አብርሃም የራስወርቅ መስማት የተሳነው ወጣት ቢሆንም ቤተሰቦቹ ለእሱ የአካል ጉዳት ይመጥናል ወዳሉት ትምህርት ቤት ከመላክ ወደ ኋላ አላሉም:: ወጣት አብርሃም የሚችለውን ያህል ታግሎ በብዙ ውጣ ውረድ አልፎ ከክፍል ክፍል እየተዘዋወረ የአስረኛ ክፍል ትምህርቱ ላይ ቢደርስም ከዛ በኋላ ግን ውጤት አምጥቶ ከፍተኛ ትምህርት ተቋምን መቀላቀል ሳይችል ቀረ:: ይህም ሁኔታ ለእሱና ለቤተሰቦቹ ቀላል አልነበረም፤ እጅግ ተስፋ አስቆራጭና ቀጣዩ ጊዜ ምን እንደሚሆንና ምን እንደሚፈጠር ለመገመት የሚከብድ ሆነ::
ወጣት አብርሃም በትምህርቱ መቀጠል የማይቻል መሆኑን ሲረዳ ከጓደኞቹ በታች ሆኖ ተሰማው:: በተለይም አካል ጉዳቱ እየተሰማው የሚፈልገውን ሳያገኝ ወይም ሳያደርግ ወጣትነቱ ሊያልፍ መሆኑን እያሰበ መጨነቀቁ አልቀረም:: ነገር ግን “ሳይደግስ አይጣላም” ይሉት አይነት ነገር ሆነና ያላሰበው የስራ አማራጭ በጓደኛው አማካኝነት ወደ እሱ መጣ:: ይህንን አጋጣሚም በከንቱ ለማሳለፍ ያልፈለገው ወጣት አብርሃም ወደተባለው ስራ በመሄድ ተመዘገበ::
ወጣት አብርሃም በትምህርቱ ውጤት ማምጣት አቅቶት ቤት ቁጭ ባለበት ሁኔታ ከጓደኞቹ የሰማው ኮካ ኮላ ቢቨሬጅስ አፍሪካ -ኢትዮጵያ ከኢትዮጵያ ወጣት ሴቶች ማቋቋሚያ ማህበር ጋር በመተባበር ለ 50 መስማት የተሳናቸው ወጣቶች በቀርከሃ ስራ ሙያ ለሶስት ወራት አሰልጥኖ ወደስራ ሊያስገባ መሆኑ ነው:: ይህ ትልቅ ተስፋ ያጫረበት ወጣት አብርሃም ጊዜ ሳያጠፋ በመመዝገብ ስልጠናውን አገኘ::
“…..መስማት የተሳነን ወጣቶች ብንማርም ያን ያህል ውጤታማ ለመሆን አልቻልንም፣ ነገር ግን እንደዚህ ዓይነት የሙያ ስልጠናዎች ጥሩ ከመሆናቸውም በላይ በቀላሉ ለስኬት የሚያበቁም ናቸው:: እኔም በሰለጠንኩበት ሙያ ጠንክሬ በመስራት ራሴን ከመለወጥ ባሻገር እኔን መሰል ጓደኞቼን በአቅሜ ለመደገፍ ተነስቻለሁ” ይላል አብረሃም ስልጠናውን ካጠናቀቀ በኋላ::
አሁን ላይ ኮካ ኮላ ፋብሪካ ይህንን መሰል ስልጠና ሲያመቻች መንግስት ደግሞ የማምረቻና የመሸጫ ቦታ የሰጣቸው መሆኑ ደግሞ ወደፊት ሰርቶ የመለወጥ ከፍተኛ ፍላጎትና ተነሳሽነት እንዲያድርባቸው ስለማድረጉም ያብራራል::
ሌላኛዋ ወጣት ራሄል ወንደሰን እሳም መስማት የተሳናት ስትሆን እንደ ወጣት አብርሃም ሁሉ በቀርከሃ ሙያ ስልጠናን አግኝታለች:: ወጣት ራሄል በማህበራዊ ድረ ገጽ ባገኘችው መረጃ መሰረት ስልጠናውን ለመውሰድ መመዝገቧን በማስታወስ በቀርከሃ ሙያ ሊያሰራት የሚችል እውቀት ስለመጨበጧም ታብራራለች::
ከስልጠናው ባሻገር መንግስት ያመቻቸው የማምረቻና የመሸጫ ቦታ በእጅጉ እንዳስደሰታት የገለጸችው ወጣት ራሄል፣ በቀጣይም ከመሰሎቿ ጋር ጠንክራ በመስራት ከቤተሰብ ጥገኝነት ተላቃ ትልቅ ደረጃ የመድረስ ህልም እንዳላት ተናግራለች::
ኮካ ኮላ ቤቨሬጅስ አፍሪካ- ኢትዮጵያ ለሶስት ወራት ያሰለጠናቸውን 50 መስማት የተሳናቸው ወጣቶችና ሴቶች በቀርቅሀ እደጥበብ ሙያ አሰልጥኖ ማስመረቁ ወጣቶቹ ቋሚ ገቢ ማግኘት እንዲችሉ ከማድረጉም በላይ በተለይም አካል ጉዳታቸው ሳይገድባቸው በቀርቀሃ እደጥበብ ወንበሮች፤ ጠረጴዛዎች፣ አልጋ ፣ የሶፋ ቅርጫቶች እና የአበባ ማስቀመጫዎችን ጨምሮ የቤት ዕቃዎችን እንዴት መስራት እንደሚችሉ በተግባር ያሳዩበት መሆኑ ተገልጿል:: ይህም ማህበራዊ ግንኙነታቸው የጠነከረ እንዲሆን እና በኢኮኖሚ ራሳቸውን እንዲችሉ የሚያደርግ እንደሆነም ተጠቁሟል::
የወጣቶቹን ስልጠና መጠናቀቅ ተከትሎ በተዘጋጀው መርሀ ግብር ላይ የተገኙት የስራና ክህሎት ሚኒስትር ዴኤታው አቶ ንጉሱ ጥላሁን፤ ልዩ ድጋፍ ለሚሹ የህብረተሰብ ክፍሎች የስራና ስልጠና እድል ማመቻቸት የሚደገፍ ተግባር መሆኑን ተናግረዋል። ኮካ ኮላ ለእነዚህ የህብረተሰብ ክፍሎች ያደረገውን ድጋፍ የስራና ክህሎት ሚኒስትር በማበረታታት ሌሎች ድርጅቶችም በአርአያነት በመከተል ሊሰሩ እንደሚገባቸው አቶ ንጉሱ አስረድተዋል::
የኢትዮጵያ ወጣት ሴቶች ማቋቋሚያ ማህበር ስራ አስኪያጅ መምህር መንግስቱ ጥላሁን በበኩላቸው፣ ማህበሩ ከ3 አስር ዓመታት በላይ በስራ ላይ የቆየ መሆኑን በማስታወስ በእነዚህ ጊዜያት ውስጥም አቅም የሌላቸውን ሴቶችና ወጣቶችን በመደገፍ እንዲሁም ራሳቸውን የሚችሉበትንና የሚለወጡበትን ስራዎችን ፈጥሮ በማሰማራት የላቀ ስም ያለው መሆኑን ያብራራሉ::
እንደ መምህር መንግስቱ ገለጻ ማህበሩ በስራው ላይ በርካታ ችግሮች መውደቅ መነሳቶች ቢያጋጥሙትም አቅመ ደካማ የሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎች ሰልጥነው ራሳቸውን ይችሉ ዘንድ በርካታ ጥረቶችን ስለማድረጉ ተናግረዋል::
‹‹ኮካ ኮላ ፋብሪካ ከማህበሩ ጋር በመተባበር መስማት የተሳናቸውን 50 ወጣት ወንድና ሴቶችን በቀርከሃ ሙያ አሰልጥኖ ወደ ስራ እንዲገቡ ስላደረገልን ትልቅ ምስጋና አለን፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ባህልና ቱሪዝም ቢሮ የስልጠናው ደጋፊ መሆኑም ለሙያውም ሆነ ለወጣቶቹ ጠቃሚ በመሆኑ ምስጋና ይገባቸዋል›› ሲሉም መምህር መንግስቱ ገልፀዋል::
ለሰልጣኝ ወጣቶቹ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርና የቂርቆስ ክፍለ ከተማ የማምረቻና መሸጫ ሼዶችን መፍቀዱ በተለይም ማህበሩ እስከ ዛሬ ድረስ ሲሰራ የገጠሙትን ችግሮችና በሙሉ የሚያካክስና ለወደፊቱም ለትልቅ ስራ የሚያነሳሳ እንደሆነም አክለዋል::
የኮካኮላ ቤቬሬጅስ አፍሪካ ኢትዮጵያ ማጂንግ ዳይሬክተር ዳረል ዊልስን ባደረጉት ንግግር፤ ስልጠናው ተቋማቸው ወጣት አካል ጉዳተኞች እና ሴቶች በኢኮኖሚ የተካተቱ እንዲሆኑ ማድረግ ከሚሰራቸው ስራዎች አንዱ መሆኑን አስረድተዋል:: ሴቶች፣ ወጣቶች እና አካል ጉዳተኞች ቀጣይነት ባላቸው የኢኮኖሚ አካታች ፕሮግራሞች አካል ሆነው የተሻሉ ዕድሎችን እንዲያገኙ ለማድረግም ተቋሙ እየሰራን እንደሚገኝ ጠቁመዋል:: እንደ ዳይሬክተሩ ገለፃ፤ የሚዘጋጁ የስራ ፈጣሪነት መርሃ ግብሮች ተጠቃሚዎች የራሳቸው የሆነ የንግድ ስራን ይበልጥ ለማሳደግ የሚረዱ ሆነው የተቀረጹ ናቸው:: ድርጅቱም በዘርፉ ላይ ያለውን ተጽዕኖ ፈጣሪነት በመጠቀም ለማህበረሰቡ የመፍትሔ አካል በመሆን በዓለም ላይ አዎንታዊ ለውጥ ለማምጣት ቀጣይነት ያለው ለሁሉም ምቹ የሆነ ነገን ለመገንባት እየሰራ ይገኛል:: ‹‹ዓላማችን ከንግድ ስራችን እና ከእሴቶቻችን ተጠቃሚ ለሆኑ ማህበረሰቦች የበለጠ የጋራ እድልን መፍጠር ነው›› ሲሉም ዳይሬክተሩ ተናግረዋል::
እፀገነት አክሊሉ
አዲስ ዘመን ግንቦት 24/2015
አዲስ ዘመን ግንቦት 24/2015