ታደሰ መስፍን የሚለው ስም ሲጠራ ብዙዎች አያውቁት ይሆናል፤ መቼም ከአመድ ስር የተዳፈነን እሳት አመዱን እንጂ እሳቱን ማን ያያል…እሱም ልክ እንደዚሁ ነው። የእሳቱን ኃይል የሚያውቀው ቀርቦ የተመለከተው ብቻ ነው። ታደሰ መስፍን በኢትዮጵያ ታሪክ አገራችን ካፈራቻቸው ታላላቅ ሰአሊያን አንዱ ነው፡፡ የስእልን ጥበብ ከፊደላት እኩል በመቅሰም በረዥም የጥበብ ጉዞ የአገራችን የስነ ስእል እድገት ከፍ ማድረግ የቻለ ድንቅ ሰአሊና መምህርም ጭምር ነው። ለመሆኑ ይህ ሰው ከየት ተነስቶ የት ደረሰ፣ ለስነ ስእል ዘርፍና ለአገሩስ ምን አበረከተ..የሚሉት ሀሳቦች በዛሬው የዝነኞች ገፃችን በጥቂቱ እንመልከት፡፡
የወልዲያ ምድር ያበቀለችው ሰአሊ ታደሰ መስፍን የተወለደው 1945 ዓ.ም ነው። ስእልን በሚገባ በአይኑ ተመልክቶም ሆነ ሰምቶ የማያውቀው ትንሽ ልጅ ከብቶቹን ከመስኩ ላይ አሰማርቶ እሱ ግን መሬት ላይ የእንጨት ስባሪ እያነሳ በእጅና እግሩ አንዳች ነገር ይሞነጫጭራል። የሚሞነጫጭረው ምን እንደሆነ ባይረዳውም ለነገሩ ያለው የተለየ ስሜትና ፍቅር ግን እለት እለት እየጨመረ መጣ። ከልጅነት ጨዋታዎች ይልቅ በቀንም ሆነ ማታ ለእርሱ ትልቅ ደስታን የሚሰጠው ይሄው የሚሞነጫጭረው ነገር ነበር። በህይወታችን ውስጥ መሆንና ማድረግ ለምንፈልጋቸው ነገሮች ያለን ፍላጎትና ውስጣዊ ፍቅር እጃችንን ይዘው ወደዚያው የህልማችን የስኬት መንገድ እንደሚያደርሱን የሰአሊው የታደሰ መስፍን ህይወት ምስክር ነው።
ስእል የህይወት መንገድ መሪ ብርሃን መሆኗን ገና ልጅ ሳለ ልቡ ሹክ ብሎት ነበር። በጊዜውም የስእል ፍቅር የወለዳት የስእል ጥበብ ከምናቡ አልፋ ከልቡ ላይ ማቆጥቆጥ ጀመረች። ለፍቅሩ መግለጫ ያህል ሲሞነጫጭራቸው የነበሩት ስእሎቹም ወደ ጥበብ ማሳ ይዘውት ነጎዱ። ልጅ ሳለ ለስዕል ያለውን ልዩ ፍቅር ቢረዳውም ለመደበኛ ትምህርቱ ያለውን ነገርም ችላ ለማለት አይወድም ነበር። የስድስት ዓመት ልጅ የነበረው ታደሰ መስፍን ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ትምህርት ቤት ሄዶ ከፊደላት ጋር ትውውቅ የጀመረው በዚያው በተወለደባት ወልዲያ በእቴጌ ጣይቱ ብጡል ትምህርት ቤት ነበር። ነገር ግን በትምህርት ቤቱ ውስጥ ከአንድ መንፈቅ በላይ ቆይታ አልነበረውም። ምክንያቱ ደግሞ የጀመራትን የሕይወት ጉዞ በአዲስ አበባ ለማድረግ ወደ አጎቱ ዘንድ መጣ። በወልዲያ እቴጌ ጣይቱ ብጡል የጀመረውን ከፊደላት ጋር የነበረውን ትውውቅ በአዲስ አበባዋ የስዊዲሽ ሚሽን ትምህርት ቤት ቀጥሎ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቱን አጠናቀቀ። የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን ደግሞ በበዕደ ማርያም ት/ቤት አጠናቀቀ፡፡ በዚህ ወቅትም እረኛ በነበረበት የልጅነት ጊዜ በቀጫጭን እንጨት የጀመረው የስዕል ፍቅሩ፤ ፍቅር ብቻ ሆኖ ከመቅረት ወንዝ ተሻግሮ ከራሱ እኩል አድጎ ሶታ ጎረምሳ መስሎ ነበር። በበዕደ ማርያም ትምህርት ቤት ውስጥ ሳለም በትምህርት ቤቱ ለሚዘጋጀው መጽሔት የሽፋን ስዕል ማዘጋጀት ጀመረ። በስራውም በውስጡ የነበረውን የስዕል ፍቅሩንና ድንቅ ችሎታውን ማሳየት ችሏል። ከዚህ በኋላም ሰዓሊ ብቻ ሳይሆን ታላቅ ሰዓሊ የመሆን ህልም ከአይነ ህሊናው ላይ ከብሩህ ተስፋ ጋር ታየው። ህልሙን እውን ለማድረግና የስዕል ዓለም ጥበብና እውቀትን ለመቅሰም በ1960 ዓ/ም ወደ ሥነ ጥበብ ት/ቤት አቀና፡፡
ወደ ስዕል ትምህርት ቤቱ ከገባ በኋላ እጅግ በጣም የሚወደውን የስዕልን ጥበብ ብቻ ሳይሆን የሕይወት አስተማሪው ከሆነ ከአንድ ሰው ጋር ተገናኘ። ሰዓሊ ታደሰ መስፍን ጥበብን ለመሸመት ወደ ትምህርት ቤቱ ቅጥር ግቢ ሲገባ፣ በቅጥር ግቢው ውስጥ ያላቸውን በሙሉ ለተማሪዎቻቸው በመስጠት ጥበብን በማደል ላይ የነበሩት ሰው ደግሞ ታላቁ ሰዓሊ ገብረክርስቶስ ደስታ ነበሩ። ከእሳቸው በተጨማሪም ዲዛይነር ታደሰ ግዛውን ጨምሮ ሌሎች በሕይወቱ የማይረሳቸው ድንቅ አስተማሪዎች እንደነበሩትም ሰዓሊ ታደሰ መስፍን ይናገራል። በነበረው የትምህርት ቆይታ በትምህርት ቤቱ ውስጥ ካሉ ተማሪዎች ሁሉ የላቀ ውጤት በማስመዝገብ በማዕረግ ለመመረቅ ችሏል። ከተመረቀ ከአምስት ዓመታት በኋላ እጁን ይዞ ወደ ብሄራዊ ቲያትር ቤት የሚያስገባው አንድ እድል ወደ እሱ መጣ። በጊዜው የስዕል ትምህርት ቤቱ አንድ ሰዓሊ መርጦ እንዲልክለት የሚጠይቅ ደብዳቤ ከብሄራዊ ቲያትር ደረሰው። ታላቁ የስዕል ሰው ገብረ ክርስቶስ ደስታ ደብዳቤዋን ገልጠው ማንበብ ሲጀምሩ ወዲያው አዕምሯቸው ውስጥ የመጣው ሰው ከአምስት ዓመታት በፊት ተማሪያቸው የነበረው ታደሰ መስፍን ነበር።
ታደሰ ለዚህ ቦታ ትክክለኛው ሰው ስለመሆኑ አንዳችም ጥርጥር አልገባቸውም ነበር። ጊዜ ሳያባክኑም ወዲያውኑ ወጣቱ ሰዓሊ ወደ ብሄራዊ ቲያትር እንዲያቀና አደረጉት። የወጣቱ ሰዓሊ ድንቅ ብቃት የሚያውቁት ሰዓሊ ገብረክርስቶስ ደስታ ብቻ አልነበሩም። እርሱን ያስተማሩትም ሆኑ ስራዎቹን ለመመልከት የቻሉ በሙሉ ችሎታውን ይመሰክራሉ። በዚያን ዘመን ይሰራቸው የነበሩት የመድረክ ላይ ዲዛይኖች ዛሬ በዚህኛው የቴክኖሎጂ ዘመን እንኳን እንዳልተሰሩ ብዙዎች ይናገራሉ። ለስዕል ብቃቱ ወደር የሌለው ታደሰ መስፍን ለትምህርት ወደ ባህር ማዶ በመሻገር የጥበብ አድማሱን ለማስፋት ችሏል። የሁለተኛ ዲግሪውን ለመከታተል ወደ ራሽያ አገር ያቀና ሲሆን፣ በሴንት ፒተርስበርግ ከተማ በሚገኘው ሬፒን አካዳሚ ውስጥ ከተለያዩ አለማት ከመጡ ተማሪዎች ሁሉ የላቀ ብቃቱን ማሳየት ችሏል። ያሳየው ልዩ ብቃትም በአካዳሚው ዘንድ እንዲሁ ወደአገሩ እንዲመለስ አላደረገውምና ዩኒቨርሲቲው የክብር ሽልማትን አጎናጽፎ ወደአገሩ ሸኘው። ይህም በአካዳሚው ታሪክ ከሌላ አገር መጥቶ የተሸለመ የመጀመሪያው ሰው አድርጎታል።
ሰአሊ ታደሰ መስፍን ወደአገሩ ከተመለሰ በኋላ በቀጥታ ያቀናው ወደ አዲስ አበባ የስእልና ስነ ጥበብ ትምህርት ቤት ነበር። የመጀመሪያ እቅዱ የነበረውም በውጭ አገር በነበረው ቆይታ ቀስሞ በመጣው እውቀት መሰረት በትምህርት ቤቱ ውስጥ ያለውን የስእል ንድፍ በተሻለና ዘመናዊ በሆነ መንገድ መቀይስ ነበር። በወቅቱ ከዚህ አላማው ጎን በመቆም ሲደግፉትና ሲያግዙት የነበሩትን አንጋፋውን ሰአሊ ጥሩነህ እሸቱን በመያዝ ትምህርት ቤቱ ለስኬት እንዲበቃ አድርጎታል። የኢትዮጵያን የስእል ጥበብ በመላው ዓለም ተቀባይነት እንዲኖረው ሌት ተቀን ያላለሰለ ጥረትና በውጣውረዶች የተሞላ የትግል ጉዞ አድርጓል። ለበርካታ ዓመታት ቆይታውን በስእል ትምህርት ቤቱ ያደረገ ቢሆንም የእርሱ የስእል ጥበብ የወለዳቸው እንቁ ስራዎቹ ግን በመላው የኢትዮጵያ ትልቅ አገራዊ ቅርስ ለመሆን በቅተዋል።
በደርግ ዘመነ መንግስት በተለያየ ሙያ ውስጥ ያሉ ሰዎች ለብሄራዊ ግዴታ በሚል ዜጎች ባላቸው ሙያ አገራቸውንና ህዝባቸውን ለተወሰኑ ጊዜያት ያለምንም ክፍያ ያገለግሉ እንደነበር ይታወቃል፡፡ ሰአሊው ታደሰ መስፍንም በዚህ ግዳጅ ወቅት ለአገሩ የሰራቸውን ስራዎች እንኳንስ ሌላው የደርግ መንግስት እራሱ የተረዳው አይመስልም። ስፍር ቁጥር የሌላቸው ፖስተሮችንና ሥዕሎችን በመስራት፣ የሶሻሊስት ኢትዮጵያ ዓርማን በመቅረፅ፣ ለታላቁ የሕዝብ ለሕዝብ ትዕይንት የሚሆኑ የመድረክ እና የአልባሳት ዲዛይን ደረጃውን በጠበቀ መልኩ በማዘጋጀት በርካታ ስራዎች ያቀረበ ቢሆንም በግዳጁ ሰበብና በተለያዩ ምክንያቶች አንዳችም ሳይከፈለው በነጻ ሰርቷል። ሌላው ከሰራቸው ትልልቅ ስራዎች መሃከል ደግሞ አንደኛው የአገራችን የመገበያያ ሳንቲሞች (25 ሳንቲም እና 50 ሳንቲም) ላይ የራሱን ሙያዊ አስተዋጽኦ ማድረጉ ነው። ሙያዊ አስተዋጽዖን ሲጠየቅ ወደ ኋላ ብሎ የማያውቀው ሰዓሊው ከደርግ መንግሥት መውደቅ በኋላም በተለያዩ የመታሰቢያ ሥራዎች ላይ ሙያዊ ተሳትፎን አድርጓል፡፡ ከቅርብ ጊዜ ሥራዎቹ ውስጥም ትግራይ ላይ ያለውን የሰማዕታት ሐውልት የመጀመሪያውን ንድፍ ያጠናና የፈጠረ እንዲሁም በአማራ የሰማዕታት ሐውልት ሥራ ላይ ያበረከተው የበዛ አስተዋጽኦ ከምንም በላይ ለአገሩ ያለውን ቅን ፍቅር ያሳያል። ገና በወጣትነቱ በስእል ትምህርት ቤቱ ውስጥ ላሳየው ድንቅ ብቃትና ላስመዘገበው ከፍተኛ ውጤት በቀዳማዊ ሐይለ ሥላሴ እጅ የሰዓት ሽልማት ተበርክቶለታል። በኢትዮጵያ የስነ ጥበብና የመገናኛ ብዙኀን ሽልማት ላይ ደግሞ በምርጥ ሰአሊ ዘርፍ ተሸላሚ ለመሆን ችሏል። ምንም እንኳን እነዚህንና ሌሎች በርካታ ሽልማቶችን ቢያገኝም ከሰራቸው ስራዎች አንጻር ግን እዚህ ግባ የሚባሉ አይደሉም። ሌላው ቀርቶ ብዙ የለፋበት የአዲስ አበባ የስነ ጥበብ ትምህርት ቤት ለዚህ ጀግና በቂ እውቅና አለመስጠቱ በእጅጉ የሚያሳዝን ነው።
ይህን የአገር ኩራት የጥበብ ሰው ቀርቦ የተመለከተው ስለእርሱ ሳያነሳና ሳያመሰግን አያልፍም። ስለ ሰአሊ ታደሰ አበክረው ከሚያውቁ ሰዎች መሃከልም አንደኛው አብረውት ብዙ ላይ ታች ያሉት አንጋፋው ሰዓሊ እሸቱ ጥሩነህ ሲናገሩም “እንደ ታደሰ መስፍን ዓይነት ሠዓሊ በዘመናት ውስጥ አንድ ሁለት ሰው ነው የሚታየው” በማለት አድናቆታቸውን ችረውታል፡፡ የታደሰን ብቃት የሚያህል የዕውቀትና የጥበብ ሰው እንደሌለ የሚናገሩት ሰዓሊ እሸቱ ከኢትዮጵያ አልፎ አፍሪካን የሚያስጠራ ነው ሲሉ ይገልጹታል። ሌላው ስለ ሰአሊ ታደሰ መስፍን የተናገረው የማይጠግቡትና በተለያየ ጊዜ ተማሪዎቹ የነበሩ የጥበብ ልጆቹ ደግሞ እርሱ የምን ጊዜም ምርጥ መምህራቸው ስለመሆኑ በአንደበታቸው ይመሰክሩለታል። ከልጅነት እውቀት እስከ ሽበት፣ በስነ ጥበብ የስእል መንገድ የተጋዘው ሰአሊ ታደሰ መስፍን።
ሙሉጌታ ብርሃኑ
አዲስ ዘመን ግንቦት 13/2015