ጸሐፊው በአፍሪካ የሳይንስ ከዋክብት (African Science Stars) በሚዘጋጀው፣ ታዋቂውና ተነባቢው AFRICAN SCIENCE STARS (Issue 4፣ ኦክቶበር 17, 2022) መጽሔት ላይ “The African New Year starts in September” በሚል ርእስ ለንባብ ባበቁት ምርምራዊ ጽሑፋቸው ላይ እንዳሰፈሩት የአፍሪካዊያን አዲስ አመት መግቢያ ሌላ ሳይሆን መስከረም፤ የዘመን መቁጠሪያውም ግሪጎሪያን ሳይሆን ጁሊያን ነው። በቃ፣ ይኸው ነው።
ይህ የማይነቃነቁ፣ የማያሻሙና ሳይንሳዊ መረጃዎችን ይዞ አለም አደባባይ የወጣው የምቶኮዚስ (Mthokozisi Mdlalose, PhD) ስራ ኢትዮጵያን በማሳያና ማስረጃነት እያቀረበ የተቀሩት የአፍሪካ አገራት ወደ’ዚሁ፣ ኢትዮጵያ ወደ ምትከተለው የአዲስ አመት መግቢያ (መስከረም)ና የዘመን አቆጣጠር (ጁሊያን) ማንነታቸው እንዲመለሱ በጥብቅ ያሳስባል። (ስለ ወርሀ መስከረም በሚገባ ለመረዳት የዶ/ር ሀብተማርያም አሰፋን “የኢትዮጵያ ታሪክ ጥያቄዎችና ባህሎች”ን፤ ስለቀደምት ኢትዮጵያዊያን የህዋ ሳይንስ ሊቃውንት ችሎታና ስራዎች የዶ/ር ሮዳስ ታደሰን (“አንድሮሜዳ”ን ጨምሮ) ፤ ስለ ባህረ ሀሳብ ተመራመሪዎቹ (አባትና ልጅ) አቶ ያሬድ እና ሄኖክ ያሬድን ስራዎች ይመለከታል።)
በርካታ ጥናቶች ይህንኑ የሚያረጋግጡ መሆኑን የሚናገሩት፣ በዩኒቨርሲቲው የአስትሮፊዚክስ የምርምር ማእከል (ARC) ባልደረባ የሆኑት ምቶኮዚስ ጉዳዩን በሚገባና በስፋት ያብራራውን የምርምር ስራ (African Cultural Astronomy: Current Archaeoastronomy and Ethnoastronomy Research in Africa መጽሐፍ)ንም አንባቢ እንዲመረምረው በጥብቅ ያሳስባሉ።
የአፍሪካ አገራት በቅኝ አገዛዝ ዘመን የተነጠቁት ሀብትና ንብረታቸውን፣ መሬትና ማንነታቸውን ብቻ ሳይሆን ባህልና ታሪካቸውን ጭምር ነው የሚለው ይህ የጸሐፊው ጽሑፍ አሁን ያንን የተነጠቁትን ማንነታቸውን የማስመለሻ ጊዜ መሆኑን፤ በርካታ የአፍሪካ አገራትም የአውሮፓዊያኑ ዘመን አቆጣጠር ተከትለው የሚያከብሩትን አዲስ አመት ማቆም እንዳለባቸው “African people must stop using the Northern Hemispher-based calendar.” ሲሉም የግዴታ ያህል ያሳስባሉ። በአህጉሪቱ ከቅኝ አገዛዝ በፊትና በኋላ ያለውን የአዲስ አመት አቀባበል በማስረጃ ይገልፃሉ። በመሆኑም፣ ለራሳቸው ጉዳይና አላማ ሲባል በ1582 በፖፕ ግሪጎሪ XIII ከተዘጋጀው Gregorian የዘመን አቆጣጠር ወደ ነባሩና አፍሪካዊው ጁሊያን መመለስ የግድና አሁን ሲሆን፤ እንቅስቃሴውም ተጀምሯል።
በእውቁና የደቡብ አፍሪካው ኩዋዙሉ ዩኒቨርሲቲ (University of KwaZulu-Natal) የአስትሮኖሚና አስትሮፊዚክስ ምሁር የሆኑት ዶ/ር ምቶኮዚስ ምድላሎስ ስለ መስከረም ምንነት፣ ስለ ወቅቶች መፈራረቅ፣ ስለ አፍሪካ ቱባ ባህል፤ ስለ ኢትዮጵያ ወግና ባህል ጠባቂነት፤ ስለ አስትሮኖሚና አስትሮፊዚክስ ወዘተርፈ ብትንትን አድርጎ በሚገልፀው ስራቸው የአፍሪካን የመጪው ጊዜ ብሩሀማነት ከወዲሁ የሚያሳየው (Africa’s future is astronomically bright. ይሉታል)፤ የአስትሮኖሚ ሳይንስ ለአፍሪካ ብርቅ አለመሆኑንና አህጉሪቱ ለሌላው አለም ጭምር መትረፏን (ወሳኝ ሚናውም በሰው፣ በተፈጥሮ እና በአጠቃይ ኮስሞ መካከል ሚዛን የመጠበቅ፣ ስምም የማድረግ መሆኑን “its role was crucial in bringing balance and harmony between nature, people, and the cosmos.” በማለት የሚገልፀው) በሚመሰክረው፤ ቀኝ ገዥዎች ሆን ብለው አፍሪካዊያንን አንድ የሚያደርጋቸውን፣ ይህንን የመሰለ የአስትሮኖሚ እሴታቸውን ማውደማቸውን በሚያስረዳው በዚህ ጽሑፋቸው ቁጭታቸውንም እንዲህ ሲሊ ይገልፁታል፤
ቅኝ ግዛት አፍሪካን ያላደረገው ነገር የለም። ዘረፋው በከብትና ንብረት፤ መሬት ብቻ የተወሰነ አልነበረም፤ የአፍሪካና አፍሪካውያንን ባህልና ታሪክ በራሱ አምሳል ወደ’ሚፈልገው አቅጣጫ ቀይሯል። አፍሪካዊያንን ከራሳቸው፣ ከስረ መሰረታቸም ነጥሏል፤ ማንነታቸውን አሳጥቷል። በመስከረም መከበር ያለበት የአፍሪካ አዲስ አመትም የዚሁ የማንነት ነቀላ ውጤት ነውና ሊስተካከል የግድ ነው። (ለዝርዝሩ የመጽሔቱን ገጽ 33 ይመልከቱ።)
አላማው “ሳይንስን፣ ቴክኖሎጂን፣ ኢንጂነሪንግን፤ እንዲሁም፣ የሂሳብ ትምህርትን (በምሕጻረ ቃል ውክልናው “STEM”) በመላ አህጉሪቱ ተደራሽ ማድረግና በዘርፉፎቹ እውቀትን ማስፋፋት”፤ ማንነትን ማወቅ … የሆነውን፣ ይህንን መጽሔት ከተቋሙ ድረ-ገፅ (www.africansciencestars.com) ሙሉውን በማውረድ ማንበብ የሚቻል ሲሆን፤ በዛው ልክም መሳተፍና ይህንኑ ጸሐፊውና መጽሔቱ ጉዳዬ ብለው የያዙትን፤ ከፍ አድርገው ያውለበለቡትን ርእሰ ጉዳይ (“የአፍሪካዊያን አዲስ አመት መግቢያ መስከረም ወር ነው” የሚለውን) መደገፍ፣ የበለጠም ማብራራትና እኛ አፍሪካዊያን ወደ ሙሉ አፍሪካዊነታችን እንመለስ ዘንድ አስፈላጊውን ጥረት ማድረግ፣ በተለይ በማሳያነትና ተገቢ ምሳሌነት ከቀረብነው፣ ከእኛ (ሌሎችም አሉ) ከኢትዮጵያዊያን ይጠበቃል።
ባጠቃላይ፣ ከላይ ለመጠቆም እንደተሞከረው፣ በተለይ የእኛዎቹ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት፣ የባህልና ቱሪዝም ቢሮዎች፤ የተለያዩ ማህበራዊ ድረ-ገፆች ተሳታፊዎች፣ ግለሰብ ተመራማሪዎችና ሌሎች የሚመለከታቸው ሁሉ ከዩኒቨርሲቲውና መጽሔት ዝግጅት ክፍሉ ጎን ሊቆሙኑ፤ ማብራሪያና መረጃ ሊያቀርቡ፤ የማህበራዊ ሚዲያዎቹን እንቅስቃሴዎች ሊደግፉ ይገባል። ይህ ከሆነ ልክ “ኢትዮጵያዊነት” (Ethiopianism) ከነጭ አገዛዝ ለመገላገል መታገያ ሆኖ እንዳገለገለው ሁሉ፤ ይህ “የአዲስ አመት አቀባበል” (የመስከረም) ጉዳይም የነጭ የበላይነትና ስተሳሰብ (ጠባሳውን ጭምር) ከአፍሪካ ምድር ጠራርጎ ለማውጣት ይጠቅማልና ጉዳዩን ቸል ልንለው አይገባም።
ግርማ መንግሥቴ
አዲስ ዘመን ሰኞ ግንቦት 21 ቀን 2015 ዓ.ም