለ ነዋያቸውን የበለጠ በኢትዮጵያ እንዲያፈሱ ማድረግ እና 52 ዓመታትን ያስቆጠረውን የሁለቱን ሀገሮች ታሪካዊ ግንኙነት የሚመጥን ውክልና እንዲኖር ያስቻለ፣ የሁለቱን ሀገሮች ዘመናትን የተሻገረ፣ ዘርፈ ብዙ ግንኙት ወደ ላቀ ደረጃ ያሸጋገረ ጉብኝት ሲል ሚኒስቴሩ ጉብኝቱን ገልጾታል፡፡
በእርግጥም ጉብኝቱ ያመለከታቸው ስኬቶችም ከአምስት አሥርተ ዓመታት በላይ የተሻገረው የኢትዮጵያና ቻይና ዘርፈ ብዙ ትብብርና ወዳጅነት ይበልጥ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ማረጋገጫ ናቸው፡፡ መሬት ላይ ፍንትው ብለው የሚታዩት የሁለቱ ሀገሮች የትብብርና ወዳጅነት ግንኙነት ስኬታማ ፍሬዎች ለትብብርና ግንኙነቱ በእጅጉ እየጎለበተ መምጣት ጥሩ ሕያው ማሳያዎች መሆናቸው እንዳለ ሆኖ፣ ስኬታማ ጉብኝት መደረጉ ደግሞ ትብብርና ወዳጅነቱ የላቀ ደረጃ እንዲደርስ ሌላ ትልቅ አቅም በመሆን ያገለግላል፡፡
ከቻይና መንግሥትና ሕዝብ ጋር ትብብርና ግንኙነትን ወደ ላቀ ደረጃ ማሸጋገር የሚያስችል ተግባር በጉብኝቱ ማከናወን መቻል የቻይናን ኢንቨስትመንት፣ እውቅትና ቴክኖሎጂ፣ ገበያ እና ወዳጅነት በእጅጉ ለምትፈለገው ኢትዮጵያ በእርግጥም ትልቅ ስኬት ነው!
አዲስ ዘመን ግንቦት 26/2015