አፍሪካውያን ከጸረ- ቅኝ ግዛት ትግላቸው ዋዜማ ጀምሮ አንድነታቸው የብርታትና የጥንካሬያቸው ምንጭ እንደሆነ በአግባቡ በመረዳት ጠንካራ ኅብረት ለመፍጠር ከፍ ባለ ቁርጠኝነት ተንቀሳቅሰዋል። ኅብረታቸውን እውን ለማድረግ በሄዱባቸው መንገዶ ሁሉ ያጋጠሟቸውን ፈተናዎች በአሸናፊነት ለመወጣትም ብዙ መስዋእትነቶችን ከፍለዋል።
የኅብረቱ እሳቤ ብዙም ምቾት ያልሰጣቸው አውሮፓውያን ቅኝ ገዥዎች፣ ገና ከጅምሩ የአፍሪካውያኑ ትግል ተናጠላዊ ሆኖ አቅም እንዲያጣ ሰፊ የመከፋፈል ዘመቻዎችን አካሂደዋል። የተለያዩ ሴራዎችንም ፈጥረው የነፃነት ትግሉ ሆነ አህጉራዊ ኅብረት የመፍጠሩ ንቅናቄ መራርና ብዙ መስዋዕትነት የሚጠይቅ እንዲሆን አድርገውታል።
በቅኝ አገዛዝ ስር የነበሩ አፍሪካውያን የነፃነት ትግል ስኬታማ ሆኖ ጋና የመጀመሪያዋ ነፃ አገር ስትሆን፤ በአፍሪካውያን መንፈስ ውስጥ የተቀጣጠለው የነፃነት መሻት፤ አድማሱ እየሰፋ መላው አፍሪካ የትግል አውድማ እንደሆነች፤ ለነፃነት የሚደረጉ ትግሎችም አህጉራዊ ድጋፍና ዓለም አቀፍ እውቅና እንዲያገኙ የተለያዩ ጥረቶች መካሄድ መጀመራቸውን የታሪክ መዛግብት ያትታሉ።
በወቅቱም በብዙ የተጋድሎ መስዋዕትነት ነፃነቷን አስጠብቃ የቆየችው ኢትዮጵያን ጨምሮ፤ ባልተጠበቀ ፍጥነት ነፃነታቸውን በመስዋእት ትግል የተጎናጸፉ የአፍሪካ አገራት መሪዎች በዓለም መድረክ ተሰሚነታቸውን በማጎልበት ለነፃነት ትግሉ አቅም መሆን የሚያስችል የትብብር ግንባር ለመፍጠር የሚያስችል ሰፊ ንቅናቄ ፈጥረዋል።
ንቅናቄው በዓለም አቀፍ ደረጃ አህጉራዊ ተሰሚነትን ከመፍጠር ባለፈ፤ በነፃነት ትግል ውስጥ ያሉ አፍሪካውያንን በሁለንተናዊ መንገድ በመደገፍ ትግላቸው ስኬታማ ሆኖ፤ ፈጥነው የነፃነት አየር እንዲተነፍሱ ማስቻልን ተልዕኮው አድርጎ ተንቀሳቅሷል። በሂደትም ለነፃነት ትግሉ ትልቅ ተጨባጭ አቅም መሆን ችሏል።
ንቅናቄው በሁለት ቡድኖች ተከፍሎ የነበረ ሲሆን፣ የመጀመሪያው በወቅቱ የጋና ፕሬዚዳንት ክዋሜ ንክሩማ የሚመራውና «ካዛብላንካ ቡድን» በመባል የሚታወቀው ነው። ጋና፣ አልጄሪያ፣ ጊኒ፣ ሞሮኮ፣ ግብጽ፣ ማሊ እና ሊቢያን በስሩ ያቀፈ፤ ሁለተኛው ደግሞ በሴኔጋሉ የወቅቱ ፕሬዚዳንት ሊዮፖልድ ሴዳር ሴንግሆር የሚመራው ፤ ሴኔጋል፣ ናይጄሪያ፣ ላይቤሪያ እና ኢትዮጵያ በአባልነት የያዘው የ«ሞኖሮቪያ ቡድን» ነበር።
የቡድኖቹ መሠረታዊ ልዩነት በአብዛኛው በስትራቴጂ ላይ ያተኩር እንጂ ዋነኛ ዓላማቸው በፖለቲካና በኢኮኖሚ ነፃ የሆነች አህጉር መፍጠር እንደነበርም የታሪክ መዛግብት ያትታሉ። ሁለቱ ቡድኖች በወቅቱ የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በነበሩት በአቶ ከተማ ይፍሩ እና በግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ድጋፍ አዲስ አበባ መጥተው እንዲወያዩ ተደርጎ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት መመስረቻ የስምምነት ውል ከስልሳ አመት በፊት ግንቦት 17 ቀን 1955 ዓ.ም በ32 የአህጉሪቱ ነፃ አገሮች ተፈርሞ ድርጅቱ ተመስርቷል።
አገራችን ኢትዮጵያ አህጉራዊ ኅብረቱን እውን በማድረግ ሂደትም ሆነ፤ የአፍሪካውያን ወንድሞቻችንን የነፃነት ትግል ስኬታማ ሆኖ ነፃነታቸውን እንዲጎናጸፉ ሁለንተናዊ ድጋፍ በማድረግ ግንባር ቀደም በመሆን፤ በአፍሪካውያን ወንድሞቻችን ዘንድ ከፍተኛ ከበሬታ ተጎናጽፋለች። በአፍሪካውያን የነፃነት ትግል ታሪክ ውስጥም በደማቅ ቀለም የተጻፈ ታሪክ ባለቤት መሆን ችላለች።
ኢትዮጵያውያን ለነፃነት ካላቸው ቀናኢነት የሚመነጨው ይህ ለአፍሪካውያን ወንድሞቻቸው የነፃነት ትግል ያበረከቱት መንፈሳዊ፣ ሥነልቦናዊና እና ቁሳዊ አስተዋጽኦ፤ ስለ ነፃነት የሚከፈል ዋጋ እጅግ የከበረና ትውልድ ተሻጋሪ መሆኑን በተጨባጭ ማረጋገጥ ያስቻለ፤ በጨለማ ውስጥ ለነበሩ አፍሪካውያን ወንድሞቻችን የብርሃን ወጋገን መሆን የቻለ ነው!
አዲስ ዘመን ግንቦት 18/2015