ሀገራችን ከግብር ስራ ጋር ረጅም ዘመናት አብረው ከተጓዙ የዓለም ሀገራት አንዷ ነች። ዘርፉ ለበርካታ ክፍለ ዘመናት ለሀገሪቱ ፖለቲካዊ ኢኮኖሚያዊ መሰረት በመሆንም አገልግሏል፤ በቀጣይም የሀገሪቱን ነገዎች ብሩህ ለማድረግ በሚደረገው ጥረት ውስጥ ትልቁ አቅም እንደሚሆን ይታመናል።
ሀገሪቱ ለግብርናው ዘርፍ የሚመች ተስማሚ የአየር ጸባይ ፣ ሰፊ የመሬት እና የውሃ ሀብት እንዳላት የተለያዩ ጥናቶች ቢያረጋግጡም፤ እነዚህን ሀብቶች በአግባቡ አቀናጅቶ በመጠቀም ዘርፉን ውጤታማ ለማድረግ በተለያዩ ወቅቶች የተደረጉ ጥረቶች ስኬታማ ሳይሆኑ ቀርተዋል።
ከዚህም የተነሳ ሀገሪቱ በተለያዩ ወቅቶች በተከሰቱ የድርቅ አደጋዎች ምክንያት ለከፋ ረሀብ የተጋለጠችባቸው ጊዜያት ጥቂት አይደሉም። በዚህም ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ዜጎች ለሞት እና ለስደት ተዳርገዋል። እንደ ሀገረም የረሀብ ተምሳሌት ለመሆን የተገደደችባቸው አጋጣሚዎች ብዙ ናቸው።
በአንድ በኩል የግብርናው ዘርፍ ሲመራበት የኖረው ኋላቀር አስተሳሰብ እና አስተሳሰቡ የወለደው አሰራር፣ በሌላ በኩል በሀገሪቱ በተለያዩ ወቅቶች ተግባራዊ የተደረጉ የመሬት እና የግብርና ፖሊሲዎች ዘርፉ በሚጠበቀው ደረጃ እንዳያድግ ዋነኝ ተግዳሮት ሆነዋል።
እነዚህን ችግሮች በመፍታት ዘርፉን ውጤታማ ለማድረግ ከለውጡ ማግስት ጀምሮ የተለያዩ ጥረቶች እየተደረጉና ተስፋ ሰጭ ውጤቶች እየታዩ ነው። ከዚህ ውስጥ አንዱ የኩታ ገጠም እርሻን በማስፋፋት ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ የሚደረገው ጥረት ነው።
ኩታ ገጠም ግብርና በአንድ የተወሰነ አካባቢ ያሉ አርሶ አደሮች አጎራባች መሬቶችን አንድ ላይ በማሰባሰብ፣ ምርታማነታቸውን ለማሳደግ አብረው የሚሰሩበት፣ ሀብትና ዕውቀት የሚጋሩበት፤ ልምድ የሚለዋወጡበት አሰራር የሚፈጥር ነው።
በዋናነት አርሶ አደሮች ከተበጣጠሰ የማሳ አጠቃቀም ወጥተው በአንድ ላይ እንዲያመርቱ የሚያስችል፤ ለተሻለ ውጤታማነት ተደራጅቶ ለመንቀሳቀስ፣ የግብርና ግብአቶችን እና የሜካናይዜሽን አገልግሎቶችን በቀላሉ እንዲያገኙም የሚያግዝ ነው።
ለዘርፉ ሁለንተናዊ እድገት የግብርና ባለሙያዎች የሚሰጣቸው አገልግሎቶች፣ ድጋፎች እና ክትትሎች የበለጠ ውጤታማ እንዲሆኑ፤ በምርምር ተቋማት የሚገኙ የምርምር ውጤቶችም ፈጥነው ወደ ስራ እንዲገቡ የተሻለ እድል ሊፈጥር የሚችል እንደሆነም ይታመናል።
ከግብርና ሚኒስቴር የተገኘ መረጃ እንደሚያመለክተው፤ በሀገር አቀፍ ደረጃ በ2015/16 የመኸር ምርት በክላስተርና በመደበኛ ከሚሸፈነው 16 ሚሊዮን ሄክታር መሬት ውስጥ 8 ነጥብ 5 ሚሊዮን ሄክታሩ መሬት በኩታ ገጠም እርሻ የሚሸፈን ነው፡፡ ከዚህም 8 ነጥብ 5 ሚሊዮን ሄክታር መሬት 299 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ይጠበቃል።
መረጃዎች እንደሚያመለክቱት፤ እስካሁን በኩታ ገጠም እርሻ ከሚመረቱት ውስጥ በዋነኛነት ስንዴ፣ ገብስ፣ ጤፍ፣ በቆሎና ማሽላ ተጠቃሽ ናቸው። በተለይም በኩታ ገጠም ግብርና የበጋ መስኖ ስንዴን ማምረት ከተጀመረ አንስቶ አርሶ አደሮች ከእርሻው የላቀ ምርት መሰብሰብ ችሏል።
ይህ እንደ ሀገር እየተመዘገበ ያለው ትልቅ ስኬት በዓለም አቀፍ ደረጃ እውቅና እየተቸረው ነው፤ ከዛም ባለፈ ሀገሪቱ ሚሊዮን ዶላሮችን ወጪ በማድረግ የስንዴ ምርት ወደ ሀገር ውስጥ ከማስገባት ወጥታ የዓለም የስንዴን ገበያን መቀላቀል አስችሏታል።
እንደ ሀገር አሁን በዘርፉ ካለው ውጤታማ አፈጻጸም እና የአርሶ አደሩ የላቀ ተጠቃሚነት አንጻር የኩታ ገጠም እርሻን ማስፋፋት በምግብ እህል እራሳችንን ለመቻል እያደረግነው ላለው ጥረት ስኬት፤ ከግብርና ወደ ኢንደስትሪ መር ኢኮኖሚ ለምናደርገው ጉዞም ዋነኛ አቅም ሊሆን እንደሚችል ይታመናል።
ይህንን ተጨባጭ እውነታ ታሳቢ በማድረግም በተለይም የግብርና ተቋማት፣ ባለሙያዎች፤ በዘርፉ የተሰማሩ አካላት የኩታ ገጠም እርሻዎች በፍጥነት የሚስፋፉበትን መንገድ የጋራ ስራቸው አድርገው ባላቸው አቅም ፤ በቁርጠኝነት ሊንቀሳቀሱ ይገባል።
አርሶ አደሩም ቢሆን ከሚታየው ተጨባጭ እውነታ በመነሳት ልቡን ክፍት አድርጎ እራሱን፤ ከዛም አልፎ መላውን ሕዝብና ሀገሩን ተጠቃሚ ለማድረግ እራሱን ማዘጋጀት ይጠበቅበታል። ከልመና ወጥተን ብሔራዊ ክብራችንን መልሰን ለመገንባት በምግብ እህል እራሳችንን የመቻላችን ጉዳይ ወሳኝ ነው!
አዲስ ዘመን ግንቦት 25/2015