ኋላቀርና ከእጅ ወደ አፍ የሆነው የኢትዮጵያ ግብርና ሰፊ የሰው ጉልበት ይፈልጋል። በዚህ ውስጥ ደግሞ የልጆች ጉልበት ሚና ከፍተኛ ነው። በመሆኑም አርሶ አደሩ ልጁን ወደ ትምህርት ቤት ከመላክ ይልቅ የግብርና ሥራውን ቢያግዘው ይመርጣል። ቤተሰብ ልጁን ለማስተማር ቁርጠኛ በሆነ ጊዜም ልጁ ባለው ትርፍ ጊዜ በግብርናው እንዲሳተፍ ይጠብቃል።
ልጅ ተማሪ ብቻ አይደለም፤ የአርሶ አደሩ ረዳትም ነው። በዚህ ላይ በመኖሪያ መንደሩ አቅራቢያ ትምህርት ቤት ባለመኖሩ ብዙ ኪሎ ሜትሮችን መጓዝ ይኖርበታል።
የዕለቱ የስኬት እንግዳችን በዚህ ሁኔታ ውስጥ አልፈው ነው አሁን ለደረሱበት የስኬት ማማ የበቁት። በለጋ ዕድሜያቸው ለእግራቸው መጫሚያ ጫማ ሳይኖራቸው በባዶ እግራቸው ብዙ ኪሎሜትሮች በመጓዝ፣ ባዳፋ ቁምጣቸው ብርድና ቁሩን ተቋቁመው ነው ትምህርታቸውን የተከታተሉት፤ ከትምህርት ላለመስተጓጎል ድካምን ተቋቁመው ተራራ መውጣት መውረድ የየዕለት ተግባራቸው ነበር። በዚህ ሁኔታ ትምህርታቸውን ከግብ ያደረሱት እንግዳችን አቶ እሸቱ ዘለቀ ይባላሉ። አቶ እሸቱ የግሎባል ኦይል ባለቤትና ሥራ አስኪያጅ ናቸው።
ሶማሊያ ኢትዮጵያን በወረረችበት ወቅት የሁለት ዓመት ሕፃን የነበሩት አቶ እሸቱ፤ በቀድሞ ባሌ ክፍለ አገር ነው ተወልደው ያደጉት። በወቅቱ ጦርነቱ ያሰጋቸው ወላጆችም የመጀመሪያ ልጃቸውን አቶ እሸቱን ይዘው ከባሌ ወደ ሰላሌ ሄዱ። ከአራት ዓመታት ቆይታ በኋላ ደግሞ አቶ እሸቱ እትብታቸው ወደ ተቀበረበት ወደ አያቶቻቸው መንደር የመመለስ አጋጣሚ ተፈጠረላቸው። በወቅቱ የእብድ ውሻ በሽታ በአካባቢው በመግባቱ ምክንያት የሀበሻ መድኃኒት ፍለጋ ነው ወደ አያቶቻቸው ያቀኑት። አያቶቻቸው አቶ እሸቱን መድኃኒቱን ብቻ ሰጥተው ሊሸኟቸው አልፈቀዱም፤ ‹‹እኛ እናስተምረው›› በማለት እዚያው ባሌ እንዲቀሩ አድረጉ።
በአያት እጅ የማደግ ዕድሉ የገጠማቸው አቶ እሸቱ ግን ከወላጆቻቸው መለየታቸው አልተመቻቸውም። ከወላጅ አባታቸው በተበረከተላቸው አንድ ብር ተታለው የአያቶቻቸው ዘንድ ቆይታቸውን አጸኑ። ጠፍተው ለመመለስ ቢሞክሩም አልተሳካላቸውም።
ከአንደኛ እስከ ስድስተኛ ክፍልን ባሌ ጃፈራ ሁሉቆ፤ ሰባተኛ ክፍልን ደሎ ሰብሮ፤ ስምንተኛ ክፍልን ደግሞ ቱሉ ሚልኪ መለስተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሩ። በትምህርት ውጤታቸውም ሆነ በባህሪያቸው በብዙ የተመሰከረላቸው አቶ እሸቱ፤ በመምህሮቻቸው ዘንድ እጅግ ተወዳጅና ተናፋቂ እንደነበሩም ያስታውሳሉ።
የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በገርበጉራቻ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተከታትለዋል። የሁለተኛ ደረጃ ተማሪ እያሉ ሕክምና የመማር ከፍተኛ ጉጉት የነበራቸው አቶ እሸቱ፤ ለተፈጥሮ ሳይንስ ትኩረት ሰጥተው ይተጉ እንደነበር ያስታውሳሉ።
ጊዜው ደርሶም የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተናን በ1986 ዓ.ም ወሰዱ። በውጤታቸውም ሦስት ነጥብ ስምንት ማምጣት ቢችሉም እንዳሰቡት ወደ ሕክምና ትምህርት ቤት አልገቡም። አራተኛ በሆነው የትምህርት ምርጫቸው አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ገብተው በቢዝነስ አድሚኒስትሬሽን የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን በከፍተኛ ውጤት ማጠናቀቅ ችለዋል፤ ሁለተኛ ዲግሪያቸውንም ከጅማ ዩኒቨርሲቲ አግኝተዋል።
አቶ እሸቱ ሥራ ለማግኘትም አልተቸገሩም። ገና ከዩኒቨርሲቲ ሳይወጡ ከአንድም ሁለት የሥራ ዕድሎች ገጥመዋቸዋል፤ በመጀመሪያ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጥሩ ውጤት ያላቸውን በቅጥር ሊወስዳቸው በሂደት ላይ እንዳለ በወቅቱ በአገሪቱ ከነበሩ አራት ነዳጅ ማደያዎች መካከል አጂፕ የተባለው የጣልያን ኩባንያ በተመሳሳይ ጥሩ ውጤት ያላቸውን አራት ተማሪዎች ለመቅጠር የዩኒቨርሲቲውን ደጅ ይጠና ጀመር። በዚህ ጊዜ ‹‹ከእኔ የሚበልጡ አሉ›› በማለት ብዙም ተስፋ አላደረጉም ነበር። ይሁንና ኩባንያው የሚፈልጋቸውን የትምህርት ዓይነቶች ከፍተኛ ውጤት ማምጣት የቻሉት አቶ እሸቱ ከአራቱ አንዱ ሆነው ተመረጡ።
‹‹ሀ›› ብለው ሥራ የጀመሩበት አጂፕ ወደ ሼል፤ ከዚያም ኦይል ሊቢያ ሲዘዋወር እሳቸውም በኩባንያዎቹ ሠርተዋል። በአጠቃላይ በኦይል ኢንዱስትሪ ውስጥም ለ26 ዓመታት አገልግለዋል።
በዚህ የረጅም ጊዜ አገልግሎታቸውም ከዘርፉ ጥልቅ ዕውቀትና ልምድ አግኝተዋል። በዘርፉ ለመሰማራት የሚያስችሉ የንግድ ሃሳቦችን ማመንጨትና ለሥራው የሚያግዙ ቅድመ ሁኔታዎችን (ፕሮፖዛል) እንዴት ማዘጋጀት እንደሚቻል ክህሎት አግኝተውበታል። ልምድና ተሞክሮውን እንዲሁም መልካም አጋጣሚውን ተጠቅመው ወደ ንግዱ ሥራ ለመግባት የሚያስችሏቸውን እቅዶች አውጥተዋል።
የተማረ ሰው ማግኘት እንደ ብርቅ ይታይ በነበረበት በዚያን ጊዜ፤ ከአርሶ አደር ቤተሰብ ወጥተው በወጣትነት አፍላ ዕድሜያቸው ንጹህ አዕምሮን እንደያዙ ከዩኒቨርሲቲ ወጥተው አጂፕን የተቀላቀሉት አቶ እሸቱ፤ የመጀመሪያ ሥራቸውን ለመሥራት ሻሸመኔ በተላኩበት ወቅት ከፍተኛ የሆነ የነዳጅ እጥረት በአገሪቱ የነበረበት ሁኔታ ዛሬም ድረስ አግራሞትን ይጭርባቸዋል።
ነገሩ እንዲህ ነው፤ ‹‹ነዳጅ የአገር ሀብት ነው›› የሚሉት አቶ እሸቱ፤ በወቅቱ የነበረው የነዳጅ እጥረት ለብልሹ አሠራር በር የከፈተ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ አንዳንድ በመንግሥት መዋቅር ውስጥ የነበሩ ሰዎች እጃቸውን ለማስገባት አልመች ቢሏቸው፤ ከሀቅ ውጪ ሌብነትን እምቢኝ አሻፈረኝ ሲሉ ወንጀል እንደሠራ ሰው ለእስር ዳርገዋቸዋል። ያም ቢሆን በወጣትነት ሙቅ ልባቸው ውስጥ ሀቀኝነታቸው ፍንትው ብሎ የታየው መልካም ሰው ገጥሟቸውና ብዙም ሳይቆዩ ከእስር እንዲለቀቁ ይደረጋል።
ሥራቸውን በኃላፊነት ስሜት በመወጣታቸው ድርጅታቸው በወቅቱ ማትረፍ እንደቻለም ይናገራሉ። እርሳቸው እንዳሉት፤ ለእዚህ ምክንያቱ ደግሞ የዕውቀት፣ የልምድና ጥብቅ የሆነ የሥራ ሥነምግባርን ከማጎልበት በተጨማሪ ሥራውን ሊያሳልጡ የሚያስችሉ ድጋፎችን በቀላሉ ማግኘት መቻላቸው አንዱ ሲሆን፤ ያዳበሩት የሥራ ባህልም በእጅጉ ጠቅሟቸዋል። ሥራቸውን ማሳለጥ እንዲችሉ ድርጅቱ የግል መኪና እንዲገዙ ዕድሉን አመቻቸላቸው። ድርጅቱ ይህን ማድረጉ ሠራተኞች በሥራቸው ውጤታማ እንዲሆኑና ተረጋግተው እንዲሠሩ ለማስቻል ቢሆንም፣ እርሳቸውም ሆኑ ድርጅቱ በጋራ ተጠቃሚ መሆን ችለዋል።
አቶ እሸቱ፤ በአጂፕ ለሁለት አመት እንዳገለገሉ ኩባንያው ለሼል ነዳጅ ማደያ ተሸጠ። እርሳቸውም በአዲሱ ኩባንያ ሥራቸውን በመቀጠል በተለያዩ የሥራ ክፍሎች ውስጥ አገልግለዋል። ቀጥሎም እኤአ በ2008 ዓ.ም ሼል ካምፓኒ ለኦይል ሊቢያ በመሸጡ ወደ ኦይል ሊቢያ ተዘዋውረው በማርኬቲንግ ማናጀር፣ በኔትወርክ ዴቨሎፕመንት ማናጀር፣ በኮሜርሻል ማናጀርና በሌሎች የሥራ ኃላፊነቶች ጭምር ለአስር ዓመታት አገልግለዋል።
ለዓመታት በኦይል ኢንዱስትሪ ውስጥ የቆዩት አቶ እሸቱ ግን በዚሁ መልኩ መቀጠል አልፈለጉም፤ ውጭ ያለውን ሁኔታ ለመረዳት ጉጉት አደረባቸው። ድርጅቱ በማንኛውም መንገድ ተመራጭና ምቾት ያለው ቢሆንም፣ ‹‹ምቹ ሁኔታው አንድ ቀን ቢቋረጥ ምን እሆናለሁ›› የሚል ሀሳብ ይገባቸውም ጀመር።
ያላቸውን ዕውቀትና እምቅ አቅም ከልምድ ጋር አጣምረው የግል ሥራ ለመሥራት ተነሱ። የመጀመሪያ ሙከራቸውም ኦይል ካምፓኒ ማቋቋም ነበርና ፕሮፖዛላቸውን ለመንግሥት አቅርበው ጥሩ ግምገማ ቢያገኝም፣ በወቅቱ መቀጠል አልተቻለም። ያም ቢሆን የተለያዩ የቢዝነስ ፕሮፖዛሎችን በማዘጋጀት የተለያዩ የቢዝነስ አማራጮችን የማፈላለግ ልምድ ነበራቸውና ጥረታቸውን ቀጠሉ። ኦዳ ኢነርጂን ከኦዳ ባስ ጋር በማቋቋም ሂደት ውስጥ በፕሮፖዛል ዝግጅት ሚና እንደነበራቸው አቶ እሸቱ ይገልጻሉ፤ የኩባንያው ባለአክሲዮን እንደነበሩም አስታውሰዋል፡፡
‹‹ዙሪያው በምቾት የታጠረ ሰው አንድ ቀን ከዚያ አጥር ውስጥ ሲወጣ ሁሉም ነገር ይጨልምበታል›› የሚል አመለካከት ያላቸው አቶ እሸቱ፤ ኦይል ሊቢያን የለቀቁት ከዚህ በመነጨ አስተሳሰብ እንደሆነ ይናገራሉ። ኦይል ሊቢያን በለቀቁ ጊዜ የነበራቸው የሥራ ድርሻ ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉትን የኦይል ሊቢያ ካፓኒዎች በሙሉ የመቆጣጠር ድርሻ ነበራቸው። ይሁንና ‹‹ምቾት እስከመቼ፤ ውጪ ያለውንም እስኪ ልሞክረው›› በማለት የጀመሩት ቢዝነስ እንዳሰቡት ሳይሆን ቢቀርም ተስፋ ሳይቆርጡ የተሻለ ሥራ ማማተራቸውን ቀጠሉ።
በዚህ ወቅት ልምድና ዕውቀታቸውን የሚያውቅ አንድ ሰው በጋራ የመሥራት ፍላጎት እንዳለው ገልጾላቸው ኦይል ካምፓኒ እንዲያቋቁሙ ጠየቃቸው። ሁለት ጊዜ ሳያስቡ ለጥያቄው ምላሽ በመስጠት ከዜሮ ተነስተው በአጭር ጊዜ አፍሪካን ኦይል የሚል ካምፓኒ ብራንዲንጉን (ምልክቱን) ጭምር ሠርተው በማስረከብ ውጤታማ ሥራ መሥራት መቻላቸውን አቶ እሸቱ ይገልጻሉ። በዚህ የተነቃቁት አቶ እሸቱ፤ የቆየውን ዕቅዳቸውን ለማሳካት ባደረጉት ጥረት ግሎባል ኦይል ካምፓኒን መመስረት ቻሉ።
ግሎባል ኦይል በአሁኑ ወቅት በምዕራብ፣ በምሥራቅና በደቡብ ኢትዮጵያ አካባቢዎች ማደያዎች አሉት፤ በጥቅሉ 40 የሚደርሱ ማደያዎች ተቋቁመው በሥራ ላይ ይገኛሉ። የነዳጅ ሥራ በተለያየ መንገድ እንደሚሠራ ያስረዱት አቶ እሸቱ፤ ነዳጅ ሙሉ ለሙሉ በመንግሥት ቁጥጥር ሥር እንደሆነ ይገልጻሉ፤ ወደፊት የነዳጅ አቅራቢዎች፣ ማደያዎች እንዲሁም በትራንስፖርት ዘርፍ ያሉት ተዋናዮች አቅም ሲደራጅ ሙሉ ለሙሉ በመንግሥት ቁጥጥር ሥር ላይሆን እንደሚችልም ይናገራሉ። አሁን ላይ ግን መንግሥት፣ ከውጭ ተጫርቶ ከማምጣት ጀምሮ ዋጋ እስከ መተመን ድረስ መቆጣጠሩ የግድና አስፈላጊ እንደሆነም አስረድተዋል።
ዘርፉን ጠንቅቀው የሚውቁት አቶ እሸቱ፤ ወደ ዘርፉ ለሚገቡ አዳዲስ ኢንቨስተሮች ልምድና ዕውቀታቸውን በማካፈል ገበያው ምን እንደሚመስልና እንዴት መሥራት እንዳለባቸው ጭምር የማማከር አገልግሎት እንዲሁም ስልጠና ይሰጣሉ። በቀጣይም በአዲስ አበባ ከተማ ክፍተት ያለባቸው የተለያዩ አካባቢዎች ላይ ማደያዎችን ለመክፈት አቅደዋል፤ ሌሎች ከዘርፉ ጋር ተያይዞ የሚታዩ ክፍተቶችንም ለመሙላት እንዲሁም አዳዲስ አሠራሮችን መዘርጋት የሚያስችል ዕቅድ እንዳላቸውና ለዚህም ፕሮፖዛል አዘጋጅተው ለመንግሥት ማቅረባቸውን ይናገራሉ።
ነዳጅ ከውጭ ገብቶ ማደያዎች ጋ እስኪደርስ የተለያዩ ተዋናዮች እንዳሉት የጠቀሱት አቶ እሸቱ፤ ከጅቡቲ ወደ አዲስ አበባ የሚያመጡት የትራንስፖርት ባለቤቶች ጭምር ተሳታፊዎች ናቸው ይላሉ። በዚሁ ሰንሰለት ውስጥ በርካታ የሥራ ዕድል እንደሚፈጠርም ነው የገለጹት።
እሳቸው እንዳሉት፤ በግሎባል ኦይል ጅቡቲ ሆነው ነዳጁን ወደ አዲስ አበባ የሚልኩ ሁለት ኢትዮጵያውያን፤ የአስተዳደር ሠራተኞች 15፤ ነዳጁን የሚያጓጉዙ 30 ቦቴዎች ላይ ያሉ ሹፌሮችና ረዳቶች፤ 40 በሚደርሱ ግሎባል ኦይል ማደያዎች ውስጥ የሚሠሩ 280 ሠራተኞችን ጨምሮ በድምሩ ከ300 ለሚልቁ ዜጎች የሥራ ዕድል ፈጥረዋል።
ለረጅም ዓመታት ከውጭ ካምፓኒዎች ጋር መሥራታቸው ብዙ ልምድና ዕውቀት ማካበት እንዳስቻላቸው አቶ እሸቱ ይናገራሉ። ከነጮች ጋር መሥራት መቻላቸውም ለሥራቸው ቀላል የማይባል ድርሻ እንዳለው ይናገራሉ።
አቶ እሸቱ ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ ማህበራዊ ተሳትፎ ማድረግ ያስደስታቸዋል። በግላቸው ከሚያደርጉት ማህበራዊ ተሳትፎ በተጨማሪ ማህበረሰቡን በማስተባበር በመኖሪያ አካባቢያቸው መንገዶችን በመሥራት ባደረጉት የልማት ተሳትፎ፣ በጦርነት ምክንያት ለተፈናቀሉና የወደሙ ተቋማትን መልሶ ለመገንባት በሚደረገው ርብርብ አሻራቸውን ማሳረፋቸውን ጠቅሰው፣ ለመንግሥት ማንኛውም ጥሪ ምላሽ ለመስጠት ሁለት ጊዜ አያስቡም።
አቶ እሸቱ፤ በአሁኑ ወቅት በካበተ ዕውቀትና ልምድ የመሠረቱት ግሎባል ኦይል በጥሩ መሠረት ላይ የተገነባ መሆኑን ይናገራሉ። በቀጣይ አምስት ዓመት ራሱን አደራጅቶ ተጨማሪ 150 ቅርንጫፎችን መፍጠር የሚችል ካምፓኒ እንደሚሆን ጠቅሰው፣ የሥራ ዕድልም በዚሁ መጠን እንደሚጨምር አመላክተዋል። ‹‹በአገር ውስጥ ያለውን በርካታ ሀብት ገና አልተጠቀምንበትም›› የሚሉት አቶ እሸቱ፤ ይህንን ሀብት በመጠቀም ወደ ሥራ የመቀየር ዕቅድ እንዳላቸው ጠቅሰው፣ ቀስ በቀስ ወደ መሬት እንደሚያወርዱትም ተናግረዋል።
ፍሬሕይወት አወቀ
አዲስ ዘመን ግንቦት 19/2015