በኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚ፣ አዲስ አበባ እና አበበ ቢቂላ ስታዲየሞች በመካሄድ ላይ የሚገኘው 52ኛው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ቻምፒዮና ዛሬ ሶስተኛ ቀኑን ይዟል። የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን በየዓመቱ ከሚያዘጋጃቸው ቻምፒዮናዎች መካከል ትልቁና አንጋፋ የሆነው ይህ ውድድር ስመ ጥር አትሌቶችን በማፍራት ይታወቃል። ከ1963 ዓ.ም አንስቶ ሲካሄድ የቆየው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ቻምፒዮና በግማሽ ክፍለ ዘመን ጉዞውም ከሻምበል አበበ ቢቂላ አንስቶ እስካሁን ድረስ በኦሊምፒክ እና በተለያዩ ዓለም አቀፍ የአትሌቲክስ ቻምፒዮናዎች አገራቸውን የወከሉ አትሌቶችን አሳትፏል።
ቻምፒዮናው ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ዝነኛ አትሌቶች ተሳትፏቸውን በማራቃቸው ምክንያት በጀማሪ አትሌቶች ተወስኖ ከቀድሞውም ተቀዛቅዞ ይካሄድ ነበር። ነገር ግን ፌዴሬሽኑ ታዋቂ አትሌቶች በመሰል የአገር ውስጥ ቻምፒዮናዎች ክለቦቻቸውን ካልወከሉ በዓለም አቀፍ ውድድሮች ምርጫ ውስጥ የመካተት ዕድላቸው እንደሚቀንስ በማስታወቁ የተነሳ ቻምፒዮናው መነቃቃት እያሳየ መጥቷል። ከጥቂት ወራት በኋላ በሃንጋሪዋ ከተማ ቡዳፔስት ለሚከናወነው የዓለም አትሌቲክስ ቻምፒዮናም በ10ሺ ሜትር ርቀት የአትሌቶች ቅድመ ማጣሪያ ሆኖ የሚያገለግል ሲሆን፤ በርካታ አትሌቶችም ብቃታቸውን የሚለኩበት እንደሚሆንም ይጠበቃል።
ይህ በአጭር፣ በረጅም ርቀት እና በሜዳ ተግባራት ውድድሮች የሚከናወነውና ከፍተኛ ፉክክር የሚያስተናግድ መድረክ የስፖርት ማዘውተሪያዎች እጥረት ችግር ሆኖበታል። በዚህም ምክንያት ዛሬ ሶስተኛ ቀኑን የያዘው 52ኛው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ቻምፒዮና በርካታ ውድድሮችን በኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚ የተቀሩትን ደግሞ በእድሳት ላይ በሚገኘው የአዲስ አበባ ትንሿ ስታዲየም እንዲሁም በአበበ ቢቂላ ስታዲየም እያከናወነ ይገኛል። በኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን የውድድርና ተሳትፎ ዳይሬክተር አቶ አስፋው ዳኜ፤ የኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚ በዚህ ወቅት ለፌዴሬሽኑ እያደረገ ላለው ዘርፈ ብዙ እገዛ ምስጋናቸውን አቅርበዋል። ይሁን እንጂ አሁን ውድድር እየተካሄደበት የሚገኘው የአካዳሚው ሜዳ ሲገነባ ለውሃ ማስኬጃ በሚል የተቀበሩ መሳሪያዎች ለውድድር ፈታኝ መሆናቸውን አልሸሸጉም። በመሆኑም እንደ ጦር፣ አሎሎ፣… ያሉ የሜዳ ተግባራት ውድድሮች በሚካሄዱበት ወቅት አትሌቶች ሊጎዱ የሚችሉ በመሆኑ መሰል ውድድሮችን ማድረግ እንዳልተቻለ አስረድተዋል።
ስለዚህም ፌዴሬሽኑ የአሎሎ፣ መዶሻ እና ዲስከስ ውርወራ ስፖርቶችን በትንሿ የአዲስ አበባ ስታዲየም እንዲሁም የጦር ውርወራ ውድድርን ደግሞ በአበበ ቢቂላ ስታዲየም በማከናወን ላይ ይገኛል። ይህም ፌዴሬሽኑ ቻምፒዮናውን በተለያዩ ቦታዎች ከመምራት ባለፈ፤ ዳኞችን በሶስት ስፍራዎች በመመደብ ውድድር ማካሄድ አድካሚ አድርጎታል። በመሆኑም ለኢትዮጵያ ባለውለታ የሆነው ይህ ስፖርት መሰል ችግር እንዳያስተናግድ በመንግስት በኩል ትኩረት ሰጥቶ ቢቻል የመምና የሜዳ ተግባራትን ውድድሮች ማካሄድ የሚችል ማዘውተሪያ፤ ካልሆነ ግን በግንባታ ላይ የሚገኙ ስታዲየሞች ቢጠናቀቁ መልካም እንደሚሆን አስተያየት ሰጥተዋል።
ቻምፒዮናው በዚህ ፈተና ውስጥም ሆኖ በተለያዩ ውድድሮች ጠንካራ ፉክክሮችን እያስተናገደ ይገኛል። በትናንትናው ዕለት በተካሄዱ ውድድሮች በ400 ሜትር፣ 100 ሜትር እና 800ሜትር በሁለቱም ጾታዎች እንዲሁም በወንዶች የስሉዝ ዝላይ ፍጻሜያቸውን ያገኙ ውድድሮች ሆነዋል። በሌላ በኩል ለዓለም አትሌቲክስ ቻምፒዮና ቅድመ ማጣሪያ የሆነውና በሁለቱም ጾታ ከአንድ እስከ ስምንት የወጡ አትሌቶች ወደ ማጣሪያ የሚገቡበት የ10ሺ ሜትር ርቀትም በሁለቱም ጾታዎች መካሄዳቸውም ተረጋግጧል።
ዛሬ በሚኖረው የውድድሩ 3ኛ ቀን ውሎም፤ ማጣሪያ ከሚደረግባቸው ውድድሮች ባለፈ የሴቶች ስሉዝ ዝላይ፣ በወንዶች ዲስከስ ውርወራ፣ የሴቶች ርዝመት ዝላይ፣ የሴቶች 100ሜትር መሰናክል እንዲሁም የወንዶች 110 ሜትር መሰናክል ፍጻሜ ይከናወናል። ቻምፒዮናው እስከ መጪው እሁድ ግምቦት 13/2015 ዓም ድረስ ቀጥሎ የሚካሄድም ይሆናል።
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን ግንቦት 10/2015