አፍሪካውያን ከፍ ያለ መስዋዕትነት የጠየቀውን ነጻነታቸውንም ሆነ በቀጣይ ተስፋ ያደረጓቸውን ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ተስፋዎቻቸውን እውን ለማድረግ የዛሬ 60 ዓመት የአፍሪካ አንድነት ድርጅትን (የዛሬውን የአፍሪካ ሕብረት) በፓን አፍሪካኒዝም እሳቤ መመስረት ችለዋል፡፡
በወቅቱ ነጻነታቸውን ያገኙ የአፍሪካ አገራት መሪዎችም በድርጅቱ ማዕቀፍ ውስጥ ሆነው በተለያዩ መስኮች አብረው ስለሚሰሩባቸው ሁኔታዎች መክረዋል፤ ለተግባራዊነታቸውም ተንቀሳቅሰዋል፡፡ በዚህም አፍሪካ ሉዓላዊ ነጻነቷን ከመጎናጸፍ ባሻገር በማህበራዊም ሆኑ ኢኮኖሚያዊ እድገትና መስተጋብሮች ላይ አብረው መስራት የሚችሉባቸውን አቅጣጫዎች አስቀምጠዋል፤ ተግባራዊ ርምጃዎችንም ጀምረዋል፡፡
የአህጉሪቱ ህዝቦችን በመሰረተ ልማት እና በንግድ በማስተሳሰር፤ በብዙ ተጋድሎ የተገኘውን ነጻነት በጠንካራ የኢኮኖሚ መሰረት ላይ ለማዋቀር የሚያስችሉ እሳቤዎችን በማፍለቅ ፤ተግባራዊ ለማድረግ በብዙ ፈተናዎች ውስጥ ሆነውም ቢሆን የአቅማቸውን ያህል እየተንቀሳቀሱ ነው። ይህን ሁሉ ተከትሎም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ተስፋ ሰጭ ውጤቶች እየተስተዋሉ ናቸው፡፡
ዛሬም የቀደምቶቻቸውን መንገድ የተረዱት የአፍሪካ መሪዎች የአህጉሪቱ ህዝቦች ሁለንተናዊ ነጻነት እውን የሚሆነው አሁን ካሉበትና ብዙ ዋጋ እያስከፈላቸው ከሚገኘው የኢኮኖሚ ጥገኝነት መላቀቅ ሲችሉ ብቻ መሆኑን በመገንዘብ ፣ አጀንዳ 2063ን ቀርጸው ለተግባራዊነቱ እየሰሩ ይገኛሉ።
አጀንዳው በዋናነት አፍሪካን እኤአ በ2063 ብልጽግናዋ የተረጋገጠ፤ የጥይት ድምጽ የማይሰማባት፤ አገራት እርስ በእርስ የሚተሳሰሩባቸው ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ መሰረተ ልማቶች የተመቻቹላቸው ማድረግን ግብ አድርጎ ያስቀመጠ ነው፡፡ በግብርና፣ በመሰረተ ልማት፣ በስራ እድል ፈጠራ፣ በንግድ ትስስር፣ በሰላምና ደህንነት፣ ጤና እና ሌሎችም ለአህጉሪቱ ሁለንተናዊ ብልጽግና በሚያግዙ መስኮች ላይ ትኩረት ሰጥቶ መስራትን የሚጠይቅ ነው፡፡
አሁነኛ በሆነው አፍሪካዊ እውነታ ይሄን ትልምና ጅምር ተግባር ከዳር ማድረስ በቀላሉ የሚታሰብ አይደለም። የአህጉሩ ህዝቦችን በተለይ ደግሞ የመሪዎችን ከፍ ያለ ቁርጠኝነት ይጠይቃል፤ በብዙ መልኩ መናበብንና መደማመጥንም ይፈልጋል፡፡
የአብዛኛዎቹ የአፍሪካ ሀገሮች ኢኮኖሚ የተለያዩ ፍላጎቶችን በተሸከመ፤ በብድርና ርዳታ ስም በሚገኝ የፋይናንስ ጥገኝነት አውድ ውስጥ በሆነበት ሁኔታ በኢኮኖሚ ራስን በመቻል ወደ ብልጽግና የሚደረግ ጉዞ አልጋ በአልጋ እንደማይሆን ይታመናል። ይህ ሁኔታ ምናልባትም ከቅኝ ግዛት ነጻ ለመውጣት በተደረገው ትግል ወቅት ከተከፈለው ዋጋ ያልተናነሰ ፈተና ይዞ ሊመጣም ይችላል።
የበለጸጉት ሀገራትም ሆኑ አበዳሪ ተቋማት አሁን አሁን ሰው ተኮር ለሆኑ ፕሮጀክቶች ማስፈጸሚያ የሚሆን ፋይናንስ በእርዳታም ሆነ በብድር ለመስጠት እያስቀጧቸው ያሉ መስፈርቶች ለዚህ እውነታ ተጨባጭ ማሳያ እንደሚሆኑ መገመት አይከብድም ፤
አፍሪካውያን እህል አምርተው የምግብ ዋስትናቸውን እንዳያረጋግጡ በአፈር ማዳበሪያ ግዥ ላይ ሳይቀር ማእቀብ እስከመጣል የሚደርስ ጫና እየተደረገባቸው ነው፤ ይህም አፍሪካውያን ከቅኝ ግዛት ቢላቀቁም፣ በኢኮኖሚ ጥገኝነቱ ክፉኛ እየተፈተኑ ስለመሆናቸው ተጨባጭ ማሳያ ተደርጎ ይወሰዳል። ሁኔታው አፍሪካውያን ለኢኮኖሚ ነጻነታቸው ጠንካራ ትግል እንደሚጠብቃቸውም ያመላክታል፡፡ ለእዚህ ደግሞ የአህጉሪቱ ህዝቦች ያሏቸውን የተለያዩ የተፈጥሮ ሀብቶች፣ ከፍተኛ ቁጥር ያለው አምራች ዜጋ ጉልበት፣ እውቀትና ክህሎት እንዲሁም ያላቸውን ፋይናንስ ውጤታማ በሚሆን መንገድ በማቀናጀት በቁርጠኝነት መንቀሳቀስ ይጠበቅባቸዋል፡፡
ለእዚህ ደግሞ ከችግሮቿ ወጥታ ከስንዴ ጠባቂነት ወደ ስንዴ ላኪነት መሸጋገር የቻለችውን ኢትዮጵያን እንደ ጥሩ ተሞክሮ መውሰድ ይቻላል፡፡ ሀገሪቱ በስንዴ ልማት ላይ ሰፊ ትኩረት ሰጥታ በመስራት፤ ለወዳጅም ለጠላትም የምስራች መልእክት ያስተላለፈ ስኬት አስመዝግባለች፡፡
እንደ ሀገር የበጋ መስኖ የስንዴ ልማት በተጀመረበት በ2020 አ.እ,አ ሶስት ነጥብ ስድስት ሚሊዮን ኩንታል፣ በሁለተኛው አመት ደግሞ 24 ነጥብ አምስት ሚሊዮን ኩንታል ስንዴ ማምረት መቻሏን መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ አሁን አዝመራው እየተሰበሰበ ባለው የበጋ ስንዴ መስኖ ልማት ደግሞ 5 3 ሚሊዮን ኩንታል ስንዴ እንደምታመርት ይጠበቃል፡፡
ሀገሪቱ በበጋ ስንዴ መስኖ ልማት ያስመዘገበችው ስኬት በመቶ ሚሊዮን ዶላሮች በማውጣት ከውጪ ታስገባ የነበረውን ስንዴ በሀገር ውስጥ ምርት እንድትተካ ፤ እንዲሁም ስንዴ ወደ ጎረቤት ሀገራት ኤክስፖርት እንድታደርግ አስችሏታል፡፡ ይህ በብዙ ፈተናዎች ውስጥ የተገኘ ስኬት ጠንክሮ መስራት ከተቻለ የኢኮኖሚ ነጻነትን ማረጋገጥ እንደሚቻል እንደ ማሳያ ተደርጎ ሊወሰድ የሚችል ነው፡፡
ከዚህም ባለፈም የዓባይ ግድብ ጨምሮ ኢትጵያውያን በራሳቸው አቅም እየገነቧቸው ያሉ ታላላቅ ሜጋ ፕሮጀክቶች የኢኮኖሚ ነጻነቷን ያረጋገጠች አፍሪካን ለማየት ሆነ ፤ የቀደሙት የነጻነት አባቶች ተስፋ ያደረጓትን የበለጸገች አፍሪካ እውን ለማድረግ የሚያስችል ተግባራዊ እንቅስቃሴ ነው።
ከዚህም ባለፈ “ለአፍሪካዊ ችግር አፍሪካዊ መፍትሄ ” በሚል የሰሜን ኢትዮጵያን የሰላም እጦት ለመፍታት የሄዱበትም መንገድ በርግጥም አፍሪካውያን የራሳቸውን እጣ ፈንታ የመወሰን አቅሙም ብቃቱም እንዳላቸው በተጨባጭ ያመላከተ፤ ለተቀሩት የአህጉሪቱ ህዝቦችም ሊቀመር የሚችል ተሞክሮ ነው ። አፍሪካውያን የችግሮቻቸው መፍቻ ቁልፍ በእጃቸው እንዳለ ማረጋገጥ የሚያስችሉ ናቸው፡፡
አዲስ ዘመን ግንቦት 19/2015