የኢሕአዴግ መንግሥት ተሸኝቶ ለውጥ ከመጣ እነሆ አምስት ዓመት ሞላው። የለውጡ አየር መንፈስ እንደጀመረ በኢትዮጵያ በርካታ ተስፋ ሰጪና አበረታች ተግባራት ተከናውነዋል። በዚህም መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ተስፋውን አይቶ በጎ ምላሽ ለለውጡ መንግሥት ሰጥቷል። ቀደም ሲል በቀድሞው መንግሥት አኩርፈው የነበሩና ቁርሾ ውስጥ ገብተው የቆዩ የተለያዩ የፖለቲካ ቡድኖችም ለለውጡ መንግሥት ያላቸውን ድጋፍ አሳይተዋል ።
በሂደት ግን ነገሮች መልካቸውን እየቀየሩ ግድያ፣ መፈናቀል፣ ስደት፣ የእርስ በርስ ግጭትና ጦርነት የአገሪቱ መገለጫዎች ሆነው ሰንብተዋል። በዚህም ሕዝባችን ከለውጡ ማግስት ጀምሮ በሀገሪቱ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ሕይወት ላይ አሳድሮት የነበረው ተስፋ እየተሸረሸረ መጥቷል። ቅድሚያ የሚሰጡት ዋነኛ የትኩረት አጀንዳቸውም ሰላምና ደህንነት ሆኗል።
መንግሥትም ቢሆን ካለፉት ሁለትና ሦስት ዓመታት ወዲህ ሀገሪቱን ከገባችበት የፖለቲካዊ፣ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ውጥንቅጦች ለመታደግ ብዙ ሲጥር ከርሟል። ከለውጡ ማግስት ጀምሮ የፖለቲካ ችግሮችን በሰላማዊ መንገድ በድርድር ለመፍታት ሲሄድበት የነበረውን መንገድ በማጠናከርም ሀገሪቱ አሁን ላይ የሰላም አየር መተንፈስ ጀምራለች።
በየትኛውም ሀገር ውስጥ የፖለቲካ፣ የሀሳብና የርዕዮተ ዓለም ልዩነት ይኖራል፤ ይጠበቃልም። ነገር ሀሳብንና ልዩነትን በንግግርና በመደማመጥ መፍታት የሰለጠነ መንገድ ነው። አዲሱ መንግሥትም ኢሕአዴግን አሸንፎ ወደ ሥልጣን የመጣው በሃሳብ በልጦ ነው:: ነገር ግን ዛሬም ድረስ ከሃሳብ ይልቅ ኃይልን እንደአማራጭ ወስደው የሥልጣን እርካብ ለመቆናጠጥ የሚፈልጉ በርካታ ኃይሎች አሉ::
ሰላምና ደህንነት የሕዝቡ ዋነኛ አጀንዳ ሆኖ ሳለ በመሣሪያ ኃይል አራት ኪሎ ቤተመንግሥት ለመግባት የሚቋጡም በርካቶች ናቸው:: ይህ ግን አዋጭ አይደለም:: ግዜው ያለፈበት የፖለቲካ ስልት ነው:: አዋጪ በሃሳብ ለማሸነፍ አዳዲስ ሃሳቦችን ይዞ ብቅ ማለት ብቻ ነው:: አዳዲስ ሃሳቦች ያሉት የፖለቲካ ቡድን ደግሞ ሃሳቡ በሕዝቡ ዘንድ ተቀባይነትን እስካገኘ ድረስ ሁሌም አሸናፊ ነው::
የፖለቲካን ልዩነትንም ቢሆን ማንፀባረቅ የሚቻለው በአዳዲስ ሀሳቦችና በዲሞክራሲያዊ መንገድ ነው:: በዚህ የትግል መንገድም ነው የፖለቲካ ዓላማን ማሳካት የሚቻለው:: ይህ ሲሆን ሕዝብን በልዩ ልዩ መልኩ መጥቀም ይቻላል። ሰላምና ደህንነት ይረጋገጣል::
ሕዝቡም ከደህንነት ስጋት ተላቆ ሙሉ ትኩረቱን ወደ ልማት ያደርጋል:: ልዩነት ያላቸው የፖለቲካ ቡድኖች የፖለቲካ ሽኩቻቸውን ትተው በሰላማዊ መንገድ በመታገል ለሀገሪቱ ሰላምና ደህንት መረጋገጥ የበኩላቸውን አስተዋፅኦ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል::
ኢትዮጵያ በርካታ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የሚገኙባት ሀገር ናት:: የበርካታ ቋንቋዎች፣ እምነቶች፣ ባሕሎችና ታሪኮች ባለቤትም ናት:: እንዲህ የተለያዩ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በብዛት በሚገኙባት ሀገር ውስጥ የመብት፣ የእኩልነትና የማንነት ጥያቄዎች በስፋት መነሳታቸው አይቀርም። እነዚህ ጥያቄዎች ኃይልና ጉልበት የሚቀላቀልባቸው ከሆነ ውጤቱ የሕይወት መጥፋት፣ የንብረት መውደም መፈናቀልና ስደት ይሆናል።
ከዚህ አንፃር እነዚህና መሰል የመብት፣ የእኩልነትና የማንነት ጥያቄዎች በኃይልና በጉልበት የማይመለሱ በመሆናቸው ሌሎች ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ መንገዶችን መከተል የግድ ይላል:: እነዚህ ጥያቄዎች በሰላማዊ መንገድ የሚቀርቡ ከሆነ ደግሞ የግዜ ጉዳይ እንጂ በሂደት መልስ ማግኘታቸው አይቀሬ ነው። ይህ በመሆኑም በሀገሪቱም ዘላቂ መፍትሔና ሰላም ያመጣሉ። ስለዚህ ለጥያቄዎቹ መልስ ለማግኘት በሰላማዊ መንገድ መጠየቅ ያስፈልጋል::
በተለየ መልኩ ታሪክን ብቻ ነጥሎ ማየት ከተፈለገ ደግሞ ይህች ሀገር የበርካታ ታሪኮች ባለቤት ብትሆንም በመንግሥታት በኩል የፖለቲካና የርዕዮተ ዓለም መለዋወጥን ተከትሎ የታሪክ ሽሚያ ይስተዋላል። ይህም በብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በኩል እኔ ከፍ ያለ ታሪክ አለኝ የኔ ታሪክ ደግሞ ኮስሷል፤ ይሄ ታሪክ የኔ ነው እናንተ ታሪክ የላችሁም፤ የሚሉና መሰል የታሪክ አተያይና አመለካከቶች እያበቡ መጥተዋል። ይህም በሕዝቦች መካከል የተዛባና ወጥነት የሌለው የታሪክ ትርክት እንዲኖር አድርጓል። በዚሁ የተዛባ የታሪክ ትርክት ምክንያት የተከሰቱ አለመግባባቶችና ግጭቶችም ቀላል አይደሉም ።
ከዚህ አንፃር ታሪክን ከስር መሠረቱ ማጥናትና የተዛቡ የታሪክ ትርክቶችን ማስተካከል ብሎም ትክክለኛውን ታሪክ ለሕዝቡ ማስተላለፍ ይገባል። ለዚህ ደግሞ የታሪክ ምሑራን ሚና ወሳኝ በመሆኑ የተዛቡ ታሪኮችን በማስተካከልና ወጥነት እንዲኖራቸው በማድረግ ረገድ የድርሻቸውን ሊወጡ ይገባል። የፖለቲካ ቡድኖችም ተከታዮቻቸውን በተዛባና የውሸት ታሪክ ግራ ማጋባታቸውን ትተው ትክክለኛውን ታሪክ እንዲውቁ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል::
የሰላም ዋጋዋ ምን ያህል ከፍ ያለ እንደሆነ በሰሜኑ ጦርነት የተማርን ይመስላል:: በሁለቱም ወገኖች ለሰላም የሚደረጉ ጥረቶችም መልካም ጅምሮች ናቸው:: መንግሥት ከሌሎች ኃይሎች ጋር እያደረጋቸው ያሉ ውይይቶችም ለሰላም መፅናት አስተዋፅዋቸው የጎላ ነው::
የኢትዮጵያ ሕዝብ በበርካታ ችግሮች ውስጥ እንዳለ ይታወቃል:: የኑሮ ውድነት፣ የመኖሪያ ቤት እጦት፣ እና ሌሎችም ችግሮች ተደራርበውበት ጫንቃው ጎብጧል:: አሁን ትልቁ ሥራችን መሆን ያለበት ሀገራዊ ሰላሙን በማጽናት፣ ችግሮቻችንን ፈጥኖ መሻገር የሚያስችል ሁለንተናዊ ዝግጁነት መፍጠርና ወደ ሥራ መግባት ነው::
ከመንግሥት ባሻገር ለሀገሪቱ ሰላም መፅናት ኅብረተሰቡ፣ ተሰሚነት ያላቸውና ተፅዕኖ ፈጣሪ ግለሰቦች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ ፖለቲከኞችና ሌሎችም የኅብረተሰብ ክፍሎች የበኩላቸውን ድርሻ መወጣት ይኖርባቸዋል:: ምንም እንኳን በበርካታ ችግሮች ውስጥም ቢሆን ሕዝቡ ሰላም ዋስትናው ነውና ለሰላም መረጋገጥ የበኩሉን በመወጣት ከመንግሥት ጎን ሊቆም ይገባል:: ሰላም ለሀገራችን ሰላም ለሕዝባችን!
ዞስካለስ
አዲስ ዘመን ግንቦት 15/2015