
ከጊዜ ወደ ጌዜ ተወዳዳሪነት እያየለ በመጣበት የስፖርት ዓለም፣ በሕዝብ ዘንድ አድናቆትንና ዝናን ያተረፉ ንጹህ ላባቸውን ጠብ አድርገው ለውጤት ዘወትር የሚታትሩ በድንቅ ሥነ ምግባር የታነፁ ስፖርተኞች በርካቶች ናቸው። ከዚህ በተቃርኖ በተለያዩ ምክንያቶች ዝናን፤ ውጤታማነትና አሸናፊነትን ለመቀዳጀት ጠንክሮ ከመሥራት ይልቅ አቋራጭ መንገድን የሚከተሉ ስፖርተኞች መመልከትም አድካሚ እየሆነ አይደለም።
የስፖርቱን መንደር የሚፈታተነው ከሥነ ምግባር ውጪ የሆነው አቋራጭ መንገድ ሲደረስበትም ውጤቱ ስፖርተኞቹ አንገት በማስደፋት ብቻ አይወሰንም። የወከሉትን ሀገር ብሎም ክለብ እስከ ማዋረድና መዘባበቻ እስከማድረግ የሚሻገርም ጭምር ነው።
አሁን ላይ የስፖርትን የውድድር ንፁህ መንፈስ ከሚበርዙና ከሚያደፈርሱ፣ አቋራጭ መንገዶች አንዱም የእድሜ ማጨበርበር ወይንም አንዳንዶች እንደሚገልጹት የእድሜ ውስልትና ከግንባር ቀደሞቹ ተርታ የሚቀመጥ ነው።
በአትሌቲክሱ ዘርፍ በተለይም በረጅም ርቀት ገናና ስም ያተረፈችው ኢትዮጵያ ምንም እንኳን አትሌቶቿ በተቻለ መጠን በብቃታቸው የሚተማመኑ ከራሳቸው አልፈው ሀገራቸውንና ክብራቸውን የሚያስቡ ቢሆንም የችግር ተጋላጭ ከሆኑት ሀገራት አንዷ እንደሆነች ይታወቃል።
የአትሌቶች የእድሜ ማጭበርበር ጉዳይ አሳሳቢ እየሆነ መምጣቱን በተደጋጋሚ ሲገለፅ ቆይቷል። ስፖርት ቤተሰቡ እስከ ባለሙያዎች፣ ከአሠልጣኞች እስከ ራሳቸው ተወዳዳሪ አትሌቶች እንዲሁም የውድድሩ ባለቤት የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ድረስ የዕድሜ ተገቢነት ጉዳይ ማድበስበስ በማይቻልበት ሁኔታ ጎልቶ ሲስተዋልም ታዝበናል።
ይህን ችግር ከመከላከልና ከመቆጣጠር አንፃር በወረቀትና በሪፖርት ደረጃ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራበት መሆኑ ሲገለፅ ቆይቷል። ይሁንና መሬት ላይ የሚታየው ሃቅ ከዚህም የተለየ ምስልን የሚያንፀባርቅ ነው። ሕገ ወጥ አካሄዱ በአስተሳሰብም በተግባራም መቆም እንዳልቻለ ለመረዳትም ከቀናት በፊት ይፋ የሆነውን የምርመራ ውጤት በቂ ምስክር ሆኖ ሊወሰድ የሚችል ነው።
የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ከቀናት በፊት ኢትዮጵያን ወክሎ ከጁላይ 16-20/2025 በናይጄሪያ አቡኩታ ከ 18 ዓመት በታች እና ከ 20 ዓመት በታች አትሌቲክስ ሻምፒዮና ላይ የሚሳተፉ አትሌቶች የእድሜ ውጤት ምርመራ አከናውኗል።
ፌዴሬሽኑ በኢትዮጵያ ፖሊስ ሆስፒታል የፎረንሲክ ሜዲሲንና ሥነ-ምረዛ ምርመራ ክፍል ለ 76 አትሌቶች የእድሜ ምርመራ አድርጓል። የተደረገው ምርመራ የትውልድ ጊዜ፣ ኤምአርአይ (MRI)፣ የትምህርት ደረጃ፣ አጠቃላይ የሰውነት እድገትና አቋም ሁኔታ፣ የጥርስ አበቃቀልና የዕድገት ደረጃ በራጅ ኢሜጂንግ የሰውነት አጥንቶች ዕድገት ደረጃ የእድሜ ምርመራው የተደረገ ሲሆን፣ በሆስፒታሉ የፎረንሲክ ሜዲሲንና ቶክሲኮሎጂ ስፔሻሊስቶች ተደርጓል።
በውጤቱም 18 ዓመት በታች ከተመዘገቡ ወንድ አትሌቶች መካከል ምንም አይነት ከ18 ዓመት በታች የሌለ ሲሆን፣ 4 አትሌቶች ከ 20 ዓመት በታች መሆናቸውን በእድሜ ምርመራው ተረጋግጧል።
ከ18 ዓመት በታች የተመዘገቡ ሴት አትሌቶች ውስጥ 2 አትሌቶች ብቻ ከ18 ዓመት በታች ሲሆኑ 9 አትሌቶች ከ 20 ዓመት በታች መሆናቸውን ተረጋግጧል።
ከ20 ዓመት በታች ከተመዘገቡ ወንድ አትሌቶች ውስጥ 2 አትሌቶች ብቻ ከ 20 ዓመት በታች መሆናቸውን ተረጋግጧል። ከ20ዓመት በታች ከተመዘገቡ ሴት አትሌቶች መካከል 5 አትሌቶች ብቻ ከ20 ዓመት በታች መሆናቸው ተረጋግጧል። በዚህም መሠረት የእድሜ ምርመራውን ካደረጉ 76 አትሌቶች መካከል ያለፉ አትሌቶች ውስጥ 6 ወንድና 16 ሴት በድምሩ 22 አትሌቶች መሆናቸው ታውቋል።
የእድሜ ማጭበርበርን ለመከላከልና ለመቆጣጠር ሊወሰዱ ስለሚገቡ መፍትሄዎች የዘርፉ ምሁራን ሲጠቁሙም፣ ስለ ዕድሜ ማጭበርበር አሉታዊ ተፅዕኖዎችና ስለ ሕጎችና ደንቦች ግንዛቤ ከማስጨበጥ በላይ ‹‹የዕድሜ ማጭበርበርን በግልጽ የሚከለክሉና ጥሰት ሲፈፀምም የሚወሰዱ ከባድ ርምጃዎችን ማሳወቅ ብሎም መተግበር ይህም አትሌቶችን፣ አሰልጣኞችን፣ ክለቦችንና ማንኛውም ተሳታፊ አካል ሊያካትት እንደሚገባ አፅእኖት ይሠጡታል።
በቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን ማክሰኞ ሰኔ 24 ቀን 2017 ዓ.ም