አንዳንድ ጥንዶች በችግር ወቅት ፈተና የመቋቋም ትዕግስት የላቸውም። ፍቅራቸው በፈተና ይሸረሸራል። አንዳቸው ወይም ሁለቱም ትዕግስት ያጣሉ፤ ብስጩ ይሆናሉ። በተለይ ወንዱ ፈተና ሲበዛ በችግር ተሸንፎ ሴቷን ከነልጆቿ ባዶ ቤት ጥሎ እስከመሄድ ይደርሳል። ለችግሩ መፍትሔ ከመፈለግ ይልቅ ይሸሻሉ። ብዙ አባወራዎች ሚስቶቻቸው ሥራ ውለው እንዲገቡ ሳይሆን የነሱ ጥገኛ ሆነው ኑሯቸውን ስቃይ በተሞላበት ችግር እየተጠበሱ እንዲገፉ ይፈልጋሉ።
አቶ ሽኩር አብደላ እንዲህ ዓይነት ባል እንዳልሆነ ባለቤቱ ወይዘሮ ሀዋ አብደላ አሊ ትመሰክርለታለች። እሷም እሱም ሠርተው በጋራ ጎጇቸውን እንዲያሞቁና ልጆቻቸውን እንዲያሳድጉ አጥብቆ የሚሻ እንደሆነም ትናገራለች። እንደነገረችን ሲገናኙ ሁለቱም ሥራ አልነበራቸው። በዚህ መካከል ሁለት ልጆች ይወልዳሉ። እሷ ልጆቿን ለእናቷ ትሰጥና ሥራ ፍለጋ ወደ ግብፅ ታመራለች። ለሦስት ዓመታትም እየሠራች በምትልከው ገንዘብ እናቷ ልጆቿን ያሳድጋሉ። በዚህ መካከል እናቷ ይሞታሉ። ይሄኔ መምጣቷ ግድ ነበርና ወደ ኢትዮጵያ ተመለሰች። ሆኖም ፊቱንም እዛ የምታገኘው ለልጆቿ ማሳደጊያ ብቻ ነበርና ምንም ሳንቲም ሳትቋጥር መጣች።
ለዓረብ አገር ተመላሾች መንግሥት የሥራ ዕድል ይፈጥራል መባሉ ተስፋ ሆኗት ነበር። ፈጥናም ልጆቿን በጀርባዋ አዝላና በእጇ እየጎተተች የሥራ አጥ ካርድ አወጣች። ወረዳና ክፍለ ከተማም እግሯ እስኪቀጥን ስትመላለስ ከረመች። ሆኖም ጠብ የሚል መፍትሔ አላገኘችም። በዚህ ሁኔታ ስምንት ወር ተቆጠረ። ተስፋ ቆረጠችና በአካባቢዋ ትንሽ የጉሊት ሥራ ጀመረች። በዚህ ሁሉ መካከል ባለቤቷ ያገኘውን እየሠራ ኑሯቸውን ከመደጎም ባሻገር በባለቤቱ ሁኔታ አብዝቶ ይጨነቅ ነበር።
በቅርቡ የጎጇቸውን ችግር የሚፈታ መፍትሔ ይዞላት እንደሚመጣም በተደጋጋሚ ቃሉን ሰጥቷታል። ቃሉን ወደ ተግባር ለመለወጥ ወረዳና ክፍለ ከተማ መመላለሱን ባወቀች ጊዜ ሀዋ እሷን መፍትሔ በመንፈግ ሲያለፋት ኖሮ ተስፋ ያስቆረጣት በመሆኑ በእጅጉ ተበሳጨች። ‹‹ለኔ መፍትሔ ባልሰጡኝ ቦታዎች በመመላለስ ጊዜውን በከንቱ ከሚያጠፋ ያገኘውን ሠርቶ ልጆቻችንን እንድናሳደግ” በማለት አብዝታ ለመነችው፤ ሆኖም እሱ ያለ መፍትሔ ለወራት መመላለሱን ሳይ ትዕግስት አጣሁ። በቃ ከነልጆቼ ጎዳና ሊያስወጣኝ ነው ብዬ መመላለሱን እንዲያቆም ደጋግሜ ነገርኩት ።ግን ፈቃደኛ አልሆነም። ለአንቺ ቋሚ ሥራ መፍጠር አለብኝ ብሎ ውሎውን ሙሉ ወረዳ አደረገ ትላለች። ሀዋና ባሏ በዚህ ምክንያት ከመነጫነጭ አልፈው መጋጨት ጀመሩ። ‹‹ሳይሰለች መመላለሱ ስለሚያናድደኝ ሲገባና ሲወጣ እቆጣው ሁሉ ነበር›› ስትልም ሁኔታውን ታስታውሰዋለች፡፡
‹‹ኑሮ እየናረ ሲመጣ በጉሊት ሥራ ብቻ ጎጇችንን ማቆም ሲከብደኝ ቁጭ ብዬ አለቅሳለሁ›› የምትለው ሃዋ ‹‹ችግር ብልሃትን ይወልዳል›› እንዲሉ ባለቤቷ በበኩሉ ችግራቸውን በዘለቄታው የሚፈታበትን መፍትሔ ፍለጋ ይሮጣል፤ እሷም ዝም ብላ አልተኛችም ።
የሃዋ ስለ ባለቤቷ ስትናገር “ትልቅ ሕልም ሰንቆ ለልጆቻችን ቆርሰን መስጠትና እኛም የምንበላው እስከማጣት የዘለቀ ችግር ሲገጥመን እንኳን ከማማረር ይልቅ ፈጣሪውን ማመስገንና መፍትሔውን መፈለግ ነበር የሚቀናው። ማንኛውም የሥራ ፈጠራና መፍትሔ የሚመነጨው ከችግር ነው። አይዞሽ ለችግራችን በቅርቡ ዘላቂ መፍትሔ እናገኛለን ሲለኝ ያመመው ሁሉ ስለሚመስለኝ ጭንቅላቴን እየነቀነቅኩ ትቸው እወጣ ነበር›› ስትል ሁኔታውን ትገልፀዋለች ።
እያንዳንዱ ሰው ወደዚህች ዓለም ሲመጣ፣ ችግር መፍቻ መፍትሔ ይዞ ነው የሚለው የሃዋ ባለቤትና ‹‹መልሶ መጠቀም›› የሚል ማኅበር ሥራ አስኪያጅ የሆነው አቶ ሽኩር አብደላ ብዙም ሳይርቁ የሥራ ፈጠራ መፍትሔውን በእዛው በሚኖሩበት በጉለሌ ክፍለ ከተማ አቅራቢያ አገኙ ።ክፍለ ከተማውና ወረዳው ቦታ ፈቀዱላቸውና መነን አካባቢ ‹‹የመልሶ መጠቀም›› ማኅበራቸውን አምስት ሆነው በ 40 ሺ ብር አቋቋሙ።
አቶ ሽኩር የውጭውን ሥራ ማለትም የታሸገ ውሃ ላስቲክን ጨምሮ ቁርጥራጭ ብረታ ብረቶች፤ ወረቀት፤ ካርቶን፤ የተሰባበሩ ወንበሮች፤ ሳህኖችና ሌሎች ቁሳቁሶች ከውጭ ሲሰበስብ እሷ ደግሞ ቁሳቁሶቹን ሰብስበው ወደ ማኅበሩ የሚያመጡ ሰዎችን መረከብና ክፍያ መፈጸም የሥራ ድርሻዋ ሆነ ።
ሀዊ መረከብ ብቻ ሳይሆን ወደ ፋብሪካ በሚላክ ጊዜ መኪና ላይም ታስጭናለች። 55 ኩንታል በሚይዙ ማዳበሪያዎች ውስጥ የታሸጉ ውሃ እቃዎችን እየጠቀጠቀች ትሞላለች። ማኅበሩ ያሉት 5 ሠራተኞች ሁሉም የየራሳቸው የሥራ ድርሻም አላቸው። በሦስት ቀን አንዴ ከአንድ ሺ ኪሎ ግራም በላይ የታሸጉ ውሃ እቃዎችን እንዲሁም አንድ መኪና ለመልሶ መጠቀም የሚያገለግሉ ቁሳቁሶችን መልሰው ለጥቅም ወደ የሚያውሏቸው ፋብሪካዎች ይጭናሉ። ግብዓቱን በአብዛኛው ያሉበት ድረስ ኅብረተሰቡ ይዞላቸው ይመጣል ።
‹‹ አሁን ገበያችን ሞቆልናል፤ እኛም ከችግር ተላቀናል›› የሚሉት ጥንዶቹ የጉለሌ ክፍለ ከተማ አስደንታ ከሚባል ድርጅት ጋር ስላዋዋላቸው በሦስትና በአራት ቀን ፤አንድ መኪና ካርቶን እንደሚጭኑም ይናገራሉ። በ40 ሺህ ብር የተጀመረው ሥራ አሁን ላይ የማኅበር የገንዘብ አቅም በ 100 ሺዎች በመቆጠር ላይ ከመገኘቱም በላይ ለብዙ ወጣቶች የሥራ ዕድል መፍጠር መቻሉንም ያስረዳሉ።
ጭለማው ሳይገልጥ በየአካባቢው እየዞሩ የወዳደቁ የውሃ እቃዎችንና ሌሎች ቁሳቁሶችን የሚለቃቅሙ በርካታ ወጣቶች በነ ሀዋ ማኅበር የሥራ ዕድል ተፈጥሮላቸዋል ። ከነዚህ አንዱ የሆነው የ27 ዓመቱ ወጣት አሸናፊ ከበደ እንደነገረን ከሦስት ወር በፊት ማልዶ የለቃቀመውን ቁሳቁስ እንደ ሌሎች ወጣቶች ሁሉ ለማኅበሩ ያቀርብ ነበር። አሁን ላይ ቋሚ የማኅበሩ ተቀጣሪ ሆኖ በየወሩ አራት ሺህ ብር ይከፍሉታል።
‹‹ በቀን እስከ 14 ማዳበሪያ የውሃ እቃዎችና ካርቶኖች እጠቀጥቃለሁ። መኪና ላይ እጭናለሁ” በማለት ከራሳቸው አልፎ ለሌሎች ወጣቶች የሥራ ዕድል መፍጠር ስለቻለው ማኅበር ውጤታማነት ይናገራል ።
ሰላማዊት ውቤ
አዲስ ዘመን ግንቦት 17/2015