‹መማር ያስከብራል፤ አገርን ያኮራል› የሚለው ብሂል፤ ትምህርት ለግል አዕምሯዊ እድገት ብቻ ሳይሆን ለአገርም ምን ያህል ፋይዳ እንዳለው ያመላክታል። አገር በትምህርት ውስጥ የሚያልፉ ዜጎቿ በጨመሩ ቁጥር፣ ምክንያታዊ ትውልድን እያፈራች እድገትና ልማቷን የማፋጠን አቅሟ እየጨመረ ይሄዳል። እነዚህ ዜጎቿ ችግሯን የሚሸሹ፣ ሲከፋም ችግር የሚፈጥሩባት ሳይሆን በቅርብ ሆነው መፍትሄ የሚሰጡና የችግርን መፍቻ ቁልፍ የታጠቁ ናቸው። ይህ ሳይሆን ሲቀር ግን ዜጎች ለአገር ሸክም ይሆናሉ። የተሠራን የሚያጠፋና የሚያወድም ትውልድም ይፈጠራል።
ኢትዮጵያ በተለያዩ ክልሎች በጦርነት እና ግጭቶች የነገ ተስፋዎቿ የሚፈልቁባቸው በርካታ ትምህርት ቤቶቿ ወድመውባታል። እነዚህም የወደሙ ትምህርት ቤቶችን መልሶ ለመገንባትም ትምህርት ሚኒስቴር ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር ጥረት ማድረግ ከጀመረ ሰነባብቷል። በዚህም በተለያዩ ክልሎች በርካታ በከፊልና ሙሉ በሙሉ የወደሙ ትምህርት ቤቶች በተሻለ መልኩ ተመልሰው ተገንብተዋል። መልሶ ለመገንባት የመሰረት ድንጋይ የተቀመጠላቸው በርካታ ትምህርት ቤቶችም አሉ። ግንባታቸው ተጀምሮ በተለያዩ ችግሮች ያልተጠናቀቁም ጥቂት አይደሉም።
ወቅቱ የ2015 ዓ/ም የትምህርት ዘመን መገባደጃና ለ2016 የትምህርት ዘመን የምንዘጋጅበት እንደመሆኑ በመልሶ ግንባታው የተጀመሩ ትምህርት ቤቶችን ተረባርቦ ማጠናቀቅ የግድ ይላል። ያልተጀመሩትም በተቻለ ፍጥነት ወደ መልሶ ግንባታ እንዲገቡ ማድረግ ለነገ የሚተው የቤት ስራ አይደለም።
በጦርነት እና በተለያዩ ግጭቶች በአፋር፣ አማራ፣ ቤኒሻንጉል፣ ኦሮሚያ እና ደቡብ ክልሎች የወደሙ ከ1 ሺህ 300 በላይ ትምህርት ቤቶችን ለመገንባት ከ80 ቢሊየን ብር በላይ እንደሚያስፈልግ የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ መናገራቸው ይታወሳል። በአማራ ክልል ብቻ የወደሙ የትምህርት ተቋማትን መልሶ ለማቋቋም ከ11 ቢሊዮን ብር በላይ እንደሚያስፈልግ የትምህርት ሚኒስቴር መረጃ ያመለክታል።
በዚህ ረገድ ያልተጠናቀቁትን በፍጥነት ለማጠናቀቅና ግንባታቸው ያልተጀመረውንም ለማስጀመር የበጀት እጥረት ትልቅ እንቅፋት እንደሚሆን ቀድሞም የታወቀ ነው። ይህ ግዙፍ የቤት ስራ በትምህርት ሚኒስቴር ጫንቃ ላይ ብቻ ወድቆ የሚፈለገው ውጤት እንደማይመጣ ግልፅ ነው። ስለዚህ እስከ ቀጣዩ የትምህርት ዘመን ድረስ ካለው አጭር ጊዜ አኳያ ትምህርት ቤቶቹን ዝግጁ ለማድረግ የባለ ድርሻ አካላት ርብርብ ከምንጊዜም የበለጠ አስፈላጊ ነው።
ትምህርት ለሰው ልጆች ኑሮ ቅልጥፍና፣ ለአገር ዕድገትና ልማት፣ ባህልንና እውቀትን ከትውልድ ወደ ትውልድ ለማሸጋገር እንደ ድልድይ ሆኖ የሚያገለግል ስለመሆኑ ማንም ጥርጣሬ የለውም። ይህ ትምህርት ቤቶችን መልሶ የማቋቋም ትልቅ አገራዊ ኃላፊነትም የአንድ የመንግስት ተቋም ጉዳይ ብቻ የማይሆነውም ለዚህ ነው።
የዓለም ተምሳሌቱ የነፃነት ታጋዩ የደቡብ አፍሪካ የቀድሞ ፕሬዚዳንት ኔልሰን ማንዴላ በአንድ ወቅት ስለትምህርት ሲናገሩ፣ “ትምህርት ዓለምን ለመለወጥ ልትጠቀምበት የምትችለው በጣም ኃይለኛ መሣሪያ ነው” ያሉት ካለምክንያት አይደለም። ኢትዮጵያም በተለይም በዚህ ወቅት የገጠሟትን አገራዊ ችግሮች በዘላቂነት ፈታ የብልፅግና ጎዳናዋን ለማቅናት በትምህርቱ ዘርፍ ገና አውጥታ ያልተጠቀመችው ብዙ አንጡራ ሃብት አላትና ብዙ ትጠብቃለች። ለዚህ ደግሞ በቀጣይ ትውልድ ግንባታ ክፍተት እንዳይፈጠር የወደሙና የፈረሱ ትምህርት ቤቶችን በፍጥነት ጠግኖ ወደ ስራ ማስገባት የግድ ይላታል።
የትምህርት ተቋማቱ የደረሰባቸውን መጠነ ሰፊ ጉዳት መልሶ ለመገንባት በሚደረገው ጥረት የተለያዩ ግብረ ሰናይ ድርጅቶች፣ ባለሃብቶችና የኅብረተሰቡ ድርሻ የላቀ ነው። በመሆኑም ግብረ ሰናይ ድርጅቶች እና ሌሎች አጋር አካላት ድጋፋቸውን አጠናክረው ሊቀጥሉ ይገባል።
በዚህ ረገድ የዲያስፖራው እንዲሁም የባለሃብቶች ሚናም ግዙፍ እንደመሆኑ መጠን በአገር ውስጥም በውጭም ይህን ማስተባበር ከተቻለ ባለው አጭር ጊዜ የሚታይ ለውጥ ማምጣት እንደሚቻል ማስታወስ ተገቢ ነው።
ትምህርት ሚኒስቴር “ኑ የፈረሰውን የትውልድ ማፍሪያ ተቋም መልሰን እንገንባ !” በሚል መሪ ቃል የገቢ ማሰባሰቢያ ለማድረግ እንደ ኢትዮ-ቴሌኮም ከመሳሰሉ ትልልቅ አገራዊ ተቋማት ጋር ቀደም ሲል የጀመረውን እንቅስቃሴ በማስፋትና ከሌሎችም አቅም ያላቸው ተቋማት ጋር አጠናክሮ በመቀጠል ውጥኑን ከዳር ማድረስ እንዳለበትም ነጋሪ አያሻም !
አዲስ ዘመን ግንቦት 22/2015