ጽንፈኝነት በተለያዩ አውዶች የራሱ ትርጓሜ ያለው ቢሆንም፤ በሃይማኖት፣ በብሄርተኝነት እሳቤና አተያይ ወይም የፖለቲካ ርዕየተ ዓለም ውስጥ የመጨረሻው የጥላቻ ጥግ ላይ መሰለፍ መሆኑን ምሁራን ይናገራሉ:: የፅንፈኝነት እሳቤው ከፍ ያለ ደረጃ ሲደርስ ደግሞ ተመሳሳይ ፖለቲካዊ ርዕዮተ ዓለም ኖሯቸው እንኳን አንዱ ሌላውን የሚያጠፋ ስለመሆኑም ይነገራል::
በኢትዮጵያም የፅንፈኝነት ምልክቶች እና ድርጊቶች መስተዋል ከጀመሩ የሰነባበቱ ሲሆን፤ መልካቸውን በመቀያየር አገርን ቅርቃር ውስጥ እያስገቡ ነው:: በቅርቡ በዚሁ ሳቢያ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎችን ጨምሮ የፖለቲካ ሹመኞች የጥፋት ቃታ የተሳበባቸው መሆኑ ይታወቃል:: ከዚህ አለፍ ሲልም መንገዶችን በመዝጋት እና ኢ-መደበኛ አደረጃጀት በመፍጠር አገሪቱን ፈተና እንዲበዛባት ማድረጋቸው ይታወሳል:: ለመሆኑ ጽንፈኝነት እንደአገረ መንግስት የሚፈጥረው ቀውስ እስከምን ድረስ ነው? መፍትሄውስ? በሚል የሕግ ባለሙያዎችን አነጋግረናል::
በሰመራ ዩኒቨርሲቲ የፌደራሊዝምና ህግ መምህር አቶ ኑሩ መኩሪያ፤ ፅንፈኝነት እየተባባሰ ሲሄድ የአገራትን ህልውና የሚፈታተን እና አገረ መንግስትን ለከፋ አደጋ የሚያጋልጥ ነው:: ከዚህም በዘለለ አገርን ለውስጣዊ እና ውጫዊ ችግሮች የሚያጋልጥ እንደሆነም ምሁሩ ያብራራሉ::
ጽንፈኝነት በመሰረታዊነት የሌሎችን ፍላጎት እና እይታ ካለማክበር፣ ካለመስማት በብዛት እኔነት በተሞላው እሳቤ ብቻ የተቃኘ በመሆኑ፤ አብሮነትን የሚጋፋ ስንኩል ሐሳብ እንደሆነ ያብራራሉ:: ይህ ደግሞ የሚመነጨው አንዳንዶች ከሚከተሉት ፖለቲካ እሳቤ ነው:: የዚህ አገር ዋነኛ የፖለቲካ መሰባሰቢያ መድረክ ዘውግ ወይም ብሔርተኝነት ላይ ብቻ ያነጣጠረ መሆኑ ደግሞ ጽንፈኞችን ለማፍራትም ዕድል ስለመፍጠሩ ይጠቁማሉ::
ቀደም ሲል በዓለም አቀፍ ደረጃ ፅንፈኝነት ሃይማኖትን መሰረት አድርጎ ብቻ ይታይ የነበረ ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅት መልኩን እየቀየረ ስለመምጣቱም ይናገራሉ:: እንደ አገራት ነባራዊ ሁኔታም ኢትዮጵያ ውስጥ ብሔርን ማዕከል በማድረግ የሚታይ ጽንፈኝነት ስለመኖሩም ይጠቁማሉ:: እነዚህ የዘውጌ አስተሳሰቦችም በየጊዜ እያደጉና ገጽታቸውን እየቀያየሩ ስለመሆኑም ያስረዳሉ::
እርሳቸው እንደሚሉት ከሆነ፤ በኢትዮጵያ ህዝብ አብሮነት ላይ የተጋረጠ፣ በግልፅ የሚታይ ፈታኝ ፅንፈኝነት አለ:: ስለዚህም ለዚህ ስጋት መፍትሄ ለማግኘት መትጋት ያስፈልጋል። አሰባሳቢ ማንነትን እንዴት ወደ መድረኩ እናምጣው? በሚለው ላይ ውይይትም ያስፈልጋል::
እንደ አቶ ኑሩ ገለፃ፤ የፅንፈኝነት አስተሳሰቦች የህዝብ አጀንዳ እንዳይሆኑ መንግስት በእጅጉ ሊጠነቀቅ ይገባል:: በተለይም እነዚህ አካላት ማህበረሱን ሸብበው ከያዙና እሳቤያቸውን የማስረጽ ዕድሉን ካገኙ እጅጉን አሳሳቢ ይሆናል:: ለተወሰነ ቡድን ወይም ብሔር ብቻ ሳይሆን እንደ አገረ መንግስትም ህልውናን ውስብስብ የማድረግ አቅም አለው::
ፅንፈኝነትን መኮነንና መታገል ለመክሰሙ ሁነኛ መፍትሄ መሆኑን የሚናገሩት አቶ ኑሩ፤ ምናልባትም መንግስትም ከህዝቡ እና መሰል ቡድኖች ጥያቄዎች ሊኖሩ ስለሚችሉ መፍትሄ ምንድን ነው ብሎ ማሰብም ይጠበቃል ይላሉ:: የህዝብ ጥያቄ መመለስ እና ፅንፍኞችን ከህዝብ መነጠል ዋናው ጉዳይ ሊሆን ይገባል:: የህዝብ ጥያቄ እየተመለሰ ከመጣ ጽፈኞችን ነጥሎ ለመምታትም ዕድሉን ይሰጣል:: ይሁንና ግን እነዚህ የቤት ሥራዎች ሳይሰሩ ጽንፍ ረገጥ አስተሳሰቦችን መስበር አይቻልም የሚል እምነት አላቸው::
በኢትዮጵያ ውስጥ የፅንፈኝነት መንሰዔዎች መካከል አንዱ በሕገ መንግስቱ ውስጥ የተሰነቀሩ አንቀፆች መኖራቸው አንዱ መሆኑን አቶ ኑሩ በመጠቆም፤ ይህን ሊያርም የሚችል አሰራር እየተዘረጋ መሆኑ አንዱ እፎይታ የሚሰጥ ጉዳይ እንደሆነም ያብራራሉ:: በተለይም ህግ እና ህገ ወጥነትን እያጣቀሱ ለሚንቀሳቀሱ አካላት ህገ መንግስቱ ሁሉን ማዕከል ባደረገ እና የአገር ህልውናን ለአደጋ በማያጋልጥ መልኩ መቃኘት አለበት የሚል እሳቤ አላቸው::
የሕግ ባለሙያው አቶ በፍርዴ ጥላሁን በበኩላቸው፤ ፅንፈኝነት አደገኛ እና መስመር የሌለው ትግል ነው ይሉታል:: ፅንፈኝነት ሌሎችን አለመስማት፣ የሌሎችን ሃሳብም ለመስማት ዝግጁ አለመሆን፤ የእኔ ብቻ ይሁን፣ በሁሉም ነገሮች የእኔ ብቻ እና የእኔ ብቻ የሚል አባዜ የተጠናወተው አስተሳሰብ መሆኑን ይጠቁማሉ:: በዙሪያው ያሉትን አለመቀበልም ሌላኛው መገለጫው ነው:: እንደ ቡድን ሲወራ የእኛ ብቻ መሰማት አለበት የሚል ብሂልም የተላበሰ ነው::
የራስን ሐሳብ ብቻ ገዥ አድርጎ ማሰብና በጭፍን መሟገት ብሎም የሃሳብ የበላይነትን ያለመቀበል መገለጫዎቹ ናቸው:: ታዲያ ወደዚህ አስተሳሰብ የሚወሰድው ደግሞ አሁናዊ የዓለምን ነባራዊ ሁኔታ አለማገናዘብ እና በሰፈርና ቀበሌ መታጠር ነው:: ከዚህም አለፍ ሲልም በሰፈሬ ካሉት ሁሉ የተሻልኩ ነኝ ከሚል ከጥበትም የጠበበ እይታ ውስጥ የተዘፈቀ ስለመሆኑም ይጠቁማሉ:: ይህ አስተሳሰብ ወደ ቡድን ሲያድግ ደግሞ የእኔ ብሔር፣ ሃይማኖት እና ቋንቋ የበለጠ ዋጋ አለው ብሎም ሌሎችን ማራከስ ነው:: በታሪክ ደረጃም የእኔ ታሪክ ብቻ ከከፍታው ማማ ላይ ነው በሚል የሌሎች ዋጋ እንደሌለው አድርጎ ማሰብ ነው::
ፅንፈኞች ይህን ዓላማቸውን ለማሳካት የእነርሱን ሃሳብ የሚያራምዱትን የራሳቸው አካል ያደርጋሉ:: ውድድር ውስጥ በመግባትም የሌላው ጉዞ እና ሃሳብ ማደናቀፍ ይፈልጋሉ:: ይህን ለማሳካት ደግሞ ብሔር፣ ሃይማኖት፣ ቋንቋ፣ ተመሳሳይ የፖለቲካ እሳቤ ያላቸውን የመጠርነፍ እና አንድ ላይ የመሆን ፍላጎት አለ:: ዋናው ነገር ዓላማቸውን ያሳኩ እንጂ ከማን ጋር ማበር አለብን የሚለው ለፅንፍኞች ደንታ አይሰጥም:: ይህም ዋነኛ ዓላማቸውን ለማሳካት ማንኛውም አጋጣሚ እና ሁኔታ የሚጠቀሙ ናቸው:: በአሁኑ ወቅትም በአገሪቱ የሚስተዋለው ከዚህ ያልተለየ መሆኑን ያስገነዝባሉ::
ታዲያ ይህን ሥርዓት ለማስያዝ መንግስት የመንግስትነት ሚናውን መወጣት አለበት:: እንደ አስፈላጊነቱ እርምጃ መውሰድና ብዙሃኑን መታደግ ግድ ይለዋል:: ጽንፈኞች ባሉበትና በፈሩበት አገር ወይም ቦታ የዴሞክራሲ ሥርዓት ያብባል ወይም ያድጋል ብሎ ማሰብ የህልም እንጀራ ነው የሚሉት አቶ በፍርዴ፤ መንግስት ጡንቻውን ፈርጠም አድርጎ ተገቢውን እርምጃ መወሰድ አለበት ባይ ናቸው:: አገር ከባድ ችግር ውስጥ በምትገባበት ወቅት ህግና ሥርዓት ማስከበር ግድ ይላል::
ፅንፈኝነት ለመዳኘት በህግ ማዕቀፍም የራሱ እይታ አለው የሚሉት የህግ ባለሙያው፤ የኢትዮጵያ መደበኛው ህግ ይህን ስለማይዳኘው የጥላቻ ንግግርን በተመለከተ አዋጅ መውጣቱን ይናገራሉ:: በህዝብና ህዝብ መካከል ጥርጣሬ መንዛት፣ ማሸበር፣ ሠላም መንሳት እና ኢ-ሰብዓዊ የሆኑ እርምጃ መውሰድ መገለጫው ሲሆን፣ ይህም በህግ ዓይን ሲታይ ደግሞ በከባድ ወንጀል ድርጊት ውስጥ የሚያርፍ ነው:: ይህ ደግሞ በሂደት አገረ መንግስት አደጋ ላይ የሚጥል እና ህዝብን ለከፋ እንግልትና ችግር የሚዳርግ ነው::
ጽንፈኝነት አካሄዱ አደገኛ እና የትግል ስልቱም ውል የሌለው በመሆኑ ሄዶ ሄዶ ማረፊያው ሽብርተኝነት መሆኑን በመጠቆም፤ ሊዳኙ የሚችሉት በጸረ ሽብር ማዕቀፍ ውስጥ የሚሆን ነው:: በዓለም ላይ በጽንፈኝነት እሳቤ እና ድርጊት ተነስቶ እስከመጨረሻ ዓላማውን ያሳካ ቡድን የለም:: መጨረሻውም እርስ በእርስ መጠፋፋት ስለሚሆን ግብ የሚመታ ሀቀኛ የትግል ስልት የለውም:: በመሆኑም የጽንፈኝነት መጨረሻው ራስን በራስ ማጥፋት ነው:: ይህ የሚሆነውም ሃሳቡ ገዥ ስለማይሆንና ህጋዊ ቅቡልነት የማይኖረው በመሆኑ ነው::
የአገሪቱ ፖለቲካ ከሴራ ያልተላቀቀው በምንም ሳይሆን በአንዳንድ ልሂቃኖቻችን ጽንፈኝነት ባህሪ መሆኑን የሚናገሩት አቶ በፍርዴ፤ የዚህ ሁሉ መሰረቱ ሲወርድ ሲዋረድ የመጣው አጥፊ የፖለቲካ ባህላችን የራሱ አስተዋጽኦ አለው ይላሉ:: ይህም ልዩነቶችን በንግግር ሳይሆን ከሆነ በጠብ፣ በሴራ፣ ካልሆነ በኩርፊያ መፍታት ይስተዋላል:: ነገር ግን በተወሰነ የግል ጥቅምና እና የተሻልኩ ነኝ በሚል እርስ በእርስ በመጠፋፋትና ለአሁኑ ፖለቲካ መጥፎ ጠባሳ ጥለው አልፈዋል:: በህግ አለመመራት፤ አገር አለማስቀደም፤ ቁርጠኛ አለመሆን ችግሮች መኖራቸው አሁንም ድረስ በአገሪቱ ለሚስተዋለው ጽንፍ ረገጥ እሳቤዎች መጥፎ እርሾ እንደሆነም ያብራራሉ::
እንደ ምሁራኑ ገለፃ፤ ፅንፈኝነት በሂደት የአገረ መንግስት ስጋት መሆኑ መታወቅ አለበት:: ጽንፈኝነት ምንም እንኳን ዓላማውን ለማሳካት ዘርፈ ብዙ ስልቶችን ቢጠቀምም ግብ የሚመታ አይደለም:: ይህም በመሆኑ የተለያ ጉዳዮችን ለማድረስ የማይፈነቅሉት ደንጋይ የለም:: ጽንፈኞች የተሻለ እና የሚሸጡት ሃሳብ የሌላቸው በመሆኑ ፍላጎታቸውን መግለጽ የሚፈልጉት በኃይል እና በአፈ ሙዝ ነው፤ በመሆኑም ይህን ለመመከት መንግስት ሁሌም ቢሆን ንቃቱን አስጠብቆ መቀጠል ይኖርበታል:: መንግስት ጽንፈኞችን መግራትም ለይደር የማይተው ጉዳይ መሆን አለበት:: የፅንፈኝነት አስተሳሰቦች የህዝብ አጀንዳ እንዳይሆኑ መንግስት በእጅጉ ሊጠነቀቅ ይገባል የሚል ምክረ ሃሳብ አላቸው::
ምሁራኑ፣ አገር እና ህዝብን ለመታደግ ሲባል ከመንግስት የመረረ እርምጃ መውሰድ ግድ ይላል ባይ ናቸው:: ሀገሪቱ ውስጥ የሚገኙውን የፖለቲካ አደረጃጀትና የቀጣይ ዘመናትን ዕጣ ፋንታ ከግምት ውስጥ ያስገባ ስርዓትና የፖለቲካ ስሪት መፍጠር ለይደር የማይተው መሆኑንም ያሳስባሉ:: ፅንፈኝነትን በአዎንታዊ ትርክት የሚያጎሉና የሚያወድሱ አካላትንም በህግ አግባብ አደብ ማስያዝ ችግሩን ለመወጣት ከሚያግዙ የመፍትሄ አቅጣጫዎች ውስጥ መሆኑንም ምሁራኑ ያብራራሉ:: በአገሪቱ ውስጥ ዘመናትን የተሻገረውን የመጠፋፋት እና የሴራ ፖለቲካ በማስወገድ ለሃያ አንደኛው ክፍለ ዘመን የሚመጥን አዲስ እይታ እና የፖለቲካ ምዕራፍ ማመላከትም አስፈላጊ ስለመሆኑ ያስገነዝባሉ::
ክፍለዮሐንስ አንበርብር
አዲስ ዘመን ግንቦት 15/2015