ባለፉት አምስት ዓመታት እንደ ሃገር በዓለም አቀፍ ደረጃ ውጤትና ሞገስ ካገኘንባቸው ጉዳዮች አንዱ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ አነሳሽነት የተጀመረው የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ነው። ዋነኛ ዓላማውም የሃገሪቱን አረንጓዴ ገጽታ በማላበስ ለዓለም ስጋት እየሆነ የመጣውን የአየር ንብረት ለውጥ የሚቋቋም መልክዓ ምድር መገንባት፤ በዚህም ሀገርና ሕዝብን ለዘለቄታው ከስጋቱ መታደግ ነው ፡፡
በርግጥ ሀገራችን በቀደሙት ዘመናት በደን ሃብቷ ከአፍሪካ ግንባር ቀደም ከሚባሉ ሃገራት ተጠቃሽ እንደነበረች፤ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የመጣው የሕዝብ ብዛት፣ ለእርሻና ለግጦሽ የሚሆን ተጨማሪ መሬት በመጠየቁ የደን ሀብቱ ለከፋ ጭፍጨፋ መዳረጉን፤ በየወቅቱ ችግሩን ለመከላከል የተደረጉ ጥረቶችም ውጤታማ እንዳልሆኑ የታሪክ መዛግብት ያወሳሉ።
አሁናዊ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት ደግሞ፤ አሁን ላይ ከሃገሪቱ የቆዳ ስፋት በደን የተሸፈነው 15 በመቶ/17 ሚሊዮን ሄክታር የሚሆነው ብቻ ነው፡፡ ከዚህ ውስጥም 15 ነጥብ 8 ሚሊዮን ሄክታሩ የተፈጥሮ ደን፤ የተቀረው ደግሞ በችግኝ ተከላ የተሸፈነ ነው። ከዚህ በተጨማሪም በሀገሪቱ በደን ምንጠራ ባዶ የሆነና ለደን ልማት ምቹ የሆነ 18 ሚሊዮን ሄክታር ባዶ መሬት አለ፡፡
ይህንን ለሃገርና ለሕዝብ ሁለንተናዊ ስጋት የሆነውን ችግር ለዘለቄታው ለመፍታት የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ሲጀመር በአራት ዓመት ውስጥ 20 ቢሊዮን ችግኝ መትከልን ዓላማ አድርጎ ነበር። በዚህም በመጀመሪያው ዓመት/በ2011 ዓ.ም 5 ቢሊዮን ለመትከል ታቅዶ 4 ነጥብ 7 ቢሊዮን ችግኝ መትከል ተችሏል፡፡ በ2013 ዓም 7 ቢሊዮን፤ በ2014 ዓ.ም 6 ቢሊዮን ችግኝ ለመትከል የተደረገው ጥረትም የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ጥላ ቢያጠላበትም ስኬታማ ነበር፡፡
በ2011 ዓ.ም ሐምሌ ወር በተደረገው የመጀመሪያ የችግኝ ተከላ ፕሮግራም በአንድ ቀን ብቻ 200 ሚሊዮን ችግኝ ለመትከል ግብ ተቀምጦ አብላጫ በሆነ መጠን 354 ሚሊዮን ችግኝ በመትከል በዓለም አቀፍ ደረጃ በዘርፉ ተይዞ የነበረውን ሪከርድ መስበር ተችሏል፤ በዚህም እንደ ሀገር የመነጋገሪያ ርዕስ ለመሆን ችለናል ፡፡
በመርሐ ግብሩ በግጦሽ መሬት፣ በውሃና በደን ሃብት እጥረት የሚፈጠረውን ግጭት በማስወገድ ስደትንና ከመኖሪያ ቀዬ መፈናቀልን የሚያስቀር እንደሆነ በማመንም፤ ጎረቤት ሀገራት ትኩረት እንዲሰጡ አንድ ቢሊዮን የሚጠጉ ችግኞችን ወደ ጎረቤት ሀገራት በመላክ ለጋራ ተጠቃሚነት በጋራ እንዲሠሩ ጥረት አድርጋለች።
መርሐ ግብሩ የተሻሻለ የግብርና አሠራር በማስፈን፣ የምግብ ዋስትናን በማረጋገጥ፣ የውሃ ሃብትንና የብዝሃ ሕይወት ጥበቃን በማረጋገጥ ዘላቂ ተጠቃሚነትን የሚያስገኝ ከመሆኑም ባለፈ፣ የግሪን ሀውስ ጋዝን ለመቀነስ ዓለም አቀፍ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ የራሱን አስተዋፅዖ እንዳለው ይታመናል ፡፡
ከዚህም ባለፈ ከተሞችን ከማስዋብ በዙሪያቸው የሚገኙ የተበከሉ ወንዞችን ደህንነት በማስጠበቅ የአረንጓዴ ውበት ማስጠበቂያ ቦታዎችን በዋና ዋና ከተሞች ተደራሽ ለማድረግ ያስችላል፡፡ ወጣቶችና ሴቶች ችግኝ በማፍላትና በመንከባከብ በስፋት ተጠቃሚ እንዲሆኑ በማስቻልም የሚኖረው አስተዋፅዖ ከፍተኛ ነው ፡፡
በያዝነው የአምስተኛው ዓመት የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር 6.5 ቢሊዮን ችግኝ ለመትከል ዝግጅት መደረጉን፤ ለመትከል ከተዘጋጁት ውስጥም አብዛኞቹ የፍራፍሬ ዛፍ ችግኞች መሆናቸውን ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሰሞኑን ማስታወቃቸው ይታወሳል። ይህም የመርሐ-ግብሩን ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ የላቀ እንደሚያደርገው ይታመናል ።
የአየር ፀባይ ለውጥ የሚያስከትለውን አውዳሚ ተጽዕኖ በመላው ዓለም በተለያዩ ቦታዎች ላይ በተጨባጭ እየታየ ባለበት በዚህ ወቅት የጀመርነው የአረንጓዴ አሻራ መርሐ-ግብር ባለፉት አምስት ዓመታት እያስገኘልን ካለው ዘርፈ ብዙ ተጠቃሚነት አንጻር ለዓላማው ስኬታማነት ዛሬም እንደ ትናንቱ ልንረባረብ ይገባል።
የመርሐ-ግብሩ ስኬታማነት ከአሁናዊ ጠቀሜታው ባለፈ ለመጭው ትውልድ መኖሪያ የተሻለች ሃገር መፍጠር የሚያስችል በመሆኑ፤ በችግኝ ተከላው ከፍ ባለ የኃላፊነት መንፈስ ልንሳተፍ፤ ለስኬቱም ያለን ቁርጠኝነት ከመትከል ባለፈ በመንከባከብ ላይ በተጨባጭ ሊታይ ይገባል!
አዲስ ዘመን ግንቦት 20 ቀን 2015 ዓ.ም