ቅርሶች የሚዳሰሱና የማይዳሰሱ ተብለው በሁለት ይከፈላሉ፡፡ የማይዳሰሱ ከሚባሉት ቅርሶች መካከል ባህላዊ ቅርሶች ይገኙበታል፡፡ እነዚህ ቅርሶች ከባህላዊ መገለጫቸው በተጓዳኝ በውስጣቸው ለዘመናት የካበተ ዕውቀት፣ ክህሎት፣ ጥበብና ተሞክሮ የሚገኙባቸው ናቸው፤ ይህ መገለጫቸው በማህበረሰቡ ውስጥ ጉልህ አበርክቶ ያለውና ማህበራዊ ፋይዳውም እጅግ የላቀ ነው።
ኢትዮጵያ በሁለቱም አይነት ቅርሶች በእጅጉ ትታወቃለች፤ በዚህም የቱሪስት መዳረሻ ሀገር በመሆንም ትታወቃለች፡፡ እነዚህን የሚዳሰሱና የማይዳሰሱ ቅርሶች መዝግቦ በማቆየት በኩል የኢትዮጵያ ቅርስ ባለሥልጣን ኃላፊነቱን ወስዶ እየሰራ ይገኛል፡፡
ባለሥልጣን መሥሪያቤቱ የማይዳሰሱ ቅርሶች ብሎ ከሚጠቅሳቸው መካከልም ምስጋና፣ መከባበር፣ ማድነቅ፣ ተሞክሮን ማካፈል፣ ወጣቱን ትውልድ መቅረጽና መልካምና በጎ የሆኑ ባህልና ወጎችን ለትውልድ ማስተላለፍ የሚሉት ጥቂቶቹ ናቸው፡፡ ይህንኑ መሠረት በማድረግም ‹‹በኢትዮጵያዊነት ባህልና ወግ አንጋፋዎቻችንን በማክበር ልምድ እንካፈል›› በሚል መሪ ሃሳብ ከሰሞኑ ባካሄደው መርሃግብር አንጋፋ የዘርፉ ባለሙያዎችን በማመስገን ዕውቅና ሰጥቷል፡፡
ምስጋናና እውቅና ከተሰጣቸው አንጋፋዎች መካከል አቶ ዓለሙ ሃይሌ አንዱ ናቸው፡፡ አቶ ዓለሙ፤ በባህል ሚኒስቴር መስሪያ ቤት ውስጥ ለ32 ዓመታት አገልግለዋል፡፡ እሳቸው እንዳሉት፤ በኢትዮጵያ ከሚዳሰሱ ቅርሶች የተለያዩ ሐውልቶችን ጨምሮ በቅዱስ ላልይበላ፣ ጎንደር፣ በሀረርና በሌሎች አካባቢዎች በርካታ የቱሪስት መስህቦች ይገኛሉ፡፡
ከእነዚህ በተጨማሪ በግዕዝና በአረብኛ ተጽፈው የተቀመጡ ልዩ ልዩ የጥንት ሥነጽሁፍና የታሪክ መጽሐፍት እንዳሉና እንዳልተተረጎሙ ነው የገለጹት። ሀገሪቱ እነዚህን ሀብቶች ለቱሪስት መስህብነት በመጠቀም ከዘርፉ ማግኘት የሚገባትን ጥቅም እንዳላገኘች በቁጭት አቶ አለሙ ይጠቁማሉ፡፡
እነዚህ መጻህፍት ወደ አማርኛ ተተርጉመው ቢቀርቡ ከፍተኛ ጠቀሜታ አላቸው የሚሉት አቶ ዓለሙ፤ ዘመናዊ ትምህርቱ በአብዛኛው በአንግሊዝኛ የሚሰጥ ስለሆነ አሁን ላይ ግዕዙን ብዙም የሚመለከተው እንደሌለ ይገልጻሉ፡፡ የግዕዝ ትምህርት በቤተክህነት ብቻ የሚሰጥ እንደሆነና ቤተክህነቱም ቢሆን በአሁኑ ወቅት እንደቀደመው ጊዜ አጠናክሮ ይዞታል ብለው እንደማያምኑ ተናግረዋል፡፡
ለዚህም ዋናው ምክንያት ትምህርቱ የሚሰጠው በገጠር ውስጥ እንደሆነና መምህራኑም በቂ ደመወዝ የሌላቸው መሆኑን ተከትሎ ወደ ከተማ እየመጡ በተለያዩ ሥራዎች እየተሰማሩ መሆናቸውን ይጠቁማሉ። ስለዚህ ቤተ ክህነቱም ሆነ ቤተመንግሥቱ ከቅርስ ጥበቃ ባለሥልጣን ጋር በጋራ በመተባበር በግእዙ የተጻፉ መጽሃፍት እንዲተረጎሙ መስራት እንደሚገባ ይጠቁማሉ፡፡ አቶ አለሙ ግዕዙ፣ አረብኛውና ሌሎችም የጥንት ቋንቋዎች እንዲጠኑና ምርምር በማድረግ ቢሠራባቸው በአገሪቱ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸውን ቱሪስቶች መሳብ ይቻላል ባይም ናቸው፡፡ ኢትዮጵያ በዘርፉ ትልቅ አቅምና እምቅ ሀብት አላት ብለዋል፡፡
ከሚዳሰሱ ቅርሶች በተጨማሪ ኢትዮጵያ በማይዳሰሱ ቅርሶችም ዕምቅ ሀብት እንዳላት የተናገሩት አቶ ዓለሙ፤ በተለይም አሁን አሁን እየጠፉ የመጡ በርካታ ባህልና ወጎች እንዲሁም እሴቶች ስለመኖራቸው ነው የሚናገሩት፤ የድሮ አባቶች እንዴት መኖር ፣ መሰልጠን፣ መሥራትና ማገልገል እንዳለብን በጥሩ ባህልና ወግ አስተምረው አልፈዋል ሲሉ ይገልጻሉ፡፡ ይህን በጎ ባህል አውጥቶ ለትውልዱ ማስተማር እንዳልተቻለ ጠቅሰው፤ አሁን ከባህልና ወግ ያፈነገጡ ችግሮች እዚህም እዚያም መታየታቸውም በዚሁ ምክንያት ነው ብለዋል፡፡
‹‹እርግጥ ነው ሁሉም ባህል፣ ሁሉም ቅርስ ጥሩ ላይሆን ይችላል›› የሚሉት አቶ ዓለሙ፤ ‹‹…ጥሩ ባህል አለ፤ መጥፎ ባህል አለ፤ ጥሩ ልማድ አለ፤ መጥፎ ልማድ አለ፤ ጠንቋይ ይኑር ነው ወይ ሰው እንዳታለለ›› የሚለውን የመንግሥቱ ለማን ሃሳብ አስታውሰው ጠቃሚ የሆኑ ባህልና ወጎችን በመለየት ብንንከባከባቸውና ወጣቶችን ብናስተምርባቸው አገር በብዙ ታተርፋለች ሲሉ አስገንዝበዋል፡፡
ሌላው ቀርቶ ከአበላል፣ ከአጠጣጥ፣ ከአቀማመጥና እንግዳ ሲመጣ እንዴት መነሳትና መቀበል እንዳለብን ጭምር አባቶች አስተምረው እንዳለፉ አመላክተው፣ አሁን ላለው ትውልድ እነዚህንና ሌሎች በጎና መልካም የሆኑ ዕሴቶችን ማስተማር እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል፡፡
የማይዳሰሱ ቅርሶች በተለይም ህዝብን በማስተሳሰር በማስተዋወቅና በማቀራረብ ረገድ ጉልህ ፋይዳ እንዳላቸው ጠቅሰው፣ መንግሥትን ጨምሮ፤ የኢትዮጵያ ቅርስ ባለሥልጣንና ትምህርት ቤቶችም ጭምር ብዙ ሊሠሩበት እንደሚገባና ኃላፊነት ያለባቸው መሆኑንም ነው ያስገነዘቡት፡፡
አቶ ዓለሙ፤ ግዕዝ የተማሩ በመሆናቸው 32 ዓመታት በባህል ሚኒስቴር ሲያገለግሉ የአማርኛ መዝገበ ቃላትን ጨምሮ የተለያዩ በግዕዝ የተጻፉ መጽሐፍቶችን ወደ አማርኛ ተርጉመው ለንባብ አብቅተዋል፡፡ እርሳቸው ያዘጋጁት የአማርኛ መዝገበ ቃላት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አማካኝነት ታትሟል። ስያሜ ክፍል በማገልገል ሁሉም የሳይንስና ቴክኖሎጂ ቃላትን ወደ አማርኛ ቋንቋ ተርጉመዋል፡፡ በርካታ ቁጥር ያላቸውን የግዕዝ መጽሐፍትንም እንዲሁ ወደ አማርኛ በመተርጎም የጎላ አስተዋፅኦ አበርክተዋል፡፡
ሌላኛው ከአንጋፋዎቹ መካከል ዕውቅናና ምስጋና የተቸራቸው አቶ ከበደ ገለታ የሂስቶሪካል አርኪኦሎጂ ባለሙያ ናቸው፡፡ ከ1975 ዓ.ም ጀምሮ በጡረታ እስከተገለሉበት 2010 ዓ.ም ድረስ በሙያው አገልግለዋል። የኢትዮጵያ የቅርስ አጠባበቅ የኢትዮጵያ ቅርስ እንዲጠበቅና ለትውልድ እንዲተላለፍ በማድረግ ሂደት ሥራው የተጀመረው በቤተመጽሐፍት ደረጃ እንደነበር አስታውሰዋል፡፡ ኢትዮጵያ የበርካታ ቅርስ ባለቤት ብትሆንም ብዙ አልተጠቀመችበትም፤ ለዚህም ምክንያቱ በዘርፉ የተማረ የሰው ኃይል ባለመኖሩ ምክንያት ነው ይላሉ፡፡
እሳቸው እንደሚሉት፤ የኢትዮጵያን ቅርስ የሚያጠኑት በአብዛኛው ነጮች ናቸው፡፡ ኢትዮጵያ በቅርስ ሀብቷ መጠቀም ያልቻለችው አንድም ዘርፉ በተማረና በሠለጠነ የሰው ኃይል መመራት ባለመቻሉ ነው፡፡ ወጣቱ ትውልድ በዘርፉ ሰልጥኖ ዘርፉን መምራት አለበት፡፡ ቅርስ እንዴት መጠበቅና መጠቀም እንዳለበት ትምህርትና ስልጠና ቢሰጠውና ዕውቀቱ ቢተላለፍ ኢትዮጵያ ከዘርፉ ይበልጥ መጠቀም ትችላለች፡፡
ወይዘሮ ቀለሟ መኮንን በኢትዮጵያ ቅርስ ባለሥልጣን የማይዳሰሱ ቅርሶች ከፍተኛ ተመራማሪ ናቸው፡፡ እሳቸው እንደሚሉት፤ ባለሥልጣን መስሪያ ቤቱ በዕለቱ አንጋፋዎቹን ማመስገንና ዕውቅና የሰጠው ከማይዳሰሱ ቅርሶች መካከል አንዱን የሆነውን የምስጋና ባህልን ለመተግበር ነው፡፡
የቅርስ ጥበቃ ባለሥልጣን መስሪያ ቤት ሥራው ከቅርስ ጋር የተገናኘ በመሆኑ ኢትዮጵያዊ ባህልና ወግ የሆኑ በጎ እሴቶችን አስጠብቆ ለማስቀጠል ይሠራል ያሉት ወይዘሮ ቀለሟ፣ ቅርሶችንም ተንሳቃሽና የማይንቀሳቀሱ በሚል ለይቶ እንደሚመዘግብ ይገልጻሉ፡፡
የማይንቀሳቀሱ ቅርሶች የሚባሉት ከመሬት ጋር ስሪት ያላቸው እንደ ሐውልቶች፣ መካነ መቃብሮች፣ የተለያዩ ህንጻዎችን፣ ላልይበላ፣ አክሱም ሐውልት፣ ፋሲል ግንብ የመሳሰሉት ናቸው፡፡ ተንቀሳቃሽ ቅርስ የሚባሉት ደግሞ በቀላሉ ከቦታ ቦታ መንቀሳቀስ የሚችሉ የቅርስ እሴት ያላቸው ናቸው፡፡ በዕለቱ ‹‹በኢትዮጵያዊነት ባህልና ወግ አንጋፋዎቻችንን በማክበር ልምድ እንካፈል›› በሚል መሪ ሃሳብ የተካሄደው የተቋሙ ፕሮግራም አንዱ ከማይዳሰሱ የቅርስ እሴቶች መካከል ይጠቀሳል፡፡
ኢትዮጵያ የሚዳሰሱ ወይም ቋሚ የሆኑ ቅርሶች በዩኔስኮ በማስመዝገብ ከአፍሪካ ቀዳሚ መሆኗን ጠቅሰው፣ እስካሁን ዘጠኝ የሚደርሱ ቋሚ ወይም የሚዳሰሱ ቅርሶችን በዩኒስኮ ማስመዝገቧን ወይዘሮ ቀለሟ ይገልጻሉ፤ በማይዳሰሱ የቅርስ ዘርፎች ደግሞ አራት የቅርስ እሴቶችን ማስመዝገቧን ተናግረው፣ በድምሩ በዩኒስኮ 13 የተመዘገቡ ቅርሶች እንዳሏትና በቀጣይም ሊመዘገቡ በሂደት ላይ ያሉ ተንቀሳቃሽና የማይንቀሳቀሱ ቅርሶች ስለመኖራቸው ተናግረዋል፡፡
ወይዘሮ ቀለሟ እንዳስታወቁት፤ ኢትዮጵያ የበርካታ ቅርሶች ባለቤት እንደመሆኗ እነዚህን በርካታ ቅርሶች ለትውልድ በማስተላለፍ ሂደት ውስጥ መንግሥትን ጨምሮ እያንዳንዱ ግለሰብ ኃላፊነት አለበት ፤ አንጋፋዎች ለወጣቱ የሚያስተላልፉት በርካታ ቁም ነገር እንዳለ ሁሉ ታላላቆችም ለታናናሾቻቸው መከባበርንና መታዘዝን ማስተማር ይኖርባቸዋል፤ በቅርስ ጥበቃና እንክብካቤ ከአንጋፋዎቹ ልምድ በመውሰድ ወጣቱ ትውልድ ኢትዮጵያዊ የሆኑ ቅርሶችን መጠበቅ፣ መንከባከብ፣ መጠቀምና ለቀጣዩ ትውልድ ማስተላለፍ ይኖርበታል፡፡
በተለይም የማይዳሰስ ቅርስ በዕለት ተዕለት የሕይወት እንቅስቃሴያችን የሚተገበር እንደመሆኑ ቀጣይነት ያለው ነው፡፡ ስለዚህ ይህን አይነት እንቅስቃሴና መስተጋብር ማጎልበት፣ ማሳደግና ማስቀጠል ይገባል፡፡ እንደ ቅርስ ጥበቃ ባለሥልጣን የተለያዩ በጎ እሴቶችን ከማስቀጠል አንጻር በርካታ ሥራዎች እየተሠሩ እንደሆነም ወይዘሮ ቀለሟ ገልጸዋል።
ከጥንት ጀምሮ የነበሩና በጎ እሴት ያላቸው ኢትዮጵያዊ ባህሎች አሁን አሁን እየተሸረሸሩ እንደሆነ በማንሳት እነዚህን ችግሮች ለመቅረፍ ግንዛቤ የማስጨበጥ ሥራ ይሠራል ሲሉም ጠቅሰው፣ ክፍተቶችን ለመሙላትም በየጊዜው የተለያዩ ሥልጠናዎችን እንዲሁም የፓናል ውይይቶች ይደረጋሉ ብለዋል፡፡ ትውልዱ ባህሉን እየተወና እየዘነጋ የመጣው ለምንድነው የሚሉ ጥያቄዎችን ለመመለስ ባለሥልጣን መስሪያ ቤቱ ትኩረት አድርጎ እየሠራ እንደሆነም ወይዘሮ ቀለሟ ተናግረዋል፡፡
ይህን አይነት ሥራ ለመሥራትም ፌዴራል ተቋሙ ብቻውን ሳይሆን ከክልሎች ጋር በመሆን እየሰራ ነው ያሉት ወይዘሮ ቀለሟ፤ በአሁኑ ወቅትም ዘመናዊነት ወጣቱ ላይ የሚፈጥረውን ጫና በጥናት በመለየት የተለያዩ ሥልጠናዎችን በመስጠት እንዲሁም ግንዛቤ በመፍጠር ነባሩ ትውፊት እንዲዳብርና እንዲቀጥል የማድረግ ሥራ በተለይም ከክልሎች ጋር እየተሰራ እንደሆነ ተናግረዋል። ይህም ባህልና ማንነት ያለውን ትውልድ ለመቅረጽ የሚያስችል እንደሆነም ነው የገለጹት፡፡
ዜጎችን ማብቃት ከስር እንደሆነ ያነሱት ወይዘሮ ቀለሟ፤ ትምህርት ቤቶች በተለይም ኢትዮጵያዊ የሆኑ በጎ ባህሎች እንዲጎለብቱና ቀጣይነት እንዲኖራቸው ትልቅ ኃላፊነት ያለባቸው በመሆኑ የቅርስና ባህል ክበባትን በማጠናከር ብዙ ሥራ ሊሠራ እንደሚገባም አመላክተዋል፡፡
ኢትዮጵያ ባላት የቅርስ መጠን ከዘርፉ መጠቀም እንዳልቻለች በብዙ ቢነገርም አበረታች ሥራዎች መሰራታቸውም አይካድም፡፡ በዘርፉ ከተሠሩ አበረታች ሥራዎች መካከል እ.ኤ.አ በ2003 ዓ.ም የወጣውን የማይዳሰሱ ቅርሶች ጥበቃ ስምምነት ሰነድ እ.ኤ.አ በ2006 ዓ.ም ኢትዮጵያ ተቀብላ ከፈረመች በኋላ በሀገር አቀፍ ደረጃ የሰባ ስድስት ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቅርሶች እንዲሁም በዓለም ወካይ ቅርስነት አራት ቅርሶች እንዲመዘገቡ ተደርጓል፡፡
እነዚህ በዓለም ወካይ ቅርስነት ከተመዘገቡት መካከልም የመስቀል በዓል አከባበር፣ የፍቼ ጨምበላላ / የሲዳማ የዘመን መለወጫ በዓል/፣ የገዳ-ሥርዓት /የኦሮሞ ባህላዊ የዴሞክራሲ አስተዳደር ሥርዓት/ እና የጥምቀት ክብረ-በዓል ናቸው፡፡
ቅርሶች ባህላዊ ይዘታቸውንና እሴታቸውን ጠብቀው ለትውልድ መተላለፍ እንዲችሉ በማድረግ በኩል መንግሥትን ጨምሮ ሁሉም ዜጋ ኃላፊነት ያለበት በመሆኑ ቅርሶችን በማወቅ፣ በመጠበቅ፣ በማስተዋወቅና ታሪክን በማቆየት ለሰው ልጅ የሚሰጡትን ጥቅም ማሳደግ ያስፈልጋል፡፡
ፍሬሕይወት አወቀ
አዲስ ዘመን ግንቦት 20 ቀን 2015 ዓ.ም