የሀገራችን የማዕድን ልማት በተለይ የወርቅ ልማት እጅግ አድካሚ መሆኑን በዘርፉ የተሰማሩ አካላት ይገልጻሉ፡፡ ማዕድኑ አንዳንድ ጊዜ ሊገኝ፤ ሌላ ጊዜ ደግሞ ብዙ ተደክሞም ላይገኝ ይችላል፡፡ ማዕድንን በባህላዊ መንገድ የሚያለሙ አካላት ቁፋሮውን የሚያካሂዱት በጥናትና በሳይንሳዊ መንገድ ታግዘው አይደለም፤ ይህ ሁኔታም ማዕድን የማልማቱን ስራ እጅግ አድካሚ ያደርገዋል፡፡
ልማቱ የቱንም ያህል አድካሚ ቢሆን፣ ውጤቱ አርኪ ነውና የማዕድን ሀብቱ በሚገኝባቸው በተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ባህላዊ ማዕድን አልሚዎች በዘርፉ ተሰማርተው ይገኛሉ፡፡ ከማዕድን ልማት በሚያገኙት ገቢም ቤተሰባቸውን ከማስተዳደር፣ ኑሯቸውን ከመለወጥም ባለፈ ለሀገር ምጣኔ ሀብት እድገት በተለይ የውጭ ምንዛሬ በማስገኘት ፣ የስራ እድል ከፍተኛ ድርሻ አስተዋጽኦ ያበረክታሉ፡፡ ወርቅን ብንመለከት እስከ አሁን ባለው ሁኔታም ወደ ብሄራዊ ባንክ ከሚገባው ወርቅ ከፍተኛውን ድርሻ የሚይዘውም በባህላዊ አልሚዎች በኩል የሚገኘው ወርቅ መሆኑን መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡
በዚህ የማዕድን ልማት ከሚታወቁት ክልሎች አንዱ የትግራይ ክልል ነው፡፡ በክልሉ አስገደ ወረዳ በርካታ ማህበራት በባህላዊ መንገድ ወርቅ በማምረት ላይ ተሰማርተዋል፡፡ በልማቱ ከተሰማሩት አንዱ የወረዳው ነዋሪ አቶ ገብረሕይወት አብራልኝ ናቸው። አቶ ገብረሕይወት በልማቱ ላይ ለአምስት ዓመታት ቆይተዋል፡፡ የሚያለሙትን ወርቅ ህጋዊ ለሆነ ወርቅ ገዥ ያቀርባሉ፡፡
በልማቱ ባገኙት ገቢ ዘመናዊ መኖሪያ ቤቶች ከተማ ውስጥ ገንብተዋል፡፡ ልጆቻቸውም በሚገባ እያስተማሩ መሆናቸውን ይናገራሉ፡፡ ለመንግሥት የሚጠበቅባቸውን ክፍያም (ሮያሊቲ) በወቅቱ እንደሚከፍሉ ይገልጻሉ፡፡
አቶ ገብረሕይወት፤ በወርቅ ማዕድን ልማቱ ጠንክረው ሲሠሩና በኑሯቸው የበለጠ ስኬታማ ለመሆን ጥረት ሲያደርጉ በነበረበት ወቅት የሰሜኑ ጦርነት መቀስቀሱን ያስታውሳሉ፡፡ ጦርነቱ እቅዳቸውን ከመፈጸም እንዳስተጓጎላቸው ይናገራሉ፡፡
እርሳቸው የሚኖሩበት ትግራይ ክልል ሽሬ አካባቢ ከፍተኛ የወርቅ ማእድን የሚገኝበት መሆኑን ጠቅሰው፣ ከባህላዊ አልሚዎች በተጨማሪ በኩባንያ ደረጃ ኢዛና የሚባል ኩባንያ በአካባቢው በወርቅ ልማት መሰማራቱንም ይገልጻሉ፡፡
ከጦርነቱ በፊት ጥሩ የሚባል የልማት እንቅስቃሴ እንደነበር ያስታወሱት አቶ ገብረሕይወት፤አስር አባላትን የያዘ ማህበር መሥርተው ይሰሩ እንደነበርም ነው የሚናገሩት፡፡ ማህበራቸው ከጦርነቱ በፊት በነበረው የትግራይ ክልል አስተዳደርና ከፌዴራል መንግሥት ማበረታቻዎች ይደረግለትም እንደነበር ያስታወሳሉ፡፡
እርሳቸው እንዳሉት፤ ዘርፉን አስመልክቶ በተለያየ ጊዜ በክልልም ሆነ በፌዴራል በሚዘጋጁ የውይይት መድረኮች በመሳተፍ ማህበራቸው በልማቱ ላይ የሚያጋጥመውን ችግር ከማሳወቅ በተጨማሪ ገንቢ ሀሳቦችም በማቅረብ ሰፊ ተሳትፎ ያደርግ ነበር፡፡
ማህበራቸው በማዕድን ልማቱ ስኬታማ እንደነበር ይገልጻሉ፡፡ በቁፋሮ ማዕድኑ ሳይገኝ ሲቀር መረጃ አደራጅቶ በወረዳው ቀድሞ ውሃና ኢኒርጂ ተብሎ በሚጠራው ተቋም ውስጥ አንድ ዘርፍ ለነበረው ማዕድን ጽሕፈት ቤት በየወሩ የማሳወቅ ልምድ ነበረው፡፡ በነቃ ተሳትፎው፣በመልካም አፈጻጸሙና ሕጋዊ አሰራርን ተከትሎ በመሥራቱ ከማዕድን ሚኒስቴር የእውቅና የምስክር ወረቀት ሽልማት አግኝቶ እንደነበርም ይገልጻሉ። ለማህበሩ ‹‹ገብረሕይወት፣ጽላል፣ ሐጎስና ጓደኞቹ›› የሚል ስያሜ የሰጠው ማዕድን ሚኒስቴር መሆኑን በማስታወስ፣ እርሳቸው ማህበሩን በመምራት እያገለገሉ መሆናቸውን ይገልጻሉ፡፡
አቶ ገብረሕይወት እንደገለጹት፤ የወርቅ ልማቱ ይከናወን የነበረው ከሽሬ በጥቂት ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በሚገኘው አስገደ ወረዳ፣ ማይበረበረ በሚባል አካባቢ ነው፡፡ አካባቢው በወርቅ ማዕድን የሚታወቅ ቢሆንም፣ ማዕድኑን ለማግኘት ብዙ ተቆፍሮም የማይገኝበት አጋጣሚም ይፈጠራል፡፡ በለስ የቀናቸው ጊዜ ደግሞ እስከ 150 ኪሎግራም የሚደርስ ወርቅ ያገኛሉ፡፡ ይህን ያህል መጠን ያለው ወርቅ የሚገኘውም በተወሰነ ጊዜ ነው፡፡ ለቁፋሮ የሚጠቀሙበት የሥራ መሣሪያ ዘመናዊ ባለመሆኑ በጥልቀት ቁፍሮ ማዕድኑን ለማግኘት ያደክማል፤ ጊዜም ይወስዳል፡፡ ያም ሆኖ ግን መተዳደሪያቸው አድርገው ይዘው በመቀጠል ጦርነቱ ሥራቸውን እስከ አስተጓጎለበት ጊዜ ድረስ ሲሰሩ ቆይተዋል፡፡
በሰላም መደፍረስና በኋላም በተካሄደው ጦርነት ምክንያት አቶ ገብረሕይወትና ጓደኞቹ በማህበር ሲያከናውኑት የነበረው የወርቅ ማዕድን ልማት እየተዳከመ መጥቶ በኋላም ሥራ ለማቆም ተገዷል፡፡ የቁፋሮና ማዕድኑ የሚገኝበትን አካባቢ ለመጠቆም የሚያስችሏቸው የሥራ መሣሪያዎቻቸውን ጨምሮ የተለያዩ መገልገያዎቻቸው ከጥቅም ውጭ መሆንና ውድመት ደርሶበታል፡፡
ከማዕድን ልማቱ በሚያገኙት ገቢ ኑሮቸውን መምራትም አልቻሉም፡፡ በብዙ ድካም ያፈሩትን ሀብትና ንብረት በአንድ ጊዜ ማጣታቸውና ያለሥራም ለዓመታት መቆየታቸው የጦርነቱ አስከፊነት ማሳያዎች እንደሆኑ አቶ ገብረሕይወት ይገልጻሉ፡፡ አቶ ገብረሕይወት ጦርነቱ በልማቱ የነበራቸውን ትልቅ ተስፋ እንዳጨለመባቸውና መልሶ ለማገገም ‹ሀ› ብለው ከዜሮ መጀመር የግድ እንደሆነባቸው ያጫወቱን በሀዘን ስሜት ነው፡፡
የኢፌዴሪ መንግሥትና ሕዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ(ሕወሓት)ፕሪቶሪያ ላይ ስምምነት ካደረጉ በኋላ በአካባቢያቸው የሰላም አየር መተንፈስ ከጀመሩ ማግሥት አንስቶ እነ አቶ ገብረሕይወት ለኑሮ ደፋ ቀና ማለት እንደጀመሩ ጠቅሰው፣ ወደ ሚያውቁትና ወደ ለመዱት የወርቅ ማዕድን ልማት እንደተመለሱ ይናገራሉ። መቆፈሪያና አካፋ ይዘው በለመዱት መንገድ ወርቅ ማልማታቸውን ተያይዘውታል፡፡
ጦርነቱ ቢቆምም ልማቱን የሚከታተለውና ሕጋዊ መሥመር በማስያዝ እንዲከናወን ሲያደርግ የነበረው መንግሥታዊ ተቋም አደረጃጀት ወደ ሥራ ሂደት እስኪገባ ድረስ ያለውን ክፍተት በመጠቀም ማዕድኑ በሚገኝበት ሥፍራ ህገወጥነት ተስፋፍቶ እንደነበርም አንስተዋል። እነዚህ ህጋዊ ያልሆኑ አካላት እንደ ዶዘር ያሉ ከፍተኛ መሣሪያዎች በመጠቀም ጭምር ቁፋሮ ሲያካሂዱ እንደነበርም ተናግረዋል፡፡
በማህበር የተደራጁ የአካባቢው ወጣቶችና የህብረተሰብ ክፍሎች በህጋዊ መሥመር እንዲንቀሳቀሱ በጥብቅ ቁጥጥር ይከናወን የነበረው የማዕድን ልማት ለህገወጦች ተጋልጦ ማየታቸውን በቁጭት የሚገልጹት አቶ ገብረሕይወት፤ አሁን ላይ ግን ህገወጦችን ከአካባቢው ለማስወጣት ጥረት እየተደረገ እንደሆነ ማየታቸውን አመልክተዋል፡፡
አቶ ገብረሕይወት እንደነገሩን፤እንዲህ ባለ አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ሆነው ወደ ሥራ ከተመለሱ ሁለት ወራት አስቆጥረዋል፡፡ በዚህ ጊዜ ውስጥ ወደ 50 ግራም የወርቅ ማዕድን አግኝተዋል፡፡
የማህበሩ አባላት በጦርነቱ ያጡትን መልሰው ለመተካትና ኑሯቸውን ለመምራት ተነሳሽነቱም ፍላጎቱም አላቸው፡፡ የሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት ትኩረት ሰጥተው ለሥራቸው አስፈላጊ የሆነ ለማዕድን ልማት የሚውል የሥራ መሣሪያ እንዲያሟሉላቸው ፍላጎታቸው እንዳላቸው ይገልጻሉ፡፡ በተለይም በነጭ ድንጋይ ውስጥ የሚገኝ የወርቅ ማዕድንን ለይቶ የሚያወጣ ዘመናዊ የሥራ መሣሪያ(ማሽን)አቅርቦት ቢያገኙ ለሥራቸው ቅልጥፍና እና በጥራትም ለማምረት እንደሚያግዛቸው አቶ ገብረሕይወት ይናገራሉ፡፡ ይህንኑ ሃሳባቸውን ለአካባቢያቸው ለሚመለከተው ወረዳ አቅርበዋል፡፡ ወረዳው ወደ ልማት እንዲገቡ ጥሪ ባደረገላቸው ወቅትም ተስፋ እንዳይቆርጡ በማበረታታትና ከሚመለከተው አካል ጋር በመነጋገር የሚችለውን ሁሉ እንደሚያደርግም ተስፋ ሰጥቷቸዋል፡፡
አቶ ገብረሕይወት ያለፈውን ወደኋላ ትተው ለወደፊት እድገትና ለውጥ ለመሥራት የሚመሩት ማህበርም ሆነ በግላቸው ዝግጁ እንደሆኑ ነው የነገሩን። ‹‹ሰላም ካለ ተስፋ አለ፡፡ ሰርተን ራሳችንን ብቻ ሳይሆን መንግሥት ከዘርፉ ማግኘት ያለበትንም ጥቅም እንዲያገኝ እናደርጋለን›› በማለት አካባቢው በማዕድን ሀብት የታደለና ብዙ መሥራት የሚያስችል መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ሌላው የአቶ ገብረህይወትን ሀሳብ የሚያጠናክር አስተያየት የሰጡን አቶ ኃይለ ገብረሚካኤል የእነ አቶ ገብረሕይወት ማህበር አባል ናቸው፡፡ አቶ ኃይለ በወርቅ ማዕድን ልማት ሥራ የተሰማሩበትንና የማህበሩም አባል የሆኑበትን አጋጣሚ አጫውተውናል። ገብረሕይወት፣ጽላል፣ሐጎስና ጓደኞቹ ማህበርን ከመቀላቀላቸው አስቀድሞ በግላቸው ይሠሩ ነበር። ወደ ልማቱ ለመግባት መነሻ የሆናቸውም ከመኖሪያ አካባቢያቸው ቅርብ ርቀት ላይ የወርቅ ማእድን ማየታቸው ነው፡፡ ለተወሰነ ጊዜ እንደሰሩ የማዕድን ሀብቱን የሚከታተለው የሚመለከተው የወረዳው አካል ልማቱ በግል ሳይሆን፣በማህበር በመደራጀት መከናወን እንዳለበት ግንዛቤ በመፍጠር ያስቆማቸዋል፡፡ በዚሁ መሠረት ነው ማህበሩን የተቀላቀሉት፡፡
ማህበሩን ተቀላቅለው ለሁለት ዓመታት እንደሰሩ ነበር ጦርነቱ ከልማቱ ያስተጓጎላቸው፡፡ ምንም እንኳን በማህበሩ የነበራቸው ቆይታ አጭር ጊዜና በግላቸውም ሲሰሩ ጥቂት ወቅቶች ቢሆንም ኑሮቸውን እንደመሩበትና ለማደግም ትልቅ ተስፋ አድርገው ነበር በሙሉ አቅማቸው በልማቱ ውስጥ የቆዩት፡፡ጦርነቱ የነበራቸውን ተስፋ ብቻ ሳይሆን ከእለት ኑሮቸውም እንዳስቀየራቸው በሀዘን ስሜት ይናገራሉ፡፡ ጦርነቱ አስከፊ ጉዳት አድርሷል፤ በግለሰቦች ላይ ብቻ ሳይሆን ጉዳት ያደረሰው፣በሀገር ደረጃም ከፍተኛ ኪሰራ ማድረሱን ነው የገለጹት፡፡ ሀገር ከዘርፉ ታገኝ የነበረውን የውጭ ምንዛሪ ጥቅም በማሳጣት ኢኮኖሚው ላይ ጫና ማድረሱንም ተናግረዋል፡፡
ከአስከፊውና ከአውዳሚው ጦርነት በኋላ የተገኘው ሰላም በማዕድን ልማቱ ለማደግ የነበራቸውን ተስፋ እውን ለማድረግ እንደገና እንዳነሳሳቸው የገለጹት አቶ ኃይለ፤ ምቹ ሁኔታዎች ከተፈጠሩ ለውጥ ለማምጣት የሚሰስቱት ጉልበት እንደሌለ ነግረውናል፡፡
በሰላሙ ጊዜ በአስገደ ወረዳ ውስጥ በባህላዊ ወርቅ ማዕድን ልማት ላይ ተሰማርተው ይሰሩ የነበሩ በርካታ ማህበራት ነበሩ፡፡ ማህበራቱ በተለያየ ስያሜ የተደራጁ በማህበራቸውም የተለያየ ቁጥር ያለው አባል ይዘው ይሰሩ እንደነበርና በልማቱ ሰፊ ቁጥር ያለው የሰው ኃይል መሰማራቱን በአስገደ ወረዳ መሬት ማዕድን ጽሕፈትቤት የማዕድን ዘርፍ አስተባባሪ አቶ ገብረመድህን እሸ ይገልጻሉ፡፡
በሰላሙ ጊዜ በባህላዊና በመካከለኛ ደረጃ ወርቅ አልሚዎች እንዲሁም ለግንባታ ግብአት የሚሆኑ እንደ አሸዋ የመሳሰሉ የማዕድን አይነቶች ላይ ተሰማርተው የሚሰሩ ማህበራት እንደነበሩ አቶ ገብረመድህን አስታውሰው፤ ጽሕፈትቤቱ ልማቱ በአግባቡ እንዲከናወን በመከታተልና የቁጥጥር ሥራ በማከናወን መንግሥት ማግኘት ያለበትን ጥቅም እንዲያገኝ በማድረግ ኃላፊነቱን ይወጣ እንደነበርም ገልጸዋል፡፡
በጦርነቱ ምክንያት የተበታተኑ ማህበራትን መረጃ የያዘ ሰነድ ለመፈለግ በየቀበሌው በመዘዋወር ተሰርቷል፤ በአጠቃላይ ከሰላሙ በኋላ ስላለው እንቅስቃሴ አቶ ገብረመድህን ሲያብራሩ እንዳሉት፤ በጦርነቱ መረጃ የያዙ ሰነዶች በመውደማቸው የተወሰኑ ማህበራትን ሰነድ ብቻ ነው ማግኘት የተቻለው፡፡ በአጋጣሚ ከተገኘው ሰነድ በተጨማሪ በየቀበሌው በመሄድ በተሰራው የማሰባሰብ ሥራ ማህበራት መሰባሰብ ጀምረዋል፡፡
ጽሕፈት ቤቱ ማህበራቱን እንዴት እየተቀበላቸው እንደሆነም አቶ ገብረመድህን ለቀረበላቸው ጥያቄ በሰጡት ምላሽ፣ አንዳንዶች የውል ጊዜያቸው ያለቀ ቢሆንም በሰላሙ ጊዜ በነበረው አሰራር ነው እንዲቀጥሉ የተደረገው ብለዋል፡፡ ጽሕፈት ቤቱ ይህ መረጃ እስከ ተጠናከረበት ጊዜ ድረስ እስከ 25 አባላት ያላቸው 96 የሚደርሱ ባህላዊ ወርቅ አምራች ማህበራትን አሰባስቧል። በአነስተኛ የተሰማሩትንም በተጨማሪ በማሰባሰብ ላይ ይገኛል፡፡ወደ ልማቱ የተመለሱትም ሥራ ጀምረዋል፡፡
ከልማቱ ጋር በተያያዘ ስላለው ወቅታዊ ሁኔታ በተለይም ህገወጥነትን በተመለከተ አቶ ገብረመድህን እንደገለጹት፤ ከወረዳው ውጭ ነዋሪ የሆኑ ከክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች የወርቅ ማዕድንን በህገወጥ ማውጣት ላይ መሰማራታቸው ተደርሶበታል፡፡ ህገወጥነቱም በከፍተኛ የቁፋሮ መሣሪያ የታገዘ ነው፡፡ ችግሩን ለመከላከል በወረዳው አስር ቀበሌዎች በተደረገው ጥረት ውጤት ተገኝቶበታል፡፡ የመከላከሉ ተግባርም ተጠናክሮ ቀጥሏል፡፡ ህገወጦቹ በተቀመጠላቸው የጊዜ ገደብ አካባቢውን ለቀው ባይወጡ ኖሮ ህግ ተላልፎ የተገኘ የሚቀጣውን እስከ 500 ሺ ብር ለመቅጣት ጭምር ዝግጅት ተደርጎ ነበር፡፡ ህገወጥነትን ለመከላከል የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ያላሰለሰ ጥረት በማድረጉ ነው ውጤት የተገኘው፡፡
ሙሉ ለሙሉ ወደልማቱ ለመግባት ከፍተኛ ድጋፍ እንደሚያስፈልግ የገለጹት አቶ ገብረመድህን፤በሰላሙ ጊዜም ቢሆን ለማዕድን ዘርፍ የተሰጠው ትኩረት አነስተኛ እንደሆነ በዘርፉ ሥራ ላይ ለስምንት ዓመታት በቆዩባቸው ጊዜያቶች መረዳታቸውን ይገልጻሉ፡፡ ዘርፉ ቢደገፍና ቢበረታታ ለሀገር ከፍተኛ ጥቅም እንደሚያስገኝ ተናግረዋል፡፡ አሁን ደግሞ ጦርነቱ ባስከተለው ጉዳት በክልሉ ያለው የማዕድን ልማት መዳከሙንና ከፍተኛ እገዛ እንደሚፈልግ ገልጸውልናል፡፡
ጦርነቱ በክልሉ ካደረሰው ጉዳት፣ የማዕድን አልሚዎቹና ማዕድን ልማቱን ከሚመራው አካል መረዳት እንደተቻለው አልሚዎቹ የመንግሥት የተለያዩ ድጋፎች ያስፈልጋቸዋል፡፡ ማህበራቱ ወደ ስራ ተመልሰው የሚችሉትን እያደረጉ ናቸው፤ በዚህ ላይ የመንግሥት ድጋፍ ቢታከልበት ልማቱን ይበልጥ ማጠናከርና አምራቾቹ ወደ ተጠቃሚነታቸው የሚመልሱበትን ማፋጠን፣ ሀገርም ከዘርፉ ማግኘት ያለባትን እንድታገኝ ማድረግ ይቻላል፡፡
ለምለም መንግሥቱ
አዲስ ዘመን ግንቦት 25/2015