እንደመነሻ …
በየቀኑ መልከ ብዙ ገፅታዎች የሚያልፍበት ሰፊ ግቢ ኀዘንና ደስታ፣ ዕንባና ሳቅ ፣ ሞትና ውልደት ሲመላለስበት ኖሯል። ይህ በርካታ ነፍሶች የረገጡት አጸድ ለዓመታት በመውደቅ መነሳት፣ በመሳቅ ማልቀስ፣ በማግኘት ማጣት የተቃኘን ታሪክ አሳልፏል።
በዚህ ስፍራ ብዙዎች ያለቀሱ ስቀዋል። ብዙዎች ያጡ አግኝተዋል። ‹‹ቀን ጨለመብን፣ ዙሪያው ገደል ሆነብን›› ያሉ ከደልዳላው ሜዳ ቆመው፣ ከጨለማው መንገድ ወጥተዋል። በየቀኑ ዕንባ በሚታበስበት፣ በየዕለቱ ቋጠሮ በሚፈታበት ግቢ ደጋግ ልቦች ከመልካም እጆች ተጣምረው መላ ሲያበጁ ቆይተዋል።
ዛሬም በዚህ መሰሉ ሻካራ መንገድ የሚያልፉ፣ የኑሮ ጫናቸውን፣ የሕይወት ስብራታቸውን የሚጠግኑላቸው ርህሩህ ልቦች ከጎናቸው ይቆማሉ። አሁንም ግቢው በኑሮ ለተገፉ፣ በሕይወት ለተከፉ ብዙኃን ክፍት ውሎ ያድራል።
የሙዳይ በጎ አድራጎት ማህበር መሥራችና ሥራአስኪያጅ ወይዘሮ ዙፋን ምትኩ ላለፉት ሃያ ሦስት ዓመታት የበርካቶችን ነፍስ ከችግር ለመታደግ ስትታትር ቆይታለች። እነዚህ ዓመታት በእሷና በድርጅቱ ሠራተኞች በውጤትና ፈናዎች የታለፉ፣ በአይረሴ ትዝታና ታሪኮች የሚታወሱ ናቸው።
በግቢው ያለፉ እውነታዎችን ጠልቆ ለማውሳት የሙዳይን ጠንካራ ክዳን መክፈት ያሻል። ሙዳዩ በውስጡ እንደአለላው ቀለም ደምቀው የታተሙ ግዙፍ ታሪኮችን ሰንቋል። ይህ የተዘነቀ ገበታ ብዙዎች ኖረው ያለፉባቸው፣ የሕይወት ማስታወሻን እየጠቆመ፣ እንደጥላ አልፈው ያላለፉ እውነታዎችን፣ የማንነት ታሪኮችን እንዲህ ያስታውሳል።
ሙዳይ ሲከፈት …
የዕለቱን ቆይታ በሙዳይ ግቢ ለማድረግ ከግቢው የደረስኩት ገና በማለዳው ነው። በስፍራው ያሉ ሠራተኞች ዛሬም እንደ ወትሮው ከሥራ ላይ ናቸው። መለስ ብዬ ዙሪያገባውን ቃኘሁ። ሁሉም በያዘው ተግባር ላይ አተኩሯል። ለቀጠሮዬ በሰዓቱ ከቢሮው ያገኘሁት የሙዳይ በጎ አድራጎት ማህበር የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያ ታደለ አየለ ካለፉት የግቢው ታሪኮች መሀል ጥቂቱን እየመዘዘ ያጫውተኝ ይዟል።
አንገት ደፊው ልጅ …
የባልና ሚስቱ ሰላም ማጣት ለኑሯቸው አልበጀም። ንፋስ የገባው ትዳር ከታመመ ቆይቷል። በውይይትና በሽምግልና ያልዳነው ጥምረት ፍቺ ተበይኖበት ከውሳኔ ደርሷል። ባልና ሚስቱ ሰማንያ ቀደው፣ ንብረት ተካፍለዋል። ከዚህ በኋላ ‹‹የእኛ›› የሚያስብል ጥምር ሕይወት የላቸውም።
የጋራ ልጃቸው ገና ተማሪ ነው። በዚህ ዕድሜው የእናት አባቱ መለያየት፣ የቤተሰቡ መፍረስ ይጎዳዋል። የሁለቱ አንድነት ለእሱ በሰላም ማደግ ቢበጅም ይህ መሆን አልቻለም። ጥንዶቹ በአብሮነት መቀጠል ባይሹ መለያየት፣ መፋታት ምርጫቸው ሆኗል።
ከፍቺው ማግስት አባቱ ዘንድ እንዲቆይ የተወሰነበት ልጅ እናቱን ሸኝቶ ከአባቱ ጋር በቤት ቀርቷል። እናት ልጇን ለወላጁ አስረክባ የራሷን ሕይወት ይዛለች። አሁን ከጣራው ስር አባትና ልጅ በአብሮነት ሊኖሩ ግድ ብሏል። አባት ከሥራው፣ ትንሹ ልጅ ከትምህርትቤት ይውላሉ።
አባትዬው ሥራ ውሎ ቤት ሲገባ ትንሹ ልጅ ይረበሻል። ሁሌም በስካር የሚናውዘው አባወራ ለልጁ ተመችቶ አያውቅም። ቤት በገባ ቁጥር ያንገላታዋል። ያስፈራራዋል። ይህ ልምዱ ስቃይ የሆነበት ታዳጊ ሁሌም ኀዘንተኛ ነው። ፊቱ ፈገግታ የለውም። በትካዜ፣ በዝምታ አንገቱን ደፍቶ ይውላል ።
ትንሹ ተማሪ ቤት ሲገባ እንደልጅ የሚያይ፣ የሚያጎርሰው የለም። የሰካራም አባቱ ግድ ማጣት ከርሀብ ቢጥለው ከሙዳይ ግቢ እየዋለ ይመገባል። በሙዳይ ገበታ እንደ እሱ ኑሮ የከበዳቸው ፣ ችግር ያንገላታቸው ወገኖች በየቀኑ በልተው፣ ጠጥተው ያድራሉ።
ታዳጊው ትምህርት ቤት የቅርብ ባልንጀራ ይሉት የለውም። እንደ እኩዮቹ፣ መጫወት፣ መዝለል፣ መሳቅን አያውቅም። ዝምታው የሚያስፈራቸው ጓደኞቹ ከእሱ መቅረብን አይሹም። ዝም ሲል፣ ዝም ይሉታል። ሲሸሻቸው ይርቁታል።
የልጁ ዝምታ፣ የሚያሳስባቸው የሙዳይ ቤተሰቦች ዘወትር ባህሪውን እያጤኑት ነው። ልጁ ከማንም አይቀርብም። ማንም በተለየ እንዲጠጋው፣ እንዲያወራው አይፈልግም። ከግቢው ሲደርስ የቀረበውን ተመግቦ ይወጣል። ማግስቱን ሲመለስ እንደትናንቱ በዝምታ ተውጦ ነው። ዘወትር በትካዜ ተቀምጦ በኀዘን አንገቱን ይደፋል ።
አንድ ቀን ወይዘሮ ሙዳይ ትንሹን ልጅ በፍቅር ቀርባ አናገረችው። ዝምታው ያስጨንቃል፣ ትካዜው ያሳስባል። ሙዳይ ይህ እውነት ያለምክንያት እንዳልመጣ ገብቷታል። እንደ እናት እያዋየች፣ እንደ ሐኪም መረመረችረው። ትካዜ ኀዘኑን መዝና፣ ስለምን? ስትል ጠየቀችው።
ልጁ ለሙዳይ የውስጡን ችግር፣ የልቡን ኀዘን ለመንገር አልዘገየም። ቢጨነቅም፣ ቢፈራም፣ ዕንባ እያነቀው የማይታመነውን እውነታ ዘረገፈላት።
ትንሹ ልጅ ከእናቱ ከተለየ ወዲህ የአባቱ ብቸኛ ልጅ ሆኖ ጊዜያትን ቆጥሯል። እነዚህ ጊዜያት ለዚህ ምስኪን ልጅ የጨለማ ሕይወት ያወረሱ ናቸው። ለእሱ እያንዳንዱ ሌሊት እጅግ ከባድና አሰቃቂ ነው። ሰካራም አባቱ አምሽቶ በገባ ቁጥር እያሰቃየ ግብረሰዶም ይፈጽምበታል። ሲነጋ ምንም እንዳልፈጸመ ደረቱን ነፍቶ ወደ ሥራው ይሄዳል።
ትንሹ ልጅ ትምህርቤት ሲሄድ ያለፈውን ምሽት እያሰበ፣ በሆነበት ሁሉ እየተከዘ ነው። የአባቱ ክፉ ድርጊት ፊቱ በዞረ ቁጥር ውስጡ ይጨነቃል፣ ሰውን ይሸሻል፣ ራሱን ከእኩዮቹ አርቆ አንገት ደፍቶ ይውላል። ሙዳይ ግቢ ሊመገብ ሲመጣ ከማንም አይቀርብም።
ያለፉት ጊዜያት ለትንሹ ልጅ ጥርሳማ፣ እሾሀማ ነበሩ። የጀንበሯ መጥለቅ ፣ የምሽቱ መድረሰ በእጅጉ ያስፈራዋል። አባትዬው ትናንት በፈጸመው ድርጊት ተፀፅቶ አያውቅም ። አምሽቶ በገባ ቁጥር በገዛ ልጁ ላይ ደጋግሞ ግብረሰዶም ይፈጽማል። ልበ ሰባራው ታዳጊ በአባቱ ድርጊት ተሳቆ ይውላል። የውስጡን ቁስል፣ የቤቱን ችግር ቀርቦ የሚያዋየው የለም። በዝምታ፣ በመገለል፣ በብቸኝነት ራሱን ደፍቶ ይውላል።
ወይዘሮ ሙዳይ ይህን እውነት የሰማችው በታላቅ ድንጋጤና ኀዘን ነበር። አባት በልጁ ላይ የፈጸመው ድርጊት ፈጽሞ ያልተለመደና ለጆሮ የሚከብድ ነው። አሁን ለትንሹ ልጅ አስቸኳይ መፍትሄ ያሻል። የመጀመሪያው ርምጃ ልጁ ወደቤቱ እንዳይሄድና በሙዳይ ግቢ እንዲቆይ ማድረግ ሆኗል።
ትንሹ ልጅ በግቢው እንዲቆይ ሲወሰን የተናገረው እውነት በምስጢር እንዲጠበቅ ተደርጓል። አባት የፈጸመው ድርጊት እንደወጣበት ካወቀ በልጁ ላይ ጥቃት ሊያደርስ እንደሚችል ተገምቷል። የታቀደው እንደታሰበው ሆኖ በደለኛው ልጅ ሰላማዊ የዕንቅልፍ ሌሊቶችን በግቢው አሳለፈ። ውሎ አድሮም የሥነልቦና ባለሙያዎችን ድጋፍ አገኘ። ጉዳዩ ግን በዚህ ብቻ አልታለፈም። በደል የፈጸመበት ወላጅ አባቱ በሕግ እንዲጠየቅ ሆነ።
እነሆ ! ይህ ታሪክ ካለፈ ጥቂት ዓመታት ተቆጥረዋል። ዛሬ የትናንቱ አንገት ደፊ ልጅ የልብ ስብራቱ ተጠግኖ የአስረኛ ክፍል ተማሪ ሆኗል። በሙዳይ በጎ አድራጎት ግቢ ከሚኖሩ ጠንካራ ቤተሰቦች መሀልም አንደኛው ነው።
በዚህ ልጅ ውስጠት የትናንቱ እሳት ፈጽሞ አይዳፈን ይሆናል። የነገው ተስፋ ግን በእጁ ላይ እንደተቀመጠ ነው። ያለፈው ጨለማ በወደፊት ጥረቱ ብ ሩህ ሆ ኖ ይ ደምቃል ። ይ ህ ይ ሆን ዘንድ የሙዳይ ግቢ መላው ቤተሰቦች ሁሌም ከጎኑ እንደቆሙ ናቸው።
ከአቶ ታደለ ጋር ውይይቴን ቀጥያለሁ ። ታደለ አሁንም የሙዳይን ሰፊ ክዳን ከፍቶ የግቢውን እውነታ እያሳየኝ ነው ። ባለፉት ዓመታት በሙዳይ አጸድ ፣ የተሻገሩ አሳዛኝና አስገራሚ ታሪኮች፣ ያልፉ የማይመስሉ እውነታዎች በታሪክ መዝገብ በጉልህ ሰፍረዋል። ዛሬን በምክንያት ሊኖሩት እስትንፋሳቸው የቀጠለ፣ ነገን ለማየት ብሩህ ተስፋ ውስጣቸው የታሰረ በርካታ ነፍሶች በሙዳይ ግቢ የግል ምስጢርና እውነታን እንደያዙ መኖርን ቀጥለዋል።
ከአፍ ያመለጠች ጥሬ …
ገና በጠዋቱ እናት አባቷን በሞት ያጣችው ብላቴና ዕጣ ፈንታዋ ከአያቶቿ እጅ ወድቋል። ትንሽዋ ልጅ በዕድሜ ከፍ ማለት ስትይዝ ከሁሉም ተግባባች። ያየችውን የምትቅርብ ፣ የቀረበችውን የምትወድ ሆነች። ትኩረት ያጣችው ልጅ ከቤት መውጣቷን እንጂ መዋያ ስፍራዋን የሚጠይቃት የለም። የትም ውላ፣ ተጫውታ ትመጣለች።
አያቶቿ አቅመ ደካማ ናቸው። የእሷን በቅርብ መኖር እንጂ መግቢያ መውጫዋን አይጠይቁም። በቤቱ ሌሎች ቢኖሩም እሷን እንደ ልጅ የሚያስብ፣ የሚያስታውሳት የለም። አምሽታ ስትገባ እንደ እናት የሚፈልጋት፣ እንደ አባት የሚቆጣ፣ የሚቆነጥጣት ታዛቢ ኖሮ አያውቅም።
ገና ስድስተኛ ዓመቷን የተሻገረችው ሕፃን ጠዋት ወጥታ ምሽቱን ትመለሳለች። ማለዳ ከቤት ስትወጣ የእሷን መድረስ በጉጉት የሚጠብቁ ዓይኖች በርቀት ይቀበሏታል። ውላ ስትገባ እንደተለመደው ነው። ከነማን እንደነበረች የሚጠይቃት የለም። እሷ ግን ለሚቀርቧት ጥቂት ሰዎች ውሎዋን መናገር ጀምራለች።
ትንሽዬዋ ልጅ ከቤት በወጣች ቁጥር ጎረምሶች ያገኟታል። ባገኟት ጊዜ ልጅነቷ አያሳዝናችውም። ወላጅ አልባ መሆኗ፣ ሰብሳቢ ማጣቷ ግድ አይሰጣቸውም። እጃቸው ስትገባ ሕፃንነቷን ይረሳሉ። ሴት መሆኗን ብቻ ያስባሉ። ሁሌም ያሻቸውን ለማድረግ ፈጣን ናቸው። ጎረምሶቹ ድርጊቱን ሲፈጽሙ መረጃን አይተዉም። በየቀኑ ያሻቸውን ሲፈጽሙ በድብቅ ነው።
ውሎ አድሮ ሕፃኗ ለሌሎች ሰዎች የሆነባትን ሁሉ መንገር ጀመረች። ሁኔታውን የሰማው የሙዳይ ድርጅት ዝም አላለም። ተጠቂዋን ሕክምና አድርሶ ለሚመለከታቸው የሕግ ክፍሎች ጉዳዩን አሳወቀ።
በወቅቱ ጎረምሶቹ እነማን እንደሆኑ አልተለዩም። ትንሽዋ ልጅ የበደሏትን፣ ደጋግመው የደፈሯትን ወጣቶች በስም መጥራት፣ በአካል ማወቅ አልሆነላትም። እንደዋዛ ከእጅ ወጥታ የትም ስትውል የነበረችው ሕፃን በትኩረት ማጣት ብዙ ፈተናዎችን አሳልፋለች።
ይህን እውነት መርምሮ የደረሰበት የሙዳይ ድርጅት የልጅቷ ሕይወት በነበረበት እንዲቀጥል አልወደደም። ተበዳይዋን ከአሳዳጊዎቿ ተረክቦ በማዕከሉ መልካም ኑሮ፣ አዲስ ሕይወት፣ እንዲኖራት ዕድል ችሯታል።
እነዚህን ሕፃናት የመሰሉ በርካታ ወገኖች በሙዳይ በጎ አድራጎት ማህበር ውስጥ ሕይወትን እንዲህ ቀጥለዋል። በዚህ ስፍራ ያለፈ በደል ተረስቶ አዲስ የኑሮ መስመር፣ ሌላ የሕይወት ገጽ ይገለጣል። ሁሌም ጥሩ ህሊና ፣ መልካም ልቦችና ቸር እጆች በእነዚህ በደለኞች ዙሪያ ሲሆኑ ሰፊ ትርጉም አላቸው። ዕንባን ሲያብሱ፣ ታሪክን ሲቀይሩ፣ ተስፋን ሲያጭሩ መቼም ‹‹ደከመኝ፣ ሰለቸኝ›› አይሉምና።
መልካምሥራ አፈወርቅ
አዲስ ዘመን ግንቦት 19/2015