የአማራ ክልል ካለው እምቅ የኢንቨስትመንት አቅም መካከል ክልሉ ለአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ (Manufacturing industry) ያለው ምቹነት ተጠቃሽ ነው:: ክልሉ በርካታ ኢንዱስትሪዎች ያሉት ሲሆን፣ 28 ለኢንዱስትሪ መንደሮችም ይገኙበታል:: በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ከፍተኛ ጉዳት የደረሰበት የክልሉ የአምራች ኢንቨስትመንት ዘርፍ ከጦርነቱ በኋላ መነቃቃት እያሳየ እንደሚገኝ መረጃዎች ያመለክታሉ፤ ይህን ተከትሎ ያስመዘገባቸው ውጤቶች ተስፋ ሰጪ እንደሆኑ ይገለጻል::
የአምራች ዘርፉን ጨምሮ ሌሎች የኢንቨስትመንት ዘርፎችን የሚመራውና የሚቆጣጠረው የክልሉ የኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ በሁለት ዘርፎች የተከፈለ ነው:: አንዱ የአምራች ዘርፉ ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ሌሎች የኢንቨስትመንት ዘርፎችን (የአገልግሎት፣ ሪልስቴት፣ ግብርና…) ያካተተ ነው::
የአምራች ክፍለ ኢኮኖሚው ደግሞ የጨርቃ ጨርቅና ቆዳ፣ የእንጨትና ብረታ ብረት፣ የኬሚካልና ኮንስትራክሽን እና የግብርና ማቀነባበሪያ ዘርፎችን ይዟል:: በክልሉ 28 የኢንዱስትሪ መንደሮች የሚገኙ ሲሆን፤ የኢንዱስትሪ መንደሮችን የማልማት፣ መሰረተ ልማቶችን የማሟላት፣ ወደ ኢንዱስትሪ መንደሮች የሚገቡ አምራቾችን በመመልመል የመወሰንና የግንባታ ሂደታቸውን እስከምርት ድረስ የመከታተል ተግባራት በኢንዱስትሪ ዞን የሥራ ዘርፍ ይመራል::
በክልሉም ሆነ በአገር አቀፍ ደረጃ የህዝብን ተጠቃሚነት በማረጋገጥና አገራዊ ምጣኔ ሀብትን በመደገፍ ረገድ ከአምራች ዘርፉ የሚጠበቁ ዋናዎቹ ግቦች የስራ እድል ፈጠራ፣ የውጭ ምንዛሪ ግኝት እና ተኪ ምርቶች ማምረት ናቸው:: ክልሉ የአምራች ዘርፉን ምርትና ምርታማነት በማሳደግ እነዚህን ግቦች ለማሳካት ባለፉት ዘጠኝ ወራት የተለያዩ ስራዎችን አከናውኗል:: የአማራ ክልል ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ተፈሪ ታረቀኝ ክልሉ በአምራች ዘርፍ ባለፉት ዘጠኝ ወራት ስላከናወናቸው ተግባራት ለ‹‹አዲስ ዘመን›› ጋዜጣ የሰጡትን ማብራሪያ በዛሬው የኢንቨስትመንት አምዳችን ይዘን ቀርበናል::
ኢንቨስትመንቶችን የመሳብ ተግባራት
እንደ እሳቸው ገለጻ፤ ክልሉ በአምራች ዘርፍ ያለውን የኢንቨስትመንት አቅም በማስተዋወቅ ተጨማሪ ኢንቨስትመንቶችን ወደ ክልሉ ለመሳብ ብዙ ጥረቶችን አድርጓል:: ከዩኒቨርሲቲዎች ጋር የጋራ እቅድ በመንደፍ የክልሉ የአምራች ዘርፍ የኢንቨስትመንት አቅም በቦታ፣ በመጠንና በጥራት ተለይቶ እንዲታወቅ የሚያስችሉ ስራዎች ተከናውነዋል:: ከባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር ዝርዝር ጉዳዮችን የሚያመለክት ክልላዊ የኢንዱስትሪ ልማት ፍኖተ ካርታ (Regional Industrial Development Roadmap) እንዲዘጋጅ ማድረግ ተችሏል::
በዘጠኝ ወራት ውስጥ በሁሉም ዘርፎች የኢንቨስትመንት ፈቃድ ከወሰዱ ከሦስት ሺ 600 በላይ ባለሀብቶች መካከል አንድ ሺ 800 የሚሆኑት በማምረቻው ዘርፍ ለመሰማራት ፍላጎት ያሳዩ ናቸው:: ከእነዚህም ውስጥ አንድ ሺ 248 ፕሮጀክቶች አዋጭነታቸው ተገምግሞ ተቀባይነት አግኝተዋል:: በዚህ ረገድ ከሌሎች አስፈፃሚ ተቋማት ጋር በመተባበር ካለፉት ዓመታት የተሻለ አፈፃፀም ማስመዝገብ መቻሉ አቶ ተፈሪ አስታውቀዋል::
እንደ እሳቸው ማብራሪያ፤ የአርሶ አደሩ መሬት ለኢንቨስትመንት ሲከለል እቅድ ተዘጋጅቶለት ባለሀብቱ ካሳውን እየከፈለ ወደ ስራ እንዲገባ በማድረግ ረገድ በየአካባቢው የተሻሉና ውጤታማ የሆኑ የመሬት ማስተላለፍ ስራዎች ተሰርተዋል:: ከዚህ በተጨማሪ በስራ ላይ ያሉት ኢንዱስትሪዎች የማምረት አቅማቸው እንዲያድግ የኢንዱስትሪ ኤክስቴንሽን አገልግሎት የመስጠት እና መሰረተ ልማቶችንና የፋይናንስ አቅርቦትን የማሟላት ተግባራትም ተከናውነዋል::
የመሰረተ ልማትና የፋይናንስ አቅርቦት
በአምራች ዘርፉ ውጤታማነት ላይ ጉልህ ሚና ካላቸው ግብዓቶች መካከል የመሰረተ ልማት ዝርጋታዎችና የፋይናንስ አቅርቦት ተጠቃሽ ናቸው:: ክልሉ በኢንቨስትመንት ዘርፍ ለሚሰማሩ አልሚዎች የመሰረተ ልማት፣ የኃይል አቅርቦትና የመሬት አቅርቦትን ጨምሮ ሌሎች ለኢንቨስትመንት አመቺ የሆኑ ድጋፎችን እያደረገ ይገኛል::
በአማራ ክልል በአምራች ዘርፉ ከሚታዩት ችግሮች መካከል አንዱ የኃይል አቅርቦት እጥረት ነው:: የኃይል አቅርቦት ችግሩ ከማከፋፈያዎች አቅም ውስንነት እና ከኃይል መቆራረጥ ጋር የተያያዘ ነው:: ቀደም ሲል ጀምሮ ለክልሉ ልማት የሚመጥን የኃይል አቅርቦት እንደሌለ እንደሚታወቅ ምክትል ስራ አስኪያጁ ጠቅሰው፣ ማከፋፈያዎች እንዲገነቡ ከፌዴራል መንግሥት ተቋማት ጋር መግባባት ላይ መደረሱን አስታውቀዋል:: የተወሰዱት የመፍትሄ እርምጃዎች የችግሩን ስፋት የሚመጥኑ ባይሆኑም አራት ማከፋፈያዎች እየተገነቡ ይገኛሉ ይላሉ::
እሳቸው እንዳሉት፤ ለኢንዱስትሪ መንደሮች የሚያገለግለው የኃይል አቅርቦት በቀጥታ ከማከፋፈያዎች መምጣት ሲገባው፣ የኢንዱስትሪ መንደሮቹ ግን ኃይል የሚያገኙት ከአካባቢዎቹ መደበኛ (የነዋሪዎች) የኃይል አቅቦት ጋር በጋራ ነው:: ይህ ደግሞ በጥቃቅን ምክንያቶች ሁሉ የኃይል መቆራረጥ ሲያጋጥም የኢንዱስትሪ መንደሮቹም የኃይል አቅርቦት ችግር እንዲያጋጥማቸውና ለከፍተኛ ኪሳራ እንዲዳረጉ ምክንያት ይሆናል:: ይህን ችግር ለማቃለል የክልሉ መንግሥት ባለፈው ዓመት 200 ሚሊዮን ብር መድቦ የኢንዱስትሪ መንደሮቹ በቀጥታ ከማከፋፈያዎች ኃይል እንዲያገኙ ባደረገው ጥረት አምስት የኢንዱስትሪ መንደሮች በዚህ መንገድ የኃይል አቅርቦት እንዲኖራቸው ተደርጓል፤ ለሌሎቹ የኢንዱስትሪ መንደሮች ኃይል የሚያቀርቡ ማከፋፈያዎችም እየተገነቡ መሆናቸው ተመላክቷል::
በመንገድ ረገድም በክልሉ የመሰረተ ልማት አቅርቦት ተደራሽ ያልሆነባቸው ብዙ ኢንዱስትሪዎች አሉ:: በዘንድሮው የበጀት ዓመት የክልሉ መንግሥት የኃይል አቅርቦትን ጨምሮ ሌሎች የመሰረተ ልማት ችግሮችን በማቃለል የኢንዱስትሪ መንደሮቹን ምርታማነት ለማሳደግ 464 ሚሊዮን ብር በጀት መድቦ እየሰራ ነው:: የተወሰዱት የመፍትሄ እርምጃዎች የኢንዱስትሪዎችን የማምረት አቅም ማሳደግ ችለ ዋል::
በፋይናንስ አቅርቦት ረገድ ለአምራቾች የሚደረጉት ድጋፎች የሊዝ ፋይናንስ፣ የስራ ማስኬጃ ፋይናንስ፣ የፕሮጀክት ፋይናንስ እና የውጭ ምንዛሪ አቅርቦትና ድጋፍ ናቸው:: ከኢትዮጵያ ልማት ባንክና ከግል ባንኮች ጋር በመቀናጀት አምራቾች የሁለት ነጥብ ስምንት ቢሊዮን ብር የስራ ማስኬጃ ፋይናንስ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ማድረግ ተችሏል:: በሊዝ ፋይናንስ ደግሞ በዘጠኝ ወራት ውስጥ 262 አምራች ኢንዱስትሪዎች 503 ሚሊዮን ብር ተጠቃሚ ሆነዋል:: ይህ አፈፃፀም ካለፉት ዓመታት የተሻለ መሆኑ ተጠቁሟል::
የስራ እድል ፈጠራና የውጭ ምንዛሪ ግኝት
ከአምራች ዘርፉ ከሚጠበቁ ዋና ዋና ግቦች መካከል የስራ እድል ፈጠራ፣ የውጭ ምንዛሪ ግኝት እና ተኪ ምርቶች ማምረት ግንባር ቀደም ሆነው ይጠቀሳሉ:: በዚህ ከሥራ እድል ፈጠራ አንጻር በበጀት ዓመቱ በክልሉ በአምራች ዘርፉ ለ24ሺ ዜጎች ቋሚ የስራ እድል ለመፍጠር ታቅዶ፣ በዘጠኝ ወራት ውስጥ 18ሺ741 የስራ እድሎችን መፍጠር ተችሏል:: የስራ እድሎቹ አዲስ አምራቾችን አቋቁሞ ወደ ስራ በማስገባት እና ነባሮቹን በማጠናከርና በማስፋፋት የተፈጠሩ ናቸው::
በዘጠኝ ወራት ውስጥ በክልሉ በሚገኙ ኢንዱስትሪዎች ተመርተው ወደ ውጭ ከተላኩ ምርቶች 85 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ተገኝቷል:: ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በአገር ውስጥ በማምረት 904 ሚሊዮን ዶላር የውጭ ምንዛሪ ማዳን ተችሏል:: ከውጭ ይገቡ የነበሩ የግብርና፣ የጨርቃ ጨርቅ፣ የእንጨት፣ የብረታ ብረትና ሌሎች ምርቶችን በጥራትና በብዛት በማምረት የአገር ውስጥ ገበያ ፍላጎትን ለማሟላት ጥረት እየተደረገ መሆኑ ተመላክቷል::
የኢንዱስትሪ ሽግግር
የኢንዱስትሪ ሽግግር የክልሉ ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ ከሚያከናውናቸው ተግባራት መካከል አንዱ ነው:: በዘጠኝ ወራት 12 ኢንዱስትሪዎች ከመካከለኛ ወደ ከፍተኛ ተሸጋግረዋል:: ከዚህ በተጨማሪም የኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮው 126 ኢንዱስትሪያሊስቶችን ከክልሉ ስራና ስልጠና ቢሮ ተረክቧል::
የመልሶ ማቋቋም ተግባራት
የክልሉ መንግሥት በጦርነቱ የተጎዱ ኢንዱስትሪዎችን ለማቋቋም በወሰደው ርምጃ ከተከናወኑ ተግባራት መካከል ጉዳቶቹን በጥልቀት መመልከት፣ ባለሀብቶችን ማወያየትና ስነ ልቦናቸውን መገንባት፣ ችግሮቹ በየደረጃው እንደሚፈቱ ዝርዝር የአፈፃፀም ቅደም ተከተል ማውጣት እና ልዩ ልዩ ድጋፎችን ማድረግ የሚሉት ይጠቀሳሉ::
ኢንዱስትሪዎቹን ወደ ስራ ለመመለስ ጥረቶች እየተደረጉ መሆናቸውን አቶ ተፈሪ ጠቅሰው፣ የውጭ ምንዛሪ አቅርቦት እጥረት አሁንም ከፍተኛ ችግር ሆኖ ቀጥሏል ሲሉ ያስገነዝባሉ:: ችግሩን ከገንዘብ ሚኒስቴር ጋር በመነጋገር ለመፍታት ጥረት እየተደረገ እንደሚገኝም ነው የጠቀሱት:: የድጋፍ ዓይነቶቹ ኢንዱስትሪዎቹ እንደደረሰባቸው የጉዳት ዓይነቶች የተለያዩ መሆናቸውን ተናግረው፣ በክልሉ አቅም የሚሰጡ ድጋፎች ለኢንዱስትሪዎቹ እየቀረቡ ይገኛሉ ብለዋል::
‹‹ኢትዮጵያ ታምርት›› ንቅናቄ
መንግሥት የኢንዱስትሪው ዘርፍ ችግሮችን ለማቃለል እየተገበራቸው ከሚገኙ የመፍትሄ ርምጃዎች መካከል በሚያዝያ 2014 ዓ.ም ይፋ የተደረገው የ‹‹ኢትዮጵያ ታምርት›› አገራዊ ንቅናቄ ይጠቀሳል:: የአገራዊ ንቅናቄው ዋና ዋና ዓላማዎች የአምራች ኢንዱስትሪውን ችግሮች በጋራ በመፍታት ለዘርፉ ዘላቂ ልማትና ተወዳዳሪነት ምቹ ሁኔታዎችን በመፍጠር ዘርፉ ለኢኮኖሚያዊ መዋቅራዊ ሽግግር የበኩሉን አስተዋጽኦ እንዲወጣ ማስቻል እንዲሁም በዘርፉ ያለውን የስራ ባህል ማሻሻል ብሎም የኢንዱስትሪ ምርቶችን ጥራትና ተወዳዳሪነት በማሻሻል ገቢ ምርቶችን የመተካት ሽፋንን ማሳደግ ናቸው::
ቅናቄው የአምራች ኢንዱስትሪዎችን ምርትና ምርታማነት ለመጨመር ብሎም የዘርፉን ልማት ለመደገፍ እንዲሁም አምራች ኢንዱስትሪዎችን በጥራትና በቁጥር ለማሳደግ የሚያስችሉ ተግባራት የሚከናወኑበት ሲሆን፣ የኢንዱስትሪ ዘርፉን ከተለመደው አሰራር በማሻገር ምርታማነትን ለመጨመር እንደሚያግዝ ታምኖበታል:: በአሁኑ ወቅት ኢንዱስትሪዎች ለአገር ውስጥ ምርት እድገት እያበረከቱት ያለውን አነስተኛ አስተዋፅኦ እንደሚያሳድግም ተስፋ ተጥሎበታል::
ክልሎች በኢንቨስትመንት አቅሞቻቸውና ሌሎች ነባራዊ ሁኔታዎቻቸው ላይ ተመስርተው ‹‹ኢትዮጵያ ታምርት›› አገራዊ ንቅናቄን የተገበሩ ሲሆን ንቅናቄው በኢንዱስትሪው ዘርፍ ያጋጠሙ ችግሮችን በቅንጅት በመፍታት ውጤታማ ስራ መስራት እንዳስቻላቸውና በንቅናቄው ትግበራም አበረታች ውጤቶችን እያገኙ እንደሆነ ገልጸዋል:: ንቅናቄው በአማራ ክልል የአምራች ኢንዱስትሪዎችን ችግር በማቃለል ረገድ ከፍተኛ አስተዋፅኦ እያበረከተ ይገኛል::
እንደ እሳቸው ማብራሪያ፤ ንቅናቄው በክልሉ መተግበሩ ብዙ የአምራች ዘርፍ ችግሮች እንዲቃለሉ እገዛ አድርጓል:: ባለድርሻ አካላትን በማቀናጀት የዘርፉን ማነቆዎች የመፍታት ዓላማ ስላለው የአምራች ዘርፉ ተዋንያን የተሻለ ቅንጅት እንዲኖራቸው አስችሏል:: ስለዘርፉ ችግሮች ከባለሀብቶች ጋር ለመወያየት የሚያስችል እድል ፈጥሯል:: የፋይናንስ፣ የመሰረተ ልማት ችግሮችና ሌሎች እጥረቶች ተለይተው እንዲቃለሉ አግዟል:: በንቅናቄው አዳዲስ ባለሀብቶች ወደ አምራች ዘርፉ እንዲገቡ ለማድረግ በተከናወኑ ስራዎችም ብዙ ባለሀብቶች ወደ ክልሉ እንዲሰማሩ ማድረግ ተችሏል:: ድጋፍና ክትትል በማድረግና ርምጃ በመውሰድ ከዚህ ቀደም የነበረውን የባለሀብቶች መሬት ወስዶ አጥሮ የማስቀመጥ ድርጊት ለማስተካከል ጥረት ተደርጓል::
የሲሚንቶ አቅርቦት ችግር ቢፈጥርም በዚህ ጥረት ብዙ ተቋማት ግንባታ እንዲጀምሩና ወደ ምርት እንዲገቡ ማድረግ ተችሏል:: ዩኒቨርሲቲዎች የአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፉ በጥናት መደገፍ እንዳለበት ትኩረት በመስጠት ብዙ ድጋፎችን አድርገዋል:: በአጠቃላይ በኢትዮጵያ ታምርት›› ንቅናቄ የተፈጠሩ እድሎችን በመጠቀም በአምራች ዘርፉ የተሻለ ውጤት ማስመዝገብ ተችሏል:: የንቅናቄው ተግባራት በሂደት በክልሉ ብሎም በአገር አቀፍ ደረጃ መዋቅራዊ የምጣኔ ሀብት ሽግግር እውን እንዲሆን ያስችላሉ ብለዋል::
በአጠቃላይ በአማራ ክልል ባለፉት ዘጠኝ ወራት በኢትዮጵያ ታምርት›› ንቅናቄ፣ በኢንቨስትመንት ፕሮሞሽን፣ በአስፈፃሚ ተቋማት ትብብር በተከናወኑ ተግባራት አማካኝነት በአምራች ዘርፉ ካለፉት ዓመታት የተሻለ አፈፃፀም ማስመዝገብ መቻሉ ምክትል ስራ አስኪያጁ አስታውቀዋል::
አንተነህ ቸሬ
አዲስ ዘመን ግንቦት 24/2015