ኢትዮጵያ፣ በጦርነት ዐውድ ውስጥ ሕልውናቸውን አስጠብቀው ዘመናትን ከተሻገሩ ሃገራት አንዷ ብትሆንም፤
በውስጧ የሚነሱ ተደጋጋሚ ሽኩቻዎች ግን የውስጥ አለመረጋጋቷን አሳድገው ወደ እርስ በእርስ ግጭትና ጦርነቶች
ስታመራ ቆይታለች፡፡
ይሄ ደግሞ በተለያዩ ቡድኖችና የፖለቲካ ኃይሎች ጥቅምና ፍላጎት ላይ ቢመሠረትም፤ ሂደቱ ሕዝብን ታክኮ፣ ተግባሩም
አገርን ለሕልውና አደጋ አጋልጦ መሆኑ ችግሩን ያከፋዋል፡፡ እናም እነዚህን ለሃገር ሕልውና አደጋ የሆኑ ቡድኖችንና
የፖለቲካ ኃይሎችን አደብ ለማስያዝ ሲባል በሚከሰት ጦርነት ሃገር እንደ ሃገር ከፍ ያለ ሰብዓዊ እና ኢኮኖሚያዊ ዋጋዎችን
ስትከፍል ኖራለች፡፡
ባለፉት አምስት የለውጥ ማግስት ዓመታትም የለውጡ ህሳቤና መንገድ ከግልና ከቡድን ፍላጎታቸውና ሕልማቸው
ጋር አልጓዝ ያላቸው ኃይሎች፤ ሕዝብን እንደ ሕዝብ፣ ሃገርንም እንደ ሃገር ችግር ውስጥ የከተቱ ግጭቶችን እዚህም እዚያም
ሲያስነሱና መጨረሻም ከፍ ወዳለ ጦርነት ሲያመሩ ታይተዋል፡፡
ጎልቶ የሚጠቀሰው የሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል ጦርነት አንዱ ሲሆን፤ በኦሮሚያ እና በሌሎችም በርካታ አካባቢዎችም
መሰል ግጭቶች ተከስተዋል፡፡ በእነዚህ ግጭቶችና ጦርነቶች ታዲያ ሃገር ከፍ ያለ ሰብዓዊና ምጣኔ ሃብታዊ ዋጋ ከፍላለች፡፡
መረጃዎች እንደሚያሳዩት፣ በእነዚህ ጊዜያት በተካሄዱ ግጭቶችና ጦርነቶች ምክንያት አገር በትሪሊዮን የሚተመን
ኢኮኖሚያዊ ሃብቷን አጥታለች፡፡ በዚህም የመንግሥት እና የግለሰብ ሃብቶች፣ የሕዝብ መገልገያ መሠረተ ልማቶች
(ትምህርት ቤቶች፣ የጤና ተቋማት፣ መንገድና ሌሎችም)፣ የማምረቻ ኢንዱስትሪዎች፣ የአየር ማረፊያዎች፣ ሆቴሎችና
የቱሪዝም መዳረሻዎችን የመሳሰሉ ለሃገርም ለሕዝብም ከፍ ያለ ሚና ያላቸው ተቋማት የመቃጠል፣ የመፍረስ፣ የመዘረፍና
ከአገልግሎት ውጪም የሆኑበትን ጉዳት አስተናግደዋል፡፡
ይሄ ደግሞ ተማሪዎችን ከትምህርት ገበታ ውጪ ያደረገ፤ ታማሚዎችን ከመታከሚያ ማዕከላት ጋር እንዳይገናኙና
በመድኃኒት እጦትና በሕመም ተሰቃይተው እንዲያልፉ ያስገደደ፤ ሕዝቦች ከመንግሥት አገልግሎት የሚያገኙበትን
መንገድ ያረዘመ፤ ዜጎች በአየርም ሆነ በየብስ የመንቀሳቀስ ዕድላቸውን ያጨነገፈ፤ ሆኖ ቆይቷል፡፡ ይሁን እንጂ ጦርነት
ያወደመውን ንብረት፣ ያከሰመውን ሕይወት ነፍስ ሊዘራበት ሰላም ቦታውን ሲረከብ፤ በጦርነት የተጎዱ የሰው ልጆችን
ለመደገፍ፣ የወደሙ መሠረተ ልማቶችንም ለመመለስ የሚያስችሉ ዘርፈ ብዙ ተግባራት ተከናውነዋል፤ እየተከናወኑም
ይገኛል፡፡
በዚህም የሰብዓዊ ድጋፍ ያለገደብ ለተጎዱ ዜጎች እንዲደርስ ተደርጓል፤ መንገዶች ተጠግነው ለአገልግሎት ክፍት
ተደርገዋል፤ ጉዳት የደረሰባቸው አምራች ኢንዱስትሪዎች ወደ ምርት የሚገቡበትን ዕድል አግኝተዋል፤ ተማሪዎችም
በተቻለ መጠን ወደ ትምህርት ገበታቸው እንዲመለሱ ተሠርቷል፤ የጤና ተቋማትም በመድኃኒትና ቁሳቁስ ተደራጅተው
መሠረታዊ አገልግሎቶችን እንዲሰጡ ማድረግ ተችሏል፡፡
ለምሳሌ፣ ከሰሞኑ ይፋ የተደረገው የጤና ሚኒስቴር ሪፖርት እንዳመለከተው፣ በግጭቶቹ በተለያየ አካባቢዎች
ባሉ ጤና ተቋማት ላይ ከፍ ያለ ጉዳት ደርሷል፡፡ ለአብነትም፣ በአፋር እና አማራ ክልሎች 42 ሆስፒታሎች፣ 499 ጤና
ጣቢያዎች እና አንድ ሺህ 728 ጤና ኬላዎች እና አራት የደም ባንኮች፤ እንዲሁም የደሴ የመድኃኒትና ሕክምና መሳሪያ
ማከማቻ ቅርንጫፍም አገልግሎት መስጠት በማይችሉበት ሁኔታ ጉዳት ደርሶባቸዋል፡፡ በትግራይ ክልልም በተመሳሳይ
በርካታ ተቋማት ጉዳት ደርሶባቸዋል፡፡
በመሆኑም ከጤና ሚኒስቴር እና ከክልል ጤና ቢሮዎች ቀጥተኛ ድጋፍ፣ ከልማት አጋሮች እና ከዲያስፖራው ርዳታ
በማሰባሰብ እነዚህን የተጎዱ ተቋማትን ለማደራጀት በተደረገው ጥረት ከአንድ ቢሊዮን 225 ሚሊዮን 943 ሺህ ብር በላይ
ወጪ ያላቸው የሕክምና ግብዓቶችን ማሰራጨት ተችሏል፡፡
በአማራ ክልል አብዛኛዎቹ የጤና ተቋማት መሠረታዊ አገልግሎት መስጠት የጀመሩ ቢሆንም፤ 70 በመቶ የሚሆኑት
ግን አሁንም በከፊል ነው አገልግሎት እየሰጡ ያሉት፡፡ በአፋር ክልልም ሥራ ካልጀመሩ ሁለት ጤና ጣቢያዎች በስተቀር
ሌሎቹ የጤና ተቋማት በከፊል አገልግሎት መስጠት ጀምረዋል፡፡
በትግራይ ክልልም የሕክምና መሣሪያዎች ተጠግነው ወደአገልግሎት እንዲመለሱ ተደርጓል፤ 312 ነጥብ አራት
ሚሊዮን ብር መጠን ያላቸው ክትባቶች፣ የሕይወት አድን መድኃኒቶችና ግብዓቶች ተደራሽ ሆነዋል፤ የመቀሌ እና ሽሬ
የመድኃኒት ማከፋፈያ ቅርንጫፎችም ወደ ሥራ ተመልሰዋል፡፡ በኦሮሚያና በቤኒሻንጉል ክልሎችም አስፈላጊ የሆኑ የጤና
ግብዓቶችን ለማኅበረሰቡ ማድረስ ተችሏል፡፡
ምንም እንኳን በዚህ መልኩ መልካም የሚባል ተግባር የተከናወነ ቢሆንም፤ ከችግሩ ስፋትና ግዝፈት አኳያ አሁንም
እነዚህን የጤና ተቋማት በተሟላ መልኩ ወደሥራ ማስገባት ጊዜ የሚሰጠው ጉዳይ አይደለም፡፡ በመሆኑም እናቶች
በጤና ተቋማት እንዲወልዱ፤ ሕጻናት ተገቢውን የጤና ክብካቤ እንዲያገኙ፤ ዜጎች በተገቢው ቦታና ተገቢውን የሕክምና
አገልግሎት እንዲያገኙ እነዚህን በጦርነቱ ምክንያት የተጎዱ የጤና ተቋማትን ቀድሞ ከነበሩበት በተሻለ ማደራጀት
ያስፈልጋል፡፡ ይሄም የአንድ አካል ብቻ ሳይሆን የሁሉን ኃላፊነት መሆኑን ተገንዝቦ ድጋፉን አጠናክሮ መቀጠል ይገባል!
አዲስ ዘመን ግንቦት 15/2015