አገር የሚጸናው በዜጎች ባለቤትነትና ተሳትፎ ነው:: ስለአገራቸው የሚቆረቆሩ ዜጎች ባሉበትና በማንኛውም ጉዳይ ላይ በባለቤትነት የሚሳተፉ ዜጎች በበዙበት አገር ላይ ልማት ይስፋፋል፤ ሰላም ይሰፍናል፤ ብልጽግና ያብባል:: በተቃራኒው የሕዝቦች ተሳትፎ በቀነሰበት፤ ጉዳዮችን ሁሉ ለአንድ አካል የሚሰጡና ኃላፊነታቸውን ለመወጣት በሚሸሹ ዜጎች በበዙበት አገር ህገወጥነት ይስፋፋል፤ ወንጀል ይበራከታል:: ማህበራዊ ቀውስ ይሰፍናል:: ስለዚህም ለአንድ አገር እድገትና ብልጽግና በማንኛውም መልኩ የዜጎች ተሳትፎ መተኪያ የሌለው ነው::
ማንኛውም ወንጀልና ህገወጥ ድርጊት ከሕዝብ የተሰወረ አይደለም:: ሕዝብ የማይሰማው፤ ህዝብ የማያየው ሁኔታና ድርጊት የለም:: ለዚህም ነው ሕዝብ ያመነበትና የተሳተፈበት ነገር ሁሉ ውጤት የሚያመጣው:: በተለይም ሕዝብና መንግስት እጅና ጓንት ሆነው የተሳተፉባቸው እንቅስቃሴዎች ሁሉ ውጤት ማምጣታቸው፤ ፍሬ ማፍራታቸው አይቀርም::
ከዚህ አንጻር ሰሞኑን የአዲስ አበባ ጸጥታ ቢሮ ከህዝቡ ጋር በመቀናጀት በህገወጥ ጫኝና አውራጆች ላይ የወሰደው እርምጃ ዕውቅና ሊሰጠው የሚገባው ተግባር ነው:: ከህዝብ በቀረበ ጥቆማ በቁጥጥር ስር የዋሉት እነዚህ ህገወጥ ድርጊት ፈጻሚዎች ለዘመናት ሕዝብን ሲያማርሩ የቆዩ ናቸው:: በኢ-መደበኛ በሆነ መንገድ በመደራጀት ህብረተሰቡን ከፍተኛ ዋጋ የሚጠይቁ የነበሩት እነዚሁ ህገወጦች በአብዛኛው በኮንዶሚኒየም አካባቢዎች በስፋት በመንቀሳቀስ ህብረተሰቡን ከ90ሺሕ እስከ 100ሺሕ ብር በመጠየቅ ለከፍተኛ ማማረር እና አላስፈላጊ የፀጥታ ችግር ሲፈጥሩ የቆዩ ናቸው::
እነዚህም ያልተገባ ዋጋ መጠየቅ፣ የተገልጋዩን ዕቃ ከመኪና አውርዶ በመጣል በመሰባበር ተገልጋዩ መብት እንደሌለው አድርገውም ሲቆጥሩ የቆዩ ናቸው:: ኅብረተሰቡ ባደረገው ጥቆማም ችግር ሲፈጥሩ የነበሩ 44 ማህበራት እና 505 አባሎቻቸውን በህግ የመጠየቅ ስራ መከናወኑን እንዲሁም 97 ግለሰቦች በህግ ጥላ ስር እንዲውሉ ተደርጓል::
በተመሳሳይ መልኩ ከወረዳ ጀምሮ በየደረጃው የሚታዩ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመቅረፍ የሕዝቡ ተሳትፎ ወሳኝ ነው:: ከመታወቂያ አሰጣጥ ጀምሮ በደንብ ማስከበር፤ በቤቶች አሰጣጥ፤ በግንባታ ፍቃድ፤ በመሬት አቅርቦትና በመሳሰሉት ዘርፎች የሚስተዋሉ ችግሮችን ለይቶ በማውጣትና ያልተገባ ድርጊት ፈጻሚዎችን በማጋለጥ ረገድ ሕዝብ የሚጫወተው ሚና መተኪያ የሌለው ነው::
በተለይም በአሁኑ ወቅት የኑሮ ውድነቱን ከተገቢው በላይ የሚያጦዙና ከኅብረተሰቡ ችግር ማትረፍ የሚፈልጉ ስግብግብ ነጋዴዎችን በማጋለጥና ለህግ እንዲቀርቡ ማድረግ የሚቻለው ሕዝብ ሲተባበር ብቻ ነው:: በኅብረተሰቡ ላይ የኑሮ ጫና እየፈጠሩ የሚገኙ ህገወጥ ነጋዴዎች በሰዓታት ልዩነት የሸቀጦች ዋጋ እንዲንር በማድረግ ኅብረተሰቡን ለምሬት መዳረጋቸው የዕለት ተዕለት ተግባራቸው ቢሆንም የጊዜ ጉዳይ ካልሆነ በስተቀር ከሕዝብ አይን ሊያመልጡ አይችሉም:: ስለሆነም ለእነዚህ ስግብግቦችና ህገወጦች ጊዜ መስጠት የበለጠ ዋጋ ያስከፍላልና ሕዝቡ ነቅቶ ሊጠብቃቸው ይገባል::
ህገወጥነት በተስፋፋበት ሁሉ ሰላም ይደፈርሳል፤ ህግ ይዛባል፤ የዜጎች በሰላም ወጥቶ መግባት ይስተጓጎላል:: ይህ ሲሆን ደግሞ ህገወጦችና ሙሰኞች ምቹ መደላደል ይፈጠርላቸዋል:: እንደልባቸው ህዝብን እያማረሩ ሀብት ያጋብሳሉ፤ መደላድላቸውን ያጠናክራሉ፤ የሴራ ገመዳቸውን ያጠብቃሉ:: ስለዚህም እነዚህን ህገወጦችንና ህገወጥ ተግባራትን ሳይዘናጉ ማስተዋልና ችግሮች ተፈጥረው ሲገኙም ለሚመለከተው የመንግስት አካል ማሳወቅና አጥፊዎችም የእጃቸውን እንዲያገኙ ማድረግ የእያንዳንዱ ዜጋ ኃላፊነት ሊሆን ይገባል::
ህገወጦች ነፍስ የሚዘሩት ምንቸገረኝነት ሲሰፍን ነው:: አገር የዜጎች ናትና ህገወጥነትን አይቶ እንዳለየ ማለፍ ዜግነትን አሳልፎ መስጠትና ህገወጥነት እንዲስፋፋ ማድረግ መፍቀድ መሆኑም መረዳት ይገባል:: በየደረጃው የሚገኙ የመንግስት ኃላፊዎችም ቢሆኑ ከእያንዳንዱ ዜጋ የሚመጡ ጥቆማዎችን ዋጋ በመስጠት አጥፊዎች ተገቢውን ፍትህ እንዲያገኙ በማድረግ ረገድ ኃላፊነታቸውን ሊወጡ ይገባል::
በአጠቃላይ በምንቸገረኝነት የሚታለፉና የመንግስት ኃላፊነት ብቻ ተደርገው በቸልታ የሚታለፉ ህገወጥ ተግባራት በመጨረሻ የሚጎዱት አገርንና ሕዝብን ነው:: ስለዚህም ሕዝቡ በያገባኛል ስሜት በመንቀሳቀስ የሚታዩ ህገወጥ ተግባራትንና ብልሹ አሰራሮችን ሊታገልና መስመር ሊያሲዛቸው ይገባል!
አዲስ ዘመን ግንቦት 24 ቀን 2015 ዓ.ም