ሞቅ ካለው መናሃሪያ መሀል ማደጉ ልጅነቱን በወከባ እንዲያሳልፍ አድርጎታል። ለእሱ ግርግርና ጨኸት ብርቁ ሆኖ አያውቅም። ከመኪኖች መግባትና መውጣት ጋር የሰዎችን ማንነት ጭምር ጠንቅቆ ያውቃል። ኪሱ በሌብነት የሚዳሰሰው፣ ተዘረፍኩ ብሎ የሚጮኸው፣ በስራ የሚሮጥና የሚጋፋው ሁሉ ለወጣቱ ተክላይ በርሄ አዲስ አይደለም።
ቤተሰቦቹ በሀብት የከበሩ አልነበሩም። ለእሱ መልካም ሆኖ ማደግ ግን ከአቅማቸው በላይ ጥረዋል። ተክላይ ከዚህ ቤተሰብ መሀል መገኘቱ ልጅነቱ ሳይጎረብጠው እንዲያድግ አግዞታል። በዚህ ዕድሜው የጠየቀው ሳይጎድልበት፣ ያሻው ሁሉ ሲሟላለት ቆይቷል። ከፍ እያለ ሲሄድ ግን ራሱን ሊችል ግድ ሆነ። ወላጆቹን መርዳት ታናናሾቹን ማገዝ አለበት። ኃላፊነቱን ለመውሰድ ገና ልጅ ቢሆንም ጀብሎ እያዞሩ መሸጥ አልከበደውም።
በአቅሙ ሰርቶ የሚያገኘው የዕለት ገቢ የገንዘብን ጥቅም አሳወቀው። ይህን ሲያውቅ ለትምህርቱ ጊዜ መስጠትን ዘነጋ። ሁሌም እየጠየቀና እየተጠየቀ ከእጁ ያለውን ሲሸጥ ብርና ሳንቲም መቁጠርን ለመደ። እንዲህ መሆኑ የልቡን ፍላጎት ሞላው። ገንዘብ በመያዝ ራስ መቻልን አወቀ። ይህኔ ህይወት በየቀኑ እንደሚያዞረው ማስቲካና ከረሜላ ትጣፍጠው ያዘች።
አሁን ተክላይ በዕድሜው ጠንክሯል። የገንዘብ ማግኛ ፍንጩ፣ ሰርቶ የማግኘት ምንጩ ከየት እንደሚጀምር ገብቶታል። ሁሌም ካለበት አርቆ የሚወስደው ሀሳብ ደግሞ ወንዝ እያሻገረ ይመልሰዋል። የእሱ ምኞት ተወልዶ ባደገበት ከተማ እየኖሩ ማርጀት አይደለም። እንደሌሎች ሁሉ አዲስ አበባ ገብቶ የተሻለ ኑሮን መቀጠል ይሻል።
ተክላይ ያሰበው ተሳክቶለት ከመቀሌ አዲስ አበባ ደረሰ። እንዳሰበው ሆኖ ግን ህይወት በስኬት አልተቀበለችውም። ብዙዎቹ ሲሉት እንደሰማው መንገዱ አልጋ በአልጋ አልሆነም። ውሎውን ፒያሳ ዙሪያ ሲያደርግ የቀድሞ ስራውን አስታወሰ። እሱኑ ከመቀጠል ሌላ ምርጫ አልነበረውም። ውሎ ሲያድር በአዲስ አበባ ጎዳናዎች ላይ ጀብሎውን ማዞር ጀመረ። ለዕለት ጉርሱ የሚሆን አላጣም። ኑሮ ግን ከገመተው በላይ ከባድ ሆነበት። ለሆዱና ለማዳሪያው እጅ ሲያጥረው አይኖቹ ሌላ የስራ ምርጫን ማማተር ቀጠሉ።
መቀሌ ያደገው ስመ ሞክሼው ተክላይ ሀጎስ ደግሞ ትምህርት ይሉትን ጉዳይ ቢጠሩበት አይሻም። እሱም ቢሆን የልጅነት አስተዳደጉ ክፉ የሚባል አልነበረም። በወላጆቹ ትከሻ ተንቀባሮ የማደግ ዕድልን አግኝቷል። ከፍ ሲል ግን እንደ እኩዮቹ ትምህርት ቤት ውሎ መመለስን አልሞከረውም። ባልንጀሮቹ ቀለም ቆጥረው ሲገቡ እሱ ቤት ያፈራውን እየበላ ከወላጆቹ ጋር መዋል ልማዱ ሆነ።
በእሱ ዕድሜ የነበሩ በርካቶች ተምረው ለዩኒቨርስቲ ሲበቁ፣ ተክላይ ከመንደር ውሎ አልወጣም። የተማሩት ስራ ይዘው ባለ ደመወዝ ሲሆኑም ከነበረበት ህይወት ፈቀቅ ማለት አልቻለም። ልጅነቱን ጨርሶ ወጣትነት ላይ ሲደርስ ግን ገንዘብ መያዝ ፈለገ። ለዚህ ያለው ዕድል ደግሞ በጉልበቱ ሰርቶ ማግኘት ነበር። በጊዜው ለእሱ የሚሆን ውሎ በጫኝና አውራጅ ስራ ላይ መሰማራት ነበር።
በማህበር የተደራጀበት ስራ ለዓመታት የገቢ ምንጭ ሆነለት። ኪሱ ገንዘብ መያዝ ሲለምድም ለራሱና ለቤተሰቦቹ ፍላጎት ተረፈ። ገቢው ያሻውን ለመከወን ቢመቸውም እያደር ግን ስራው ይሰለቸው ጀመር። በየቀኑ ከደንበኞች ጋር መጨቃጨቅና መጣላቱ አዳጋች ሆነበት። የውሎውን ፈተና
ሲያስብ ልቡ ርቆ ይሸፍታል። ካለበት ስራ የበለጠ እንደሚያገኝ ሲገምትም በሀሳቡ አዲስ አበባ ደርሶ ይመለሳል። አንዳንዴ ደግሞ «ብር ብለህ ጥፋ» ከሚለው ስሜቱ ጋር ሲሟገት ውሎ ያድራል። መልሶ ደግሞ በውሳኔው ይለዝባል።
አንድ ቀን ግን ተክላይ ከአካባቢው ለመሄድ ቆርጦ ተነሳ። ከመቀሌ አላማጣ በሚወስደው መንገድ የረዳትነት ስራ ጀምሮም ርቆ መሄድን ተለማመደ። በዚህ ስራው አንድ ዓመት ያህል ሲቆይ የገንዘብን ጥቅም ይበልጥ አወቀ። ከሰዎች ሲግባባና ሲላምድም የአዲስ አበባን መንገድ አመላከቱት። ሁሌም ስለከተማዋ የሚሰማው ይማርከው ኖሮ መንገዱን ሊገፋበት ከራሱ መከረ።
አዲስ አበባን በአዲስ ዓመት የተዋወቃት ተክላይ የታክሲ ረዳትነቱን አልተወም። በከተማዋ ጥቂት እንደሰራ ወደ መቀሌ እየተመላለሰ ገቢውን አዳበረ። ጥቂት ቆይቶ ግን ይህም ስራ መልሶ ሰለቸው። ከቦታ ቦታ መመላለሱ የታከተው ወጣት ቆም ብሎ የሚያስብበት ጊዜ አገኘ። በስራ አጋጣሚዎቹ በርካታ እውነታዎችን ማወቅ ችሏል። ሰርቶ እንደማግኘት ሁሉ አጭበርብሮና ሰርቆ መኖር እንደሚቻልም ተረድቷል።
ተክላይ ይህን ማድረግ እየተቻለ መልፋት፣ መድከም ብቻውን እንደማያወጣ አዕምሮው ይነግረው ከጀመረ ሰንብቷል። በዚህ ሀሳብ ትክክለኛነትም መተማመን ጀምሯል። ውሎውን ቀይሮ ከሌሎች ጋር ሲዛመድ ደግሞ ይህን ዕምነቱን የሚያጠነክር አጋጣሚ በጁ ይገባለት ያዘ። አዳዲሶቹ ጓደኞቹ እንደዋዛ በኪሳቸው የሚሞሉትን ገንዘብ እያየ ሰላም ማደር አልቻለም። እሱም በእነሱ መንገድ ተጉዞ ኪሱን በገንዘብ ሊሞላው ይሻል።
ባልንጀሮቹ የስርቆት ልምዳቸውን ለማካፈል አልሸሸጉትም። ውሎውን ከእነሱ ካደረገ ወዲህ ኪሱን በገንዘብ ለመሙላት ህልሙ ሲል የሌሎችን ኪስ ለመዳሰስ ሞክሯል። በዚህ ድርጊቱ ግን እምብዛም አልቀጠለም። እጅ ከፍንጅ ተይዞ ወህኒ ወረደ። የወህኒ ቆይታው ግን ከሌሎቹ ሌሎች የሌብነት መንገዶችን እንዲያውቅና ራሱን እንዲያዘጋጅ ረዳው።
ከእስር ከተፈታ በኋላም ከበርካታ ዝርፊያዎች መሀል በመኖሪ ቤቶች የሚፈጸመው ድምጽ አልባ ስርቆት የተክላይን ልብ በእጅጉ ማረከ። ተክላይ ይህ ዘዴ በአግባቡ ከተሰራበት አትራፊ እንደሚያደርግ ተማምኗል። ይህ ስርቆት በዘመንኛ መኖሪያ ቤቶች በተለይም ሻተር መስኮት ባላቸው ህንጻዎች ላይ የሚያተኩር ነው። እንዲህ አይነቶቹ ቤቶችም ጭር ባሉ አዳዲስ ሰፈሮች መሀል ይገኛሉ።
ተክላይ ጥቂት ጊዚያትን በመስማት ብቻ ልምድ ከቀሰመ በኋላ ቀጥታ ወደ ተግባር ለመግባት አልከበደውም። ተንሸራታቾቹን መስኮቶች እየከፈተ ወደ ሰፊዎቹ ሳሎኖች ዘው ማለት ቀላል ሆነለት። ይህን ለማድረግ ምቹ የሚሆነው ደግሞ የለሊቱ ክፍለ ጊዜ ነው። በተለይ ለተክላይ ውድቅት ዘጠኝ ሰዓት ሁሌም እንዳመቸው ነው። በዚህ ሰዓት አብዛኞቹ በከባድ እንቅልፍ ይወድቃሉ። እንዲህ በሆነ ጊዜ ደግሞ የእሱ አይኖች ነቅተው ከዕንቅልፍ ይፋታሉ። እግሮቹ የግንብ አጥሩን ዘለው ከመሀል ግቢው ለማረፍ ይቁነጠነጣሉ።
ተክላይ ይህን የዝርፊያ ተግባር ከጀመረ ወዲህ ለድርጊቱ የሚበጀውን ባልንጀራ ለይቷል። ባልንጀራው ያገሩ ልጅና ስሙ ሞክሼው ነው። እንዲህ መሆኑ ደግሞ ይበልጥ እንዲመቸውና በሙሉ ልቡ እንዲያምነው አስችሎታል። በተለየ ቀረቤታ የስርቆት ሙያውን ሲያወርሰው ተማሪው ከእሱ ልምዱን ለመረከብ ፈጽሞ አልዘገየም። በአንድነት ወደ ተግባሩ ከገቡ በኋላም የሁለቱ ተክላይ እጆች በአንድ ለመጣመር ጊዜ አልወሰዱም። ይህ ቅልጥፍናው የማረከው አስተማሪ ሞክሼ ጓደኛውን
«ጆሊ ጁስ» እያለ ይጠራዋል።
አሁን ሞክሼዎቹ በስም ብቻ ሳይሆን በግብርም አንድ ሆነዋል። በአይን ተያይተው ይግባባሉ። በእኩል ተጣምረው ይጓዛሉ። ህልማቸው ሁሌም ቢሆን ተመሳሳይ ነው። ያሰቡትን ሲከውኑ ዕቅዳቸው ይሰምራል። ሀሳባቸው ይሳካል። ሁለቱም ለተሰማሩበት ተግባር አይቀልዱም። አንዳቸው በአጥር ግንቡ ዘለው ሲገቡ ሌላቸው አካባቢውን ይቃኛሉ። ወጪ ወራጁን በማየት ውስጥ ላለው ዘራፊ መረጃን ለማቀበል ከደጅ የቆመው አጋር ሁሌም እንደነቃ ነው።
ሁለቱ እንደ አንድ ሆነው በገቡበት ስፍራ ፍላት ቴሌቪዥኖች፣ የኤሌክትሮኒክስ ዕቃዎች፣ ኮምፒውተርና ላፕቶፖች፣ ከእነሱ እጅ አያመልጡም። አልባሳትና ሌሎች ንብረቶችንም ቢሆን ያለምንም ኳኳታ ይዘዋቸው ሲወጡ ጥላቸው አይታይም። አንዳንዴ ሰዎቹ እንደተኙ ከሳሎንና ከመኝታ ክፍሉ ዘልቀው ንብረቶችን ይዘርፋሉ። በዚህ መሀል ከዕንቅልፉ ነቅቶ የሚተናነቃቸው ቢኖር ርምጃቸው የከፋ ይሆናል።
አንድ ቀን ስመ ሞክሼዎቹ የለሊት ስራቸውን ለመከወን ቀን ቆርጠው ሰዓት ወሰኑ። ቀጠሯቸውን እውን ከማድረጋቸው አስቀድሞ ደግሞ በቤቱና በአካባቢው ላይ ጥናት ሲያደርጉ ቆይተዋል። ሁለቱም ለሊቱን ገስግሰው በቦታው ሲደርሱ የሚሆነውን ሁሉ ያውቃሉ። ወረዳ አስራ ሁለት ከሚገኘው አንድ ህንጻ ላይ ስራቸውን ለመጀመር የመረጡት ጊዜ ደግሞ የተለመደውን የለሊቱን ዘጠኝ ሰዓት ነው። ዛሬም እንደ ሁልግዜው የስራ ድርሻቸውን ለይተዋል። አንዳቸው አቀባይ ሌላቸውም ተቀባይ በመሆን ተከፋፍለዋል። ለዚሁ የውዴታ ግዴታ ደግሞ ከእስከዛሬው ልምዳቸው ብዙ ተምረዋል።
እነ ተክላይ ለሊቱን አንደኛ ፎቅ ከሚገኘው መኖሪያ ዘለው ሲገቡ ያየ የሰማቸው አልነበረም። በዚህ ስፍራ አስቀድመው ምን እንደሚገኝ አውቀዋል። የቤቱ ባለቤት ራቅ ወዳለ ስፍራ መሄዳቸውንም አረጋግጠዋል። እነሱ ሊጎበኙት ባሰቡት ክፍል ማንም እንደማያድር መረጃው አላቸው። ከውስጥ የገባው ቁጥር አንድ ተክላይ የግንቡን አጥር ለመዝለል እምብዛም አልተቸገረም። በግቢው ደርሶ የሳሎኑን ተንሸራታች መስታወት ለመክፈትም እጆቹ የሰሉ ሆነዋል።
ደጅ የሚጠብቀው ቁጥር ሁለት ተክላይ ዓይኖቹ ከወዲያ ወዲህ እየተመላለሱ የሰው ኮቴ ያዳምጣል። እሱ በዚህ ሰዓት ማንኛውንም ኮሽታ አያምንም። ልቡ በጠረጠረ ጊዜ ደግሞ ለባልንጀራው በእጅ ስልኩ ደውሎ ያስጠነቅቀዋል። አሁን ውስጥ ያለው ተክላይ ከውበት ሳሎኑ መሀል ያገኘውን ኮምፒውተር መፍታት ጀምሯል። በአቅራቢያው የሚታዩትን አልባሳትና ሌሎች ጠቃሚ ንብረቶች በአግባቡ ጠቅልሎም ለጉዞ አዘጋጅቷል።
ዝርፊያው እንደተጠናቀቀ ውጭ የቆመው ተክላይ ንብረቶቹን በጥንቃቄ ተረከበው። እምብዛም ሳይቆዩ አጠገባቸው ከተፍ ያለው ባለ ላዳ ጓዛቸውን ሸክፎ ወዳመላከቱት አቅጣጫ ተፈተለከ። በማግስቱ ዕቃዎቹን ጭነው ወደ ጎጃም በረንዳ አመሩ። በዚህ ስፍራ ሁሌም የሚያመጡትን እየተረከበ ለሌሎች የሚሸጥ ደንበኛ አላቸው። ዕቃዎቹን ተደራድሮ ሲገዛቸውም ነገ ምን ማምጣት እንዳለባቸው ጭምር ያሳውቃቸዋል።
እነተክላይ ተንሸራታች መስኮቶችን በቀላሉ እየከፈቱ ያሻቸውን ማድረግ ተመችቷቸዋል። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የሚገነቡ ቤቶች ምርጫ በእንዲህ አይነቶቹ መስኮቶች ላይ ማተኮሩም ሀሳባቸውን አሳክቶታል። እንዲህ እንደ አሁኑ ወቅቱ ብርድ ሲሆንና ለሊቱ በዝምታ ሲዋጥ ደግሞ ለእነሱ ከምንግዜውም በላይ ይመቻል። ዝናብና ዳመናበሆነ ጊዜም ያለምንም ከልካይ ያሻቸውን ለመፈጸም መንገዱ ነጻ ነው።
ሁለቱ ተክላዮች የዘረፉትን ንብረት ለደንበኛቸው ሸጠው የድርሻቸውን ከያዙ በኋላ ቀጣዩን ዕቅድ ለመፈጸም እየተወያዩ ነው። የዛሬውን የዝርፊያ አቅጣጫም ንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ልዩ ቦታው «ሁለት ሺህ» ከተባለ ስፍራ አድርገዋል። ስራውን ከመጀመራቸው በፊትም የተለመደው የቅድመ መረጃ ቅኝት በአግባቡ ተጠናቋል። ሞክሼዎቹ ባሰቡት ቀንና ሰዓት ከስፍራው ደርሰው የዝርፊያ ወንጀሉን ለመፈጸም ያገዳቸው የለም።
ዛሬም ቁጥር አንድ ተክላይ አጥሩን ዘሎ ከግቢው መሀል ደርሷል። ደጅ የቆመው ቁጥር ሁለት ተክላይ ደግሞ በተሸሸገበት ጥግ ሆኖ የለሊቱን ጭርታ በራሱ ዝምታ ይቆጣጠራል። ሁሌም ቢሆን ውስጥ የገባው ባልንጀራው የያዘውን ይዞ እስኪመለስ እፎይታ ይሉት አይሰማውም። አሁን ግን ሁለቱም የምሽቱን ጉዳያቸውን በድል አጠናቀዋል። ታክሲ ጠርተው የዘረፉትን ካስጫኑ በኋላም ማግስቱን ለተለመደው ደንበኛ ሸጠው የድርሻቸውን ወስደዋል።
ሁለቱ ተክላዮች ከቀናት በኋላ ለታላቅ ምክክር ዳግም ተገናኝተዋል። የአሁኑ የዝርፊያ አቅጣጫ ደግሞ ቦሌ ክፍለ ከተማ «ሰሚት የለስላሳ መጠጥ ፋብሪካ» አካባቢ ካለ መኖሪያ ቤት ላይ አነጣጥሯል። ቁጥር አንድ ተክላይ በስራው የሚደሰትበትን አጋሩን «ጆሊ ጁስ» እያለ ይጠራው ጀምሯል። ስራው ሁሉ ለእሱ ስኬት ታላቅ እርካታ ሆኖታል። ለዛሬ ግን ለጥንቃቄ ያህል በተለየ መልኩ እያስገነዘበው ነው። ይህ አይነቱ ማስጠንቀቂያ ደግሞ ሁሌም ከስራ በፊት ሊሆን የሚገባ ግዴታ ሆኗል።
ለሊት ዘጠኝ ሰዓት ላይ ሞክሼዎቹ ካቀዱት ሰፈር ሲደርሱ አካባቢው በጭርታ ተውጦ ነበር። አልፎ አልፎ ከሚሯሯጡ ውሾች በቀር በስፍራው የሚዘዋወር አልነበረም። በዚህ ሰዓት አብዛኛው ሰው ለከባድ ዕንቅልፍ እጅ ይሰጣል። እንዲህ መሆኑ የእነ ተክላይን ልብ ይበልጥ አጀግኗል። እንደተለመደው አንዱ ዘላይ ሌላው ተቀባይ ሆነው ስራቸውን ጀምረዋል።
ውስጥ የዘለቀው ቁጥር አንድ ተክላይ የአንደኛ ፎቁን ደረጃው እንዳለፈ በመስኮት ወደ ውስጥ አጮለቀ። በቤቱ ሳሎን አንድ ትልቅ የቴሌቪዢን ስክሪን በግልጽ ይታያል። ለእሱ ያየውን ፈጥኖ ከእጁ ለማድረግ ደግሞ መቼም ከባድ ሆኖ አያውቅም። ተንሸራታቹን መስኮት በቀላሉ ከፍቶ የቴሌቪዥኑን አካል ለመፍታት እጆቹ በተለየ ልምድና ችሎታ የተካኑ ናቸው።
ተክላይ በአይኑ የገቡ ንበረቶቹን በእጁ አስገብቶ ደጅ ለቆመው ጓደኛው አቀበለ። ወዲያው አካባቢውን ፈጥነው ለመልቀቅም ልማደኛው ባለ ታክሲ ፈጥኖ ደረሰላቸው። በማግስቱ የዘረፏቸውን ዕቃዎች ለአውቶቡስ ተራው ደንበኛቸው አስረክበው ገንዘባቸውን በእኩል ተከፋፈሉ።
የፖሊስ ምርመራ
አሁን ከየአቅጣጫው ለፖሊስ ጆሮ የሚደርሱ ጥቆማዎች ተበራክተዋል። በተለይም በርና መስኮቶች ሳይሰበሩ ንብረቶች የመሰረቃቸው እውነት ብዙዎችን ለስጋት እየዳረገ ነው። በተንሸራታች መስኮቶች በኩል ንብረቶቻችን ተዘረፉ የሚሉ ነዋሪዎች የፖሊስ ደጃፍን ማጨናነቃቸው ፖሊስ መረጃን እንዲያሰባስብ እያገዘው ነው። በተለይም የድርጊቱ ተመሳሳይ መሆን አቅጣጫውን በአንድ እንዲቃኝና በቂ መረጃዎችን እንዲያገኝ ምክንያት ሆነ።
የበርካታ ተበዳዮችን አቤቱታ የያዘው ፖሊስ የምርመራ አባላቱን አደራጅቶ «ደጋጋሚ» የሚባሉ ተጠርጣሪዎችን ለማግኘት እንቅስቃሴውን ቀጠለ።
የለሊት ዘጠኝ ሰዓት ዘራፊዎችን አድኖ ለመያዝም በሳጂን አለማየሁ ለገሰ የሚመራው ቡድን ስራውን በይፋ ጀመረ። ፖሊስ የሲቪል ክትትሎችን አሰማርቶ ባደረገው ጥንቃቄ የተሞላበት ጉዞ አውቶቡስ ተራ የሚገኘውን የሌቦች ተቀባይ በቀለ ደጉን አስሶ ደረሰበት።
በቀለ በፖሊሶች በተደረገለት ጥብቅ ምርመራ እስከዛሬ ሲፈጽመው የቆየውን ድርጊት አንድ በአንድ ዘርዝሮ አመነ። ሞክሼዎቹ ባልንጀሮች እየሰረቁ የሚያስረክቡትን ንብረቶች በመግዛት አትርፎ እንደሚሸጥና እነሱም ብሩን በጋራ እንደሚከፋፈሉ ተናገረ። ይህ መሆኑ ተጠርጣሪዎችን አድኖ ለመያዝ ለፖሊስ አመቺ ሆነለት።
የፖሊስ የምርመራ መዝገብ ቁጥር 496/07 በተበዳዮች፣ ከአይን እማኞችና ከበርካታ ምስክሮች የተደራጀውን መረጃ በየዕለቱ ይከትብ ያዘ። በማስረጃዎች የተጠናከረ ክስ ይመሰረት ዘንድም ተፈላጊዎችን ለመያዝ የአዳኝ ቡድን አደራጀ። ከሁለቱ ሞክሼዎች መሀል ተክላይ ሀጎስ በተመሳሳይ ወንጀል ማረሚያ ቤት ቢገኝም ሞክሼውን ተክላይ በርሄን ፖሊስ በቁጥጥር ስር አዋለው። ባልንጀራውን ከማረሚያ ቤት በትዕዛዝ አስወጥቶም ድርጊታቸውን ሁሉ መርተው እንዲያሳዩት አደረገ።
ውሳኔ
የሁለቱ ተጠርጣሪዎች የክስ መዝገብ በጥምረት እንዲታይ በተደረገው መሰረት ሞክሼዎቹ ባልንጀሮች በአንድ ተቆራኝተው ፍርድ ቤት ቀረቡ። ፖሊስ በበቂ የሰነድና የአይን እማኝነት፣ በአሻራ ምርመራና በተጠርጣሪዎች የዕምነት ክህደት ቃል የተደራጀውን መዝገብ ለአቃቤ ህግ አሳልፎ አስረከበ።
የፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ 6ኛ ወንጀል ችሎት በመዝገብ ቁጥር 495/07 እና 496/07 በጥምር የቀረበለትን የክስ መዝግብ መርምሮ ለውሳኔ አቀረበ። ፍርድቤቱ ሚያዝያ 19 ቀን 2007 ዓ.ም በዋለው ችሎት አንደኛ ተከሳሽ ተክላይ ሀጎስ በአስራ አራት ዓመት ጽኑ እስራት፣ እንዲሁም ባልንጀራው ተክላይ በርሄ በአስራ ሁለት ዓመት ጽኑ እስራት እንዲቀጡ ሲል ውሳኔውን አሳለፈ።
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሚያዝያ 26/2011
መልካም ስራ አፈወርቅ