እንደ ኢትዮጵያ ባሉ አገራት ከኢንቨስትመንት ዘርፎች መካከል ለአገሪቱ የኢኮኖሚ ዕድገት ትልቅ ድርሻ የሚኖረውና በርካታ የስራ እድል በመፍጠር የአንበሳውን ድርሻ የሚይዘው የኮንስትራክሽን ዘርፍ ነው። ይህ ለወጣቱ ሰፊ የስራ እድል በመፍጠር የኢኮኖሚው የጀርባ አጥንት የሆነ ግዙፍ ዘርፍ ባለፉት ጥቂት ዓመታት በበርካታ ምክንያቶች ተቀዛቅዞ ቆይቷል።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን የተቀዛቀዘውን ዘርፍ ለማነቃቃት መንግሥት የተለያዩ ርምጃዎችን እየወሰደ ይገኛል። ይሁን እንጂ ዘርፉ ከሚገጥሙት በርካታ ችግሮች አንፃር በሚፈለገው ደረጃ ለመመንደግ አሁንም ብዙ ፈተናዎች ይጠብቁታል። የኮንስትራክሽን ፕሮጀክቶች ግንባታ ሥራ ትልቁን ድርሻ የሚይዘው በወቅቱ የግብዓቶች አቅርቦትን የማረጋገጥ ሥራ ነው።
በኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ ውስጥ የሚካሄዱ የኮንስትራክሽን ፕሮጀክቶች 60 በመቶ የግብዓት አቅርቦት የማረጋገጥ ሥራ መሆኑን በዘርፉ የተሰሩ ጥናቶች ያመለክታሉ። የግብዓት አቅርቦትን በበቂ ሁኔታ ማረጋገጥ መቻል የአንድን የኮንስትራክሽን ፕሮጀክት አብዛኛውን ሥራ እንደመሥራት ይቆጠራል። ሆኖም በኢትዮጵያ ውስጥ ዘርፉን ጠፍንገው ከያዙት ችግሮች ውስጥ የግብዓቶች እጥረት በግንባር ቀደምትነት ተጠቃሽ ነው። የአገር ውስጥ የግንባታ ግብዓት አቅርቦት የፍላጎቱን ያህል ባለመሆኑ ከውጭ አገር ወደ አገር ውስጥ በከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ የሚገቡ ግብዓቶች መጠን በጣም ከፍተኛ ነው።
ሰሞኑን በሚሊኒየም አዳራሽ የከተማ እና መሠረተ- ልማት ሚኒስቴር ከዓለም አቀፉ ዲ ኤም ጂ ኢቨንትስ እና ከአገር አቀፉ አጋር ኢትኤል ኢቨንት እንዲሁም የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ሥራዎች ኮርፖሬሽን ጋር በጋራ በመሆን ያዘጋጁት ዓለም አቀፍ «የቢግ 5 ኮንስትራክት ኢትዮጵያ» የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ ኤግዚቢሽን፣ ሲምፖዚየም እና የንግድ ትርኢት ዘርፉ ያለበትን ችግር ለመቅረፍ የማይናቅ አስተዋፅኦ አለው።
መድረኩ በኢትዮጵያ መዘጋጀቱ ለኮንስትራክሽን ሥራዎች ውጤታማነት በሚያገለግሉ ግብዓቶች ፍላጎትና አቅርቦት መካከል ያለውን ክፍተት በመሙላት በዘርፉ ያለውን ችግር ለመፍታት ትልቅ እገዛ ያደርጋል ተብሎ ይጠበቃል። ከዚህ ባሻገር ዓለም አቀፍ ተሞክሮና የቴክኖሎጂ ሽግግርን ለማሳለጥ የሚያስችል ትልቅ መድረክ እንደመሆኑ የግንባታ ዘርፉን ለማነቃቃት ትልቅ ፋይዳ ይኖረዋል።
የአገር ውስጥ እና የውጭ የዘርፉ ባለሙያዎች አገሪቱ ያላትን የኮንስትራክሽን ግብዓቶች እምቅ አቅም አውቀው መዋዕለ ንዋያቸውን በማፍሰስ ዘርፉን እየፈተነ ያለውን የኮንስትራክሽን ግብዓት እጥረት እንዲቀርፉ እንዲህ አይነቱ መድረክ ትልቅ እድል ይፈጥራል። ይህን እድል በማስፋት በተለይም ምንጊዜም አንገብጋቢ ለሆነው የወጣቶች የስራ እድል ፈጠራ መ ጠቀም ከተቻለ በአንድ ድንጋይ ሁለ ት ወፍ እንደመምታት ነው።
ኢትዮጵያ ለኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ ምቹ የሆኑ እና በሰፊው ጥቅም ላይ ሊውሉ የሚችሉ በርካታ የተፈጥሮ ሀብቶች ቢኖሯትም አሟጦ ጥቅም ላይ በማዋል ረገድ ክፍተቶች አሉ። የአገር ውስጥ እና የውጭ የዘርፉ ባለሙያዎች አገሪቱ ያላትን የኮንስትራክሽን ግብዓቶች እምቅ አቅም አውቀው በዘርፉ መዋዕለ ንዋያቸውን በስፋት ማፍሰስ አለመቻላቸው ለዚህ አንዱ ምክንያት ነው። በዘርፉ የዓለም አቀፍ ኤግዚቢሽን በኢትዮጵያ መዘጋጀቱ የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪውን ለማነቃቃት እና በግንባታው ዘርፍ ያሉ ማነቆዎችን ለመፍታት አንዱ የመፍትሄ ርምጃ ነው።
በአገር ውስጥ ያለውን የግብዓት ማምረቻ የጥሬ ዕቃ ክምችት ለዓለም በማሳየት ኢንቨስትመንትን በመሳብ፣ የዘርፉን ተዋናዮች እርስ በርስ ለማስተዋወቅና አብሮ የመሥራት ባህልን ለማዳበር፣ የቴክኖሎጂ አቅምን ለማሳደግና በዘርፉ ያለውን ዕምቅ አቅም ከማስተዋወቅ ባሻገር ለቱሪዝም ኢንዱስትሪው መስፋፋትም ትልቅ አቅም የሚፈጥር ይሆናል።
በኢትዮጵያ በአሁኑ ሰአት የመንገድ፣ የባቡር፣ ግድቦችና ሌሎች የግንባታ ፕሮጀክቶች በስፋት እየተከናወኑ መሆኑንና ይሄም በኮንስትራክሽን ዘርፍ ለተሰማራ የውጭ ኩባንያ መዋዕለ ነዋይ ለማፍሰስ መልካም አጋጣሚ የሚፈጥር ይሆናል። በኢትዮጵያ የኮንስትራክሽን ዘርፍ ያለውን የቢዝነስ አማራጭ ይበልጥ ለመረዳትም አጋዥ ነው።
ስለሆነም መሰል ዓለም አቀፍ መድረኮችም በዘርፉ የሚስተዋለውን የአቅም፣ የክሂሎት፣ የአመለካከትና የአስተሳሰብ ችግሮችን ከመፍታት ባሻገር የወጣቶችን ተጠቃሚነት በአግባቡ ማረጋገጥ ከማስቻላቸውም በላይ ኢትዮጵያ ልታሳካ እየተጋችብት ላለው ብልጽግና ፋይዳው ብዙ ነውና ተጠናክረው ሊቀጥሉ ይገባል!
አዲስ ዘመን ሰኞ ግንቦት 14 ቀን 2015 ዓ.ም