አንዱ በሌላው ላይ፣ ወገን በወገኑ ላይ ፈጸመ የሚባለውን ጉድና ደባ ሰምቶ ዝም ማለት አልሆንላት ብሎ፤ እውነቷን ነው ማንስ ቢሆን እንዴት ዝም ይላል። ተለጉመው የነበሩ የስሜት ሕዋሳት ነጻነት በተቀዳጁበት ዘመን ላይ ነው የምንገኘዋ። ‹‹የማሰብ ነጻነት፣ የመናገር ነጻነት፣ የመሰብሰብ ነጻነት፣ የመጻፍ ነጻነት….ወዘተ›› አንደኛ ዓመት ክብረ በዓል ብንለውስ?
እንደው ማን ይሙት! ልብ ብሎ ለተመለከተን ‹‹ከገመዱ አፈትልኮ የወጣ እንቦሳ›› መስለን አርፈነዋልሳ። በጨዋ ወግና ባህል ተኮትኩቶ ያደገ ኢትዮጵያዊ ሲናገርም ልክ አለው፤ ሲጽፍም ልክ አለው፤ ሲጠላም ልክ አለው፤ ኧረ ሲወድም ልክ አለው። እንዲህ እንደ አሁኑ ልካችን ልኩን ከማጣቱ በፊት ለሁሉም ነገር ከልክ በታች ነበረ አይደል እንዴ?
‹‹አንድ ሰው ነጻነት በሰጠኸው ቁጥር የበለጠ ኃላፊነት በትከሻው እንዳረፈ ይሰማዋል›› ብሎ የተናገረው ምሁር፣ ፈላስፋ፣ ተመራማሪ፣ ሳይንቲስት ማን ነበር? ብዬ ቀና አልኩና ከቅርብ ጓደኛዬ ምስክርነት ተማጸንኩ። እሱም ‹‹ባውቀው ምን አስደበቀኝ ብሎኝ እርፍ!›› ከት ከት ከት ብዬ ሳቅኩኝ።
ትናንት የፕሬስ ነጻነትን ልክ ለማስረዘም ረጅም መዘዝ በራሳቸው ላይ ያስከተሉ ሰዎች ቁጥራቸው ቀላል አይደለም። ዛሬ ያስረዘሙትን ነጻነት ወርዱ ከቁመቱ ተስተካክሎ በልክ እንድናምርበት የማድረጉ ኃላፊነት ከእነሱ በላይ ባለቤት የት ይመጣለታል። ካልተመጠነ ለሌላው እንቅፋት መሆኑ የት ይቀራል። እያንዳንዱ ነገር ልክ ከሌለው ለእልክ ይዳርጋል ይላሉ አባቶች ሲመክሩ።
መቼም ‹‹ወሬን ወሬ ያነሳዋልና›› የድሮው ፐብሊክ ሰርቪስና የሰው ሀብት ልማት ሚኒስቴር በሕይወት እያለ ‹‹መብትና ግዴታውን ጠንቅቆ የተረዳ፣ የሕዝብ አገልጋይነት መንፈስ መላበስ›› የሚሉ ነገሮች መለጣጠፍ ያበዛ ነበር። እንደው በጥናት የተረጋገጠ ባይሆንም በርካታ ሰዎች ‹‹የአገልጋይነት ሳይሆን የአጎብዳጅነት መንፈስን የተላበሰ›› ሰራተኛ ነው የተፈጠረው ሲሉ ይደመጣሉ።
ለዚህ መገለጫው ‹‹መረጃ የማግኘት መብት››ን ብቻ ማየቱ በቂ ማሳያ ነው ይላሉ። ሠራተኛው በራሱ ተማምኖ ሙያው የሆነውን ጉዳይ እንኳን መረጃ ሊሰጥህ አይደፍርም። በሥራው ተማምኖ ከመኖር ይልቅ አጎብድዶ መኖር ጥቅም እንደሚያስገኝ ይነገራል። ስለዚህ ‹‹የአገልጋይነት መንፈስ ተላብሷል›› ሳይሆን ‹‹ክፉ መንፈስ ተዋርሷል›› ቢባል የተሻለ ይሆናል። ያው እንደልብ መተንፈስ ተችሏል፤ በተነፈሱት ልክ ያውም በልጥ አድርጎ ማስተንፈስም ቀርቷል ብዬ ነው የተነፈስኩላችሁ። አለበለዚያማ የተነፈሱትን ትንፋሽ ያስቆጥር ነበር ያ የትናንቱ ክፉ ቀን።
እርግጥ ነው ዶክተሩ የመረጃን ዋጋ አሳምረው ያውቃሉ። መረጃ የመሸጥ ጥበብንም ተክነውበታል። በመረጃ ነጻነት ግኡዝ አካሉ ውስጥም ነፍስ ሊዘሩበት እየጣሩ ነው። ከሥልጣን ዕድሜያቸው አኳያ የመገናኛ ብዙኃንና የመረጃ ነጻነትን ከቀብር አፋፍ ታድገውታል። ቁርጠኝነታቸውን አለማድነቅ አይቻልምና።
ትናንት ሐሳብ በማፍለቃቸው፣ በመጻ ፋቸው፣ በመናገራቸው ለመከራ የተዳረጉ ወጣቶችና ጋዜጠኞች ብዙ ናቸው። ዛሬ በማጎሪያ ቤት የሉም። የተለየ ሐሳብ ይዞ መምጣት የሚያኮራ እንጂ የሚያሳፍር፣ የሚያሳስር መሆኑ ያከተመ ይመስላል።
ዓለም እኛን የሚመለከትበት የተንሸዋረረ ዓይን ወደ መስተካከል ተጠግቷል። ይልቁ ንስ እኛ ራሳችንን የምናይበት ዓይን፣ እኛ ዜጎቻችንን የምንመዝንበት ሚዛን፣ የምናቀ ርብበት የሜትር ልክ መስተካከል ተስኖት እንደተንጋደደ ይሄው እያገዳደለ ቀጥሏል።
የነጻነት ልኩን ማወቅ ተስኖን፣ የመናገር ወሰኑ ጠፍቶን ይሄው እርስ በርሳችን የሰላማችን ፀር ሆነናል። ገዳይ ወንድም፣ ሟች ወንድም፣ አፈናቃይ ወንድም፣ ተፈናቃይ ወንድም ሆኖ ቀጥሏል። ዕድሜ ለሚዲያ ነጻነት እንጂ የቀረርቶ፣ የፉከራና የሽለላ ጫካው በእጃችን ላይ ሆኗል፤ ፌስቡክ።
ኢትዮጵያ ለረጅም ዘመናት ስሟን ጥላሸት ሲቀቡ የነበሩ ድርጊቶቿ በአንድ ዓመት ከስመዋል። በሰብዓዊ መብት አያያዝ፣ በሐሳብ ብዝሃነት ማስተናገድ፣ በሚዲያ ነጻነት አጠባበቅ ከፍተኛ ለውጥ መታየታቸውን አሁን ላይ መስካሪዎቹ እኛ አይደለንም። ሌሎቹን ለማሳመን የተመናመነ የሃሳብ ጥይት ከመፈለግ ተገላግለናል።
ስለ እኛ የሰብዓዊ መብት አያያዛችን ላይ ‹‹እትፍ እትፍ ይልመድባችሁ›› የሚሉ መስካሪዎች ፍለጋ ከጫፍ ጫፍ መኳተንና ማሰልጠን ቀርቷል። አልሆን ሲልም ረብጣ ገንዘብ ለእጅ መንሻ በቀዳዳ ልኮ አፍ ማዘጋት ዛሬ የለም፤ አንዳንድ ያልጠራ ሁኔታ ግን ሊኖር ይችላል። ሆሆይ ጉድ እኮ ነው። አልሰማንም እንዳትሉ! ለሥራ ከምናውለው ገንዘብ በላይ ቆሻሻ አመላችንን አለያም ገመናችንን ለመሸፈን እንከፍል እንደነበር ከውስጥ አዋቂዎች ውስጡን ጠይቁ። እኛ ተንፍሰናል።
የመገናኛ ብዙኃን አቅም በማቆጥቆጥ ላይ ነው። በዘርፉ የሚሰማሩ የሚዲያ ሰዎች በሙያዊ ሥነምግባር እንጂ በፖለቲካ ርዕዮት ዓለም የተሞረዱ መሆናቸው ታሪክ ሊሆኑ እየተቃረበ ይመስላል። የሚዲያ ተቋማት መጡልን እንጂ መጡብን በሚል መብቀላቸውን ለማክሰም በጎሪጥ የሚመለከት ባለሥልጣን የለም። ተወዳዳሪነት እንጂ አቋራጭ እርምጃዎች መጥበብ ጀምረዋል። የመንግሥትን ካዝና በማለብ ዕድሜያቸውን የሚያራዝሙ የግል ሚዲያ ጣቢያዎች ልሳናቸው (ደማቸው) ደርቋል። ሕዝብን ረስቶ የፓርቲን እስትንፋስ እየተከተሉ ማላዘን አሁን ላይ ሳንቲም አለመውለድ ላይ ለመድረስ እየተጠጉ ይመስላል።
የሚዲያው ባለቤት ባለሥልጣን፣ ጋዜጠኛው ወፍዘራሽ አለያም የእህት ልጅ፣ ፈቃድ ሰጪው አጎት፣ ሸላሚው የሚስት ወንድም፣ የገንዘብ ምንጭ (ስፖንሰር) መንግሥት፣ ዋና ሥራ አስኪያጅ ሚስት ሆነው በሕዝብ ላብ ጅምላ ንግድ አሁን አይሰራ ይሆናል፤ ይህ በሩ እየጠበበ ነው።
ዓለም አቀፍ ሚዲያዎች ስለህጸጻችን ምን ያወሩብን ይሆን? ምን ይናገሩብን ይሆን? እያሉ መርበትበት ታሪክ ሊሆን ተቃርቧል። ይልቁንስ የእኛ ሚዲያዎች አቀንቃኝ እነሱ አስወንጫፊ ሆነው አብረው በመዘመር ላይ ናቸው። ኢትዮጵያ እንዲህ የዓለምን ቀልብ ስባ የታየችበት አጋጣሚ ምናልባትም ከአድዋ ድል ቀጥሎ ሁለተኛው ሳይሆን አይቀርም።
የሰብዓዊ መብት ተቆርቋሪዎች፣ የዓለም ጋዜጠኞች መብት ተሟጋቾች፣ አክቲቪስቶችና የዓለም ሚዲዎች በኢትዮጵያ መዲና በቅርቡ ይከትማሉ። እንደከዚህ በፊቱ የክስ አቤቱታ ለማሰማት አይምሰላችሁ።ልምድ ለመቅሰም እንጂ። የለውጡ የአንድ ዓመት ፍሬ የሩብ ምዕተ ዓመት ስብራትን መጠገን ችሏል።
ኢትዮጵያ የመገናኛ ብዙሃንና የመረጃ ነጻነት የዓለም የፕሬስ ቀን የዘንድሮ ተሞሻሪ ናት።ከዚህ በፊት በዘርፉ ደረጃ ደልዳዮች ከነበረችበት 150ኛ ደረጃ በአንድ ዓመት ውስጥ 40 ደረጃዎችን ማሻሻል ችላለች። እሰይ ሀገሬ።
በዚህ ብቻ የሚወሰን አይምሰላችሁ። እየተውተረተረ ያለው የሚዲያዎቻችን አቅም መለወጥ ይኖርበታል። ጋዜጠኞቻችን ለሙያው ሥነምግባርና ለእውነት የሚቆሙ ብሎም ለህዝብ ጥቅም የሚፋለሙ ሊሆኑ ይገባል።
ከግል ሚዲያ ተቋማት እስከ ሕዝብ ሚዲያዎች በጥቅም ትስስር የግለሰቦችን ሥም ለማጥፋት ዘመቻ ይውላሉ የሚሉ አሉባልታዎች ቢነሱም ከአሉባልታ አይዘሉም። በአጠቃላይ የፕሬስ ነጻነቱን በደስታ ስናከብር በምንጠቀምባቸው ሚዲያዎች በኩል የጥላቻ ንግግርን ከማስተላለፍ ብንቆጠብ ከእኛነታችን የሚቀነስ ነገር ይኖር ይሆን? ሁሉም ነገር ትናንትን ስቦ የእኛ ነገር አጃኢብ እንዳያሰኝ ስጋት አለኝ። ምክንያቱም ‹‹ሲለጉሙን እዳ ሲፈቱንም እዳ፣ ተቻችሎ መኖር አሁን ማንን ጎዳ›› እንዳለችው ሴትዮ እንዳይሆንብን ነዋ።
አዲስ ዘመን ሚየዝያ 24/2011
ሙሐመድ ሁሴን