እትብታቸው በጥንታዊቷ ሐረር ከተማ ትልቁ ገበያ እየተባለ በሚጠራው አካበቢ ነው የተቀበረው። ውልደታቸው ከሐረሪ ቢሆንም ቅሉ ያደጉትም ሆነ እስከ እርጃና ዘመናቸው የኖሩት በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ነው። 1ኛና 2ኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በወሰን ሰገድና ልዑል መኮንን ትምህርት ቤቶች የተከታተሉ ሲሆን 12ኛ ክፍል ሲደርሱም ከፍተኛ ውጤት ካላቸው ተማሪዎች ጋር ለመምህርነት በመታጨት ወደ አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ አቅንተዋል። የማስተርስ ዲግሪያቸውንም በኦክስፎርድ ዩኒቨርስቲ የተከታተሉ ሲሆን በአገሪቱ በሚገኙ በርካታ መካነ ቅርፆች ላይ ሰፋፊ ጥናቶች በማካሄድና በተባበሩት መንግሥታት የባህል የትምህርት የሳይንስ ድርጅት(ዩኒስኮ) መዝገብ ውስጥ በቅርስነት እንዲመዘገቡ መሪ ሚና ስለመጫወታቸው ይነሳል።
በተለይም የሐረር ከተማ በቅርስነት እንድትመዘገብ ከ30 ዓመታት በላይ ለፍተዋል፤ ከፍተኛ ዋጋም ከፍለዋል። በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በኢትዮጵያ ጥናትና ምርምር ተቋም በሚገኘው ሙዚየም በኃላፊነት ከ40 ዓመታት በላይ አገልግለዋል፤ በአሁኑ ወቅትም በአስተባባሪነት እየሰሩ ሲሆን በቅርቡ በተቋቋመው የእርቀ- የሰላም ኮሚሽን ውስጥም አባል ናቸው። የዛሬው የዘመን እንግዳችን እኚህ የታሪክና የስነ ቅርፅ አጥኚ ረዳት ፕሮፌሰር አህመድ ዘካሪያ ናቸው። ከእንግዳችን ጋር በታሪክ፥ በቅርሶችና በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ያደረግነውን ውይይት እንደሚከተለው አቅርበነዋል።
አዲስ ዘመን፡- የልጅነት ህይወትና የትምህርት ቤት ቆይታዎትን በማስታወስ ውይይታችንን ልንጀምር እንችላለን?
ረ/ፕሮፌሰር አህመድ፡– የተወለድኩት ሐረር ቢሆንም ያደኩት በአዲስ አበባ መርካቶ አካባቢ ነው። ይሁንና ትምህርት ቤት በሚዘጋበት ጊዜ ሐረርና ድሬዳዋ እሄድ ስለነበር ለምስራቆቹ ሐረርጌዎች የማወቅ እድሉን አግኝቻለው። ስለዚህ አስተዳደጌ በሶስት ከተሞች ላይ የተሞረከዘና የተለየዩ የአኗኗር ዘይቤን ቀስሜ እንዳድግ አድርጎኛል።
ትምህርቴንም እየተቀባበሉ ያስተማሩኝ ሶስቱ የሃይለስለሴ ቤተዘመድ ትምህርት ቤቶች የሚባሉት ደጃዝማች ሉልሰገድ፥ ልዑል መኮንን፥ ልዑል በዕደ ማርያምና አሁን የማገለግልበት የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በቀድሞ ስሙ በቀዳማዊ ሃይለስላሴ ዩኒቨርስቲ ነው።
ከፍተኛ ትምህርት ስጋባ ህግ የመማር ፍላጎት ቢኖረኝም 12ኛ ክፍል ስደርስ ጥሩ ውጤት የነበረን ተማሪዎች ተመርጠን በታሪክ መምህርነት እንድንሰለጥን በመደረጉና ወደ ህግ ትምህርት ክፍል መግባት ደግሞ 550 ብር መክፈል ይጠበቅ ስለነበር እኔን ያንን ብር መክፈል ባለመቻሌ ታሪክ ለማጥናት ተገድጃለሁ። የሚገርመው ወቅቱ አብዮት የፈነዳበትና አገሪቱም በጦርነት ውስጥ በመሆንዋ ምክንያት በአራት ዓመታት ሊያልቅ የሚገባውን ትምህርት በስምንት ዓመታት ነው የጨርስኩት።
አዲስ ዘመን፡- በጦርነት ምክንያት አቋርጠው ነው?
ረ/ፕሮፌሰር አህመድ፡- እውነት ነው፤ በጦርነቱ ምክንያት ሁለት ዓመት ዩኒቨርስቲው ተዘግቶ ነበር፤ ሁለቱን ዓመት ደግሞ በግዳጅ እንድንዘምት በመደረጉ አንድ ዲግሪ ለማግኘት ስምንት ዓመት ፈጅቶብኛል። ትምህርቴን እንደጨረስኩ በዚሁ ዩኒቨርስቲ ማስተማር ጀመርኩ። ይሁንና የማስተማሪያ ክፍሎቹ ሰፋፊ አዳራሾች በመሆናቸውና የኔም ድምፅ ለአዳራሹ ሙሉ ጎልቶ መሰማት የማይችል በመሆኑ እንዲሁም የመድረክ ፍራቻ ስለነበረብኝ ማስተማሩ ላይ ብዙ አልገፋሁበትም።
ስራውን አቋርጬ በአርኪዮሎጂ የማስተርስ ዲግሪ መማር ጀመርኩ ግን ይህንንም በመተው አሁን ድረስ በማገለግልበት ዩኒቨርስቲው ስር በሚገኘው የኢትዮጵያ ጥናትና ምርምር ተቋም ሄጄ ሙዚየም ስራ መሰራት ቀጠልኩ። እዛ እያለሁም በቤተመዘክር ጥናት ዘርፍ ላይ ማስተርሴን ሰራሁ።
በቤተ መዘክሩ ባለኝ ቆይታ ቁሶችን በማናገር ህይወት የመስጠት ስራ ላይ ተጠመድኩ፤ አገሪቱ ያሏትን ቅርሶች ፈልፍሎ የማወቅ ፍላጎቴን እየናረ መጥቶ ለዚህም ይረዳኝ ዘንድ ኦክስፎርድ ዩኒቨርስቲ በመሄድ ሁለተኛውን ማስተርሴን በአርኪሎጂ ዘርፍ አጥንቻለሁ። ለነገሩ ስለ ሐረር የማወቅ ጉጉት ስለነበረኝ የመጀመሪያ ዲግሪዬን ማሟያ የሰራሁት በሐረር መስጊዶች ላይ ነው። በጥናቴ ትንሿ ከተማ ሐረር ብዙ ታሪካዊ ቅርሶችንና ሀብቶችን የያዘች መሆንዋን ለማረጋገጥ ችያለሁ። በጣም የሚገርመው በስምንት ሄክታር ውስጥ 82 መስኪዶች ነው ያሉት። ይህም በአለም በርካታ መስኪዶች ያሉባት ከተማ ያደርጋታል።
በሐረር ከተማ ላይ ተጫማሪ የቁፋሮ ስራ ለማከናወን ብፈልግም በፋይናንስ የሚደግፈኝ በማጣቴ ፊቴን ወደ ሲራራ ንግድ ላይ አዞርኩ። ወቅቱ ግን ከሱማሊያ ጋር ጦርነት ውስጥ የነበርንበት ወቅት ስለነበር፤ ቃለ መጠይቅ የሚሰጡኝ ሰዎች በጦርነቱ ምክንያት ስለተረበሹ የእነሱን ይሁንታ ማግኘት አልቻልኩም። እሱንም ትቼ ወደ ቤተ መዘክር ውስጥ መጣሁ። ያው ተቀራራቢ መስክ በመሆኑ እሱን ሳጠና ከረምኩ። ማስተርሴን ኦክስፎርድ ዩኒቨርስቲ በሰራሁበት ወቅትም ስለጥንታዊ የሃረር ገንዘቦች ላይ ጥናት አድርጊያለሁ።
እንደሚታወቀው የአርኪዮሎጂ ምንጭ አንዱ ገንዘቦች ናቸው። ኢትዮጵያ እድለኛ በመሆንዋ ልክ እንደ አክሱም ሁሉ ሐረርም ከ16ኛ ክፍለ ዘመን በፊት የምትገበያየው ራሷ ባመረተችው ገንዘብ ነበር። እንዲህ እንዳሁኑ ከውጭ እያስመረትን ከማስመጣታችን በፊት ማለቴ ነው። እናም የኔ የጥናቴ ትኩረት ሀረሮች ያደርጉት የነበረውን የገንዘብ ልውውጥና ምርት ላይ ነበር።
በተጨማሪም የሐረርን ጥንታዊ ቆሻሻ አወጋገድ ስርዓት ላይ ጥናት አድርጊያለሁ። ሐረሮች እንደ አሁኑ ሃረር በቆሻሸ ሳትዋጥ በፊት ከሌላው ማህበረሰብ በተለየ መልኩ ቆሻሻ የሚያስወግዱት በአህያ እያስጫኑ ነበር። ይህ ባህላዊ ስርዓት ታዲያ ተፈጥሯዊ ውደቱን ጠብቆ እንዲሄድ በማድረግ ተጨማሪ ጥቅምም ያስገኝላቸው ነበር።
አዲስ ዘመን፡– በጥንታዊቷ ሐረር ቆሻሻ ለሌላ አገልግሎት ይውል የነበረው በምን መልኩ እንደነበር ሊያብራሩልኝ ይችላሉ?
ረ/ፕሮፌሰር አህመድ፡– ሐረሮች የሰዎች አይነም ድርና የከብቶችን እዳሪዎችን ከየቤቱ በመልቀም በአህያ እያስጫኑ ለገበሬዎች እርሻ ማዳበሪያነት ይጠቀሙበት ነበር። የሚያከማቹበትም ልዩ ስፈራ ነበራቸው። ያንን ቆሻሻ መልሰው አትክልትና ፍራፍሬ ያመርቱበት ነበር። ይሁንና ያንን ቆሻሻ ይሸከሙ የነበሩ አህዮች በሱማሊያ ጦርነት ጊዜ በማለቃቸውና ማዘጋጃ ቤቱም በምትካቸው ሌላ አህያ ባለማምጣቱ ዛሬ ሐረር ከብዙ 100 ዓመታት በላይ የዘለቀውን ጥንታዊ የቆሻሻ አወጋገድ ስርቷን በመተው በቆሻሻ ታጥራ ትገኛለች። ነዋሪዎቿም ለጤና እና ሌሎችም ችግሮች ተዳርገዋል። እኔም በዚህ ጉዳይ ላይ ጥናት በማድረግ ህዝቡ ላይ ግንዛቤ ለመፍጠር ጥረት አድርጊያለሁ። በነገራችን ላይ በሐረርም ሆነ በሌሎች መካነ ቅርሶች ላይ ሌሎች የጀመርኳቸው ጥናቶችም አሉኝ።
አዲስ ዘመን፡- እንደነገሩኝ በርካታ ስራዎችን ጀምረው አንዱ ሳይሳካ ሌላ አዲስ ሀሳብ በማመንጨት ሙከራዎትን ይቀጥላሉ። ይህ ፅናት ከምን የመነጨ ነው ይላሉ? ከበስተጀርባ ያለውን ሚስጥር ለአንባቢዎቼ ቢገልፁልኝ?
ረ/ፕሮፌሰር አህመድ፡- ይህንን ለመግለፅ ወደ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቴን ወደተከታተልኩበት ወደ ወሰንሰገድ ትምህርት ቤት መመለስ ግድ ይለኛል። በወቅቱ የነበሩት የትህርት ቤቱ ቤተመፃህፍት ቤት ኃላፊ ጋር እንቀራረብ ስለነበር በቤተመጽሐፍት ስራው ላይ እረዳው ነበር።
ግለሰቡ አካል ጉዳተኛም ስለነበር አብሬው በመዋል እደግፈው ነበር። ያም አጋጣሚ ስለቤተመጽሐፍት ትምህርት እንድቀስም አደረገኝ። ገና የአምስተኛ ክፍል ተማሪ እያለሁ ብዙ መጽሐፍትን አነብ ስለነበር ያለ እድሜዬ በርካታ እውቀቶችን ለመቅሰም ችያለሁ። ዛሬ ላይ ራሴ ሰርቼ ባልዘልቀውም መስራት ለሚችሉ ሰዎች አማክራለሁ፤ እውቀቴን አካፍላለሁ።
እስካሁንም ለበርካቶች መንገድ ማሳየት በመቻሌ ደስተኛ ነኝ። አሁንም አነባለሁ፤ በብዙ መድረኮች ላይ በመገኘት ሀሳብ አካፍላለው። ትልቁ ነገር የሰው ልጅ ማንበብ ከቻለ አድማሱ ይሰፋል፤ አድማሱ ከሰፋ አማራጭ ያያል። በእኔ እምነት እውቀት ማለት አማራጭ ነው። አማራጭ ካለሽ ችግርሽን በአማራጭ ትፈችዋለሽ ማለት ነው።
በዚያ ምክንያት ነው አንዱ ሲዘጋ ሌላው የሚከፈተው። ተዘግቶ የሚቀር ነገር ይኖራልም ብዬ አላስብም። በነገራችን ላይ እኔ ቁጭ ብዬ የጽሁፍ ሰው ነኝ ብዬ አልፎክርም። እንዳውም ካለኝ እውቀት ጋር ሳወዳድረው በጽሁፍ ያበረከትኩት ስራ በጣም ትንሽ ነው።
አዲስ ዘመን፡- አብዛኞቹ የጥናትና ምርምር ስራዎቾት ሐረር ላይ የመመርኮዛቸው ሚስጥር ሃረር መወለድዎ ይሆን? ወይስ በቅርሶቿ ተጠቃሚ አልሆነችም በሚል ቁጭት?
ረ/ፕሮፌሰር አህመድ፡– ሐረር የኢትዮጵያ ተምሳሌት ናት። ሚስጥሯም በጣም ጥልቅ ነው። በእኔ እምነት ስለ ሃረርም ሆነ ከሌሎች አካባቢዎች ያለን ግንዛቤ ከዜሮ በታች ነው። ይህንን ለማስታረቅ ብዙ መስራት አለብን ብዬ አምናለሁ። እስካሁን የሰራነው ስራ እዚህ ግባ የሚባል አይደለም። የቅርስ ባለቤት ነን እያሉ መፎከር አንድ ነገር ነው። ስለቅርሶቻችን አውቀን ማሳወቅና ለትውልድ ማስተላለፍ ላይ ግን ሌላ ነገር ነው። ስለዚህም ይህንን የታሪካችንን ክፍተት የምንለውጠው ወደ መሬት ስናወርደው ነው። ታሪክን ከመዘከር ብቻ ወጥተን ወደ እውቀት መቀየርና ጥቅም ላይ ማዋል ስንችል ነው ፉከራችንም የሚያመረው።
ኢትዮጵያ የሰው ልጅ መገኛ ናት ስንል ተረት አይደለም። አሁን ላይም ቢሆን ብዙ የሳይንስ ተጨባጭ ማስረጃዎች ኖሮን ነው። ኢትዮጵያ ከሚገባንም በላይ ናት። ሶስቱ የአብርሃም ሃይማኖቶች የሚባሉት ክርስትና፤ እስልምና እና የአይሁድ እምነትን ብንወስድ ኢትዮጵያን ከጥንት ነው የሚያውቋት። ከ30 በላይ በቅዱስ መጽሐፍት የተፃፈች አገር ኢትዮጵያ ናት።
ጥንታዊ መሰረት ያላትና የተቀደሰች አገር መሆንዋን ሶስቱም ሃይማኖቶች ይመሰክራሉ። በቅዱስ መፃሐፍትም ሆነ በሳይንስም የተመሰከረላት ቦታ ሆና ሳለ የሚገባትን ያህል አልተጠቀመችበትም። ያም ሆኖ በዩኒስኮ ዘጠኝ ቅርሶችን በማስመዝገብ በአፍሪካ አንደኛ ብትሆንም ስለነዚህ ቅርሶች ያለን ምርምርና ጥናት አሁንም ደካማ ነው። አለን እያልን መፎከራችን ብቻ በቅርሶቻችን ተገቢውን ጥቅም እንድናገኝ አላደረገንም።
እንዳልሽው ግን ሐረር በመወለዴ ስለሐረር የማወቅና ቅርሶቿን ፈልፍሎ የማውጣት ፅኑ ፍላጎት ስላለኝ ነው ሐረርን በዩኒስኮ እንድትመዘገብ በግሌ በርካታ ጥረት ሳደርግ ቆይቻለው። በፈረንጆቹ ከ1979 ጀምሮ ከዩኒስኩ ከመጡ ተመራማሪዎች ጋር በመሆኑን በሃረር ጉዳይ ላይ ጥናት አድርጊያለው።
ሐረርን በዩኒስኮ ለማስመዝገብ ከ30 ዓመት በላይ ፈጅቶብናል። ይህም ከሐረር ጋር ጥብቅ ቁርኝት እንዲኖረኝ አድርገዋል። ለአጥኚዎቹ ስለሐረር እውቀቴንም አካፍላቸው ነበር። ያንን የማደርገው ግን በነፃ ነው። በመስጠት ብዙ ገንዘብ የሚገኝ መሆኑን ባውቅም በነፃ በማገልገሌ ግን አልቆጭም። ደግሞ የእኔን እውቀት በሰጠው ቁጥር ብዙ እውቀት እያገኘሁ ነው የሄድኩት።
አሁንም ቢሆን ሐረር ሚስጥራዊ ከተማ ናት። የሰራኋቸው ስራዎች ጀመርኳቸው እንጂ አሁንም ብዙ የሚቀሩኝ አሉ። ከአርባ ዓመት ልፋት በኋላ በቅርቡ ባደረኩት የቁፋሮ ስራ ስለሐረር በቃልና በሰነድ የተመዘገበውን ታሪክ እውነታነት በተጨባጭ የሚያረጋግጡልኝ ፍንጭ እያገኘሁ ነው። ይህንን ወደ መስመር የማስገባቱ ስራ ስኬታማ እየሆነ ነው ያለው።
ይህ ቁፋሮ የሐረርን ቅድመ ታሪክ በ14ኛው ክፍለ ዘመን ላይ የነበረውን ወደ 10ኛው ክፍለ ዘመን እንደሆነ የሚያረጋግጥ ነው የሚሆነው። ዘንድሮም ባደረግነው ቁፋሮ አዳዲስ ግኝቶች ተገኝተዋል። ገና ቁፋሮ ስላልጨረስን ተጨማሪ ማስረጃዎች ይገኛሉ ብለን እንጠብቃለን። ስለዚህ እነዚህ ነገሮች የሚያስረዱን ኢትዮጵያ ለአለም ጥንታዊ እድገት፤ ቋንቋና ምንነትና መሰረት መሆንዋን ነው።
አዲስ ዘመን፡- ይህንን ለማለት ግን ሌሎች ካጠኑት ጥናት ጋር አይጋጭም? ለየትኞቹ የአለም ቋንቋዎች ምንጭ ስለመሆንዋ አብነት ይጥቀሱልን?
ረ/ፕሮፌሰር አህመድ፡– የአፍሮ ኤዤያቲክ ቋንቋም መሰረት መሆኖንዋን በጥናት ተረጋግጧል። ከስድስቱ የአፍሮ ኤዢያቲክ ስር ካሉት ስድስት ቋንቋዎች ውስጥ ሴሜቲክ፥ ኩሸቲክና ኦሚቴክ ዛሬም በሀገራችን አሉ። በእርግጥ የአፍሮ ኤዤያቲክ ቋንቋ የሆነው ሴሚቴክ መሰረቱ ኢትዮጵያ ናት ካልን ኃላፊነቱን ወስደን አላጠናንም። አላስተዋወቅንም። ይህም ባለቤቱ ያቀለለው አሞሌ እንደሚባለው ነገር ሆኖብናል። ይህንን ያጠኑት አለም አቀፍ ታሪካዊ ስነልሳን አጥኚዎች ናቸው።
አዲስ ዘመን፡- ግን እኮ የሴሜቲክ ቋንቋ ከደቡብ አረቢያ እንደመጣ ነው ብዙዎች የሚስማሙበት?
ረ/ፕሮፌሰር አህመድ፡- እነ አግኣዚያን መጡ የሚለው ነገር አያጣልንም። ምክንያቱም በኛ ጥናት መሰረት ከዚያ በፊት ከኢትዮጵያ ወደ አረቡ አለም የሄደ ትውልድ መኖሩና ከብዙ ሺህ ዓመት በኋላ ደግሞ የዛ ትውልድ የልጅ ልጆች ተመልሰው ወደ ኢትዮጵያ መምጣታቸውን ስለሚያረጋግጥልን ነው። ስለዚህ ኢትዮጵያ የሰው ልጆች መገኛ ብቻ ሳትሆን የበርካታ የአለም ቋንቋዎች መገኛም ጭምር ናት።
ምንጩ እኛ ነን። ይህንን እውነት ደግሞ ያረጋገጥነው እኛ አይደለንም። አለም አቀፍ ተመራማሪዎች እንጂ። በእርግጥ እውነት ስለመሆኑ መተንተን ያለብን ግን እኛ ነን። ፍሬውንና ገለባውንም መለየት ላይም አልሰራንም። ጥናቱን አስፍተን መቀጠላችን የኢትዮጵያውን ድርሻ ከፍ ያደርገዋል የሚል እምነት አለኝ።
ሌላው ኢትዮጵያን ለየት የሚደርጋት ጉዳት የብዝሃ ህይወት ሀብቷ ነው። በአለም ላይ እምቅ ብዝሃ ህይወት ሀብት ካሉ ስምንት አገራት መካከል አንዷ ናት። እነዚህ ሀብቶች መኖራቸው ደግሞ ተመራማሪዎች እንዲጠኑ ይገፋፋል። በእርግጥ አሁን አሁን ይህንን የብዝሃ ህይወት ሀብት የሚያናጉ ክስተቶች እየተባረከቱ መጥተዋል። ይሁንና በሞኝ እርሻ ሞፈር ይቆረጣል እንደሚባለው የኛን ንብረት እየወሰዱ የመከራከሪያ ጥብቅና የውጭ ምንዛሬ እያወጣን ነው።
ጤፋችንን ወሰዱ ዝም አልን። አሁንም ቡናችንን ለመውሰድ የሚሯሯጡ አሉ። አሁንም በእውቀት መከራከር ካልቻልን ዝርፊያው ይቀጥላል። ፈጣሪ የሰጠንን ፀጋ በጠራራ ፀሐይ ሲወሰድብን ለመከለካል የሚያስችል በቂ እውቀት የለንም። ስለሆነም ዩኒቨርስቲያችን የኢትዮጵያ ጥናትና ምርምር ተቋም በአገር በቀል እውቀቶች ላይ የማስተርስ ዲግሪ ለማሰልጠን አስቧል። የተማረ ኃይል ሲበራከት የመከራከር አቅማችን ይጎለብታል የሚል እምነት አለኝ። እነዚህ ስርዓቶች ሲዘረጉ ንብረቶቻችንን ማስጠበቅ እንችላለን።
እንደ አጠቃላይ በቅርስነት የተዘገቡትን ቅርሶች እንኳ በአግባቡ ብንጠቀምባቸው ከግብርና የተሻለ ገቢ ሊያስገኙልን ይችላሉ የሚል እምነት አለኝ። በሌሎች የአለም አገራት በየዓመቱ በሚሊዮች የሚቆጠሩ ጎብኝዎች ሲያስተናግዱ እኛ ግን በአፍሪካ ቀደሚ ብንሆንም ዘጠኙም ቅርሶቻችን ተደምረው አንድ ሚሊዮን ሰው አላመጡልንም። ይህም የሚያመለከተው ብዙ ስራ እንደሚቀረን ነው።
ለዚህ ደግሞ የመንግሥት አቅጣጫ ስርዓት የተበጀለት መልኩ ያለመቀረፁ ነው። ስለሆነም መንግሥት አሰራሩን መፈተሽ ይገባዋል። በተጨማሪም ህብረተሰቡ በባለቤትነት እንዲጠብቃቸው ህብረተሰቡን የማሳመን ስራ መሰራትም ይገባል። ምክንያቱም ህብረተሰቡ ሲጠቀም ነው አገር የምትለማው። እነዚህን ሀብቶቻችን ጥቅም ላይ ማዋል ከኢኮኖሚያዊ ፋይዳ ብቻ አይደለም ያለው። ዛሬ ላለንበት የፖለቲካ ችግር መድሃኒት ይሆናሉ የሚል እምነት አለኝ።
አዲስ ዘመን፡– በምን መልኩ ነው ቅርሶችን መጠበቅ ለፖለቲካ ችግሮች መፍትሄ ሊሆን የሚችለው?
ረ/ፕሮፌሰር፡– ቅዱስ መጽሐፍ እንደሚሉት የጥበብ መጀመሪያ ፈጣሪን መፍራት ነው። ፈጣሪን የሚፈራ ደግሞ ራሱን ያውቃል ይረዳል፤ ይህም ደግሞ ፈጣሪን የምንፈራ ከሆነ ተቻችሎ የመኖር ፀጋችንን በአግባቡ እንጠብቃለን። ለምሳሌ በቅርቡ ራስ ዳሽን ተቃጥሏል፤ ይህ ሀብት የኛ ብቻ አይደለም፤ የአለምም ጭምር እንጂ። ተራራው ሲቃጠል በውስጡ ኑራቸውን መሰረት ያደረጉ የአምላክ ፍጡራንን እናጣለን፤ ይህም ከሰው ብቻ ሳይሆን ከፈጣሪም ያጣላናል። ይህ ቅርስ በመቃጠሉ በህዝቡ ዘንድ ከፍተኛ ቅሬታን አስከትሏል፤የፖለቲካ ጥያቄም አስነስቷል። ስለሆነም ሀብትን የማስጠበቁ ስራ ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ ብቻ ሳይሆን ለፖለቲካ መረጋጋትም ወሳኝ ሚና አለው የምለው ለዚህ ነው።
ትልቁ የሀገራችን የፖለቲካ ችግር መነሻውና መድረሻውን አስተሳሰብ ጤናማ ያለመሆኑ ነው። በአሃዳዊ ስርዓቱ ውስጥ የነበረውን ለአንድ ወገን ያደላ የፖለቲካ አስተዳደር ትተን አሁን እንኳ ያለው ህገመንግሥት ብንመለከት ሲጀምር ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ባለቤት መሆናቸውን ይገልፃል። ዛሬ ላይ ረጋ ባለ መንፈስ ብናየውና ማነው ብሔር? ማነው ብሔረሰብ? ህዝብስ የቱ ነው? ብለሽ ብትጠይቂ መልስ አታገኚም። በዚህ ህገመንግሥት እንደሚመስለን ተርጎመን በማስቀመጣችን ነው ሁሉም መብት አለኝ ብሎ መብቱ እንዲከበርለት ጥያቄ እያቀረበ ያለው።
ደግሞም ሃይማኖት ቋንቋና ብሔር ተፈጥራዊ መብት ሆነው ሳለ የፖለቲካ አጀንዳ ሊሆን አይገባም ነበር። የፖለቲካ አጀንዳ ስናደርጋቸው ነው ልዩነት የተፈጠረው፤ ከባልሽ ባሌ ይበልጣል እንደሚባለው ሁሉ ማለት ነው። ይህንን ጨዋታ ልንተው ይገባናል የሚል እምነት አለኝ። ይልቁንም ሁላችንንም አንድ የሚያደርገንን ችግሮቻችንን ለመፍታት መጣር ነው የሚገባን። በእኔ እምነት የፖለቲካ አጀንዳ ሊሆን የሚገባው የማንነት ጉዳይ ሳይሆን ስለሀብት አጠቀቃማችን ጉዳይ ነው።
እኔ ሊያሳስበኝ የሚገባው ልጆቼና የልጅ ልጆቼ ስለመጡበት የዘር ግንድ አለማወቃቸው ሳይሆን በአገራቸው ውስጥ ሆነው መራባቸውና መጠማታቸው ነው። ስለዚህ ሁሉም ህዝብ ከዚህ አስተሳሰብ ሊወጣ ይገባል የሚል እምነት አለኝ። ሰዎች በሰብእናቸው እንጂ ሊታዩ የሚገባው በብሔራቸው አይደለም።
ስለዚህ ፖለቲካው መስራት ያለበት ለ100 ሚሊዮን ህዝብ ነው። ወደ ብሔር ካወረድነው ግን ትልቅና ትንሽ እያልን መከፋፈልን ልናመጣ ነው ማለት ነው። ይህም ደግሞ ጉልበተኛው ሁሉም የእኔ ነው ወደ ማለት ይገባል። በትልልቆቹ የብሔር ጫዋታ ትንንሾቹ ልጆች ይጨፈለቃሉ። በእኔ እምነት ፈጣሪ ለሁላችንም የሚበቃ ፀጋ ሰጥቶናል፤ ይህንን ሀብት እኩል ከተካፈልን ወደ ስራ ፊታችንን እናዞራለን ወደ ጠብም የምንሄድበት ምክንያት አይኖርም። ሌሎች የሚራኮቱበት ደሜ ወፍራም ነው፣ ቀጭን ነው በሚለው ጨዋታ ውስጥ ከቀጠልን ውጤቱ አሁን ካለው የከፋ ነው የሚሆነው።
በእኔ እምነት ብሔር ማለት መሬት ማለት ነው። ኢትዮጵያ ናት። ብሔረሰቦች ማለት ባህል ማለት ነው። ብዙ ባህሎች አሉን። ብሔረሰብ የምንለው የፖለቲካ አንድነት ስትፈጥሪ ቋንቋ ያለው በሙሉ ይነሱና ህገ መንግሥቱ ፈቅዶልኛልና ለእኔም ስልጣን ስጪኝ ይላል። 80 ቋንቋዎች አሉን።
እነዚህ በሙሉ ክልል ሊሆኑ ነው ማለት ነው። መሆናችን ባልከፋ ስራ ላይም ተመካክረን ብንሰራ ጥሩ ነው። ግን በእዛ አያቆምም። አንድ ቋንቋ የተባለ ደግሞ ቀበሌኛ ሆኖ ይመጣል። የማያቆምም ነው፣ ልክ እንደ አሜባ እየተቆራረጡ መብዛትን ያመጣል። ከእዚህ እንዴት እንውጣ የሚለው ባህላችንንና ታሪካችንን በስርዓቱ መገንዘብ ነው።
የኢትዮጵያ ህዝብ ዝንቅ ነው። እኔ የምገነዘበው የባህልና የታሪክ ሰው ስለሆንኩኝ ታሪክንና ባህልን በማጥናቴ ነው። በረሀብና ጦርነት ምክንያት እንሰደዳለን። መወለጃሽን ታውቂያለሽ እንጂ መሞቻሽን አታውቂም። ስለዚህ ስትሰደጂ ከማን ጋር እንደምትጋቢና እንደምትራቢ አታውቂም።
ዕውቀትና ትምህርት ፍለጋ የሚሄዱ አሉ። ግን ትምህርት ሲጨርሱ ጋብቻ መስርተው ወልደው ከብደው ይመለሳሉ። የኢትዮጵያን ውህደት ለማምጣት እነዚህን ነገሮች ማድነቅ፣ መመርመርና ማጥናት ያስፈልጋል። እነዚህ ትንንሽ የምንንቃቸው ነገሮች ለማጉላት ብንሞክር የአንድነት ገመዶቻችን በጣም እየጠነከሩ ይሄዳሉ። አይናችንን ከጨፈንን እና አንድ ነገር ብቻ እያየን ለመሄድ ብንሞክር ችግር ይመጣል።
እዚህ ግቢ አርባ ዓመት በላይ ያክል ቆይቻለሁ። ብዙ ተማሪ መጥቷል። በርካታ ሰራተኞችም ነበሩ። ከተለያዩ አካባቢዎች የመጡ የማይተዋወቁ ሰዎች ግቢው አገናኝቷቸው ተጋብተዋል። ገበያ ላይም ተመሳሳይ ትውወቅ ተፈጥሮ ጋብቻ የተፈጠረባቸው አጋጣሚዎች ብዙ ናቸው። እነዚህን ከተመለከትን በኋላ አሁን ካለው የፖለቲካ ጩኸት ጋር ስንመዝነው የሚገርም
ሆኖ እናገኘዋለን። ለምንድን ነው ዱላ የሚማዘዙት የሚል ጥያቄ ይነሳል። የተፈጥሮ ሀብት ከሆነ ፈጣሪ የሰጠን ስጦታ በቂ ነው። አንድ መቶ ሚሊዮን ሳይሆን ሁለት መቶ ሚሊዮን የሚቀልብ ውሀ፣ ለም አፈርና ጉልበት አለን። ግን ዛሬም ደሀ ነን፣ እንለምናለን። ለምን የሚለውን መመለስ አለብን ማለት ነው። የተሳሳትነው የት ቦታ ላይ መሆኑን መገንዘብ አለብን። የፖለቲካ ከሆነ ፖለቲካውን እናስተካክላለን።
ከግብርናው ጋር በተያየዘም አንብቤ የምመልስ ስለሆንኩኝ የኔ ግምት ገበሬው ዛሬም ነጻ አይደለም ባይ ነኝ። የኢትዮጵያ ህዝብ ከ80 በመቶ በላይ ገበሬ ነው። ይህ ገበሬ በመሬት ላራሹ ጊዜ በጊዜው ጥያቄ መሬቱን አገኘ። ምርቱን ግን አጣ። በእዚህ መንግሥት መሬት የመንግሥትም ነው፤ የግልም ነው የሚለው ለእኔ እንደ ግለሰብ አደናጋሪ ነው የሚሆንብኝ። ቁርጥ ያለ ነገር የለውም።
መሬቱ ሰፊ ነው። የግል መሬት አለ፣ የወል መሬት አለ፣ የመንግሥት መሬት አለ። ስለዚህ የግል መሬት ውስጥ ብዙ ገበሬ አለ። ለእዚህ ገበሬ መሬቱ ያንተ ነው፣ እንደ ሰውም ታስባለህ ብትይው ለልማት ዘብ ይቆምልሻል። አንቺ ብቻ የምታስቢለት ከሆነ፣ እኔ በምለው ብቻ የምትይው ከሆነ ግን ለውጥ ይመጣል ወይ ነው ጥያቄው።
ትልቁ ፈተናችን እዛ ላይ ነው። ምክንያቱም 80 በመቶ የተያዘው ጉልበት ለኢኮኖሚ ምንጭ ይሆናል ተብሎ የሚታሰበውና ወደ ኢንዱስትሪያላይዜሽን ይገባል የሚል ነው። ግን ገበሬውን ነጻ ካላደረግሽው በምን ጉልበት ወደ አግሮ ኢንዱስትሪ ይገባል። ምክንያቱም ነጻ አይደለም። ለእኔ ዙሪያ ገብ ቀለበት ውስጥ ነው ያለው። ነጻ አድርገነው እንደ ሰው ማሰብ ይችላል ስንለው ልንመካከር እንችላለን እርሱም ጋር ዕውቀት አለና።
ይህቺ ቦታ ተወልደሽ ያደግሽበት ከሆነ ታውቂዋለሽ። ግንዛቤ ቢኖረኝና ምንም አይነት የአለም ዕውቀት ባካብትም መጀመሪያ አንቺን ስለቦታው ምን ይመስላል ብለሽ ያንቺን ዕውቀት ካገኘሁ በኋላ በአለም ባካበትኩት ግንዛቤ ተነስቼ ልመክርሽ እችላለሁ፣ አቅጣጫ አሳይሻለሁ። መጀመሪያውኑ ገበሬውን ብናማክር ከገበሬው ብንማር ጥሩ ነው።
አዲስ ዘመን፡- ቅድም ወዳነሱት ነገር እንመለስና የአብሮነት፣ የመቻቻልና አብሮ የመኖር እሴታችን እየተሸረሸረ ነው ለሃገር ህልውና አስቸጋሪ የሚባል ደረጃ ላይም በመድረሱ እንደ ታሪክ ምሁርነቶ ምን ሊሰራ ይገባል ብለው ይመክራሉ?
ረ/ፕሮፌሰር አህመድ፡- የኢትዮጵያ ዝንቅነትና መሳሳባችን አሁንም አለ። ግን ይላላል። ሲላላ የሚፈጥረው ኢነርጂ ከፍተኛ ነው። ምክንያቱም 100 ሚሊዮን ከተበተነ የሚያመጣው አደጋ ከፍተኛ ነው። አሁን ትንንሽ ማስተንፈሻ አይነት ናቸው ምልክቶቹ። ግን አንድ ቀን እንደ እሳተ ገሞራ ሲንተከተክ የቆየው እውነታ ሲፈነዳ ብዙ ነገር ነው የምናበላሸው። ስለዚህ በጣም ያሳስበኛል።
ወደ ተፈጥሮው ቅድም ወዳነሳሁልሽ ልመለስና ወጣቱ ስራ ከሌለው ሀይማኖተኛ ሁን ብትይው እሺ አይልሽም። ምክንያቱም ሆዱ ውስጥ ምንም ከሌለ ሆዱ ይጮህበታል። የኢትዮጵያ ህዝብ ፈሪሃ እግዚአብሄር፣ ፈሪሃ ንጉስ በይው ያደረበት ህዝብ ነው። በወሎ ረሀብ አይቻለሁ። ረሀብ ምን ማለት እንደሆነና የደረቀ አጥንታቸው የወጣ ሰዎች አይቻለሁ። እናም ያም ሆኖ ዘርፎ አይበላም ነበር።
የኢትዮጵያ ህዝብ የተለየ ነው። በረሀብ በጸጋ የሚሞት ህዝብ ነበር። አሁን ከእዛ ዘልሎ ወደ አውሬነት ሊቀየር ይችላል የሚለው ነው የሚያስፈራራኝ። ለዚህም ነው መንግሥትም ሆነ ህዝቡ ሊረባረብ ይገባል የምለው። ትናንትና 30 ሚሊዮን ነበረ አሁን አንድ መቶ ሚሊዩን ነው። ይህንን ህዝብ ሊመጥን የሚችል ስራ ካልተሰራ ወደምንፈራውና ወደሚብሰው አዘቅት ውስጥ መግባታችን አይቀሬ ነው።
አዲስ ዘመን፡- የህዝብ ብዛት እና ስራ አጥነት ወደ ማይፈለግ አቅጣጫ አምርቶታል እያሉኝ ነው?
ረ/ፕሮፌሰር አህመድ፡- ትልቁና አንዱ ሀሳብ እርሱ ነው። ለእዚህ የፖለቲካ መዛባት ሲመጣ ደግሞ ችግሩን ያባብሰዋል። የፖለቲካ መዛባት ቅድም እንዳልኩሽ (power legitemacy) ችግር አለው። በኢኮኖሚ መዛባት ምክንያት ገበሬው ነጻ አይደለም። እኔ አሁን የእርቀ-ሰላም ኮሚሽን ውስጥ አለሁበት እነዚህ ካልተስተካከሉ አገር ሰላም ይሁን፣ ሰላም ይስፈን ብሎ መስበክ ጥሩ ነው። ግን በእዚህ ብቻ የሚቆም አይደለም። አሁን መፈታት ያለበት የፖለቲካ አቅጣጫ አለ።
ያሉት የፖለቲካ ፓርቲዎች ችግራቸውን የሚፈቱበት፣ ለልጆቻቸው ሲሉ ቁጭ ብለው የሚመካከሩበት ነገር መኖር አለበት። ያ ካልተፈታ የትም አይወስደንም። የኢኮኖሚውም ችግር የገበሬው ችግር ካልተፈታ የፖለቲካ ሰዎች ብቻ የሚፈቱት አይደለም። እነርሱ የተፈጥሮ አጠቃቀም ላይ ያላቸው አቅጣጫ ጥሩና የበሰለ ከሆነ ሊፈቱት ይችላሉ። የተፈጥሮ ጸጋ አይደለም ችግራችን አጠቃቀም ላይ እንጂ።
የአጠቃቀም ችግር ምንጮች የፖለቲካውና የኢኮኖሚው አያያዛችን ነው። እነዚህን ካስተካከልን በቂ የተፈጠሮ ሀብት አለ ማለት ነው። ወደ ሀረር እንመለስ። ከሉሲ ጋር ሀረር ሄጄ ነበር። በእዛ ጊዜ በተወሰነ መልክ ችግር የነበረበት ጊዜ ነበር። በአንድ አጋጣሚ በህይወት ለመትረፍ አጠራጣሪ የሆነ ሁኔታ አጋጥሞናል። በምን ምክንያት መሆኑን በማላውቀው ጉዳይ ጠመንጃ እየተኮሱ እኛ የነበርንበትን ሆቴል ያለፉበት ሁኔታ ገጥሞናል። ፖሊሶች ናቸው። ይሄ ያሳስባል።
ወጣቱ ቀምቶ እንዲበላ ሁኔታዎች ካመቻቸሽለት መመለሻ የሌለው ችግር ውስጥ እንገባለን። ወጣቱን ወደ ስራ ማሰማራት ካልቻልን የተፈጥሮ ሂደትን እናዛባለን። ለመብት ያነሳው ጥያቄ ወደ ሽፍትነት ከሄደ አደገኛ ይሆናል። ከመቶ 70 ወጣት ነው። አሁን ለስራ የበቃ ወደ 30 ሚሊዮን ህዝብ አለ።
ቀሪው ስራ የሌለው 30 እና 40 ዓመት የሞላው ሰርቶ ሳይሆን ከእናት ካአባቱ ሀብት ተካፍሎ የሚኖር ነው። ይህ የሚስተካከል ከሆነ ኢትዮጵያ በኢኮኖሚ ተመንድጋ እንደ ቻይና መሆን አያቅታትም ማለት ነው። የማይሰራ እጅ አለ። እንዳይሰራ ያደረገው ደግሞ ስርዓቱ ነው። ይህንን ስርዓት እንደገና ፈትሸን እንዴት ይሰራል የሚለው የሁላችንም ፈተና ነው። እኔ በሰላም ጥያቄ
እባካችሁ ሰላም ሁኑ፣ ፈጣሪን ፍሩ አትጋደሉ እላለሁ። በኢኮኖሚውም ገበሬውን እንዴት እንደ ሰው ማድረግ አለብን ብለን ማሰብ አለብን።
ዛሬም 10 እና 20 ሚሊዮን የተቸገረና ቀለብ የሚሰፈርለት ህዝብ አለን። ምክንያቱ መመለስ አለበት። መንግሥት መመለስ ይኖርበታል። ወጣቶችን እንዴት ማብቃት እንዳለበትና እንዴት መመራት እንደሚገባው አቅጣጫ የሚሰጠው መንግሥት ነው። አቅጣጫ ሲሰጥም ለህዝብ በሚሆን መንገድ ነው። አሁን ባለው ሁኔታ ለህዝብ በሚሆን መንገድ አልሆነም።
የፌዴራል አወቃቀሩ በደንብ ስራ ላይ ቢውል ኖሮ የባሰ ችግሮች እንደሚያመጣ መገመት አያስቸግርም። ምክንያቱም የስልጣን ጥያቄ ስለሚያመጣ። የስልጣን ባለቤቱ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦች ናቸው። ጥናትና ምርምር ሲሰራ አንድ አካባቢ ላይ እናንተ ከእዛኛው አካባቢ ትንሽ ለየት ትላላችሁ ስትያቸው መብት ነውና ይጠይቃሉ። ስለዚህ ከውስጥ ችግር አለ ማለት ነው።
አዲስ ዘመን፡-ፌዴራሊዝም ችግር አይደለም አተገባበሩ ነው በሚል የሚያነሱ አሉ። እርሶም ባግባቡ ቢተገበር ስጋት አለ፣ መብት ጠያቂ ይበዛል እያሉኝ ነው። ስለዚህ መፍትሄው ምንድን ነው?
ረ/ፕሮፌሰር አህመድ፡– መፍትሄው መወያየትና እንደገና ማየት ነው። ማኦ የቻይናን ህዝብ አሳድጓል። ያሳደገው የቻይናን ህዝብ ሰብዕና ጠብቆ የራሱን ፍልስፍና ይዞ ነው ህዝቡን ያሳደገው ። የስታሊንን ወይንም የሌላ ሰው ፍልስፍና ይዞ አይደለም ቻይናን ያሳደገው። አገራቸውን ያሳደገው ማኦይዝም ፍልስፍና ነው። እኛም ኢትዮጵያዊ የሆነ ፈላስፋ ያስፈልገናል። አቅጣጫ የሚያሳይ። ከእነርሱ ልምድ አንማርም ማለት አይደለም። ከውጭ የሚቀዳው የራሱ ጉዳት አለው።
ቅድም እንዳነሳነው የራሳቸው መሬት ነው ያንን ያበቀለው። የፈረንጆቹ ሂደት በራሳቸው አፈር ያደጉበት ነው። እድገታቸው በራሳቸው ተሞክሮ ላይ ተመስርቶ ነው። ማኦም በህዝቡ ሁኔታ ላይ ተመስርቶ ነው ዛሬ ቻይናን ለአለም ቁንጮነት እንድትበቃ ያደረገው። እኛም እንደርሱ አይነት ሰው ያስፈልገናል። እንጂ የስታሊን መንገድ ልክ ነው ብለን የምንገታገት ከሆነ ብዙ ጉዳት ያመጣል። እያመጣም ነው አይደል? መፍትሄ ቢሆን ምንም ችግር የለም። መፍትሄ ስላልሆነ ነው መፍትሄ እንፈልግ የምንለው።
መፍትሄ ለመፈለግ ቁጭ ብሎ የኢትዮጵያ እሴቶች የሁሉም ምንድን ናቸው ብሎ መወያየት ያስፈልጋል። ስልጣንን የምናማክለው በምን አይነት መንገድ የሚለው ጥያቄ መመለስ አለበት። ዴሞክራሲ ይባላል ዴሞክራሲም የራሱ ሂደት አለው። ወደ እዛ ሂደት የሚገባበት መንገድ ማሰብ ይገባል። ስለተባለ ብቻ አይሆንም። ወጣቱም አምኖ በስራ የሚጠመድ ከሆነ የፖለቲካ ችግራችን በሂደት ይቀረፋል። የፖለቲካ ችግር በአንድ ወገን ስራ አጥነት በሌላ ወገን የሚቀጥል ከሆነ የሚቀጣጠል እሳት ነው ማለት ነው።
አዲስ ዘመን፡– በተለያዩ አካባቢዎች ያሉ የወሰንና የማንነት ችግሮችን እንዴት መፍታት ይቻላል። ለእዚህ ዓላማ የተቋቋመው ኮሚሽን መፍትሄ ይሆናል?
ረ/ፕሮፌሰር አህመድ፡– ኮሚሽን ይኑርም አይኑርም ጉዳዩ ይህ አይደለም። አዲስ ኮሚሽን ማቋቋም ካስፈለገም ማቋቋም ይቻላል። መፍትሄው ችግሩ አለብን ብለን መቀበል ነው ዋናው ነገር። ችግሩ አለ። ሰው እየተፈናቀለ፣ እየሞተም ነው። ይህ ግን መፍታት የሚቻለው በውይይት በሂደት የሚመጣ ነገር ነው። ኮሚሽኑ ህጋዊ ነው አይደለም፣ ህገ መንግሥቱን ያከብራል አያከብርም የሚለው ጉዳይ ለእኔ ያን ያህል ሚዛን ያለው አይደለም።
አዲስ ዘመን፡- ቅርሶች ላይ አያያዛቸው ባግባቡ እንዳልሆነ፣ የምስልና የድምጽ እንዲሁም የተለዩ ቅርሶች በአግባቡ ስራ ላይ እየዋሉ አለመሆኑን በሌላ በኩል ሀብቱ እያለ ከውጭ የራሳችንን ድምፅ የምንገዛበት ሁኔታ እንዳለ ይጠቀሳል። ይህ ምን ያህል ተጨባጭ ነው?
ረ/ፕሮፌሰር አህመድ፡– በእኔ ግምት የምስልና የድምጽ ስብስባችን ውስን ነው። አንዳንድ ጊዜ የቴክኖሎጂ ችግሮች አሉብን። ወደ ዲጂታል ከተቀየረ በኋላ ሁል ጊዜ የማቀርበው መረጃ ትልቅ ሰርቨር ውስጥ አስገብቶ ለተጠቃሚ ምቹ የሚሆንበት መላ መፍጠር የሚቻልበትን መንገድ መፍጠር ነው። ለእዛ አቅም ያስፈልጋል። ለአዲስ አበባ ዮኒቨርሲቲ ብቻ ሳይሆን ለ50 የመንግሥትና ለሌሎች የግል ዮኒቨርሲቲዎች የሚጠቅም ሀብት አለ። ይህንን ሀብት ተደራሽ ለማድረግ የቴክኖሎጂ ድጋፍ ያስፈልጋል።
የተወሰኑት አሁን ዲጂታላይዝድ ሆነዋል። እነርሱን በተወሰነ መልኩ በተዘረጋው አሰራር መሰረት በአነስተኛ ክፍያ አገልግሎት ማግኘት ይቻላል። የእኔ ቅዠት በአንዴ አድጎ አንድ ትልቅ ሰርቨር ተዘጋጅቶ ቤተ መጽሐፍቱ በሙሉ ወደ ዲጂታላይዝድ ቢገባ ነው። አንዴ ከገባ በኋላ ሁሉም ቤቱ ሆኖ መጠቀም ያስችለዋል። ትልቁ ችግር ለዚህ የሚሆን አቅም መገንባት ላይ ነው። አሁን ለጥናትና ምርምር ያለውን መረጃ በማቅረብ አገልግሎት ይሰጣል። ያለው ችግር የሚፈታ ነው። ይህ እንዴት ይቻላል በሚለው ላይ ተሰባስቦ መነጋገር ይገባል።
አዲስ ዘመን፡– አንድ ታዋቂ ጋዜጠኛ የቀድሞውን ህዝብ መዝሙር ፈልጌ የለም ተባልኩ ሲል ነበረ። ይሄ የአያያዝ ክፍተት አይደለም?
ረ/ፕሮፌሰር አህመድ፡– አይደለም። ድምጹ ላይኖር ይችላል። ለምን ብትይኝ እኛ ለምነን የምንሰበስብ ስለሆነ ነው። ምናልባት ሊገኝ የሚችለው ሬዲዩ ዝግጅት ክፍል ነው። የሃይለ ስላሴ አርካይቭ ውስጥ ሊገኝ ይችላል።
አዲስ ዘመን፡- ግን እንደ ሀብት ሊታይ አይችልም?
ረ/ፕሮፌሰር አህመድ፡- ትዝታ በሙሉ ሀብት ነው። ትናንትናሽን ባወቅሽ ቁጥር ዛሬና ነገሽን የበለጠ ታስተካክያለሽ። እንደ ሀብት ግን የምትሰበስቢውን መምረጥ አለብሽ። ቦታ፣ ሀብትና ሌሎች የሚታዩ ብዙ ነገሮች አሉ።
አዲስ ዘመን፡– ለነበረን ቆይታ በአንባቢዎቼና በዝግጅት ክፍሉ ስም ከልብ አመሰግናለሁ።
ረ/ፕሮፌሰር አህመድ፡– እኔም አመስግናለሁ።
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሚያዝያ 26/2011
በማህሌት አብዱል