የኢትዮጵያ መንገድ ፈንድ ጽህፈት ቤት ከተቋቋመበት ከ1989ዓ.ም ጀምሮ በመንገድ ልማት ፕሮግራም ላይ ከ15 በመቶ ያላነሰ በጀት አቅርቦ መንገዶችን አሁን ያሉበት ደረጃ ላይ አድርሷል፡፡
ተቋሙ ለመንገድ ጥገናና ደኅንነት እርምጃዎች የሚያስፈልጉትን ወጪዎች ለመሸፈን በመንግሥት ምንጮች ለመንገድ ጥገና ከተጣለ የነዳጅ ታሪፍ፣ በክብደት ላይ ከተመሠረተ ዓመታዊ የተሽከርካሪ ፈቃድ ማደሻ ክፍያ፣ ከተፈቀደው ክብደት በላይ በመጫን ከሚጣል ቅጣት፣ እንደአስፈላጊነቱ ከሚጣል ከማናቸውም ሌላ የመንገድ ታሪፍ ገቢዎችን በመሰብሰብ የአገሪቷን የመንገድ ሀብት የተሳለጠ ለማድረግ እየሰራ ቢሆንም፤ አሁን እየሠራበት ያለውን የ2ነጥብ5ቢሊዮን ብር ዓመታዊ በጀት ወደ አምስት ቢሊዮን ብር ካላሳደገ አገሪቷ ለሚቀጥሉት አምስት ዓመታት 200ቢሊዮን ብር የሚሆን ሀብት ልታጣ እንደምትችል የጽህፈት ቤቱ ዳይሬክተር አቶ ረሺድ መሀመድ ይናገራሉ፡፡
ቢሊዮኖች የፈሰሱበትን የመንገድ ሀብት ለመጠበቅም በዘርፉ ያሉ ተቋማትን ጨምሮ ካለፉት ተግዳሮቶች በመነሳት በአዳዲስ የትኩረት አቅጣጫዎች ለመስራት መታቀዱንም ያብራራሉ፡፡
እንደ ዳይሬክተሩ ማብራሪያ፤ በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያን የመንገድ ሀብት 200 ቢሊዮን ብር ግምት አለው የሚል ከተለያዩ ጥናቶች ማየት ተችሏል፡፡ በዓለም አቀፍ ምርጥ ተሞክሮ አንድ አገር በመንገድ ጥገናና በመንገድ ሀብት እንክብካቤ ጥሩ ደረጃ ላይ ነው ሊባል የሚችለው ቢያንስ የመንገድ ሀብቱን ከሁለት ነጥብ አምስት እስከ ሦስት ነጥብ አምስት ቢሊዮን ብር በየዓመቱ ለመንገድ ጥገና በጀት መመደብ ስትችል ሲሆን፤ ከዚህ አንጻር የኢትዮጵያም የመንገድ ፈንድ አነስተኛው አምስት ቢሊዮን ብር፤ ከፍ ሲል ደግሞ ሰባት ቢሊዮን ብር ማቅረብ ይኖርበታል፡፡
ይህ ካልሆነ ግን በአጭር ጊዜ ውስጥ አገሪቷ 200ቢሊዮን ብር የሚሆን ሀብት ልታጣ ትችላለች፡፡ ይህ እንደ አንድ ደሀ አገር ተቀባይነት ስለሌለው በቁርጠኝነት ለመስራት በጀትን ከመጨመር አዋጅ እስከማሻሻል የሚያደርሱ ሥራዎች ታስበዋል፡፡
የፌደራል፣ የክልሎችና የከተሞች የመንገድ ኔትወርክ በከፍተኛ ሁኔታ እያደገ መምጣቱ፣ መንገዶች በወቅቱ ባለመጠገናቸው ሀገሪቱ ለመልሶ ግባታና ለደረጃ ማሻሻያ አምስት ጊዜ እጥፍ የጥገና ወጪ እያወጣች መሆኑ፣ አንዲት ሀገር ለመንገድ ልማት የምታወጣውን የጠቅላላ ወጪ ከሁለት ነጥብ አምስት በመቶ እስከ ሦስት ነጥብ አምስት በመቶ በየዓመቱ ለመንገድ ጥገና መመደብ አስፈላጊ መሆኑ፣ አገሪቷን በሶስተኛው ትውልድ መንገድ ፈንድ አደረጃጀት እንድትገባ በማድረግ ጠንካራ ሚና እንዲኖራት ስለሚረዳ ጽህፈት ቤቱ አዲስ አዋጅን እንዲያሻሽል ስለመገደዱ ዳይሬክተሩ ያብራራሉ፡፡
የአዋጁ መሻሻል የመንገድ ሀብትን በአግባቡ በመጠቀም በርካታ ውጤት ማምጣት ይችላል ያሉት ዳይሬክተሩ፤ በተለይም ጥገናና የመንገድ ደህንነት ተግዳሮቶች በዘላቂነት ለመፍታት እንዲያስችል፣ የተቋሙ የማስፈጸም አቅም ለማሳደግ፣ ተቋሙ በአሰራር ላይ ያጋጠሙትን የፋይናንስና የአሰራር ክፍተቶች ለመፍታት፣ የፈንዱን አሰራር በጥናትና ምርምር እንዲደገፍ ለማድረግ፣ አዳዲስ ወጪ ቆጣቢና ዘመናዊ የመንገድ ጥገና አማራጮችን ተግባራዊ ለማድረግ፣ የአሰራርና ቴክኖሎጂ ለመጠቀም የሚያስችል አደረጃጀት ለመዘርጋት፣ ቀልጣፋና እንደሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ጠንካራ የመንገድ ፈንድ ተቋም ለመፍጠር እንዲቻል የጽህፈት ቤቱ አዋጅ እንዲሻሻል መደረጉን አስታውቀዋል፡፡
በኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን የመንገድ ደኅንነት ዳይሬክተር አቶ አብርሐም አብደላ በበኩላቸው፣ በያዝነው ዓመት ዘጠኝ ወራት ውስጥ በመንገድ ጥገናና ሥራ በተደጋጋሚ የጥገና መሳሪያዎች ብልሽት ማጋጠሙን፣ የአስፓልት መሳሪያዎች እጥረት መኖሩን፣ የጥገና መሳሪያ ለኮንስትራክሽን ማሰማራት ላይ እጥረት መከሰቱን፣ ለመደበኛ ጥገና ሥራዎች ፍላጎት ማነስና ከባድ ጥገና ላይ የማተኮር አዝማሚያ እንደነበር፣ የጥገና ሥራዎች በወቅቱ ማከናወን አለመቻሉን፣ የተራዘመ የግዥ ሂደት መኖሩን፣ አስቸኳይ መፍትሄ የሚፈልጉ ሥራዎች እንቅፋት መሆንና የመሳሪያዎች የማምረት አቅም አናሳ መሆኑ በተግዳሮት መወሰዱን ገልጸዋል::
አቶ አብርሐም እንደሚሉት፤ በተለይ የግል ተቋራጮች የጥገና ግብዓቶች በታቀደላቸው ጊዜ መቅረብ አልቻሉም፡፡ የገንዘብና ግብዓት አቅርቦት ውስንነት ማጋጠሙና ለአንዳንድ የጥገና ሥራዎች ያላቸው ፍላጎት አናሳ መሆን፣ ለመንገድ የሚያስፈልጉ የጥገና አይነቶችን በታቀደላቸው ጊዜ ባለማከናወናቸው መንገዶች ለከፋ አደጋ እንዲጋለጡ አድርገዋል፡ ፡ የኮንትራት ውል ትርጓሜና አፈጻጸምን ያለመረዳትም ችግር እንደነበረባቸው አያይዘው ገልፀዋል፡፡
አቶ አብርሐም አክለውም አስፈላጊ ሪፖርቶችን በወቅቱ ያለማቅረብ፣ ተሽከርካሪዎችን በኮንትራት ስምምነቱ መሠረት ያለማቅረብ፣ ተደጋጋሚ የሰራተኞች ፍልሰት፣ ወቅታዊ የመንገድ ሁኔታ መረጃዎች መዝግቦ ያለመያዝ፣ የጥገና በጀት አፈጻጸም ክትትል ማነስ፣ የጥገና እቅድና በመከታተል አለመከለስና አስፈላጊ ግብዓቶችን ያለማቅረብ፣ ከአካባቢው ህብረተሰብና የአስተዳደር አካላት ጋር ተቀራርቦ ያለመስራት በአማካሪ በኩል የታዩ ክፍተቶች መሆናቸውን ጠቅሰዋል፡፡
ከዚህም በተጨማሪ በኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን በኩል ወሰን የማስከበር፣ የኮንትራት ውል ዝግጅት ችግር፣ የግዥ ሂደት መዘግየት፣ ከኮንትራት ውል ጋር በተያያዘ ለሚቀርቡ ጥያቄዎች በወቅቱ ምላሽ አለመስጠት እንደ ከፍተት መታየቱን አስታውቀው፤ የመንገድ ሀብቱን የበለጠ ለማጠናከር ቀጣይ የትኩረት እቅጣጫዎች መቀመጣቸውን ገልጸዋል፡፡
ቀሪ ሥራዎችን በፍጥነት በማከናወን የዝናብ ወቅት ከመግባቱ ወዲህ ማጠናቀቅና ለመደበኛ ጥገና ከፍተኛ ትኩረት በማድረግ ያልተጀመሩ ፕሮጀክቶች በፍጥነት እንዲጀመሩ ለማድረግ መታሰቡን አቶ አብርሐም አስታውቀዋል፡፡
በዚህም ከመስተዳድር አካላት ጋር በቅንጅት መስራት፣ የተቀናጀ የመንገድ ሃብት አስተዳደር ሥርዓት መዘርጋት፣ የመንገድ ክፍፍልን የአስተዳደር ሥርዓት ማሻሻል፣ ተከታይ አቅም ግንባታ ስልጠና መስጠትና በመንገድ ሀብት አስተዳደር የአስተሳሰብ ለውጥ ማምጣት እንደሚያስፈልግ አስገንዝበዋል፡፡
‹‹የመንገድ እንክብካቤ አብይ ትኩረታችን ነው›› ያሉት አቶ አብርሐም፤ ከተደራሽነት በላይ ጥራት ላይ በማተኮር፣ በመንገድ ማኔጅመንት ቅርንጫፍ ዳይሬክቶሬቶች የመንገድ ሁኔታ ክትትልና የመንገድ ጥገና ውል ማስተዳደር እንደሚገባ ጠቅሰዋል:: በግንባታ ወቅትም ጥብቅ ክትትል እንደሚደረግ አብራርተዋል፡፡
አጠቃላይ የመንገድ ሃብትን ማስተዳደር መጠገን ብቻ ባለመሆኑ ለተጠቃሚው ማኅበረሰብ ምቹና ደኅንነቱ የተጠበቀ ትራንስፖርት እንዲያገኝ ማስቻል፣ የጥገና ምንጭን በመጨመር ረገድም የመንገድ ፈንድ ተጨማሪ የበጀት ምንጮችን ማፈላለግ፣ በካፒታል በጀት ለጥገና የሚመደበውን በጀት ማስጨመር፣ በብድርና በእርዳታ ለጋሽ አካላት የሚሸፈንበትን መንገድ ማፈላለግ ሲኖርበት፤ የጥገና ወጭን በመቀነስ ረገድ ደግሞ መንገዶች ለከፋ ጉዳት እንዳይዳረጉ ቅድመ መከላከል የመንገድ ጥገና ስትራቴጂ መከተል፣ በኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣንና አቻ ተቋማት አማካኝነት በራስ ሀይል የመንገድ ጥገና አቅም መፍጠር፣ ከልክ በላይ ጭነትን በተገቢው ሁኔታ መቆጣጠር፣ በመንገድ ጥገና የግል ዘርፍ የግል ተሳትፎ ማሳደግ፣ በምርምር ዘርፍ ለጥገና የሚውሉ የተሻሻሉ የቴክኖሎጂዎችን ግብዓቶች ማፈላለግ ቀጣይ የትኩረት አቅጣጫ መሆናቸውን አቶ አብርሐም ተናግረዋል፡፡
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 25/2011
በአዲሱ ገረመው