ቀለማት እና ፋሽን

የሰው ልጅ የመኖሩን ትርጉም የሚገልጥበት ልዩ ጥበብን የታደለ ፍጡር ነው። በዚህ ጥበቡም ደስታውን ያገኛል። ከእነዚህ መካከል ደግሞ የፋሽን አልባሳት ዲዛይንና ቀለማት አንዱ ነው። ለመሆኑ የፋሽን አልባሳትና ቀለማት ትስስር በሰው ልጆች ሕይወት ውስጥ በምን መልኩ ይገለፅ ይሆን?

ፋሽንን ከውበት፣ ውበትን ከዘመን፣ ዘመንን ከጥበብ ስናዋህድ በነዚህ ሁሉ መካከል ቀለማት የአንበሳውን ድርሻ ይይዛሉ። ፈጣሪ ታላቁን የሰውን ልጅ ከአፈርና ውሃ ካበጀ በኋላ ሰው እንዲሆን ያደረገበት ጥበብ እስትንፋስ ነው። ወደ ፋሽን ጥበብ ስንመጣም የፋሽን ጥበበኛ እጆች ጨርቁን ከዲዛይኑ አጣምረው ከሠሩት በኋላ ፋሽኑን በቀለማት ነብስ ካልዘሩበት፣ ፈጠራቸው ሰውነትን ከመሸፈንና ብርድን ከመከላከል በዘለለ በዘመንና ፋሽን የውበት ማህደር ውስጥ ዋጋ አይኖራቸውም። ይህ ማለት ጣፋጭ ኬክ አዘጋጅተን ክሬሙን ሽሮ ወጥ እንደማድረግ ነው። በፋሽን ዲዛይን ውስጥ ውበትን ለመፍጠር የቀለማትን ሚስጥርና ትክክለኛ ቦታ ለይተን ማወቅ አለብን።

በዘመናዊ ፋሽን ውስጥ ቀዳሚው ነገር እይታን መሳብ ነው። በመጀመሪያ እናያለን፣ ያየነውንም እንወዳለን፣ የወደድነውንም ምርጫችን እናደርገዋለን። ገና በመጀመሪያው እይታ ቀለማት ምርጫችንን እንድንወስን የማድረግ አቅም አላቸው። በእርግጥ ውበት እንደምርጫ ነው። አንዱ የወደደውን ሌላኛው ሊጠላው፣ ያደነቀውንም ሊያንቋሽሸው ይችላል። ውበትና ፋሽን እንደምርጫችን ቢሆንም፣ በምርጫችን ውስጥ አስገዳጅ የሆኑ መመዘኛዎች አሉ። እነዚህም ባህል፣ ወግ ልማድ፣ ሃይማኖትና ያደግንበት ማህበረሰብ ናቸው።

ቀለማት ከሥነ-ውበትና ከግለሰባዊ ምርጫ ሰፋ ባለ መልኩ በባህልና እምነት እንዲሁም ሀገራት ውስጥ ልዩ ቦታና ትኩረት ይሰጣቸዋል። በሳይንሱ የሚታወቁት ቀለማትን ሀገራት ከራሳቸው ባህላዊና ሥነልቦናዊ ሁኔታ በመነሳት የሚሰጡት ትርጓሜ አላቸው። በአብዛኛው ማለት በሚቻል መልኩ በዓለም አቀፍ ደረጃ ቀለማት የሚከተለውን ትርጓሜ እንደአግባብነቱ እንዲይዙ ተደርገዋል። በዚህ መሠረትም ጥቂቶቹን ብንመለከት ቀይ ቀለም ፡- ጥልቅ ስሜት፣ ፍቅር፣ ቁጣ… ብርቱካናማ ጉልበት፣ ደስታ፣ ሕይወት… ቢጫ ፡- ደስታ፣ ተስፋ፣ ማታለል… አረንጓዴ፡- አዲስ ጅምር፣ የተትረፈረፈ፣ ተፈጥሮ… ሰማያዊ፡- ረጋ ያለ፣ ሃላፊነት፣ ኀዘን… ሐምራዊ፡- ፈጠራ፣ ንጉሣዊ፣ ሀብት… ጥቁር፡- ምስጢር፣ ውበት፣ ክፋት… ግራጫ፡- ተለዋዋጭ ስሜት፣ ወግ አጥባቂ፣ መደበኛነት… ነጭ፡- ጥሩነት፣ ንጽህና፣ በጎነት… ቡናማ። ተፈጥሮ፣ ጤናማነት፣ ጥገኛነት…የሚሉ ትርጓሜዎችን ይይዛሉ። የተዋጣለት የፋሽን ዲዛይን ለመሥራት ስናስብም አስቀድመን፣ ሥራችንን የምናቀርብለት ማህበረሰብ በየትኛው የትርጓሜ መደብ ውስጥ እንዳለ ማጤን አለብን።

ፋሽን እንደ ዘመኑና እንደ ሁኔታው ሊቀያየር ይችላል። በፋሽን ውስጥ ያሉት ቀለማት ግን ሁልጊዜ ከሰው ልጆች ሥብዕናና ማንነት ጋር ተያያዥነት አላቸው። ድምጽ አልባ መሣሪያ እንደመሆናቸውም ቃላት የማይገልጹትን እልፍ ትርጓሜዎች ይዘው ይገኛሉ። በሀገራችን ታሪክ ውስጥም በሃይማኖታዊም ሆነ ባህላዊ እሴቶች ውስጥ ቀለማት ሚስጢራዊ ይዘት እንዳላቸው እንመለከታለን። በደስታ ጊዜ የብሩህነት መገለጫ የሆነውን ነጭና በተለያየ ቀለማት ያሸበረቀውን ጥለት፣ እንዲሁም ጎላ ብለው የሚታዩ የቢጫ፣ ቀይና አረንጓዴ አልባሳት ይዘወተራሉ። በኀዘን ጊዜያት ደግሞ ደብዘዝ ብለው የሚታዩ ልብሶችን በተለይ ጥቁር ቀለም እንጠቀማለን። ታዲያ አንድ አባቱ ወይም እናቱ የሞተበት ሰው ከቀብር መልስ እቤቱ ገብቶ ነጭ በነጭ ለብሶ ቢወጣ ማህበረሰቡ የሚረዳው ይህ ሰው በአባቱ ወይም በእናቱ ሞት ደስተኛ መሆኑን ነው። ባህልና ሥርዓትን ከመጣሱ በተጨማሪ እንደ ጨካኝና አረመኔ አሊያም እንደ እብድ ሊቆጠር ይችላል። ይሄም ቀለማት በአንድ ማህበረሰብ ውስጥ ምን ያህል ዋጋ እንዳላቸው ያሳየናል።

በሃይማኖት ውስጥ ያለው የቀለም እይታና ትርጓሜ ደግሞ ከባህል የጠነከረ ነው። እያንዳንዱ የቀለም ጠብታ ልዩ ሚስጥራትን የያዘ ሆኖ እናገኘዋለን። የምንጠቀማቸው ቀለማት ራሳቸውን ችለው እንደ ፊደላት የሚነበቡ ናቸውና፣ ቀለማቱን በተገቢው ካላሰባጠርናቸው ፊደላቱ የተዘበራረቀ መጽሃፍ ጽፎ እንደማሳተም ይሆንብናል። በተመሳሳይ በፋሽኖች ውስጥም ጊዜና ሁኔታን ያላገናዘበ ቀለማትን የምንጠቀም ከሆነ የምናቀርብለት ማህበረሰብ ይህንን የመቀበል ፍላጎት አይኖረውም። ጊዜና ሁኔታዎችን ማገናዘበ በእጅጉ ወሳኝነት አላቸው። በአብዛኛው የምንከተላቸው የፋሽን ፈጠራዎች ውድቀት የሚጀምረው ከእነዚህ አንጻር ነው። የፈጠራዎቹ እድሜም በጣም አጭርና እንደ መብረቅ ብልጭታ ገና ሳይታዩ የሚከስሙ ይሆናሉ።

ፈላስፎች፣ ሳይንቲስቶች፣ የጥበብ ሰዎች እንዲሁም በርካታ የኬሚካል ምህንድስና ባለሙያዎች ስለ ቀለማት አፈጣጠርና ስብጥር በተለያዩ ጊዜያት ጥናትና ምርምር አካሂደዋል። ሁሉም የራሳቸውን መላምት ከመሰንዘር ውጭ ይሄ ነው የሚባል የቀለማትን ሥነ ልቦናዊ ቀመር የደረሰበት ግን የለም። በዓለማችን በቁጥር ከ10 ሚሊዮን በላይ ቀለማት እንዳሉ መረጃዎች የሚያሳዩ ሲሆን እያንዳንዳቸው አዎንታዊም ሆነ አሉታዊ ተጽዕኖ ማሳደር ይችላሉ። ለዚህም ነው የፋሽን ዲዛይነሮች አልባሳትን ዲዛይን በሚያደርጉበት ወቅት ከውበት አንፃር ብቻ ሳይሆን ከሥነ ልቦና ውቅርና ተፅዕኖ አንፃር የሚቃኙት። በእኛ በኢትዮጵያውያን ዘንድ ደግሞ ደማቅ ቀለማት ይፈራሉ። ደብዘዝ ያሉ ቀለማት ላይ ትኩረት እናደርጋለን። ለበዓላትና ለልዩ ልዩ ዝግጅቶች ካልሆነ በቀር ደማቅ ቀለማት ያስፈሩናል። ምቾት አይሰጡንም። አሁን አሁን ግን በከተሞች አካባቢ በተነሳው የፋሽን አብዮት ቀለማትን ደፍሮ የመጠቀምና በእነርሱ በተቃኙ አልባሳት የመዋብ ልምዱ ቀስ በቀስ እየዳበረ በመምጣቱ የባህል አብዮቱን እየቀሰቀሱት ነው።

ፋሽንና ቀለማት ነጠላ ፍቺ ሰጥተን እንደዚህ ናቸው ለማለት የማያስደፍሩ ጥልቅ የሆነ ይዘትና ሃሳብ ያላቸው አውደ ብዙ ቃላት ናቸው። በዚህ ጹሁፍ ውስጥ በብዛት ከአልባሳት አንጻር ቢገለጹም ቅሉ ተቀዝፈው የማያልቁ ውቅያኖስ፣ ተገልጠው የማያልቁ መጽሐፍት ናቸው። እኛም ጀመርነው እንጂ አልጨረስነውም።

በሙሉጌታ ብርሃኑ

አዲስ ዘመን ሰኞ ግንቦት 11 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You