አንድ ሀገር ዓለም አቀፍ ህግን መሰረት ባደረገ መንገድ ያላትን የትኛውንም አይነት የተፈጥሮ ሀብት ለመጠቀም የማንንም ይሁንታ የመጠበቅ ግዴታ የለባትም። ዓለም አቀፍ ሕጎች ያስፈለጉበት ዋነኛ ምክንያትም ያለ ምንም አምባጓሮ በሀገራት መካከል ፍትሀዊ ተጠቃሚነት በማስፈን ዘላቂ ሰላምና ወዳጅነት ለማስፈን ነው።
ሀገራችን ኢትዮጵያም እንደ አንድ ሉአላዊ ሀገር ያላትን የተፈጥሮ ሀብት ዓለም አቀፍ ህጎችን መሰረት ባደረገ መንገድ የመጠቀም መብት አላት፤ ይህንን መብቷን ተግባራዊ በማድረግ ሂደት የማንንም ይሁንታ የመጠበቅ ግዴታም ሆነ በዚህ መንገድ የሚመጡ ጫናዎችንም የሚያስተናግድ ሀገራዊ የስነ ልቦና መሰረት የላትም።
ድህነትን አሸንፎ መውጣት የህልውና ጉዳይ በሆነበት አሁናዊ ሃገራዊ አውድ ውስጥ ፤ የተፈጥሮ ሀብቶቻችንን አግባብ ባለው መልኩ መጠቀም ለአማራጭ የሚቀርብ አይደለም። በተለይም ድንበር ተሻጋሪ የሆነውን የውሃ ሀብታችንን ዓለም አቀፍ ህግን መሰረት ባደረገ መልኩ የመጠቀም መነሳሳታችን ፤ በዓለም አቀፍ ደረጃ ድህነትን ለማሸነፍ በሚደረገው ትግል ውስጥ ሊበረታታና ትልቅ ድጋፍ ሊሰጠው የሚገባ እንጂ ለድርድር የሚቀርብ አይደለም።
በተለይም የዓባይ ወንዝ ውሃን ፍትሀዊ በሆነ መልኩ በመጠቀም ለጸረ-ድህነት ትግላችን ትልቅ አቅም የሚሆነንን የኤሌክትሪክ ኃይል ለማመንጨት ያስችለን ዘንድ የጀመርነው የዓባይ ግድብ ፕሮጀክት ፤ ለሱዳንም ሆነ ለግብጽ ካለው ስትራቴጂክ ጠቀሜታ አንጻር ፤ በሀገራቱ ሆነ በዓለም አቀፉ ኅብረተሰብ ሁለንተናዊ ድጋፍ ሊቸረው የሚገባ እንደሆነ ይታመናል።
ከዚም ባለፈ ቅኝ ገዥዎች የአፍሪካውያንን የተፈጥሮ ሀብት ለመቀራመት ባልተገባ መንገድ እነሱው ውል ሰጪ እነሱው ውል ተቀባይ ሆነው አስቀምጠው ያለፏቸውን ኢ- ፍትሀዊ ውሎች ፤ዓለም አቀፍ ህጎችን መሰረት ባደረገ መንገድ በመግራት በሀገራት መካከል ዘላቂ ሰላምና ወንድማማችነትን ለማስፈን እንደ አንድ ትልቅ አለም አቀፍ ተሞክሮ ተደርጎ ሊወሰድ የሚችል ነው።
ኢትዮጵያ በጸረ -ቅኝ አገዛዝ ትግሉ ወቅት እንዳደረገችው ሁሉ፤ ድህነትን ከአህጉሪቱ ለማስወገድ ለሚደረጉ ጥረቶች እራሷን በሁለንተናዊ መንገድ እያዘጋጀች እንጂ በወንድም ህዝቦች ጉዳት ላይ ለተመሰረተ ተጠቃሚነት የምትሠራ አይደለችም። ለእንዲህ አይነቱ ማኅበረሰባዊ ማንነት የተገዛ ሀገራዊ ስብእናም ሆነ የቀደመ ታሪክ የላትም።
ራሷን ጨምሮ አፍሪካውያን ወንድሞቻችን ካሉበት ድርብርብ ችግሮች ወጥተው ፤ የራሳቸውን እድል በራሳቸው የሚወስኑበትን አቅም ለመፍጠር ፤ ከነጻነት ማግስት ጀምሮ በተናጠልም ሆነ በአፍሪካ አንድነት ድርጅትና በአፍሪካ ኅብረት በኩል ብዙ ጥረት ስታደርግ ቆይታለች ፤ዛሬም እያደረገች ትገኛለች።ይህ አቋሟ ዛሬም ቢሆን የተለወጠ አይደለም።
ላለፉት አስርት ዓመታት በላይ በዓባይ ግድብ ግንባታ ዙሪያ በዓለም አቀፍ ደረጃ ግልጽነት ለመፍጠር ያለመታከት የሄደችበት መንገድ የዚሁ እውነታ ተጨባጭ ማሳያ ነው። በተለይም ግንባታው ከዓለም አቀፍ ህግ አንጻር ችግር የሌለበት ፤ የጎረቤት ሀገራት ህዝቦችን ስትራቴጂክ ተጠቃሚ በማድረግ ጉርብትናን በጠንካራ መሰረት ላይ ለማዋቀር የተሻለ አቅም መሆኑን ለማሳየት የሄደችበት ርቀት ረጅም ነው።
ይህ በዓለም አቀፍ ህግና ዘመኑ በደረሰበት ቴክኖሎጂ የታገዘው የሀገሪቱ ጥረት ፤ ለፍትሀዊ እና ሳይንሳዊ አስተሳሰብ በተገዙ አካላት ዘንድ ትልቅ ከበሬታ እና ይሁንታን ያተረፈ ሲሆን፤ በግብጽ መንግስት በኩል ጉዳዩን የፖለቲካዊ አጀንዳ፤ የፖለቲካ መቆመሪያ ካርድ አድርጎ ለማትረፍ ከሚደረገው የተሳሳተ ሙከራ አንጻር ተገቢውን ውጤት ማግኘት ሳይችል ቀርቷል።
ከጊዜያዊ የፖለቲካ ተጠቃሚነት የማይዘለው የግብጽ መንግስት ጥረት ፤ የሁለቱን ሀገራት ሕዝቦች ወንድማማችነትና ዘላቂ የጋራ ተጠቃሚነት ከግምት የማያስገባ፤ ለቅኝ ገዥዎች ጊዜው ያለፈበት አስተሳሰብ የተገዛና ፤ ይህንኑ ለማስፈጸም የሚሞክር በመሆኑ በየትኛውም መመዘኛ ተቀባይት የለውም፤ መቼም አይኖረውም።
ይህንን አስተሳሰብ ተቀብሎ በየትኛውም መንገድ በሃገራችንና በሕዝባችን ላይ ጫና ለማድረግ መሞከር በአንድም ይሁን በሌላ በሀገሪቱ ሉአላዊነት ላይ በግልጽ ጣልቃ መግባት ነው ። ከዚህ አንጻር የአረብ ሊግ ሰሞኑን የዓባይ ግድብ አራተኛ የውሃ ሙሌትን አስመልክቶ ያወጣውን መግለጫ መልሶ በማጤን ተገቢውን ማረሚያ ሊያወጣ ይገባል። መግለጫው እራሱን ገለልተኛና ፍትሀዊ አድርጎ ከሚገምት አንድ ተቋም የሚጠበቅም አይደለም!
አዲስ ዘመን ግንቦት 16/2015