
በተለያዩ የዓለማችን ክለቦች አልፎ አልፎ ብቅ የሚሉ ትውልደ ኢትዮጵያውያን እግር ኳስ ተጫዋቾች ይገኛሉ። ከነዚህ መካከል ሰሞኑን በአውሮፓ ኮንፍረንስሊግ የግማሽ ፍፃሜ ጨዋታዎች ላይ የታየው የ18 ዓመቱ ይሳቅ ዓለማየሁ አንዱ ሆኗል። ወጣቱ ትውልደ ኢትዮጵያዊ ከሳምንት በፊት በአውሮፓ ኮንፍረንስ ሊግ ቼልሲ ላይ ግብ ካስቆጠረ በኋላ በበርካታ ኢትዮጵያውን ዘንድ መነጋገሪያ ሆኖ ይገኛል።
በርካታ ኢትዮጵያውያን የእግር ኳስ አፍቃሪዎችም ይህ ወጣት ተጫዋች የዋልያዎቹ ስብስብ አካል እንዲሆን ፍላጎታቸውን በተለያየ መንገድ ሲገልፁ ተስተውሏል። ለመሆኑ ይሳቅ ዓለማየሁ ማነው?
ይሳቅ ከኢትዮጵያዊው አባት አቶ አያሌው ዓለማየሁ እና ከኤልሳልቫዶራዊት እናት በተወለደበት ስዊድን ሀገር ከ5 ዓመቱ ጀምሮ በእግር ኳስ አካዳሚ ዘመናዊ ስልጠና እየተከታተለ ነው ያደገው። የአማካይ ስፍራ ተጫዋቹ ይሳቅ በታዳጊነቱ ለኒውካስትል ዩናይትድ አስደናቂ ብቃቱን እያሳየ የሚገኘውና የታላላቅ ክለቦች ቀልብ ያረፈበት ትውልደ ኤርትራዊው አሌክሳንድር ይሳክ ባደገበት በኤ አይ ኬ እግር ኳስ ክለብ ሰልጥኗል። እ.ኤ.አ. ከ2019 ጀምሮ እስከ አሁን በስዊድን ዋናው ኦልስቨንስካን ሊግ በሚሳተፈው ዩርጎደንስ ክለብ በአማካይ ስፍራ እየተጫወተም ይገኛል።
ይሳቅ በውሰት በኔዘርላንዱ ፌይኖርድ ክለብ በቆየበት ወቅት በቀድሞ የማንቸስተር ዩናይትድ እና አርሰናል ኮከብ ሮበን ቫን ፐርሲ አንዲሁም ለጥቂት ቀናትም በአሁኑ የሊቨርፑል አሰልጣኝ አርን ስሎት የመሰልጠን እድል ማግኘቱን አባቱ አቶ አያሌው ዓለማየሁ ከ ኤ.ኤም. ኤን (AMN) ጋር በነበራቸው የስልክ ቆይታ ተናግረዋል።
ይሳቅ ዓለማየሁ ምንም እንኳን ውልደትና እድገቱ ስዊድን ቢሆንም ለኢትዮጵያ የተለየ ስሜት እንዳለውና በአንድ አጋጣሚ ወደ ኢትዮጵያ መጥቶ እንደነበረ ወላጅ አባቱ ገልፀዋል። ልጃቸው እንደርሳቸው ሁሉ የወላይታ ድቻ ደጋፊ እንደሆነ የሚናገሩት አቶ አያሌው ከ15 ዓመቱ ጀምሮ ለስዊድን ታደጊ ብሄራዊ ቡድን እየተጫወተ እንደሚገኝ ጠቁመዋል። ነገር ግን የእናቱ ሀገር ኤልሳልቫዶርም ይሳቅ ለብሄራዊ ቡድናቸው እንዲጫወት መከታተል ከጀመሩ አምስት ዓመት ሆኗቸዋል ብለዋል።
ኢትዮጵያውያን በእግር ኳስ ብቃት እንዳላቸው በርካታ ባለ ተሰጥኦ ተጫዋቾችም በስዊድን ሊግ ላይ እየተጫወቱ እንደሚገኙ የሚናገሩት አቶ አያሌው፣ እነዚህን ታዳጊዎች ከልጅነታቸው ጀምሮ መከታተል ያስፈልጋል በማለት ምክራቸውን ሰጥተዋል።
የዘር ሀረጉ ከኤርትራ የሚመዘዘውን የአሌክሳንደር ይሳቅን እድገት በቅርበት የተመለከቱት አባት የአውሮፓ ሀገራት ወደ ምስራቅ አፍሪካ አይናቸውን እንዲያዞሩ በታዳጊዎቹ ላይ ክትትል ማድረግ ያስፈልጋልም ብለዋል። በ15 ዓመታቸው ከኢትዮጵያ መውጣታቸውን የገለጹት አቶ አያሌው የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ጨዋታን ከልጃቸው ጋር በመሆን እንደሚከታተሉም ተናግረዋል።
አባትና ልጅ በየትኛውም አጋጣሚ ለኢትዮጵያ መልካም ምኞታቸውን ከመግለጽ አይቆጠቡም። ልጃቸው ውጤታማ እንዲሆን ከአጠገቡ የማይጠፉት አባት ባለፈው ሐሙስ በኮንፍረንስ ሊግ ግማሽ ፍፃሜ የመልስ ጨዋታ ዩርጎደንስ ቼልሲን ሲገጥም በስታንፎርድ ብሪጅ የሰማያዊዎቹ ስታዲየም ተገኝተው ልጃቸውን አበረታተዋል።
ይሳቅ ለአባቱ ሀገር ኢትዮጵያም ይሁን ለእናቱ ሀገር ኤልሳልቫዶር እንዲሁም ተወልዶ ላደገባት ስዊድን ዋና ብሔራዊ ቡድን የመጫወት እድል አለው። ለየትኛው ሀገር ዋና ብሔራዊ ቡድን ይጫወታል የሚለውን ጉዳይ ግን አሁን ላይ መናገር ከባድ እንደሆነ አባቱ ገልፀዋል። ይሳቅ ዓማየሁ ለስዊድን ታዳጊ ብሄራዊ ቡድን እየተጫወተ ቢሆንም በቀጣይ የእግር ኳስ ሕይወቱን በተመለከተ እራሱ የሚወስን ይሆናልም ብለዋል።
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን እሁድ ግንቦት 10 ቀን 2017 ዓ.ም