
በፓሪስ 2024 ኦሊምፒክ የወንዶች 3ሺህ ሜትር መሰናክል የፍፃሜ ውድድር ላይ የተፈጠረውን አስደንጋጭ ክስተት ዓለም አይረሳውም፣ በተለይም ኢትዮጵያውያን። በዚያ ውድድር የወርቅ ሜዳሊያውን ለማጥለቅ ትልቅ እድል የነበረው የርቀቱ የዓለም ክብረወሰን ባለቤት አትሌት ለሜቻ ግርማ ፉክክሩን በድል ሊቋጭ ጥቂት ሜትሮች ሲቀሩት ተስፈንጥሮ ሲወጣ የመሰናክሉ አግዳሚ አደናቅፎት ወደቀ። በዚያ ቅፅበት የስፖርት ቤተሰቡ ለሜቻ የወርቅ ሜዳሊያ ከማጣቱ የበለጠ የወደቀበት አደገኛ ሁኔታ ለደህንነቱ እንዲጨነቅ አድርጎታል።
ወጣቱ ኮከብ በወደቀበት ራሱን ስቶ ወደ ሆስፒታል ከተወሰደ በኋላ የደረሰበት ጉዳት ቀላል ባይሆንም እንደማያሰጋው ተነግሯል። ይሁን እንጂ ለሜቻ ከዚያ መጥፎ አጋጣሚ በኋላ በአጭር ጊዜ አገግሞ ወደ ውድድር አልተመለሰም። አሁንም ድረስ በውድድሮች ላይ መታየት አልቻለም። ለዚህም ብዙዎች ከጥቂት ወራት በፊት መሞሸሩን ምክንያት ሊሆን እንደሚችል ገምተው ነበር። ያም ሆኖ ከሁለት ሳምንት በፊት በተጀመረው የ2025 የዳይመንድ ሊግ ውድድሮች ይታያል ተብሎ ተጠብቆ ሲጠበቅ አለመታየቱ “ወጣቱ ኮከብ በደህናው ነው?” በማለት የአትሌቲክስ አፍቃሪው መጠየቁ አልቀረም።
ለሜቻ ባለፉት የተወሰኑ ወራት በልምምድ ላይ ቆይቷል። ከዘጠኝ ወራት በኋላም ግን በኦሊምፒኩ ፍፃሜ ላይ በመውደቁ ከደረሰበት አካላዊ ግጭት ቢያገግምም ሌላ ፈተና እንደገጠመውና ከዚያም ፈተና ጋር እየታገለ በቅርቡ ወደ ውድድር ለመመለስ ጥረት እያደረገ እንደሚገኝ እውቁ የአትሌቲክስ ድረ-ገፅ LetsRun.com የአትሌቱን ወኪል ሁሴን ማኪን አነጋግሮ ያወጣው ሰፊ ዘገባ ጠቁሟል።
አንድ አደጋ የገጠመው ሰው በአካሉ ላይ የደረሰው ጉዳት ካገገመ በኋላ ዳግም ተመሳሳይ አደጋ ይገጥመኛል የሚል ሃሳብ ወይም ስጋት በአዕምሮው ሊመላለስና ፍርሃት የሚፈጥርበት የሥነልቦና ችግር ሊገጥመው ይችላል። ለሜቻም የገጠመው ተመሳሳይ ችግር ነው። ያምሆኖ ወጣቱ የመሰናክል ፈርጥ ከዚህ የሥነልቦና ፈተና ጋር እየታገለም ቢሆን በዚህ ወር ወደ ውድድር ለመመለስ እየተዘጋጀ እንደሚገኝም ዘገባው ጠቁሟል።
እንደ ወኪሉ ሁሴን ማኪ ገለፃ፣ ለሜቻ በኦሊምፒኩ ፍፃሜ ላይ የገጠመው የመውደቅ አደጋ ከሩቅ ከሚታየው የበለጠ ከባድ ነበር። የ24 ዓመቱ ድንቅ አትሌት ለሦስት ቀን በፓሪስ ህክምና ሲያገኝ ከቆየ በኋላ ተሽሎት ወደ አዲስ አበባ ቢመለስም ለማገገም ብዙ ጊዜ አስፈልጎታል። ለረጅም ጊዜም በተለያዩ የአውሮፓ ከተሞች በርካታ ዶክተሮችን ለመጎብኘት ተገዷል። በአጭር ጊዜ አገግሞ ወደ ልምምድ መመለስ ባለመቻሉም ከኦሊምፒኩ በኋላ የተለያዩ ውድድሮችን ለማድረግ ሳይችል ቀርቷል። ወደ ልምምድ የተመለሰው ከበርካታ ወራት በኋላ ባለፈው ጥር ላይ ነበር። በዚያው ወር በመሞሸሩ ምክንያትም ወደመደበኛ ልምምድ ለመመለስ ጊዜ አስፈልጎታል።
ለሜቻ አሁን ላይ በጥሩ ሁኔታና ብቃት ላይ ቢገኝም በሥነ ልቦናው ረገድ የገጠመው ችግር አልፍ አልፎ እንደሚያገረሽበት ወኪሉ ተናግሯል። አሁንም ድረስ በመውደቁ ምክንያት አዕምሮው ውስጥ ያ አደጋ ዳግም ይፈጠራል የሚል ከሥነልቦና ጋር የተያያዘ ስጋት ወይም ፍርሀት አለበት፣ ይህም በተለይም በልምምድ ወቅት በከፍተኛ ፍጥነት ላይ እያለ ይገጥመዋል።
“ልምምዱን በጥሩ ሁኔታ እየሠራ ይገኛል፣ ያምሆኖ አሁንም ድረስ በተወሰነ መልኩ ሥነልቦናው ወደቀድሞ አልተመለሰም፣ የራስ ምታት ስሜትና መሰል ነገሮች ይገጥሙታል” ያለው ወኪሉ ሁሴን ማኪ፣ በዚህም ምክንያት በአጭር ጊዜ ወደ ውድድር እንዳልተመለሰና በቻይና በተካሄዱት የውድድር ዓመቱ የመጀመሪያ ሁለት የዳይመንድ ሊግ ፉክክሮች መሳተፍ እንዳልቻለ አብራርቷል። ያም ሆኖ በዚህ ወር ወደ ውድድር እንዲመለስ እቅድ እንዳለ ጠቁሟል።
ለሜቻ በመሰናክል ውድድር በደረሰበት መጥፎ አጋጣሚና ከዚያ ጋር በተያያዘ ያለበት የሥነልቦና ችግር ምናልባትም ከዚህ በኋላ በመሰናክል ውድድር እንዳይቀጥልና ወደሌሎች ርቀቶች ፊቱን ሊያዞር ይችላል የሚሉ ስጋቶች አሉ። ለዚህ ግን ወኪሉ መልስ አለው። ለሜቻ ከመሰናክል ውድድሮች በስተቀር በሌሎች መሰናክል በሌላቸው ርቀቶች አሁንም ድንቅ ብቃት ያለው አትሌት መሆኑን የሚናገረው ሁሴን ማኪ፣ የኢትዮጵያ የ 1500 ሜትር ክብረወሰን በ3:29:51 በእጁ እንደሚገኝና፣ የ3 ሺህ ሜትር የቤት ውስጥ የዓለም ክብረወሰን በ7:23:81 ባለፈው የካቲት አሜሪካዊው አትሌት ግራንት ፊሸር እስኪያሻሽለው ድረስ የለሜቻ እንደነበረ አስታውሷል። በቀጣይ ግን በተለይም በዚህ የ2025 የውድድር ዓመት የለሜቻ ትኩረት 3ሺህ ሜትር መሰናክል ሆኖ እንደሚቀጥል አረጋግጧል።
“ስለገጠመው አደጋ ክብደት ሁላችንም ምስክር ነን፣ ይሁን እንጂ ለሜቻ አሁንም በአዕምሮው ጠንካራና ዝግጁ ነው፣ ከኦሊምፒኩ በፊት ወደነበረበት ጠንካራ ተፎካካሪነትና አሸናፊነት መመለስ ብቻ ነው ጊዜ የሚፈልገው፣ ለዚያም ነው ከመጀመሪያዎቹ የዳይመንድ ሊግ ውድድሮች ተሳትፎ የተቆጠበው፣ እቅዱም መቶ በመቶ ቀድሞ ወደነበረበት ሁኔታ ሲመለስ ለውድድር መቅረብ ነው”
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን ሰኞ ግንቦት 11 ቀን 2017 ዓ.ም