
አዲስ አበባ፦ የዘንድሮ ዓመት የበጋ መስኖ ስንዴ ምርት አሰባሰብ እየተጠናቀቀ እንደሆነ የኢትዮጵያ ግብርና ኢንስቲትዩት አስታወቀ። ከ70 በመቶ በላይ የሆነው ምርት የተሰበሰበ ሲሆን ቀሪው በተያዘው ወር ተሰብስቦ ይጠናቀቃል ተብሎ እንደሚጠበቅም ገልጿል።
በኢትዮጵያ ግብርና ኢንስቲትዩት የመስኖ ስንዴ ፕሮጀክት አስተባባሪ ዶክተር ዳንኤል ሙለታ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደተናገሩት፤ በዘንድሮ ዓመት በአገር አቀፍ ደረጃ የበጋ መስኖ ስንዴ ፕሮጀክት አንድ ነጥብ ሦስት ሚሊዮን ሄክታር መሬት ለመሸፈን ታቅዶ አንድ ሚሊዮን 356 ሺህ 743 ሄክታር መሬት መሸፈን ተችሏል። እስከ አሁን 70 በመቶ የሆነው ምርት የተሰበሰበ ሲሆን ቀሪው በያዝነው ግንቦት ወር ተሰብስቦ ይጠናቀቃል ተብሎ እንደሚጠበቅ የመስኖ ስንዴ ፕሮጀክት አስተባባሪው ዶክተር ዳንኤል ሙለታ ገልጸዋል።
በዘንድሮ ዓመት የበጋ መስኖ ስንዴ ከ52 ሚሊዮን በላይ ኩንታል ስንዴ ምርት ለመሰብሰብ ታቅዷል ያሉት አስተባባሪው፤ እስከ አሁን ድረስ ከሁለት መቶ ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በበልግ ዝናብ ሳቢያ አልተወቃም። እስከ አሁን ድረስ ተሰብስቦ ከተወቃው ግን ከ24 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ተገኝቷል ብለዋል።
ከጥቅምት ወር አጋማሽ ጀምሮ በበጋ መስኖ ስንዴ ከፍተኛ እንቅስቃሴ ሲደረግ ቆይቷል ያሉት ዶክተር ዳንኤል፤ በጥር ወር ዘር የመዝራት ሥራው የተጠናቀቀ ቢሆንም ምርቱ እስከ አሁን ተሰብስቦ መጠናቀቅ ነበረበት። ነገር ግን የዘንድሮ የበልግ ዝናብ ከሌሎች ጊዜያት ጋር ሲነጻጸር ጠንካራና ከባድ በመሆኑ ምርቱን ሰብስቦ ማጠናቀቅ አልተቻለም ብለዋል።
እንደ አስተባባሪው ገለፃ፤ በዘንድሮ ዓመት በጋ መስኖ ስንዴ ዘጠኙም ክልሎች የተሳተፉ ሲሆን አብዛኞቹ ክልሎች ዘንድሮ ለመጀመሪያ ጊዜ የተሳተፉ ናቸው። ነገር ግን ለሥራው የነበራቸው ተነሳሽነትና ተሳትፎ ልምድ ካላቸው ክልሎች እኩል ነው። ክልሎች በዘንድሮ በጋ መስኖ ያደረጉት ተሳትፎ ካለፈው ዓመት ጋር ሲነፃጸር ጥሩና ጠንካራ ነው። በክልሎች አጠቃላይ የምርት አሰባሰብ ሥራው በዚህ ወር ተሰብስቦ ይጠናቀቃል ተብሎ ይጠበቃል።
በቀጣይ የምርት አሰባሰብ በሁሉም ክልሎች በተመሳሳይ ጊዜ እንዲሆን ይሰራል ያሉት ዶክተር ዳንኤል፤ በዘንድሮ ከግብዓት አቅርቦት እና ከመካናይዜሽን ጋር የነበሩ ችግሮችን ለመፍታት ከአሁን ጀምሮ የምንሰራ ይሆናል። በዘንድሮ የበጋ መስኖ ስንዴ የተገኙ ልምዶችና ተሞክሮዎችን በሚቀጥለው ዓመት ለማጠናከር አሁን ላይ የእቅድ ሥራዎች ለመስራት በዝግጅት ላይ ነን ብለዋል።
ሳሙኤል ወንደሰን
አዲስ ዘመን ሰኞ ግንቦት 14 ቀን 2015 ዓ.ም