ደበበ ሰይፉ፡-
በትን ያሻራህን ዘር፣
ይዘኸው እንዳትቀበር።
ብሏል። የዛሬው ርእሰ ጉዳያችንም ይኸው ነው።
እውቀትን ዲሞክራሲያዊ ማድረግ ዘመኑ ይዞት የመጣው አስገዳጅ ተግባር ነው። በተለይ አሁን ያለንበት የ21ኛው ክፍለ ዘመን አጋማሽ ይህንን ግድ ይላል።
እንደምናየውም ሆነ እያደረግን እንዳለነው በአሁኑ ዘመን እውቀት ምንም አይነት ምስጢርነት የለውም። የህዝብ ከሆነ ቆይቷል። (ያልተፈለገ ብያኔ እንዳይከሰት “የህዝብ” የሚለውን በኋላ እንመለከተዋለን።)
በስያሜ ወይም መግባቢያ ደረጃ “የእውቀት ሽግግር” የሚለው ሲነገር ይሰማል። ትክክለኛ ነው። የዚህ አገላለፅ ችግሩ አስገዳጅ አለመሆኑና አንዱን ሰጪ ሌላውን ተቀባይ ማድረጉ ነው። “እውቀትን ዲሞክራሲያዊ የማድረግ”ን ከ“የእውቀት ሽግግር” የሚለየው የእውቀቱ ባለቤት እውቀቱን ዲሞክራሲያዊ የሚያደርገው ለእውቀቱ ተቀባይ ብቻ ብሎ ሳይሆን ለራሱም ጥቅም ሲል መሆኑ ነው።
እንደሚታወቀው፣ “ዘመን” የሚለው ጽንሰ ሀሳብ ከድንጋይ ዘመን ጀምሮ ሲቆጠር አይነትና ደረጃው ብዙ ሲሆን አሁን “ዘመነ ኢንተርኔት” (“የኢንፎርሜሽን ዘመን” በሚሉና ሌሎችም ይጠራል) ላይ ደርሷል። በመሆኑም፣ እውቀት የጥቂቶች መሆኑ ቀርቶ የፈለገው ሁሉ በቀላሉ፣ በአንድ ጣት ጠቅታ (ክሊክ) የሚያገኘው ሆኗል።
“እውቀትን ዲሞክራሲያዊ የማድረግ” ላይ ያጠኑና እያጠኑ ያሉ ምሁራን እንደሚሉት ዛሬ እውቀት ከጓዳ ወጥቶ አደባባይ ላይ ነው ያለው። የጥቂት ምርጦች መሆኑ ቀርቶ የሁሉም ሆኗል። ምስጢራዊነቱ አብቅቶ ገሀድ ከወጣ አምስትና ስድስት አስርታት እድሜን አስቆጥሯል። በመሆኑም፣ በዚህ በ“ዘመነ ኢንተርኔት” እውቀቴን ደብቄ፣ በምስጢር ይዤ፣ እኔ ስፈልግ ብቻ ለፈቀድኩት አጋራለሁ ማለት ወደ ኋላ እንጂ ወደ ፊት የሚያስኬድ አስተሳሰብ አይደለም። እውቀት የሕዝብ ነውና ከሕዝብ መሰወር አይቻልም። “ከህዝብ፣ በህዝብ፣ ለህዝብ” የሚለው እዚህም ይሰራል።
እዚህ ላይ “የህዝብ” የሚለው ፅንሰ ሀሳብ እንዳያደናግር አንዳንድ ሀሳቦችን እናንሳና ማለት የፈለግነውን እናስረግጥ።
በዚህ ጽሑፍ መሰረት “የህዝብ” ማለት እውቀትን ለመገብየት፣ ክሂሎትን ለማዳበር፣ አስተሳሰብን ለማበልፀግ፣ ዲሞክራሲን ባህሉ ለማድረግ ወዘተርፈ ዝግጁ የሆነውን ማለታችን ሲሆን፤ ለእዚህ ያልተዘጋጀን፣ ራሱ እውቀት ማለት ምን ማለት እንደ ሆነ እንኳን ገና በውል ያልተገነዘበውን ወገን አይመለከትም። “ገንዘብ አክባሪውን …” እንደሚባለው ሁሉ እውቀትም ፈላጊዋን ትሻለችና “የሕዝብ” ስንል እነሱን ማለታችን ነው።
እውቀት “የሕዝብ” ሆኗል ስንል ከጋን መብራትነት አፈትልኮ አደባባይ ውሏል እያልን ነው። ከአንድ ጠባብ ክፍል ውስጥ ወጥቶ ለህዝብ ሁሉ ሆኗል ማለት ነው። ከአንድ ከተከበረ የመጻሕፍት መደርደሪያ ላይ ወርዶ በእያንዳንዱ እውቀት ፈላጊ ጣት ስር ገብቷል እያልን ነው። ወይም፣ በዘመኑ አገላለጽ “ቤቴ” ብሏል ማለት ነው።
እኤአ በሰኔ 15 ቀን 2022 ለንባብ የበቃ ጥናት እውቀትን ዲሞክራሲያዊ ለማድረግ አስፈላጊው ደረጃ ምንድን ነው? በማለት ይጠይቅና መልሱንም እዛው ጋር ፈጣኑ፣ ቀልጣፋው እና ወጪ ቆጣቢው መንገድ በዘመኑ በተግባር ተሞክሮና ተፈትኖ የተሳካለትን ዘመናዊ የእውቀት አመራር ፕላትፎርም መጠቀም መሆኑን ያስረዳል። ሌሎች ጥናቶችም ይህንኑ ካረጋገጡ በኋላ ህንድ፣ ጃፓን፣ ኢንዶኔዥያ፣ ናሚቢያ፣ ቦትስዋና፣ ታይዋን፣ ደቡብ ኮሪያና የመሳሰሉ አገራት በዚህ በኩል ጥሩ ሁኔታ ላይ እንደሚገኙ ይዘረዝራሉ።
ወደ አገራችን ስንመጣ የምናገኘው እውነት እውቀት ዲሞክራሲያዊ አለመሆኑን ነው። በእኛ አገር እውቀት ገና ከአዋቂው እጅ አልወጣም፤ ከተደረደረበት ሼልፍ አልወረደም፤ ከታሸገበት ማዳበሪያ አልተዘረገፈም። በመሆኑም እውቀት የህዝብ አልሆነም ማለት ነው። ምሁሩም፣ ቄሱም፣ ሼሁም . . . ሁሉም እውቀትን ገና ከብብቱ አውጥቶ ለመላው ህዝብ “እንካችሁ፣ ያውላችሁ . . .” አላለም። በመሆኑም አገር ገና ከዳፍንት አልወጣችም። እነ አዳዲ ማሪያም ቤተ ክርስቲያንን፣ አክሱም ሀውልትን፣ ላሊበላን . . . የሰራች አገር እውቀትን ፍለጋ አለምን እየዞረች ትገኛለች። ለ“የእውቀት ሽግግር” ለአጫጭርም ይሁን ረጃጅም ስልጠናዎች የማትረግጥበት አገር የለም። የዚህ ሁሉ ችግር በአብዛኛው እዚህ አገር እውቀት “ዲሞክራታይዝ” ባለመደረጉ ነው።
ለነገሩ እኮ ስለ እውቀት ዲሞክራታይዜሽን አወራን እንጂ፣ እራሱ ትምህርት ዲሞክራሲያዊ ተደርጓልን (ለዜጎች ሁሉ ተዳርሷልን)? አልተዳረሰም። በመሆኑም፣ ስራው ገና አልተነካም ማለት ነው።
ከአገራት ተሞክሮም ይሁን ከምሁራን ምክር መረዳት የሚቻል አንድ ነገር ቢኖር አገር እንዲበለፅግና የሰለጠነ ማህበረሰብ እንዲፈጠር ከተፈለገ እውቀትን ዲሞክራሲያዊ ማድረግ የሚያስፈልግ መሆኑ ነው። ይህንን ሳያደርጉ እድገት፣ ብልፅግናንና ዲሞክራሲን ማሰብ ከየዋህነትም ባለፈ ሞኝነት ነው።
እውቀትን ዲሞክራሲያዊ ከማድረግ አኳያ ባለ ድርሻ አካላቱ በርካቶች ሲሆኑ፣ ሚዲያም የእነዚሁ ባለ ድርሻ አካላት አካል ነው።
በጥቅሉ “ሚዲያ” እንበል እንጂ እውቀትን ዲሞክራሲያዊ ከማድረግ (ለጠቅላላው ማህበረሰብ ከማሰራጨት አኳያ ከሚዲያም የህትመት ሚዲያን የሚቀድም እንደሌለ (በተለይ ከ18ኛው ክፍለ ዘመን ጀምሮ፤ የሕዝብ ቤተ መጻሕፍትም መከፈት የጀመሩት በዚሁ ክፍለ ዘመን መሆኑን ልብ ይሏል) ይህም በተለያዩ ጥናቶች ተረጋግጧል። በአሁኑ ዘመን ደግሞ ኢንተርኔት (ከርእሰ ጉዳያችን አኳያ አካታች ይሉታል)።
ለመሆኑ “እውቀትን ዲሞክራሲያዊ ከማድረግ አኳያ ምን ምን ተግባራትን ማከናወን ይጠበቃል?” የሚል ጥያቄ ከሁላችንም ቢነሳ መልካም ነው። የመልካምነቱ ምክንያት ደግሞ “ሁሉም ሰው፣ ያለ ምንም ልዩነት እውቀት በቀላሉ የሚያገኝበትን ተቋም መፍጠር እውቀትን ዲሞክራሲያዊ ማድረግ ነው፤ ዘመን አፈራሹን ኢንተርኔት ተጠቅሞ እውቀትን ማሰራጨት፣ የመማር ማስተማሪያ ሶፍትዌሮችን ማበልፀግ እውቀትን ዲሞክራሲያዊ ማድረግ ነው፤ በዘመናዊ መልክ የተዘጋጁ የማስታወቂያ ሰሌዳዎችን በየስፍራው በመትከል እውቀትን ተደራሽ ማድረግ እውቀትን ዲሞክራሲያዊ ማድረግ ነው፤ የአንድ ተቋም ሰራተኞች ሁሉም እኩል ስለ መስሪያ ቤታቸው አጠቃላይ እውቀት እንዲኖራቸው ማድረግ (የማወቅ መብት ስላላቸው ብቻ ሳይሆን ለተቋሙ ውጤታማነት ሲባል ጭምር) እውቀትን ዲሞክራሲያዊ ማድረግ ነው፤ ፖሊሲዎችን፣ መመሪያዎችን፣ ደንቦችን፣ ሕጎችን . . . ሁሉም ሰው (በየቋንቋው) በቀላሉ እንዲያገኛቸው ማድረግ እውቀትን ዲሞክራሲያዊ ማድረግ ነው፤ ምሁራን የጥናትና ምርምር ስራዎቻቸውን ለህዝብ ተደራሽ ቢያደርጉ እውቀትን ዲሞክራሲያዊ ማድረግ፤ ህብረተሰቡ በእውቀት ላይ የበላይነት ኖሮት እንዲጠቀምበት ማድረግ፣ እውቀትን ከተከማቸበት አውጥቶ እኩል የማዳረስና ማሰራጨት፣ የህዝብ ቤተመፃህፍትን ማስፋፋት፣ የተሻለ ለውጥን ማቀንቀንም እንዲሁ . . . ነውና ይህ (እኛ ዘንድ ስላልተደረገ) ይደረግ ዘንድ በማሳሰብ ጽሑፋችንን (ባይቋጭም) እንቋጫለን።
ዕውቀትን ለሌሎች ተደራሽ ለማድረግ ከልማዳዊ አመለካከቶች መላቀቅ አለብን፡፡ ለምሳሌ የባህል መዲሃኒት አዋቂዎች ለሰው የማይናገሩ አሉ፤ ፈዋሽነቱ ለተወሰኑ ሰዎች ብቻ የተገለጠ ነው በሚል ልማዳዊ አመለካከት ነው፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ እኔ ብቻ ተጠቃሚ መሆን አለብኝ በሚል ገንዘብ የሚያስገኙ ሙያዎችን ለብዙ ሰው ማሳየት የማይፈልጉም ይኖራሉ፡፡
በአጠቃላይ ከልማዳዊ አመለካከቶችና እኔ ብቻ ልጠቀም ባይነት ተላቀን ዕውቀትን ልናካፍል ይገባል፡፡
ግርማ መንግሥቴ
አዲስ ዘመን ግንቦት 12/2015