በተለያዩ ሀገሮች ውስጥ በሥልጣን ባላንጣዎች መኻከል የፖለቲካ ጉግሥ ሲካሄድ መኖሩን ለመረዳት አያዳግትም፡፡ በሀገራችንም ለሥልጣን ሲባል የተካሄደው ጦርነትና የተከፈለው መሥዋዕትነት ከፍተኛ ነው፡፡ በዚህ ዓይነት የራቀውን ትተን የትላንቱን በልጅ ኢያሱና በራስ ተፈሪ መኻከል የነበረው የፖለቲካ ትግል ብናስታውስ አስከፊ ገጽታ የነበረው መሆኑን ለመረዳት አያዳግትም፡፡ የዚህ ጽሑፍ ቅኝትም የሁለቱን መሳፍንት የፖለቲካ ፉክቻ የሚዳስስ ነውና እነሆ፡፡
ልጅ ኢያሱንና ደጃዝማች ተፈሪን በፖለቲካ ሥልጣን ጉዳይ ባላጋራዎች አስከመሆን ያደረሳቸው በመኻከላቸው የነበረው መናናቅና የሥልጣን ጉጉት ነው ለማለት ይቻላል፡፡ የሥልጣን ባላንጣዎች የሆኑት ተፈሪና ኢያሱ ለመጀመሪያ ጊዜ የተያዩትና የተዋወቁት ራስ መኮንን ከሞቱ ከሁለት ወር በኋላ በ1898 ዓ ም በአዲስ አበባ በዓፄ ምኒልክ ቤተ መንግሥት ውስጥ ነው፡፡ ያኔ ተፈሪ የአሥራ ዐራት ዓመት እድሜ ሲኖራቸው ኢያሱ ደግሞ የዘጠኝ ዓመት ልጅ ነበሩ ( ዘውዴ 1884-1922፡133)፡፡ ሁለቱም የመሳፍንት ልጆች በቤተ መንግሥት ግብር ሥነ ሥርዓት በሦስተኛ ረድፍ በሚዘረጋው ገበታ ሲቀመጡ ኢያሱ የዘውዱ የቀጥታው ዘርፍ ተከታይ በመሆናቸው ቀዳሚውን ስፍራ ሲይዙ ተፈሪ ደግሞ በሁለተኛነት ይቀመጣሉ፡፡ በመሳፍንት ልጅነታቸው አብረዋቸው ይቀመጡ የነበሩትም ልጅ ብሩ ወልደ ገብርኤል (በኋላ ራስ) ፤ልጅ ጌታቸው አባተ (በኋላ ራስ) ናቸው፡፡
የአኗኗር /ዘይቤ/ ዲሲፕሊን ሳይጫናቸው የሚፈልጉትን ነገር ሁሉ እያገኙ በነፃነት እንደልብ ያደጉት የወሎው መስፍን ኢያሱ ቁመተ ሎጋ፤መልከ ቀናና ደንዳና፤ ቀልደኛና ተጨዋች፤ በጉልበታቸው የሚተማመኑ ግልጽ ሰው ስለሆኑ በልጆች ዘንድ የመፈራት ሞገስ ነበራቸው፡፡ለታላላቅ ሰዎችና ለባለሥልጣናትም ሲሽቆጠቆጡና በትሕትና እጅ ሲነሱ አይታዩም፡፡በተቃራኒው የሐረሩ መስፍን ተፈሪ ግን በሰውነታቸው ደቃቃ፤ አጭርና ከሲታ፤ጨዋታና ቀልድ፤ ልፊያ ጨርሶ የማይወድዱ ቆምጫጫ፤ አስቸጋሪ ጠባይ ነበራቸው፡፡ እንደ ባሕታዊ ዝምተኛና ለየመሳፍንቱና ለየመኳንንቱ እጅ የሚነሱና ለጥ ብለው የሚሰግዱ ስለሆኑ ልጅ ኢያሱ ሆን ብለው ተፈሪን ለማናደድና ለማበሳጨት «አንተ ለመሬቱ በጣም ቅርብ ስለሆንክ እጅ መንሳትህ አይታይልህም» በማለት ያናድዷቸዋል፡፡ ሌላም ደም የሚያፈላ ነገር እየፈለጉ ያበሳጯቸው ነበር ይባላል፡፡
እንዲያውም በአስተሳሰብና በመንፈስ፤ በጠባይና በምግባር በእጅጉ የተለያዩት ሁለቱ አንድ ቀን ውኃ ዋና ገብተው ሲዋኙ ጉልበተኛው ልጅ ኢያሱ በውኃ አፍነውና ደፍቀው ሊገድሉዋቸው ነበር ይባላል፡፡ በኋላ ጊዜም አቤቶ ኢያሱ ሥልጣን እንደያዙ ደጃዝማች ተፈሪን ከአባታቸው ግዛት ከሐረር ሽረው ወደ ከፋ ስለመደቧቸው የእድሜ ልክ ቅሬታ አድሮባቸው ነበር፡፡ ፊታውራሪ (በጅሮንድ) ተክለ ሐዋርያት እንደጻፉት ልጅ ኢያሱ ቀስበቀስ የሥጋ ዘመዳቸውንና የሥልጣን ተቀናቃኛቸውን ተፈሪን መፍራት ይጀምራሉ፡፡ከዚህም የተነሣ ተፈሪን በወዳጅነት ለመያዝ ፈልገው የታላቅ እኅታቸውን የወይዘሮ ስኂን ሚካኤልን ልጅ ወይዘሮ መነን አስፋውን አዲስ አበባ ውስጥ ይኖሩ ከነበሩት መስፍን ከሦስተኛ ባለቤታቸው ከራስ ሉል ሰገድ አፋትተው ዳሩላቸው፡፡ ይህ የጋብቻ ዝምድና ግን በሁለቱ መኻከል የነበረውን ቅራኔ ሊያረግበው አልቻለም፡፡ ምክንያቱም ጉዳዩ የዝምድና ሳይሆን የሥልጣን ጉዳይ ስለሆነ ነው፡፡
ልጅ ኢያሱ በአዲስ አበባ ለአንድ ዓመት ከቆዩ በኋላ ዳግማዊ ዓፄ ምኒልክ በፀና ታመሙና ጥቅምት 20 ቀን 1902 በታላቁ ቤተ በንግሥት በታላቁ አዳራሽ ሚኒስትሮች፤ መሳፍንትና መኳንንት፤ ታላላቅ የጦር አዛዦችና የውጭ አገር መንግሥታት እንደራሴዎች በተገኙበት ታላቅ ጉባኤ ላይ የልጅ ኢያሱ አልጋ ወራሽነት ነጋሪት እየተጎሰመ፤ እምቢልታ እየተመታ አዋጅ ታወጀ ፡፡ ሊቀ ጳጳሱ አቡነ ማቴዎስም አዋጁን በቡራኬ ጭምር አፅንተው ከአዋጁ በሚያፈነግጠው ላይም የውግዘት ቃላቸውን አሳረፉበት፡፡ የዳግማዊ ዓፄ ምኒልክ ወራሴ መንግሥት የነበሩት ልጅ ኢያሱ የወሎው ንጉሥ ሚካኤል ልጅና የዳግማዊ ምኒልክ የልጅ ልጅ የወይዘሮ ሸዋረጋ ልጅ ናቸው፡ በመሆኑም ዓፄ ምኒልክ አቤቶ አያሱ የመንግሥታቸው ወራሽ እንዲሆኑ በ1902 በአዋጅ ጭምር አፅንተው ነበር፡፡ ልጅ ኢያሱን የከዳና የካደ የተረገም ይሁን፤ጥቁር ውሻ ይውለድ የሚል መሐላም አሳርፈው ነበር ፡፡
ዳግማዊ ምኒልክ ከዐረፉ በኋላ ግን አዋጁና መሓላው ተግባራዊ አለመሆኑን የተረዱትና የልጅ ኢያሱ አጨዋች የነበሩት ባለቅኔው አዝማሪ ነጋድራስ ተሰማ እሸቴ በማሲንቆ ምት መሓላ ተጣሰ በመላው አበሻ፤
ማን ይወልዳት ይሆን ያችን ጥቁር ውሻ፡፡
ብለው ገጠሙ ይባላል፡፡ ያችን ጥቁር ውሻም መጨረሻ ላይ ማን እንደወለዳት ለማወቅ አልተቻለም፡፡
ወይዘሮ ሸዋረጋ ምኒልክ ጥር 27 ቀን 1884 ዓ ም ለወሎው ባላባት ለራስ ሚካኤል ዓሊ ተድረው ጥር 27 ቀን 1889 ባገቡ በ5 ዓመታቸው በደሴ ከተማ ኢያሱን ወልደዋል፡፡ ልጅ ኢያሱ በተወለዱ በስድስተኛ ወራቸው ሐምሌ 13 ቀን 1889 እናታቸው ወይዘሮ ሸዋረጋ ምኒልክ ወረኢሉ (ቤተአምሐራ) ሞቱና ወረኢሉ ላይ ለቅሶ ተደረገላቸው፡፡
የወይዘሮ ሸዋረጋን ሞት ተከትሎ በሸዋ ቤተ መንግሥት የተደረገውን ኀዘን በተመለከት እንዲነግሩኝ የወሎ ተወላጅ የሆኑትን ፶ አለቃ አሰፋ ተክሌን አነጋግሬ ነበር፡፡ ፶ አለቃ አሰፋ ተክሌ የታሪክ መጻሕፍትን ተከታትለው ያነብባሉ፡፡ ግጥም መግጠም ደግሞ ተሰጥኦዋቸው ነው፡፡ ራሳቸው ይገጥማሉ፡፡ ጊዜና ወቅትን መሠረት አድርገው የተገጠሙትንም አይረሱም፡፡ በልጅ ኢያሱ፣ በንጉሥ ተፈሪ፣ በንጉሥ ሚካኤል ወቅት ከቅራኔ የተነሣ የተነገሩ ግጥሞችን አንደ ዳዊት ይደግሟቸዋል፡፡
እርሳቸውም እንደሚሉት ራስ ሚካኤል (ያኔ ራስ ነበሩ) ከዳግማዊ ምኒልክ ጋር ለመላቀስ ከደሴ ወደ ሸዋ መጥተው በእንጦጦ ቤተ መንግሥት ከአማቻቸው ጋር ኀዘን ተቀመጡ፡፡ በቤተ መንግሥቱ የውሎ ለቅሶ በተደረገበት ዕለት አንዲት የሸዋአልቃሽ፤
“ምነው በቀረባት የወሎ ጋብቻ፣ የወሎግዛት፣
ግሸን ወድቃ ቀረች የሸዋ እመቤት” ብላ አንጎራጎረች፡፡
በዚህ ጊዜ ተሰማ ጎሹ የተባለው የወሎ አልቃሽ በሴትዮይቱ እንጉርጉሮ የወሎ ሰው የከፋው መሆኑን ተረድቶ የሚቀጥለውን የለቅሶ ግጥም ገጠመ፡፡
“ምነው ወሎን ገዝታ ግሼን ብትቀበር፤
ግማደ መስቀሉ ካረፈበት አገር፡፡
ከሚካኤል ወዲያስ ምን ክብር ባል ነበር፡፡
አይስሟት ጌታየ የሴትን ወሬኛ፤
እንጦጦን አይፈራም የአምላክ መላክተኛ፡፡
አሁን ምን ያደርጋል የሴት ወዮ ባይ፡
ወሎ የመጣው ሞት ሸዋ የለም ወይ፡፡
ተይ አንቺ ሴትዮ ነገር አታጥብቂ፤
እኛ አልገደልናትም እግዜርን ጠይቂ፡፡» ብሎ በአንጎራጎረ ጊዜ ዓፄምኒልክ «ተውት ይቅር ይኸ ሁሉ ነገር ምን ያስፈልጋል!» ብለው ለቅሶውን አስቆሙት፡፡
ልጅ ኢያሱ ገና በልጅነታቸው የዓፄ ምኒልክን አልጋ ወርሰው በራስ ቢትወደድ ተሰማ ናደው እንደራሴነትና ሞግዚትነት፤ በፊታውራሪ ሀብተ ጊዮርጊስ ደጋፊነት፤ በነጋድራስ ተሰማ እሸቴና በኋላም በፊታውራሪ ተክለ ሐዋርያት አማካሪነት ኢትዮጵያን እየመሩ ወላጅ አባታቸውን ራስ ሚካኤል አሊንም ግንቦት 23 ቀን1906 ዓ.ም ደሴ ላይ «ንጉሠ ወሎ ወትግሬ ሚካኤል ንጉሠ ጽዮን » ብለው አነገሱ፡፡ ከዚያም የዲፕሎማሲውን ሥራ የሚሠሩና የጦር መሣሪያ የሚገዙ መልእክተኞችን ወደነምሳ ልከው፤ በአዲስ አበባ ውስጥ እንደፈለጉ ሹም ሽር ሲያደርጉና ሲቀብጡ ቆዩ፡፡ በኋላም በ1908 ዓ.ም ከዋና ከተማቸው ወጥተው የመንግሥቱን ሥራ ትተው በጊሚራ፤ በአዳል በሐረርጌ፤ በድሬዳዋ፤ በጂጂጋ፤ በአውሳ– እየተዘዋወሩ መጎብኘትና መዝናናት፤ ከሕዝብም ጋር መተዋወቅ ጀመሩ፡፡
አቤቶ ኢያሱ በዕለተ ዐርብ ሐምሌ 21 ቀን 1908 ዓ.ም በባቡር ተሳፍረው ወደ ሐረር ለመሔድ ከለገሐር ባቡር ጣቢያ ሲደርሱ ( ዘውዴ፡275) አንዲት አረሆ ግርግሩን አይታ አየሸለለች በመቅረብ «ጌታየ ደኅና ግባ» የሚል ድምጽ አሰማች፡፡ አቤቶ ኢያሱም በዜማዋ ስለተደሰቱ ገንዘብ ወረወሩላት፡፡ ባቡሩ ጉዞውን ከቀጠለ በኋላ ይችው አረሆ እንዲህ ስትል ትንቢትነት ያለው እንጉርጉሮ አሰማች፡፡
ደኅና ግባ ብለው ደኅና ቆይኝ አለኝ፤
ፊቱን ፈካ አድርጎ ገንዘቡን ጣለልኝ፤
አይቼ እማላውቀው ደግነት በዛብኝ፤
እንደ ወጣ በዚያው ሊቀር ነው መሰለኝ፡፡
ትንቢቱም ደረሰና አባ ጤና ኢያሱ እንደወጡ በዚያው ቀሩ እንጂ ወደ አዲስ አበባ አልተመለሱም፡፡ የጉዟቸው ዓላማ ሐረር ሆነው ደጃዝማች ተፈሪን በአዋጅ ከሥልጣን ለማውረድ ሲሆን ምክሩን እምብዛም ከማይቀበሉት የውጭ አገር ተወላጅ ከሆነውና ከአማካሪያቸው ከነጋድራስ ይድልቢ ጋር ሐረር ውስጥ አሸሼ ገዳሜ ሲሉ የሸዋ ሴራ ተፋጥኖ ከሥልጣናቸው አስወግዷቸዋል፡፡
አልጋ ወራሹ ከዋና ከተማዋ አዲስ አበባ ለብዙ ወራት ያህል በጠፉበት ጊዜ የሸዋ ቤተ መንግሥት ‹‹ አቤቶ ኢያሱ በአለባበስና በአጠማጠም ጭምር የእስልምናውን እምነት ተከትለዋል፤ ሰልመዋል፤ ከልዩ ልዩ ሴቶች ጋርም ሲቀብጡ ታይተዋል›› በሚል ዶለተባቸው ፡፡ ይህንኑ ወሬ የሰሙት ባለሟላቸው ፊታውራሪ ወልደ አማኑኤል የምሥራቁን አካባቢ ኑሮ ትተው ወደ ሸዋም እንዲመለሱ ቢመክሯቸውም አቤቶ ኢያሱ «ሸዋ ብትዶልት ምን ታደርጋለች›› ብለው ነገሩን ችላ አሉት፡፡ ዘውዴ ረታ እንደገለጹት በእስልምና አማኒነት የተጠረጠሩት አቤቶ ኢያሱ ግን በ1903 ዓ ም የደብረ ሰላም ቀጨኔ መድኃኔ ዓለምን ቤተ ክርስቲያን የመሠረቱና በዓለ ንግሱም በሐምሌ 27 ቀን ሲከበር ከሌሎች ታላላቅ ሰዎች ጋር በሥርዓተ ቅዳሴው ላይ ተገኝተው አስቀድሰዋል፡፡ ለደብረ ሊባኖስ ገዳም መተዳደሪያ የሚሆን 80 ጋሻ መሬትም አበርክተዋል፡፡
በጊዜው የሸዋን ዐድማ ሐረር ላይ ሆኖ የሰማው አንድ የልጅ ኢያሱ አሽከርም
ቀን ይምጣ ሌት ይምጣ አታውቁትምና፤
የሸዋ መኳንንት እንዳትሆኑ መና፤
አልጋውን አይለቅቅም ኢያሱ አባ ጤና፡፡
ብሎ አንጎራጎረ፡፡
በልጅ ኢያሱ ላይ ሤራ ጠንስሰው ከሥልጣን ያስወገዷቸው የዐድማው ቀንደኞች (መርስኤ ኀዘን1999፡149) እጨጌ ወልደ ጊዮርጊስ አባ ክብረት፤ ፊታውራሪ ሀብተ ጊዮርጊስ አባ መቻል፤ ሊጋባ በየነ አባ ሰብስብና ደጃዝማች ኃይለ ማርያም ለማ አባ ይባስ ናቸው፡፡ በተጨማሪም እነ ልዑል ራስ ካሣ ኃይሉ፤ራስ ወልደ ጊዮርጊስ፤በጅሮንድ ተክለ ሐዋርያት፤ከንቲባ ገብሩና ነጋድራስ ገብረ ሕይወት ባይከዳኝ የዐድማው ተሳታፊዎች ነበሩ፡፡
ዐድመኞቹ በነሐሴ ወር በቤተ መንግሥት አደባባይ በተጠራው ጉባኤ ላይ ልጅ ኢያሱ ለመስለማቸው ማስተማመኛ እንዲሆን በእንግሊዛዊው ኮሎኔል ቲ፤ኤ፤ሎሬነስ የተቀነባበረና ሐረርጌ ውስጥ ከሚኖሩ አረቦች ጋር የተነሡት ፎቶግራፍ ነው በሚል በጥሩ ሠዓሊዎች የተዘጋጀ ፎቶገራፍ መሰል ሥዕል ለተሰብሳቢዎቹ አቀረቡ፡ተሰብሳቢዎችም ፎቶ መሰል ሥዕሉን እየተቀባበሉ በማየት ሲገረሙና ሲቆጩ ደጃዝማች ተፈሪም በስተጀርባ ሆነው እሳቱን ይቆሰቁሱ ነበር ይባላል፡፡ የኦርቶዶክስና የካቶሊክ ካህናት በበኩላቸው አቤቶ ኢያሱ በአንዲት ሴት የማይረጉ ፀረ ክርስቶስና ፀረ ክርስትና መሆናቸውን እያስረገጡ ለጉባኤተኞች ተናገሩ፡፡ አድመኞቹ የእቴጌ ጣይቱን ውድቀት ጭምር አፋጥነው፤ ልጅ ኢያሱን ሽረው፤የዓፄ ምኒልክን ልጅ ወይዘሮ ዘውዲቱን አንግሠውና ራስ ተፈሪን አልጋ ወራሽና የመንግሥቱ እንደራሴ አድርገው ሾመው በየቦታው ሹም ሽር አደረጉ፡፡
ሹም ሽሩን ምክንያት አድርጎ መስከረም 17 እና 18 ቀን 1909 ዓ ም የተሰናዳውና አቤቶ ኢያሱ የተሻሩ መሆናቸውን የሚገልጸው ደብዳቤም ከአዋጅ ቃል ጋር እየተባዛ የጳጳሱ የአቡነ ማቴዎስና የእጨጌ ወልደ ጊዮርጊስ፤ የየሚኒስትሮች ማኅተም ጭምር እየታተመበት ለያገሩ መኳንንት ተላለፈ፡፡ የጽሑፍ መልእክት በቀላሉ ለማይደርሳቸውና በየዳር አገሩ ላሉት መኳንንት ደግሞ የስልክ መልእክት ሄደላቸው፡፡ ለንጉሥ ሚካኤልም የልጃቸውን የአቤቶ ኢያሱን መሻር ከደብዳቤ ይልቅ በስልክ ይነገራቸው ተብሎ መልእክቱ እንደደረሳቸው ለሰገሌ ጦርነት ተዘጋጁ፡፡ አዋጅም እንዲህ በማለት አሳወጁ፡፡
«ያገሬ ሕዝብ የወሎ ሰው ልጄን ኢያሱን ለማንገሥ ወደ ሸዋ ለመሄድ ተነሥቻለሁና ምልምል ወታደርህን አስከትለህ በቶሎ ተከተለኝ፡፡ ስንቅ ልሰንቅ አትበል፡፡ ስንቅህ እኔ ነኝ፡፡» የሚል መልእክት ለየመኳ ንንቶቻቸው አስተላለፉ፡፡
ራስ ተፈሪም በበኩላቸው ለዘመቻ ሲነሡ የሚከተለውን አዋጅ አስነገሩ፡፡
“ያገሬ የኢትዮጵያ ሰው ስማ፤ ልጅ ኢያሱ ከዓፄ ምኒልክ ፈቃድ ወጥተው ክፉ ሥራ እንዳይሠሩ የረገሟቸውን ርግማን ጥሰው እስላም ትውልዳቸውን እየቆጠሩ ከእስላሞች ጋር በመስጊድ እየሰገዱ ወደ እስላም ሃይማኖት መግባታቸውን በግልጽ ስለአሳዩ ማስተዳደርም ስላልቻሉ እርሳቸውን ሽረን፡ንግሥት ዘውዲቱን በአባታቸው አልጋ አስቀምጠን አነገሥን፡፡ ንጉሥ ሚካኤልም የልጃቸውን መስለም ያውቃሉና ከእኛ ጋራ ሆነው ለክርስቲያን ሃይማኖት ደማቸውን ያፈስሳሉ እያልን ስናስብ እንዲያውም ለእስላም ንጉሥ ካልተገዛችሁ ብለው ሊወጉን ከወሎ በግስጋሴ መጥተዋልና ወንድ ልጅ የሆንህ ተከተለኝ ” (ባሕሩ 2008፡ 80 እና 97) ፡፡
ንጉሥ ሚካኤል ሠራዊታቸው ከየቦታው ተጠራርቶ ደሴ ላይ እንደከተተ በፊታውራሪ ሥራህ ብዙ ገብሬ አዝማችነት አሰልፈው በመስከረም 20 ቀን ከደሴ ተነሥተው ሸዋ ቶራ መስክ ላይ እንደደረሱ በሸዋ በኩል የልጅ ልጃቸው የወይዘሮ መነን አስፋው ባለቤት የነበሩት ራስ ሉልሰገድ ግንባር ቀደም ሆነው ያሰለፉትን 11 ሺህ ሠራዊት፤አምስት ወይም ስድስት መድፎችን፤አሥር መትረየሶችን ፤ልዩ ልዩ ጠመንጃዎችን ንጉሥ ሚካኤል ማረኩ፡፡ የጦር ሚኒስትሩ ፊታውራሪ ሀብተ ጊዮርጊስ የራስ ሉልሰገድን መሸነፍ በሰሙ ጊዜ ደንግጠው ሃምሳ ሺህ ያህል ሠራዊት በመምራት ደብረ ብርሃን ከተማ ላይ ሰፈሩ፡፡ ሌላ ተጨማሪ ጦር እንዲመጣላቸውም ለልዑል ራስ ተፈሪ አመለከቱ፡፡
ከሁለት ሳምንታት በኋላ ሃምሳ ሺህ የሚሆን ተጨማሪ ሠራዊት በአዲሱ ከራስ ተፈሪ መንግሥት ጎን ተሰለፈ፡፡ ከፈረንሳይ የተገዛውና ብዛት ያለው የጦር መሣሪያ ጅቡቲ ወደብ እንደደረሰና በቅርቡ አዲስ አበባ እንደሚገባ ስለተገመተ ንጉሥ ሚካኤል ባሉበት ብዙ ዘመናዊ የጦር መሣሪያ እንደገጸ በረከት ሆኖ ተላከላቸው፡፡ ፊታውራሪ ሀብቴም ወታደሮቻቸውን በሰገሌ ሜዳ አካባቢ በተጠንቅ አሰልፈው ለንጉሥ ሚካኤል ለልጃቸው ለአቤቶ ኢያሱ ታማኝ መሆናቸውን የሚገልጽ የማታለያና የማዘናጊያ ደብዳቤ ጻፉላቸው፡፡ በዚህ የጊዜ ሒደት ከጂቡቲ የሚጠበቀው ዘመናዊ መሣሪያ አዲስ አበባ ደርሶ ለሸዋ ሠራዊት ታደለ፡፡ በደቡብና በምዕራብ የነበረው ሠራዊትም በግስጋሴ ደርሶ ሰገሌ ሜዳ ላይ ከተተ፡፡ ፊታውራሪም እንደገና የልጅ ኢያሱን ጥፋት የሚገልጽ ሌላ ሁለተኛ ደብዳቤ ለንጉሥ ሚካኤል ጻፉ፤ የወሎው ንጉሥ ለተፈሪም ታማኝ ሆነው እንዲቀርቡ አሳሰቧቸው ( ጎበዜ 2008 ፡ 116–18)፡፡
ፊታውራሪ የመንግሥት ሠራዊት በብዛትና በጦር መሣሪያ ጥራት እስገሚገኝ ድረስ ሲሠሩና ዝግጅት ሲያደርጉ ስንቁና ትጥቁ የላላበት የንጉሥ ሚካኤል ሠራዊት የገጠሩን ሕዝብ በመዝረፍ ላይ ነበር፡፡ በመጨረሻ ጥቅምት 17 ቀን 1909 ዓ ም አስፈሪው የሰገሌ ጦርነት ተጀምሮ ከየተራራው ላይ የመድፍና የመትረየስ ድምጽ ያስተጋባ ጀመር፡፡ ምድር ቁና ሆነች፡፡ ብዙ ታላላቅ የጦር ሰዎች በጦርነቱ ካለቁና በስትራቴጂ አያያዝ፤ በሥነ ልቡናና በጦር መሣሪያ ብልጫ የበላይነት በነበረው የሸዋ ጦር አሸናፊነትና ድል አድራጊነት ጦርነቱ ሲደመደም የጥይት እጥረት፤ የሠራዊት እልቂትና የመክዳትና የመበታተን ፈተና የገጠማቸው ንጉሥ ሚካኤል እጅ ሰጥተው ተማርከዋል፡፡
ወደ ሐረርጌ እንደወጡ የቀሩት አቤቶ ኢያሱም ዐርፈው መቀመጥ አልሆነላቸውምና በመኢሶ ከባድ ውጊያ አድርገው ወደአዳል በረሃ ወረዱ፡፡ ቆይተው አባታቸውን ለመርዳት ሲሉ 6 ሺህ ወታደሮችን እየመሩ ጥቅምት 17 ቀን በአንኮበር አልፈው ወደ ሰገሌ ሊያመሩ ሲሉ ልዑል ራስ ተፈሪ ድል አድርገውና ንጉሥ ሚካኤልንም ማርከው ወደ አዲስ አበባ መመለሳቸውን ሰሙ፡፡
፶ አለቃ አሰፋ ስለ ሰገሌ ጦርነትም የራሳቸው ግንዛቤ አላቸው፡፡ እርሳቸው እንዳወሱኝ በሰገሌ ጦርነት ወሎ የታጠቀው ጎራዴ ሲሆን ሸዋ የታጠቀው ደግሞ ለበን ነበር፡፡ በዚህ ምክንያት ንጉሥ ሚካኤል ለምን ልጄ ታሰረ? ለምንስ ከሥልጣን ወረደ? የምኒልክ ኑዛዜስ አለ አይደለም ወይ? ብለው ከሸዋ ጋር ለመዋጋት ወደ ሰገሌ መጡ፡፡ የሸዋ ጦር ለበን መሣሪያ ታጥቆ የነበረው በዓፄ ምኒልክ ውል መሠረት መሣሪያው ከፈረንሳይ ስለመጣ ነው፡፡ በንጉሥ ሚካኤል በኩል የወሎ ጦር በፊታውራሪ ሥራው ብዙ ገብሬ፤ የአድዋ ዐርበኛ የነበሩ የተመራ ሲሆን በንጉሥ ተፈሪ
ረገድ ጦሩ በፊታውራሪ ሀብተ ጊዮርጊስ እዝ ሥር ነበር፡፡ ጦርነቱ ሊጀመር ሲል በወሎ በኩል
«እኔስ ፈራ ሆዴ እኔስ ፈራ ሆዴ፤
የተፈሪን ሽጉጥ የኢያሱን ጎራዴ» የሚል ግጥም ተሰማ፡፡ ጦርነቱ ቀጠለ፡፡ አሰላለፉ የጎራዴና የዘመናዊ መሣሪያ ሆነና ንጉሥ ሚካኤል ድል ሊሆኑ ሲል የገጠሙት ግጥም የሚከተለው ነው፡፡ በወቅቱም ጎጃምና ጎንደር ይረዱኛል የሚል ሐሳብ ነበራቸውና ሳይመጡ ስለቀሩ
በጎጃም በጎንደር ደመናው ዘለቀ፤
ዘር ያላችሁ ዝሩ የእኔስ ዘር አለቀ፡፡
ብለው አዋጅ አስነገሩ፡፡ ቃላቸው ከጊዜ በኋላ ጎጃምና ጎንደር በደረሰ ጊዜ ሕዝቡ «ምነው ምነው የሚያዘምተን ሰው የለምወይ » ብሎ ተናደደ፡፡ ተቆጣ፤ ወዲያው ተማረኩ መባልን ሰምቶ ነው እንጂ የጎንደርና የጎጃም ሕዝብ ከጎናቸው ተሰልፎ ተፈሪን ለመውጋት ሐሳብ ነበረው፡፡ የወሎ ጦር አዝማችና በሰገሌ ጦርነት ቆስለው የነበሩት ፊታውራሪ ሥራህ ብዙ በጀግንነት ሲዋጉ ድል ስላልቀናቸው በዘዴ የሸዋን ጦር ሰብረው ለማምለጥ ችለዋል፡፡ የሸዋም ጦር በስለላ ተከታትሎ ደሴ ከተማ በአገኛቸው ጊዜ ተኩስ ከፍተው ብዙ ሰው ገደሉ፡፡ በመጨረሻ ራሳቸውም በእሩምታ ጥይት ሞተዋል፡፡ አስከሬናቸው ከንጉሥ ሚካኤል ጋር ሆነው በአሠሩት ደሴ መድኃኔ ዓለም ቤተ ክርስቲያን ተቀብሯል፡፡ በወቅቱም
«ሥራህ ብዙ ገብሬ ሥራው መሠከረ፤
በሠራው ቤተስኪያን ደሴ ተቀበረ፡፡»
ተብሎ ተገጠመ፡፡ ፊታውራሪ ሥራህ ብዙ ገብሬ ሰገሌ ላይ ተዋግተው ድል እንደሆኑ ሲያውቁና ሲያመልጡ የወሎ አዝማሪ ስለጀግንነታቸው እንዲህ ብሎም ነበር፡፡
የመሣሪያ እጦት ነው ሰው የሚያስደነግጥ፤
ጀግናስ ተቀምጦዋል ተመዝኖ እንደጥጥ፡፡
ወደ ወሎ ተግተልትሎ የገባው የፊታውራሪ ሀብተ ጊዮርጊስ ጦርም እኛ የምንፈልገው ልጅ ኢያሱን እንጂ ንጉሥ ተፈሪን አይደለም ብሎ ያመፀውን የወሎ ሕዝብ አይቀጡ ቅጣት እየቀጣ አሠቃየው፡፡ አዋረደው፡፡ በግድ እንዲገብርም አደረገው፡፡ የወሎ ሕዝብ በሬውና ላሙ እየታረደበት የጎተራ እኽሉ ለበቅሎ ቀለብ እየተሰጠበት፤አብያተ ክርስቲያናት እየተቃጠሉ፤ ቤቱ እየተቃጠለበት በሥቃይ ላይ እንዳለ ሕዝቡ አማርሮ ያዝንና ያለቅስ ጀመር፡፡ በወቅቱ የወሎ ገዥ የነበሩት ራስ ደምስም “ወሎ ተበደልኩ ብሎ ያስወራል፤ እስቲ በደሉ የት አለ? እስኪ ስለሕዝቡ በደል ልጃገረዶች በዘፈናቸው ምን እንደሚሉ ይናገሩ—” ምን ይላሉ”? አሉ፡፡ ከ13 ዓመት በታች የሆኑ ልጃገረዶች ሲዘፍኑ ቄስ መነኩሴው ሳይቀር ተሰባሰበ፡፡ በተለይ ተዋበች የተባለችው የዘፈኑ አቀንቃኝ ስትዘፍን
«ላሚቷ ታረደች ወተቷ ሲፈስ፤
በሬውም ታረደ ትልሙን ሳይጨርስ፤
ምን ትጠቀማለህ ሀብተ ጊዮርጊስ፤
ምን ትጠቀማለህ አንተ ራስ ደምስ፡፡
እንጀራ ጠፋ እንጂ ሥጋማ ምን ገድዶ፤
ድፍን የወሎ ሕዝብ እንደበጉ ታርዶ፡፡» ትላለች፡፡
ንጉሥ ሚካኤል ሰገሌ ላይ ተማርከው ሲያዙ አዝማሪያቸውም አብሮ ተማርኮ ታሥሮ ነበር፡፡ ተመኻል ፊታውራሪ ሀብተ ጊዮርጊስ “እስቲ ዝፈን ” አሉት፡፡ አዝማሪውም “ እኔ አልዘፍንም፤ ምርኮኛኮ መዝፈን አይገባውም ጌታየ! ተማርኳላ !****” ይላል፡፡ ነገር ግን በግድ ዝፈን ተባለ፡፡ አዝማሪውም ማሲንቆውን አንሥቶ እየተከዘ እንዲህ አለ፡፡
“እንዲሁ በከንቱ ደም ተፋሰስን እንጅ
አልጋው መች ይወጣል ተሚካኤል እጅ ”
ይኽንን የሰሙት አንድ ነገር አዋቂ ሽማግሌ “ ፊታውራሪ! ይኸ አዝማሪ ሰደበህኮ ” ይላሉ፡፡ ፊታውራሪም “ምን ብሎ “ በማለት ይጠይቃሉ፡፡ ”አንተ አነፍናፊ ነህ ከዳር ትቀራለህ፡፡ በመኻል የንጉሥ ሚካኤል ልጅ ወይዘሮ መነን ስለ አለች የእርስዋ ልጆች ይነግሣሉ፡፡ አንተ ግን ዳር ቀሪነህ፤ ዞሮ ዞሮ አልጋው የእኛ ነው ያለህ “ ብለው ያብራሩላቸዋል፡፡ ፊታውራሪም ”እከና“ ብለው ሊገርፉት ይነሣሉ፡፡ በዚህ ጊዜ አጠገባቸው ወይዘሮ መነን ነበሩና ” አትንካው፤ አይሆንም፤ ዝፈን አልከው ዘፈነ፡፡ እንደገና እንዴት ልግረፍ ትላለህ?” ብለው አዝማሪውን ከግርፋት አዳኑት፡፡
ንጉሥ ሚካኤል በመማረካቸው ምክንያት እየተብሰለሰሉ አዲስ አበባ ውስጥ በመኖር ላይ ሳሉ በፅኑ ይታመማሉ፡፡ በዚያ ወቅት ጳጳሳትና ትላልቅ ሰዎች እንዲሰበሰቡ አድርገው “ ወደ ሀገሬ ወሎ እንድሄድ ይፈቀድልኝ ብለው ራስ ተፈሪን ሲጠይቁ ራስ ተፈሪ ”እኔ ምንድን ነኝ ያሰረዎት ሸዋ ነውና እርሱን ይጠይቁ ” ብለው ከንጉሡ ፊት ገለል ይላሉ፡፡ ንጉሥ ሚካኤል ወደ ሸዋ ከመዝመት ይልቅ ወሎ ላይ የተፈሪን ጦር እንጠብቅና እንውጋው ብለው አማካሪዎቻቸው የመከሩዋቸውን ትተው አንድ የሸዋ ሰው በጥድፊያ ሸዋ ለጦርነት ገና ሳይዘጋጅና የዳር አገር ጦርም አክቶ ሳይመጣ ወደ ሸዋ እንዲዘምቱና የቸኮለ እርምጃ እንዲወስዱ ስለመከራቸው ወደ ሰገሌ ቸኩለው አምርተዋል፡፡ ከተሸነፉ በኋላ ችግሩን ለመጠቆም ፈልገው እንዲህ ሲሉ አንጎራጎሩ ይባላል፡፡
ደግ ነገር እያለ ክፉ ተናግሬ፤
ያገር ልጅ እያለ ከባሪያ መክሬ፤
አቃጠሉት መሰል ሸተተኝ አገሬ፡፡
(ባሕሩ 2008፤75 )፡፡
ንጉሥ ሚካኤል ጥቅምት 17 ቀን 1909 ዓ ም ሰገሌ ላይ በተደረገው ጦርነት ድል ሆነው ከተማረኩ በኋላ በጦር ሚኒስትሩ በፊታውራሪ ሀብተ ጊዮርጊስ አስጠባቂነት በዝዋይ ሐይቅ ደሴትና በደንዲ ተግዘው ኖረዋል፡፡ ንጉሥ ሚካኤል ዝዋይ ውስጥ ተግዘው ሲኖሩ በእድሜ ገፍተው ነበርና ሕመም ስለፀናባቸው ጳጉሜን 3 ቀን 1911 ዓ ም ዐርፈው በሆለታ መድኃኔ ዓለም ቤተ ክርስቲያን ሥርዓተ ቀብራቸው ተፈጽሟል፡፡ ከጊዜ በኋላም ዐፅማቸው ፈልሶና በሕይወት እያሉ ወደ አሠሩት ተንታ ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን ተወስዶ እንዲያርፍ ተደርጓል፡፡ ንጉሡ በሞቱበት ሰዓት አንድ የወሎ አዝማሪ
ራሴን ወገቤን ብሎ ሳይናገር፤
መድኃኒትም ሳይቀምስ ሐኪም ሳይመረምር፤
ሞቶ ተቀበረ ወሎን ያህል አገር፡፡ ብሎ አንጎራጎረ፡፡
የንጉሥ ሚካኤል ዐፅም ተንታ ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን በዐረፈበት ቀን ሕዝቡ በዕንባ እየተራጨ ሲያለቅስ በተለይ ጣይቱ አብርሃ የተባለች አስለቃሽ
«ምን ንጉሥ አለና አቤት ትላላችሁ፤
ምን ጳጳስ አለና ትባረካላችሁ፤
ምን ታቦት አለና ትሳለማላችሁ፤
ሰይጣን በቅሎ ጭኖ ሲከንፍ እያያችሁ፡፡
ወሎን ያህል አገር ጤናን ያህል ጌታ፤
ከብበው ደበደቡት እንደ ጋለሞታ፡፡ “ አለች ይባላል፡፡
በመጨረሻም አቤቶ ኢያሱ ከአዳል በረሀ ወደ ራስ ጉግሳ አርአያ ዮሐንስ ግዛት ሄደው ትግሬ ውስጥ ቢደበቁም ጥር 20 ቀን፤ በአንዳንዶቹ በሚያዚያ ውር 1913 ዓ ም በአንድ ሰው ጠቋሚነትና በአልጠረ ጠሩበት ሰዓት ደጃዝማች አርአያ እጃቸውን ይዘው ለመንግሥት ሰጥተዋቸዋል፡፡ ሰውን አሳልፎ መስጠት ከአንድ የክርስትና እምነት አለኝ ከሚል ሰው የማይጠበቅና ድርጊቱም እንደ አረመኔነት የሚቆጠር እንደሆነ በማሰብ ልጅ ኢያሱን ለመያዝ ያልተባበሩት ራስ ሥዩም መንገሻ ብቻ ሲሆኑ ለዚሁ እምቢተ ኛነታቸው ዋጋ ከፍለውበታል፡፡
አቶ አሰፋ ተክሌ እንደሚሉት በርካታ ሚስቶች የነበሯቸው ልጅ ኢያሱ ፍቼ በራስ ካሳ ግዛት በደጃዝማች አበራ ካሳ ጠባቂነት ታስረው ከቆዩ በኋላ ከእስር አምልጠው ወጡ፡፡ በጊዜው በጎጃሙ ገዥ በራስ ኃይሉ ተክለ ሃይማኖት ድጋፍና ምክር ደጃዝማች አበራ አቤቶ ኢያሱን ስለለቀቃቸው በጊዜውም
“አበራ ምን አለ አበራ ምን አለ፤
ፈትቶ ለቀቀና አላየሁም አለ ፡፡»
ተብሎ ተዘፈነ፡፡
ከሰላሌ ፍቼ እሥር ቤት ያመለጡት አቤቶ ኢያሱ በግንደበረት በኩል ጎጃም ቢገቡም ልጅ ኢያሱን ሸሽጎ የተገኘ ብርቱ መከራ እንደሚደርስበት ራስ ተፈሪ መኮንን በአዋጅ ጭምር የጎጃምን ሕዝብ ስለአስጠነቀቁ በዚህ ጉዳይም የራስ ኃይሉ ተክለ ሃይማኖት እጅ አለበት በሚል ስለተሠጋ ልጅ ኢያሱ ፊታውራሪ ገሠሠ በለው በተባለ የንጉሥ ተክለ ሃይማኖት የልጅ ልጅ ለሁለተኛ ጊዜ ግንቦት 22 ቀን 1924 ዓ ም ጎጃም ላይ ተያዙ፡፡ ከዚያም ወደ ጋራ ሙለታ ግራዋ ወደ ተባለች መንደር ሲጋዙ ራስ ኃይሉም የረጋውን መንግሥት ለማፍረስ ተነሣሥተዋል በሚል እንደ ኢያሱ ሚካኤል በሰንሰለት ታስረውና ሰኔ 24 ቀን 1924 ዓ ም በንጉሠ ነገሥቱ ችሎት ለፍርድ ቀርበው በሰይፍ ይቆረጡ፤ በስቅላት ይቀጡ ተብሎ ሞት ከተፈረደባቸው በኋላ ከግዛትም ከንብረትም ተነቅለውና የእድሜ ልክ እስራት ተፈርዶባቸው፤ በመጀመሪያ ወደ ወለጋ ደንዲ ፤ ቆይቶ ወደ ጋራሙለታ ተጋዙ፡፡
ልጅ ኢያሱም ከተያዙበት ቀን ጀምሮ እጅና እግራቸው በሰንሰለት ታስሮ ሰውነታቸውም ሰልስሎ በጋራ ሙለታ ወኅኒ ቤት ከኖሩና በማይጨው ጦርነት ዋዜማ ወደ አዲስ አበባ እንዲመጡ ከተደረገ በኋላ ኅዳር 13 ቀን 1928 ዓ ም በ37 ዓመታቸው ዐርፈዋል፡፡ ፖለቲካዊ ግድያ የተፈጸመባቸው የአቤቶ ኢያሱ መቃብርም የት እንደሆነ እስከ ዛሬ ድረስ ሳይታወቅ ቀርቷል ፡፡
ማጣቀሻዎች
– መሪ ራስ አማን በላይ (2009) የጥንቷ ኢትጵያ ትንሣኤ ታሪክ በኒባዳን ማተሚያ ቤት አዲስ አበባ፤
መርስኤ ኀዘን ወልደ ቂርቆስ (1999) የሃኛው ክፍለዘመን ኢትዮጵያ የዘመን ታሪክ ትዝታየ ካየሁትና ከሰማሁት 1896—1922 አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አዲስ አበባ፤
– መርስኤ ኀዘን ወልደ ቂርቆስ (2009) የሃኛው ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ 1922—1927 አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬስ አዲስ አበባ፤
– ባሕሩ ዘውዴ ( 2008) ሀብቴ አባ መላ ከጦር ምርኮኛነት እስከ አገር መሪነት ኢክሊፕስ ማተሚያ ቤት፤ አዲስ አበባ፤
– ተክለ ሐዋርያት ( ፊታውራረ) 1999ዓ ም ) አውቶባዮግራፊ ( ሕይወት ታሪክ) አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲፕሬስ አዲስ አበባ፤
– ተክለኢየሱስ ዋቅጅራ (አለቃ) ( 2002) የኢትዮጵያ ታሪክ ብርሃንና ሰላም ማተሚያ ድርጅት አዲስ አበባ፤
– አሰፋ ተክሌ (፶አለቃ) ቃለ ምልልስ ሐምሌ 7 ቀን 2010 ዓ ም በኮልፌ ቀራንዮ ክፍለ ከተማ ወረዳ 05 መሐንዲስ ሰፈር አዲስ አበባ ከጧቱ 4.00 ሰዓት በመኖሪያ ቤታቸው ውስጥ
– አጥናፍሰገድ ይልማ (2006) የአቤቶ ኢያሱ አነሣሥና አወዳደቅኤ ኤመቲ ማተሚያ ቤት አዲስ፤
– ዓለማየሁ አበበ ትርጉም ( 2009) የኢትዮጵያ ታሪክ ከመጀመሪያው እስከአሁኑ ዘመን ዜድ ኤ ማተሚያ ቤት ፤አዲስ አበባ፤
– ዘውዴ ረታ (—)ተፈሪ መኮንን ረጅሙ የሥልጣን ጉዞ በምኒልክ፤ በኢያሱ እና በዘውዲቱ ዘመን 1884-1922
– ዘውዴ ረታ (2005) የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ መንግሥት ርኆቦት ማተሚያ ቤት አዲስ አበባ፤
ጎበዜ ጣፈጠ (2008) አባ ጤና ኢያሱ ኢምፕሬስ ማተሚያ ቤት አዲስ አበባ፤
ጳውሎስ ኞኞ (1984) አጤ ምኒልክ ቦሌ ማተሚያ ቤት አዲስ አበባ፤
ዘመን መፅሄት ጥቅምት 2011
በታደለ ገድሌ ጸጋየ (ዶ/ር)