የህብረተሰቡን ኑሮ ሊያሻሽሉ የሚችሉ ቴክኖሎጂዎችን በማምረት ረገድ የቴክኒክና ሙያ ተቋማት ከፍተኛ ድርሻ አላቸው:: ተቋማቱ የህብረተሰቡን ችግር መነሻ በማድረግ ጥናት ላይ ተመርኩዘው ችግር ፈቺ የሆኑ ቴክኖሎጂዎችን በመቅዳት፣ በማላመድና በማሻሻል የፈጠራ ሥራዎችን መሥራት ይጠበቅባቸዋል::
በመሆኑም በየዓመቱ ከውጭ የሚገቡ ቴክኖሎጂዎችን መተካት የሚያስችሉና የህብረተሰቡን ችግር የሚፈቱ ቴክኖሎጂዎችን ሲሠሩ የሚስተዋለው በዚሁ ምክንያት ነው:: ተቋማቱ የሚሰሯቸውን ቴክኖሎጂዎች ህብረተሰቡ እንዲተዋወቃቸው ለማድረግ በየዓመቱ አውደ ርዕይ ይዘጋጃል::
ዘንድሮም ለ13ኛ ጊዜ በአዲስ አበባ ቴክኒክና ሙያ ኤጀንሲ አዘጋጅነት “ሙያና ክህሎት ለስኬት” በሚል መሪቃል በኤግዚቢሽን ማዕከል ከሚያዚያ 26 እስከ 30 ቀን 2015 ዓ.ም ተካሂዷል:: በአውደ ርዕዩ ከ180 በላይ ችግር ፈቺ የፈጠራ ውጤቶች ለእይታ የቀረቡበት መሆኑ ነው የአዲስ አበባ ከተማ የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ቢሮ ኃላፊ ሀቢባ ሲራጅ የተናገሩት፤
እሳቸው እንደሚሉት፤ አውደ ርዕዩ ከሚካሄድባቸው ዋና ዋና ዓላማዎች መካከል ዘርፉን ከማህበረሰቡ ጋር ማስተዋወቅ፣ የደረሰበትን ደረጃ ለኢንዱስትሪዎችና ለኅብረተሰቡ ማሳየት እንዲሁም በዘርፉ የተሰማሩ አንቀሳቃሾችና ተማሪዎች የውድድር መንፈስ ማጎልበት ነው።
በአውደ ርዕዩ የቴክኖሎጂ ውጤቶች ይዘው ከቀረቡት ኮሌጆች መካከል የአዲስ አበባ ተግባረ እድ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ አንዱ ነው:: የኮሌጅ የቴክኖሎጂ ልማት ባለሙያ አቶ ጌታዬ ዳምጤ እንደሚሉት፤ የአዲስ አበባ ተግባረ እድ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጁ የተቋቋመበት አንዱ ዓላማ ኢንተርፕራይዞችን ለመደገፍ ሲሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ ተማሪዎችን አሰልጥኖ ማውጣት ነው:: ኢንተርፕራይዞችን በመደገፍ ረገድ የቴክኖሎጂ፣ የክህሎትና የካይዘን ድጋፍ ያደርጋል::
በቴክኖሎጂ ድጋፍ በዓመቱ ለኢንተርፕራይዞች ሆነ ተጠቃሚዎች ምን አይነት ቴክኖሎጂ ያስፈልጋል የሚለውን ጥናት እያካሄደ በጥናቱ መሠረት የማህበረሰቡን ችግር ሊፈቱ የሚችሉ ቴክኖሎጂዎች ይሰራሉ:: እነዚህን ቴክኖሎጂዎች በኢግዚቢሽን ለዕይታ የሚቀርቡበት ዋና ዓላማ ማህበረሰቡ አይቶ እንዲያመርትና እንዲጠቀምበት ለማስቻል መሆኑን ያስረዳሉ::
በዘንድሮው ‹‹የቴክኒክና ሙያ ሳምንት ›› የአዲስ አበባ ተግባረ እድ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ የተለያዩ የቴክኖሎጂ ውጤቶችን ይዞ ቀርቧል:: ከእነዚህ ውስጥም የዘይት ማቀነባበሪያ ማሽኖች፣ የማተሚያ ማሽን፣ የተለያዩ የእንጨት ሥራ ውጤቶች፣ የአውቶሞቲቭ ቴክኖሎጂ የማስተማሪያ ሞዴል የሚሉት ይጠቀሳሉ::
እንደ እሳቸው ገለጻ፤ በኮሌጁ በየዓመቱ የማህበረሰቡን ችግር መነሻ በማድረግ ቀላልና ውስብስብ የሆኑ ችግሮችን ለመለየት ጥናት ይካሄዳል:: ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባና በሂደት መፈታት ያለበት ችግር ከተለየ በኋላ አስፈላጊውን ቴክኖሎጂ በመለየት የዲዛይን ሥራዎች ቀርበው ቴክኖሎጂው ይሠራል::
የማህበረሰቡን ችግር በመለየት ረገድ መጀመሪያ የተለየው የዘይት ማቀነባበሪያ ለማምረት የሚያስፈልገው የዘይት ማሽን መሆኑን ያነሱት አቶ ጌታዬ፤ ያለው ችግርና የማህበረሰቡ ፍላጎት ከፍተኛ እንደሆነ ተናግረዋል:: ይህንን መነሻ በማድረግ ለዚህ አገልግሎት ሊውሉ የሚችሉ ቴክኖሎጂዎች በቅድሚያ በመለየት ፣ የሰነድና ዲዛይን ሥራዎች ተሰርተው ቴክኖሎጂውን ወደ ማምረት ሥራ እንደተገባ ይገልጻሉ::
እንደ እሳቸው ገለጻ፤ የዘይት መጭመቂያ ማሽኑን ለመሥራት መጀመሪያ ላይ መሥራት ካለበት የለውዝ መፈልፈያ ማሽን ጀምሮ እስከ መጨረሻው የማሸጊያ ማሽን ድረስ አራት የሚሆኑ ቴክኖሎጂዎችን መሥራት ያስፈልጋል:: ለዘይት መጭመቂያ ማሽኑ የሚያስፈልገውን አምስተኛውን ቴክኖሎጂ መሙያና መክደኛ ለመሥራት የሚያስፈልግ ቴክኖሎጂ ሲሆን፣ በግብዓት እጥረት ምክንያት አሁንም ድረስ መሥራት እንዳልተቻለ ነው ያስረዱት::
ሌሎቹ አራቱ ቴክኖሎጂዎች ግን ከተሰሩ በኋላ የጥራት ፍተሻ ተደርጎላቸዋል ያሉት አቶ ጌታዬ፣ የዘይት መጭመቂያ ማሽኑ የጥራት ፍተሻ ከተደረገለት በኋላ የኑግና የለውዝ ዘይት በመጭመቅ ተግባራዊነቱ ተፈትሾ ለኢንተርፕራይዞች መሸጋገሩን ገልጸዋል::
እሳቸው እንደሚሉት፤ አዲስ አበባ ፖሊቴክኒክ ኮሌጅ የማስተማሪያ ተቋም እንደመሆኑ መጠን የቴክኖሎጂዎችን ፕሮቶታይፕ ናሙና ሰርቶ በማሳየት ለሚጠቀሙ አካላት በመስጠት አምርተው ለህብረተሰቡ ተደራሽ ለማድረግ ያግዛል:: ለምሳሌ የዘይት መጭመቂያ ማሽኑን ቤንሻንጉል ጉምዝ የሚገኙ ግብርና ላይ የተሰማሩ ዩኒየኖች መጥተው አይተው የዘይት መጭመቂያ ማሽን ለመጠቀም እንደሚፈልጉ ያላቸውን ፍላጎት አሳይተዋል:: ሌሎችም በብረታ ብረት ዘርፍ ተደራጅተው ወደ ኢንዱስትሪ ደረጃ እያደጉ ያሉ እነ ጎልደን ብሪጅን የመሳሰሉት ኢንዱስትሪዎች ወስደው እንዲያመርቱት እየተደረገ ነው:: ኢንዱስትሪዎቹ ማሽኑን ካመረቱት በኋላ ለተጠቃሚዎች ያደርሳሉ:: ተጠቃሚዎች ደግሞ ፋብሪካ በማቋቋም የዘይት ምርት እያመረቱ ለህብረተሰቡ ያቀርባሉ::
ማሽኑ ከውጭ ሀገር ከሚገባው የዘይት መጭመቂያ ማሽን ጋር ሲነጻጸር በማምረት ሂደትም ሆነ በጥራት እኩል ደረጃ ያለው መሆኑን የጠቀሱት አቶ ጌታዬ፤ ከውጭ ሀገር ከሚገባው ማሽን አንጻር በተሻለ ዋጋ የሚቀርብ መሆኑንም ተናግረዋል:: በኮሌጁ የተሰራው ይህ የዘይት መጭመቂያ ሁለት አይነት ጠቀሜታዎች ያሉት ሲሆን፤ የመጀመሪያው የውጭ ምንዛሪን ማስቀረት ሲሆን፤ ሁለተኛው ደግሞ በሀገር ውስጥ ዘይት ማምረት ሲቻል ከውጭ ሀገር የሚገባውን ዘይት ማስቀረት ይቻላል:: ይህም ዘይትን ወደ ሀገር ውስጥ ለማስገባት ይወጣ የነበረውን ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ማስቀረት ይቻላል ብለዋል::
ሌላኛው የቴክኖሎጂ ፈጠራ አውቶሞቲቪ ማስተማሪያ ሞዴል መሆኑን የጠቀሱት አቶ ጌታዬ፤ ቴክኖሎጂው ለተማሪዎች በተግባር የተደገፈ ትምህርት ለመስጠት የሚያገለግል እንደሆነና ለመንጃ ፈቃድ ትምህርት ቤቶች ለማስተማሪያነት የሚያስፈልግ እንደሆነ ተናግረዋል:: የአውቶሞቲቭ ቴክኖሎጂ ማስተማሪያ ሞዴል ከውጭ አገር በውድ ዋጋ የሚገባ ሲሆን፤ ለዚህ የማስተማሪያ ሞዴል የሚወጣው የውጭ ምንዛሪ ለማስቀረት የሚያስችል ሥራን ለመሥራት በኮሌጁ ባለሙያዎች በሀገር ውስጥ መገጣጠም መቻሉን ነው ባለሙያው የሚናገሩት::
ሞዴሉን ለመሥራት የሚያስፈልጉት እቃዎች (ስፔር ፖርቶቹ) ከውጭ የሚገቡ ሲሆን፣ ከውጭ በከፍተኛ ወጪ የሚመጣውን የማስተማሪያ ሞዴል አስመስሎ የመሥራትና የመገጣጠሙ ሥራ በኮሌጁ ባለሙያዎች ተሰርቶ ለተማሪዎች ማስተማሪያ እየዋለ እንደሚገኝ ይገልጻሉ:: ይህን የማስተማሪያ ሞዴል ከውጭ ሀገር ለማስመጣት 245ሺ ብር የሚፈጅ ሲሆን፣ በሀገር ውስጥ የተሰራው ደግሞ በ165 ሺ ብር ወጪ ተሠርቶ ጥቅም ላይ መዋል እንደቻለ ተናግረዋል::
በኮሌጁ የተሠራው ሌላኛው የቴክኖሎጂ ውጤት ለጋርመንት የሚሆን ማተሚያ ማሽን ሲሆን፤ ጋርመንት ላይ የሚሰሩ አካላት የተለያየ ቅርጽ ለማውጣት የሚያስችል ማሽን ነው:: ማሽኑ የተለያዩ ዲዛይኖችን በአልባሳቱ ላይ ማተም የሚችል ሲሆን፤ ይህን ማሽን ከውጭ ሀገር ለማስገባት የሚያስፈልገው የብር መጠን 52ሺ ብር ነው:: ነገር ግን በሀገር ውስጥ ሲመረት 25 ሺ ብር የሚደርስ ወጪ ጠይቋል:: አሁን ላይ በገበያ ውሉ ለሽያጭ ሲቀርብ ደግሞ የመሸጫ ዋጋው 32 ሺ ብር እንደሆነ ይናገራሉ::
አንድን ቴክኖሎጂ ስንስራ በቅድሚያ ከኢንተርፕራይዞቹ ጋር ያለውን የቴክኖሎጂ ፋላጎት እናጠናለን የሚሉት ባለሙያው፤ ከዚያም የሚፈልጉትን አይነት ቴክኖሎጂዎች በማጥናት ከውጭ ሀገር ከሚመጡት ቴክኖሎጂዎች የመቅዳት (ኮፒ የማድረግ) ሥራ ይሰራል ይላሉ:: ሀገር ውስጥ የሚሰራው ቴክኖሎጂ ከውጭ በሚገባው ቴክኖሎጂ ስታንዳርድ መሠረት ጥራቱን የጠበቀ ሆኖ እንደሚሰራ ጠቅሰው፣ ዋጋው ግን ቅናሽ እንዳለው ጠቁመዋል::
ኮሌጁ ቴክኖሎጂዎችን ከውጭ ከሚገቡት ቴክኖሎጂዎች በመቅዳት (ኮፒ) ፣ የቴክኖሎጂ ፈጠራዎች በመሥራትና ቴክኖሎጂዎችን በማሻሻል (ሞዲፊኬሽን) እንደሚሰሩ የጠቆሙት አቶ ጌታዬ፤ አንድ ቴክኖሎጂ ሲቀዳ (ኮፒ ሲደረግ) ከውጭ ሀገር ለማምጣት ብዙ ወጪ የሚጠይቀውን ቴክኖሎጂ በተመሳሳይ በሀገር ውስጥ ሰርቶ የውጭ ምንዛሪ በማስቀረት ለሀገር ውስጥ አገልግሎት እንዲሰጥ ለማድረግ ታሰቦ የሚሰራ መሆኑን አብራርተዋል::
እነዚህ ቴክኖሎጂዎች ጥቅም ላይ ውለው ያመጡት ውጤት ምንድነው ስንል ላቀረብንላቸው ጥያቄም በሰጡት ምላሽ፤ እነዚህ ቴክኖሎጂዎች ህብረተሰቡ ዘንድ ተደራሽ ሆነው ጥቅም ላይ እንዲውሉ በማድረግ ረገድ የግንዛቤ ክፍተቶች እንዳሉ ይናገራሉ:: አብዛኛውን ጊዜ ብዙ ሰው ፍላጎት የሚያሳየው ከውጭ በሚገባው ቴክኖሎጂ ላይ ነው የሚሉት አቶ ጌታዬ፤ በሀገር ውስጥ የሚሠሩት ቴክኖሎጂ ከዚያ በተሻለ መልኩ ተሰርተው የሚቀርቡ እንደሆነ ተናግረዋል:: ህብረተሰቡ ሀገር ውስጥ ስለሚሰሩ ቴክኖሎጂዎች ያለው ግንዛቤ አነስተኛ መሆኑን ጠቅሰው፤ በቴክኖሎጂዎቹ ላይ እምነት የሌለው መሆኑንም ተናግረዋል::
ይሁንና ህብረተሰቡ በሀገር ውስጥ ለሚመረቱ ቴክኖሎጂዎች ያለው አመለካከት ተቀይሮ የሀገር ውስጥ ቴክኖሎጂዎችን መጠቀም እስካልቻለ ድረስ ቴክኖሎጂ መስራት ብቻውን ጥቅም የለውም የሚሉት አቶ ጌታዬ፤ በየዓመቱ የሚሰሩ ቴክኖሎጂዎች ሥራ ላይ ውለዋል ለማለት አያስደፍርም ብለዋል::
ቴክኖሎጂዎቹን ወስደው እየተጠቀሙ ያሉ በርካታ ኢንተርፕራይዞች ስለመኖራቸው የሚጠቁሙት አቶ ጌታዬ፤ ቴክኖሎጂዎች ለኢንተርፕራይዞች ከተሸጋገሩ በኋላ የኦዲትና የግምገም ሥራ እንደሚሰራም ይናገራሉ:: በዚህ ቴክኖሎጂዎችን በማስተዋወቅ ህብረተሰቡ የሀገር ውስጥ ምርት እንዲጠቀም ለማድረግ በየጊዜው በሚዘጋጁ አውደ ርዕዮች ላይ በመሳተፍ ማስተዋወቅ እንዲሁም በተለያዩ የሚዲያ አማራጮች በመጠቀም ግንዛቤ የማስጨበጥ ሥራ እየተሰራ መሆኑን አመላክተዋል::
ለህብረተሰቡ ግንዛቤ ከማስጨበጥ ጎን ለጎን የሚሰሩ ቴክኖሎጂዎችን ጥራት ማሻሻል እንደሚገባም የጠቀሱት አቶ ጌታዬ፤ የሚሰራው ቴክኖሎጂ ከውጭ ከሚገባው ቴክኖሎጂ ጋር ሲነጻጸር በጥራትም ሆነ በጥንካሬ የሚሻል እንዲሆንና ህብረተሰቡ እምነት እንዲያድርበት ማድረግ ይገባል ብለዋል::
ለዚህም በዘንድሮ ዓመት የቀረቡት የቴክኖሎጂ ሥራዎች ከቀለም አቀባብ ጀምሮ ማራኪና ቀልብ የሚስቡ ለማድረግ ጥረት ተደርጓል:: የቀለም አቀባቡ የቴክኖሎጂ ጥራትና ጥንካሬን ባያመላክትም ቴክኖሎጂዎቹ ሳቢ እንዲሆኑ በማድረግ ህብረተሰቡን ለመሳብ ጥረት መደረጉን ነው የጠቀሱት::
የአቃቂ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ በበኩሉ በፈርኒቸር፣ በብረታብረት፣ በከተማ ግብርና ፣ በጋርመንትና በሌሎቹ ዘርፎች የተሰሩ ቴክኖሎጂዎችን ይዞ ቀርቧል:: እነዚህ ቴክኖሎጂዎች ከውጭ የሚገቡ ቴክኖሎጂ በሀገር ውስጥ መተካት የሚችሉ ከመሆናቸው ባሻገር ሁሉም የየራሳቸው ተግባራት አሏቸው:: የሚሉት የኮሌጁ የቴክኖሎጂ ዲዛይንና ማረጋገጥ ባለሙያ አቶ አበራ ደሳለኝ ናቸው::
አቶ አበራ እንደሚሉት፤ ኮሌጁ አንድን ቴክኖሎጂ ለመሥራት በቅድሚያ መነሻ የሚያደርገው ከሚደግፋቸው ኢንተርፕራይዞች ችግር በመነሳት ጥናት በማካሄድ ነው:: ከዚህም ለችግር መፍትሔ የሚሆን ችግር ፈቺ ቴክኖሎጂን በመስራት እንዲሸጋገር ይደረጋል:: ኢንተርፕራይዙ በቴክኖሎጂው ተጠቅሞ ሀብት ያፈራበታል:: ሀብት ካፈራበት በኋላ መጨረሻ ላይ ያፈራውን ሀብት የሚያሳይ የሰነድ ማረጋገጫ ለአሰልጣኞች ይሰጣል:: በመጨረሻም ኮሌጁ ያሸጋገራቸውን ቴክኖሎጂ አስመልክቶ ኦዲት የማድረግ ሥራ ይሠራል::
ቴክኖሎጂዎች የሚሠሩት ኢንተርፕራይዞቹ የሚፈልጉትን አይነት ቴክኖሎጂ በማጥናት ሲሆን፣ አብዛኛውን ጊዜ በመቅዳት( ኮፒ በማድረግ ) በሀገር ውስጥ ይሠራሉ:: ኮሌጁ ከውጭ ሀገር የሚገቡ ቴክኖሎጂዎችን በማስቀረት በሀገር ውስጥ በማምረት( በመተካት) ኢንተርፕራይዞች በቀላል ዋጋ ተጠቃሚ እንዲሆኑ እያስቻለ ይገኛል የሚሉት አቶ አበራ፤ ይህም የውጭ ምንዛሬ ከማስቀረት ባሻገር ሩቅ መሄድና መሳብ ሳያስፈልግ ከውጭ የሚመጣውን ቴክኖሎጂ የሚተካ ቴክኖሎጂ በማምረት ህብረተሰቡን ተጠቃሚ የሚያደርግ ነው ይላሉ::
አንዱን ቴክኖሎጂ ከውጭ ሀገር ስናስገባ ወጪው እጅግ ከፍተኛ ነው የሚሉት አቶ አበራ፤ ቴክኖሎጂውን በሀገር ውስጥ ማምረት እንደሚቻል በማሳየት የኢንተርፕራይዞችን ፍላጎት መሠረት ያደረጉና ችግራቸውን የሚፈታ ቴክኖሎጂ እንደሚሰሩ ገልጸዋል::
በሀገር ውስጥ በሚመረቱ ቴክኖሎጂዎች ላይ በአብዛኛው የጥራት ችግር ይነሳል:: እናንተ የምትሰሯቸው ቴክኖሎጂዎች ከጥራት አንጻር ምን ይመስላሉ ስንል ላነሳነው ጥያቄ፤ በኮሌጁ የሚሠሩት ቴክኖሎጂዎች ጥራታቸውን የጠበቁ ስለመሆናቸው አቶ አበራ ተናግረዋል:: ለዚህም ከአሰልጣኞች በየጊዜው በሚሰበሰበው መረጃ ቴክኖሎጂዎቹ ያላቸውን የጥራት ደረጃ የሚያሳይ ነው ብለዋል:: ከውጭ የሚመጡ የፈርኒቸር ውጤቶችና በአውደ ርዕዩ ላይ እኛ ይዘን ከቀረብናቸው የፈርኒቸር ውጤቶች ጋር ሲነጻጸር በጥራት የሚበልጠው ሀገር ውስጥ የተሰራ ነው ሲሉም አብራርተዋል::
ከውጭ የሚመጡት የፈርኒቸር ውጤቶች ከአንዱ ቦታ ወደሌላ ቦታ ሲንቀሳቀሱ በቀላሉ የመበላሸትና የመሰባበር ሁኔታዎች እንደሚገጥሟቸው ማረጋገጥ መቻሉን የጠቆሙት አቶ አበራ፤ በሀገር ውስጥ የሚመረቱ ምርቶች ከውጭ በሚገቡት ልክ የጥራት ደረጃቸውን የጠበቁ ስለመሆናቸው አመላክተው፤ እንደ አቃቂ ኮሌጅ ጥራቱን የተጠበቀ የቴክኖሎጂ ሥራ ሠርተው ማቅረብ እንደቻሉ በመግለጽ ሃሳባቸውን አጠቃለዋል::
ወርቅነሽ ደምሰው
አዲስ ዘመን ግንቦት 15/2015