የግብጽ መንግሥት በኢትዮጵያ የዓባይ ግድብ ግንባታ ዙሪያ የራሱን ሕዝብ ጨምሮ ዓለም አቀፉን ኅብረተሰብ በተዛቡ መረጃዎች ለማሳሳት ሰፋፊ ሥራዎችን መሥራት ከጀመረ ዓመታት ተቆጥረዋል። የጥረቱን ያህል ውጤታማ መሆን ባይችልም የተፈጥሮ ሀብቷን ፍትሐዊ በሆነ መንገድ በመጠቀም ድህነትን ለማሸነፍ ለምትተጋው ኢትዮጵያ ተግዳሮት መሆኑ አልቀረም።
ዓለም ከመቼውም ዘመን በተሻለ መልኩ ፍትሐዊ ነች በምትባልበት፤ ይህንንም ተጨባጭ ለማድረግ የተለያዩ ዓለም አቀፍ ሕጎች ተግባራዊ ሆነው ለተፈጻሚነታቸው በቁርጠኝነት እየተንቀሳቀሰች ባለችበት በዚህ ዘመን፤ የግብፅ መንግሥት ዘመኑን በማይመጥን መልኩ እየሄደበት ያለው ያልተገባ መንገድ የግብፅን ሕዝብ የማይመጥን ነው።
በዓለም አቀፍ ደረጃ ለብዙ ሥልጣኔዎች መነሻ የሆነው የግብፅ ሕዝብ ስለ ፍትሐዊነትና ከዚህ ስለሚመነጭ ዘላቂ ተጠቃሚነት አስተማሪ የሚፈልግ አይደለም። እንደ ሀገር በአንድ ወቅት ዓለም አቀፍ የእውቀት ማዕከል ከመሆኗ አንጻር ከመሪዎቿ የተዛባ የፖለቲካ እሳቤ ውጪ ለፍትሐዊነት ባእድ ነች ብሎ ለማሰብ የሚያስደፍር ነገር የለም፤ አይኖርምም።
የዓባይ ግድብ ግንባታን ፋይዳ ዘመኑ በደረሰበት እውቀት ለመገምገምም ቢሆን፤ ግብፅ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው የውሀ ባለሙያዎች ባለቤት ከሆኑ ሀገራት መካከል አንዷ ነች። ከእነዚህ ውስጥ በዓለም አቀፍ ደረጃ አንቱታ ያተረፉ ጥቂት የሚባሉ አይደሉም። እነዚህ ባለሙያዎች በግድቡ ዙሪያ በተለያዩ ወቅቶች የሰጧቸው ነፃ ሙያዊ አስተያየቶች ግንባታውን በአሉታዊ መንገድ የሚያነሱ አይደሉም።
በተለይም የቅኝ ግዛት አስተሳሰብና አስተሳሰቡ የፈጠረው የከፋ የጭካኔ ተግባር በግብፅ ሕዝብ ላይ ፈጥሮት ያለፈው ጠባሳ በአግባቡ ባላገገመበት ሁኔታ፤ መንግሥታቸው ቅኝ ገዥዎች ለራሳቸው ጥቅም አስቀምጠው ያለፏቸውን ሕጎች ዛሬ ላይ በዓለም አቀፍ አደባባይ ሳይቀር የሙጥኝ የማለቱ እውነታ በብዙ መልኩ የአስተሳሰቡ ሰለባ ስለመሆኑ በተጨባጭ እየመሰከሩ ናቸው።
ዛሬ ላይ ይህንኑ አስተሳሰብ በኢትዮጵያውያን ላይ ለመጫን የሚደረግ ጥረት በፀረ-ቅኝ ግዛት ትግሉ ወቅት የግብፅ ሕዝብን ጨምሮ አፍሪካውያን ለነጻነት የከፈሉትን መስዋዕትነቶች የሚያሳንስ፤ ለትግሉ ሆነ በብዙ ተጋድሎ ለተገኘው አሁናዊ ነፃነት ከበሬታ እንደማጣት የሚቆጠር ነው። ይህ ደግሞ ለአፍሪካውያን በተለይ ደግሞ ለኢትዮጵያውያን ምን ማለት እንደሆነ ለማሰብ የሚከብድ አይደለም ”
ኢትዮጵያውያን ለሉዓላዊ ክብራቸው፤ ነፃነታቸው እና ከዚህ ለሚመነጨው ማንነታቸው የቱን ያህል ቀናዒ እንደሆኑ ስለነፃነታቸው በየወቅቱ ከከፈሏቸው ከፍ ያሉ መስዋዕትነቶች ዓለም በተጨባጭ መማር ችሏል። ስለፍትሕም ያላቸውን ከበሬታም ሰሚ በሌለበት በዓለም አቀፍ አደባባይ ሳይቀር ድምፃቸውን ከፍ አድርገው ሲያሰሙ ታዝቧል ።
ዛሬ በግድቡ ግንባታ ዙሪያ ግልጽነትን ለማስፈን እንደሀገር እያደረጉት ያለው ጥረት ከዚሁ ፍትሐዊ አስተሳሰብና እና ከዚህ ለሚመነጭ ተግባራዊ እንቅስቃሴ ያላቸውን ቀናዒነት ለማሳወቅ ነው፤ በተለይ የግብፅ መንግሥት በየወቅቱ የዓባይ ወንዝ የውሀ አጠቃቀም ጉዳይን የሃገር ውስጥ እና ዓለም አቀፍ የፖለቲካ አጀንዳ በማድረግ በሕዝቡ ዘንድ እየፈጠረ ያለውን ያልተገባ ስጋት ለማጥራት ጭምር ነው።
ኢትዮጵያውያን የራሳቸውን ነገዎች ብሩህ ለማድረግ ዛሬ ላይ ባላቸው አቅም እንደሚተጉ ሁሉ፤ የግብፅ ወንድሞቻችንም ነገዎች ብሩህ እንዲሆኑ በጎ ሕሊና አላቸው። የሁለቱ ሀገራት ሕዝቦች እርስ በርሳቸው በጥርጣሬ ከመተያየት ወጥተው ለጋራ ተጠቃሚነት የሚሠሩበት ሁኔታ እንዲፈጠር ከምኞት ያለፈ መሻት አላቸው ።
የቀደሙትም ሆኑ አሁን በሥልጣን ላይ ያሉ የግብፅ መሪዎች የዓባይ ወንዝ ውሀ አጠቃቀምን ለሀገር ውስጥ ፖለቲካ አቅም መግዣ በማድረግ፤ በሁለቱ ሀገራት ሕዝቦች መካከል ፈጥረውት የነበረውንና አሁንም እየፈጠሩት ያለውን አለመተማመን በዘላቂ ፍትሐዊ ተጠቃሚነት በማደስ አዲስ የግንኙነት ምዕራፍ ለማስጀመርም ቁርጠኛ ናቸው ።
ይህንን የኢትዮጵያውያን እውነተኛ መሻት ታሳቢ በማድረግ፤ የግብፅ ሕዝብ መሪዎቹን ኢትዮጵያን ጨምሮ ከአፍሪካውያን ወንድሞቻቸው ጋር የነበራቸውን ተፈጥሯዊ ግንኙነት በማቀጨጭ ፈጥረው ያለፉትን ክፍተት በማጥበብ አፍሪካዊ ማንነታቸውን አጎልብተው፤ የአፍሪካዊነት መንፈስ ለመፍጠር ራሳቸውን ሊያዘጋጁ ይገባል። በየትኛውም መመዘኛ ቢታይ የዓባይ ግደብ የፍትሐዊ ተጠቃሚነት ማሳያ ነው!
አዲስ ዘመን ግንቦት 17/2015