ሰላም የሁሉ ነገር መሰረት ነው ሲባል እንዲሁ ለማለት ያህል አይደለም፡፡ ይልቁንም ያለ ሰላም ሰርቶ ንብረት ማፍራት፣ በነጻነት ተንቀሳቅሶ የመኖር፣ ዘርቶ መቃምም ሆነ ወልዶ መሳም፣ ሌላው ቀርቶ በሕይወት የመኖር ዋስትናችን እንኳን ጥያቄ ውስጥ የሚገባ በመሆኑ እንጂ፡፡ ሰላም ሲጠፋ ግለሰባዊ አቅም ብቻ ሳይሆን አገራዊ ሕልውናም ይፈተናል፡፡ ኢኮኖሚ ይዳከማል፣ ሃብት ንብረት ይወድማል፣ ሰብዓዊ ጉዳቱም በተለይም በሴቶች፣ ሕጻናትና አቅመ ደካሞች ላይ እጅጉን ይከፋል፡፡
እኛ ኢትዮጵያውያን ደግሞ የሰላምን ከፍ ያለ ዋጋ ለመረዳት አህጉር ማቋረጥ ወይም ድንበር መሻገር አያስፈልገንም፡፡ በቤታችን በራሳችን የደረሰውንና የሆነውን ብቻ በእርጋታና አስተውሎት ማጤኑ ከበቂም በላይ ነው፡፡ ምክንያቱም በዘመናት ጉዟችን ውስጥ በተለያዩ ፍላጎቶች መነሻነት ከውጭ ወራሪ፣ ከውስጥም ባንዳ ጋር ያሳለፍናቸው አያሌ ጦርነቶች ያስከፈሉንን ቁሳዊም፣ ሰብዓዊም ዋጋ ታሪክ ከትቦ ያኖረው ነው፡፡
ሰላም ባጣው ዋጋ ልክ፣ ሰላም ርቆን፤ ባሳለፍናቸው ዓመታት፤ አደገ ያልነው አገራዊ ኢኮኖሚያችን እየተሽመደመደ ቁልቁል ሲወርድ፤ ተገኘ ያልነው የዴሞክራሲ ጭላንጭላችን እየደበዘዘ፤ አበበ ያልነው ዲፕሎማሲያችን እየሻከረ፤ ለአገር ዋልታ ይሆናል ያልነው ትውልዳችንን እየተቀጠፈ፤ ከትናንት እስከዛሬ በሚገለጸው ጉዟችን አያሌ ውጣ ውረዶችን አልፈናል፡፡
ይሄ ሁነት ግን ከዛሬ እንዲያልፍ መፍቀድ የለብንም፡፡ ድጋሚ የኢኮኖሚ ጉዟችን እንዲገታ፤ የዲፕሎማሲ መልካም ገጻችን እንዲጠለሽ፤ የዴሞክራሲ ጅምራችን እንዲከስም፤ ለአገር ብዙ መስራት የሚችለው የሰው ኃይላችን ለሌላ እልቂት እንዲዳረግ እሺ ማለት አይገባንም፡፡ የሰላምን ዋጋ ዘንግቶ መገኘትም፣ ሰላምን ገፍቶ ጦር መሻት፤ አንድነትና አብሮነትን አሻክሮ መለያየትን መዝራት፤ ልማትንና ብልጽግናን ቸል ብሎ ጉስቁልናን መናፈቅ ነው የሚሆነው፡፡
በየታሪክ ምዕራፎቻችን ያየናቸው ሃቆች፤ በየመንግስት ለውጣችን ያሳለፍናቸው መከራዎች፤ በየመሃሉም የሚነሱ የእኩይ ፍላጎቶች ውጤት የሆኑ ግጭትና ጦርነቶች የዚህ ምስክር ናቸው፡፡ የንጉሣውያንን ሥርዓት ለማስወገድ በሚል የጠፋው ንብረትና ወጣት፤ የደርግ ስርዓትን ለማስወገድ በሚል የወደመው ሃብትና የተሰዋው ትውልድ፣ የኢህአዴግን አካሄድ በመቃወምና ሥርዓቱን ለመለወጥ በተደረገው ትግል የደረሰውን ቁሳዊና ሰብዓዊ ጉዳት በልኩ መገንዘብ የሰላም ዋጋ ምን ያህል እንደሆነ ለማወቅ የሚሳን አይሆንም፡፡
ከዚህም በላይ በትግል የመጣውን ለውጥ ገና አጣጥመን ሳንጨርስ በሰሜኑም በምዕራቡም የነበረው ግጭት እና አስከፊ ጦርነት ያስከተለው እልቂትና ውድመት፤ ኢትዮጵያን እንደ አገር ኢትዮጵያውያንንም እንደ ሕዝብ ያስከፈለውን ዋጋ በቁጭት ልናስበው የሚገባ ነው፡፡ የዚህ ቁስል ገና ሳይሽር፤ ዛሬም በተለያዩ ቦታዎች የሚታዩ ችግሮች ደግሞ ሰላም ዛሬስ ምን ያህል ዋጋዋ ታውቋል? የሚል ጥያቄን ለማንሳት የሚያስገድድ ሃቅ ነው፡፡
እዚህ ጋር ልብ ያልተባለው ጉዳይ ቢኖር፤ የኃይል አማራጭና ጦርነት ምናልባት ሰላምን በጊዜያዊነት ሊያመጣ ይችል ይሆናል፡፡ ነገር ግን ሰላምን ዘላቂ ማድረግ የሚቻለው በአመጽ ወይም በጉልበት መንገድ ሳይሆን ቁጭ ብሎ በልዩነቶች ላይ መነጋገር እና ችግሮችን መፍታት ሲቻል ብቻ ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ የውጪም የውስጥም ተሞክሮዎች አሉ፡፡ አገራዊ የሽምግልና እና እርቅ ስርዓቶቻችንም ይሄን ለማድረግ አቅም የሚያንሳቸው አይደሉም፡፡
ትልቁ ነገር ሰላምን ሊያደፈርሱ የሚችሉ ችግሮቻችን ምንድን ናቸው? እነዚህን ችግሮች ወደ ጦርነትና ግጭት ከማምራታችን በፊት ተነጋግረን ልንፈታቸው እንዴት ይቻለናል? ወደ ግጭት ያመራንባቸውንስ ጉዳዮች በግጭት የባሰ ጉዳት ከመድረሱ በፊት በአጭሩ ማስቀረት የምንችልባቸው ምን አማራጮች አሉም ? የሚሉና መሰል ወደ ሰላም የሚወስዱን ጉዳዮች ላይ ማተኮሩ ነው፡፡
ይሄን ማድረግ ከቻልን ጦርነትን ማስቀረትና ሰላምን ማንገስ እንችላለን፤ ይሄን ማድረግ ከቻልን ልዩነቶችን እየፈለጉ በቁርሾ ከመኖር ወጥተን የአንድነት ገመዶቻችንን እያጎለበትን አብሮነታችንን የበለጠ እናጠናክራለን፤ ይሄን ማድረግ ስንችል በጦርነት የሚወድም ሃብት፣ በጦርነት የሚቀጠፍ ወጣትን አድነን ለአገር ልማትና ብልጽግና ማስፈንጠሪያ አቅም ማድረግ እንችላለን፡፡ በመሆኑም አገር እንድትበለጽግ፤ ትውልድም የአገር ጋሻ ሆኖ እንዲቀጥል ከሰላም መንገዳችን የሚያወጡንን ጉዳዮች በውይይት መፍታት ይኖርብናል፡፡ ለዚህ ደግሞ የሰላምን ዋጋ መዘንጋት፤ ሰላምንም ከሚዛኗ ማውረድ አይገባንም !
አዲስ ዘመን ግንቦት 23/2015