የቀደሙት አፍሪካውያን አባቶቻችን በጸረ-ቅኝ ግዛት ትግላቸው ጭቆናን በሁለንተናዊ መልኩ በማስወገድ የተሟላ የነጻነት አየር የሚነፍስባት አህጉር ለመፍጠር ባላቸው አቅም፤ከፍባለ ቁርጠኝነት ተንቀሳቅሰዋል። ለዚህም ትግሉ የጠየቀውን መስዋእትነት በተነቃቃ መንፈስና በልበ ሙሉነት ከፍለዋል።
በተስፋ የተሞሉ ነገዎችን ለራሳቸውና ለመጪዎቹ አፍሪካውን ትውልዶች፣ ብሩህ በሆነ አእምሯቸው፤ በተከፈቱ አይኖቻቸው በማየት፤ ገና ከጅምሩ የአሕጉሪቱ የነጻነት ትግል የተሟላ ሊሆን የሚችለው አፍሪካውያን የራሳቸውን እድል በራሳቸው የመወሰን አቅም መፍጠር ሲችሉ ብቻ እንደነበር አበክረው መክረዋል።
በወቅቱም አፍሪካውያን የራሳቸውን እድል በራሳቸው የመወሰን ብቃት እንዳላቸው፤ ይህንንም የሚሸከም የፖለቲካ ርእዮተ አለም /የፓን አፍሪካኒዝም አስተሳሰብን/ ፈጥረው ለተፈጻሚነቱም ብዙ ርቀት ተጉዘዋል። አስተሳሰቡ ከውጪም (ከቅኝ ገዥዎች)፤ ከውስጥም (ከባንዳዎች) ለተፈጠረባቸው ተግዳሮቶችም ብዙ ዋጋ ለመክፈል ተገደዋል።
ይህ የአፍሪካውያን የነጻነት መሻት የፈጠረው የሀሳብ ልእልና በርግጥም ቅኝ ገዥዎችም ሆኑ ዛሬ ላይ በተመሳሳይ አስተሳሰብ የተቃኙ ኃይሎች እንደሚያስቡት የአህጉሪቱ ህዝቦች ለአካለመጠን እንዳልደረሰ ህጻን ሞግዚት የሚፈልጉ እንዳልሆኑ፤ ለራሳቸው የሚሆናቸውን ማሰብና መፈጸም የሚያስችል መንፈሳዊ፣ ስነልቦናዊ፣ አእምሯዊ እና አካላዊ ብቃት እንዳላቸው በአደባባይ ያረጋገጠ ነው።
ይህ የነጻነት አባቶቻችን ዘመን ተሻጋሪ አስተሳሰብ ከሁሉም በላይ የአፍሪካውያን እጣ ፈንታ በራሳቸው እጅ ላይ መሆኑን፤ለዚህ የሚሆን ሁለንተናዊ ዝግጁነት እንደሚያስፈልጋቸው፤ ለዚህ ደግሞ ከሁሉም በላይ አንድ መሆን ወሳኝ መሆኑን ያመላከተ ነው። የአፍሪካ አንድነት ድርጅትን በውስብስብ ሴራዎች መሀል መፍጠር ያስቻለም፤ ከዚያም ባለፈ በዚህ ዘመን ላለው አፍሪካዊ መንፈሳዊ መነቃቃት እርሾ በመሆንም እያገለገለ ነው።
አፍሪካውያን ቀጣይ እጣ ፈንታቸውን ብሩህ ለማድረግ አንድነታቸውን በማጠናከር ተሰሚነታቸውን ማሳደግ እንዳለባቸው አመላክተዋል፤ የኢኮኖሚ ነጻነት የፖለቲካ ነጻነትን ያህል ጠንካራ ትግልና መስዋእትነት እንደሚፈልግ፤የፖለቲካ ነጻነት በጠንካራ ኢኮኖሚ ካልተደገፈ የተሟላ ትርጉም እንደማይኖረው ከፍ ያለ ትኩረት ሰጥተው ተንቀሳቅሰዋል። ይህንን ማድረግ ካልተቻለ ለፖለቲካ ነጻነት የተከፈለው መስዋእትነት ትርጉም ጎዶሎ መሆኑንም በየአደባባዮች ሰብከዋል።
ዛሬ ላይ የአፍሪካ ኅብረት 60ኛ ዓመት የምስረታ በአል ስናከብር ከሁሉም በላይ በነዚያ አፍሪካውያን የነጻነት አባቶች ሲቀነቀን የነበረው የፓን አፍሪካኒዝም እሳቤ እና በእሳቤው ውስጥ የነበረው ተስፋ ምን ያህል መሬት ወርዶ የአህጉሪቱን ህዝቦች የተስፋቸው ባለቤት አንዳደረጋቸው በማሰብ እንዲሁም አሁን ላይ ያለን የፖለቲካ ነጻነት ምን ያህል የተሟላ እና በዓለም አቀፍ መድረኮች ተሰሚነታችንን አጽንቷል የሚለውን በማጤን ሊሆን ይገባል።
አፍሪካውያን እንደ አንድ ትልቅ ህዝብ ብዙ መስዋእትነት ከጠየቀው የነጻነት ትግል ማግስት ጀምሮ እስከ ዛሬዋ ቀን ድረስ የመጡበት ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ መንገድ እራሳቸውን የመሆን መሻታቸውን ተጨባጭ ለማድረግ የቱን ያህል አቅም መፍጠር ችሏል ለሚለው ጥያቄም ተገቢውን ምላሽ ለመስጠት አሁን ካሉበት ጊዜ የተሻለ አይኖርም ።
ከነጻነት ማግስት ጀምሮ አህጉሪቱ የግጭትና የሁከት ማዕከል፤ የድሕነትና የጉስቁልና ትርክት ዋነኛ መገለጫ የመሆኗን እውነታ የቀደሙት የነጻነት አባቶች ለአህጉሪቱ ህዝቦች ተስፋ ካደገረጉት ብልጽግና አንጻር ልንገመግመው ይገባል፡፡ የመጣንበት መንገድ እያስከፈለን ያለውን ያልተገባ ዋጋ የሚያወግዝ ማህበረሰባዊ ሰብዕና መፍጠርም ይኖርብናል ፡፡
ለዚህም ግጭቶችን ማስወገድ፣ የዲሞክራሲ ምህዳርን ማስፋት፣ለኢኮኖሚ ነጻነት መትጋት፤ የምግብ ዋስትናን በማረጋገጥ ድህነትን ማሸነፍ ላይ ትኩረት ሰጥተን መስራት ይኖርብናል። ከሁሉም በላይ ለችግሮቻችን እንደማናንስ፤የራሳችንን እድል በራሳችን የመወሰን አቅሙም ብቃቱም እንዳለን በተጨባጭ ማሳየት፤ ለዚህ የሚሆንም ሁለንተናዊ ዝግጁነት ማድረግ ይጠበቅብናል!
አዲስ ዘመን ሰኞ ግንቦት 21 ቀን 2015 ዓ.ም