መንግሥት የኢንዱስትሪውን ዘርፍ ችግሮች ለማቃለል እየተገበራቸው ከሚገኙ የመፍትሄ እርምጃዎች መካከል አንዱ የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ መሆኑ ይታወቃል። ንቅናቄው ሚያዝያ 2014 ዓ.ም የተጀመረ ሲሆን፣ ንቅናቄው የተጀመረበትን አንደኛ ዓመት በማስመልከትም በአዲስ አበባ ቀናትን የወሰደ ሰፊ መድረክ ተካሂዷል። ንቅናቄው በአገር አቀፍ ደረጃ ለአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ እድገት ተስፋ ሰጪ የሆኑ ውጤቶች እንደተመዘገቡበት በመድረኩ ተጠቁሟል።
ንቅናቄውን በዋናነት የሚያስተባብረው የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ይፋ ያደረገው መረጃ እንደሚያሳየው፣ ንቅናቄው በተጀመረበት ዓመት በአገር አቀፍ ደረጃ ከ50ሺ በላይ ባለሀብቶችና ባለድርሻ አካላት በክልሎች፣ በዞኖች፣ በወረዳዎችና በከተማ አስተዳደሮች በንቅናቄዎች በማሳተፍ ግንዛቤ ለመፍጠር እና ባለሀብቱንና አመራሩን ለማቀራረብ ትልቅ አስተዋፅዖ አበርክቷል። በዚህም ዘርፉ እንዲነቃቃ አግዟል። ከ352 በላይ ስራ አቁመው የነበሩ ኢንዱስትሪዎች ወደ ስራ እንዲመለሱ ማድረግ ተችሏል። 635 አዳዲስ ኢንዱስትሪዎች ማምረት ጀምረዋል። አራት ሺ አዳዲስ ኢንቨስትመንቶች ወደ ዘርፉ ለመግባት ፈቃድ ወስደዋል።
የአንድ መስኮት አገልግሎት አሰጣጦች በክልሎችና በየተቋማቱ እየተሻሻሉ መጥተዋል። የተቋማት ቅንጅታዊ አሰራር መሻሻል ጀምሯል። ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች ከዚህ ቀደም ይይዙት ከነበረው የኢንዱስትሪ መሰረተ ልማት ማቅረቢያ በጀት በላይ ተጨማሪ በጀት በመያዝ አስተዋፅዖ እያደረጉ ይገኛሉ። የሼድ ግንባታና የመሬት አቅርቦት ድጋፎች ተሻሽለዋል።
ክልሎች በኢንቨስትመንት አቅሞቻቸውና ሌሎች ነባራዊ ሁኔታዎቻቸው ላይ ተመስርተው ‹‹ኢትዮጵያ ታምርት›› አገራዊ ንቅናቄን ተግብረዋል፤ ንቅናቄው በኢንዱስትሪው ዘርፍ ያጋጠሙ ችግሮችን በቅንጅት በመፍታት ውጤታማ ስራ መስራት እንዳስቻላቸውና በንቅናቄው ትግበራም አበረታች ውጤቶችን እያገኙ መሆናቸውን በቅርቡ በሚሊኒየም አዳራሽ በተካሄደው የኢትዮጵያ ታምርት መድረክ ላይ አስታውቀዋል።
የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ንግድ፣ ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ አብዲ ሙክታር ‹‹ኢትዮጵያ ታምርት›› አገራዊ ንቅናቄ የአምራች ዘርፉ ችግሮች እንዲፈቱ እገዛ እያደረገ እንደሆነ አስታውቀዋል። በከተማዋ ስራ አቁመው የነበሩ አምራቾችን በ‹‹ኢትዮጵያ ታምርት›› ንቅናቄ ወደ ስራ ለመመለስ ብዙ ስራዎች ተከናውነዋል ያሉት ምክትል ኃላፊው፣ ለዚህም አስተዳደሩ እቅዶችን በማዘጋጀት ከብዙ ባለድርሻ አካላት ጋር በትብብር እየሰራ መሆኑን ነው የገለጹት።
አቶ አብዲ እንዳሉት፤ የኢንዱስትሪ-ዩኒቨርሲቲ ትስስርን በመፍጠር ረገድ ውጤታማ ስራዎች ተሰርተዋል፤ በጥናት ላይ የተመሰረተ የኢንዱስትሪ ዘርፍ ስራ ለማከናወን በወጣው እቅድ መሰረት ድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ፣ ሐረማያ ዩኒቨርሲቲ፣ ድሬዳዋ ፖሊ- ቴክኒክ ኮሌጅ እና ድሬዳዋ ሙያና ቴክኒክ ኮሌጅ በጋራ በመሆን ከአምራች ኢንዱስትሪዎች ጋር ትስስር ፈጥረው ኢንዱስትሪዎቹ ያሉባቸውን ችግሮች የመለየትና መፍትሄዎችን የማመላከት ስራዎችን እየሰሩ ይገኛሉ። በዚህ ዘርፍ የተሰራው ስራ በአገር አቀፍ ደረጃ ጭምር ትልቅ ምሳሌ ሊሆን የሚችል ሲሆን፣ ንቅናቄው ከከፍተኛ አመራሩ እስከ ታችኛው ባለሙያ ድረስ የግንዛቤ ለውጥ ፈጥሯል።
በበጀት ዓመቱ በ207 ኢንዱስትሪዎች የማምረት አቅም ላይ ተፅዕኖ ያሳደሩ ከ15 በላይ ችግሮችን (የኃይል፣ የጥሬ እቃና ግብዓት፣ የውሃና የመንገድ መሰረተ ልማት አቅርቦት) በመለየት ባለድርሻ አካላት የየድርሻቸውን ወስደው ችግሮችን እንዲፈቱ ጥረት ተደርጓል። 120 አነስተኛና መካከለኛ ኢንዱስትሪዎችን ለማቋቋም ታቅዶ 90 ማቋቋም ተችሏል። 120 ኢንዱስትሪዎችን ለማጠናከር ታቅዶ 100 ኢንዱስትሪዎችን በማጠናከር የማምረት አቅማቸው እንዲጨምር ማድረግ ተችሏል። በአዳዲስ ኢንዱስትሪዎች ከስድስት ሺ በላይ አዳዲስ የሥራ እድሎች ተፈጥረዋል። ለ200 ኢንተርፕራይዞች የኢንዱስትሪ ኤክስቴንሽን አገልግሎት ለመስጠት ታቅዶ ለ164 መስጠት ተችሏል። ከ120 እስከ 1200 ካሬ ሜትር ስፋት ያላቸውን ሼዶችን ከአነስተኛ ጀምሮ እስከ ከፍተኛ ደረጃ ላሉ ኢንዱስትሪዎች በመገንባት የማምረቻ ቦታ እጥረት ችግርን ለማቃለል ጥረት ተደርጓል። ኦክስጂን፣ ቀለም፣ የማዳበሪያ ከረጢት፣ የፕላስቲክ ውጤቶችን፣ ጨርቃ ጨርቅና ሌሎች ምርቶችን በማምረት እንዲሁም መኪና በመገጣጠም ስራ ላይ የተሰማሩ ሰባት ከፍተኛ ኢንዱስትሪዎች ስራ ጀምረዋል።
እነዚህ ሁሉ ስራዎች ሲከናወኑ ተኪ እና ለውጪ ገበያ የሚቀርቡ ምርቶችን በማምረት ላይ ትኩረት እንደሚደረግ የሚናገሩት ምክትል ኃላፊው፣ ሁሉም ስራዎች በጥናትና በቴክኖሎጂ የተደገፉ ሆነው እንዲከናወኑ ጥረት እንደሚደረግም ይገልፃሉ።
አቶ አብዲ ‹‹ድሬዳዋ ቀደም ካለው ጊዜ ጀምሮ የኢንዱስትሪ ማዕከል እንደሆነች ይታወቃል። የኢንዱስትሪ መዳረሻነቷን አጠናክሮ ለማስቀጠል እየተሰሩ ካሉ ስራዎች መካከል አዳዲስ ኢንዱስትሪዎችን የመገንባት እና ነባር ኢንዱስትሪዎችን የመደገፍ ተግባራት ይጠቀሳሉ›› ይላሉ።
ድሬዳዋን ታሪካዊ የኢንዱስትሪ መናኸሪያ እንድትሆን ካደረጓት ፋብሪካዎች መካከል አንዱ የሆነውና ለ20 ዓመታት ያህል ተዘግቶ የቆየው የድሬዳዋ ጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካ በ‹‹ኢትዮጵያ ታምርት›› ንቅናቄ አማካኝነት ባለፈው ዓመት ወደ ምርት መመለሱን ገልጸዋል። ፋብሪካው አሁን ክር እያመረተ መሆኑን ጠቅሰው፣ በቀጣይ ደግሞ ልብስ እንዲያመርት ታቅዶ እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰዋል። ‹‹ይህ ትልቅ ለውጥና ውጤት ነው›› ያሉት ምክትል ኃላፊው፣ ከዚህ በተጨማሪም የድሬዳዋ ነፃ የንግድ ቀጠናም የንቅናቄውን ዓላማዎች ለማሳካት ትልቅ አቅም እየፈጠረ እንደሚገኝም ተናግረዋል።
የሲዳማ ክልል ንግድና ኢንዱስትሪ ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ጎሳዬ ጎዳና የ‹‹ኢትዮጵያ ታምርት›› ንቅናቄ መዋቅራዊ የምጣኔ ሀብት ሽግግርን እውን ለማድረግ እንደሚያግዝ ይገልፃሉ። ንቅናቄው በአገር አቀፍ ደረጃ ከተጀመረ ወዲህ በሲዳማ ክልል የተለያዩ የንቅናቄው መድረኮች መካሄዳቸውን ጠቅሰው፣ ንቅናቄው ምርትን በአገር ውስጥ በማምረት ለገቢ ምርቶች የሚውለውን የውጭ ምንዛሬ ለማዳንና ምርቶችን ለውጭ ገበያ በማቅረብ ተጨማሪ የውጭ ምንዛሬ ለማግኘት የሚያግዝ መሆኑን ነው ያመለከቱት። ዜጎች የአገራቸውን ምርት እንዲጠቀሙ እንደሚያበረታታም ገልጸዋል።
አቶ ጎሳዬ እንደሚናገሩት፤ በበጀት ዓመቱ በሲዳማ ክልል ተመርተው ለውጭ ገበያ ከሚቀርቡ ምርቶች 77.9 ሚሊዮን ዶላር ለማግኘት ታቅዶ አመርቂ አፈፃፀም ተመዝግቧል። ባለፉት ዘጠኝ ወራት ከ47 ሚሊዮን ዶላር በላይ ዋጋ የሚያወጡ ተኪ ምርቶች ተመርተዋል። በ2015 ዓ.ም በክልሉ ለ18ሺ910 ዜጎች የሥራ እድል ለመፍጠር እቅድ ተይዞ በዘጠኝ ወራት 14ሺ ዜጎች ቋሚ የሥራ እድል ተፈጥሮላቸዋል።
ንቅናቄው የባለድርሻ አካላት ትብብር ስኬታማ እንዲሆን ትልቅ እገዛ እያደረገ ይገኛል ያሉት አቶ ጎሳዬ፣ የሲዳማ ክልል የአምራች ኢንዱስትሪ ምክር ቤት እንዲቋቋም መደረጉም የንቅናቄው ውጤት መሆኑን ነው የጠቀሱት። የቢሮው ምክትል ኃላፊ ንቅናቄው ዘርፉን የበለጠ ውጤታማ ለማድረግ የሚያስችሉ የጥናትና ምርምር ስራዎችን ለማከናወን እገዛ አድርጓል ብለዋል። ከሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር የክልሉ የአምራች ኢንዱስትሪ ፍኖተ ካርታና ስትራቴጂክ እቅዶች እየተዘጋጁ እንደሚገኙም ተጠቅሰው፣ አምራች ኢንዱስትሪዎችን በመጎብኘት ከዚህ ቀደም ግንባታቸው ተጀምሮ የቆዩ የመሸጫና ማሳያ ማዕከላት የክልሉ መንግሥት በመደበው በጀት ግንባታቸው እንዲጠናቀቅ መደረጉን አስታውቀዋል።
እሳቸው አንዳሉት፤ የአምራቾቹ ችግሮች የፋይናንስና የመሰረተ ልማት አቅራቢ በሆኑ ተቋማት ምላሽ እንዲያገኙ አቅጣጫ ተቀምጧል። በክልሉ ከአንድ ሺ በላይ የሚሆኑ የአምራች ኢንዱስትሪዎችን መረጃ የማጠናቀርና የማደራጀት ስራ ተሰርቷል፤ አምራቾች ባላቸው የካፒታል አቅምና በሚይዙት የሰው ኃይል መሰረት ስለሚደራጁ በቀጣይም መረጃው በድጋሚ የሚደራጅ ይሆናል።
አቶ ጎሳዬ በሲዳማ ክልል በአምራች ዘርፉ ባለሀብቶች በአግሮ-ፕሮሰሲንግ፣ በእንጨትና ብረታ ብረት፣ በቆዳና የቆዳ ውጤቶች፣ በኮንስትራክሽን ግብዓቶች፣ በኬሚካልና የኬሚካል ውጤቶች፣ በእደ ጥበብ እና ጨርቃ ጨርቅና አልባሳት ዘርፎች እንደተሰማሩ ጠቁመው፣ በ‹‹ኢትዮጵያ ታምርት›› ንቅናቄ በክልሉ ስራ ያቆሙ ኢንዱስትሪዎችን ወደ ስራ ለመመለስ ጥረት እየተደረገ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
የአማራ ክልል ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ ኃላፊ አቶ ኢድሪስ አብዱ በበኩላቸው ክልሉ በአምራች ዘርፉ ለአገር ማበርከት የሚገባውን ድርሻ በቅጡ ለመወጣት ንቅናቄውን እየተጠቀመበት እንደሆነ ይገልጻሉ። ‹‹ከ889 በላይ የአምራችና ከ225 በላይ የሌሎች ዘርፎች (በጠቅላላ ከ1100 በላይ) ኢንቨስትመንቶች የኃይል አቅርቦት ችግር ነበረባቸው።›› ያሉት የቢሮ ኃላፊው፣ በንቅናቄው ከኃይል አቅራቢ ተቋማት ጋር በቅንጅት በመስራት ከ600 በላይ የሚሆኑት ችግራቸው በከፊል የሚፈታበት ሁኔታ ተፈጥሯል ብለዋል።
እንደ እሳቸው ገለጻ፤ ከመንገድ መሰረተ ልማት አቅርቦት ጋር በተያያዘ የመሰረተ ልማት አቅርቦት ተደራሽ ያልሆነባቸው ብዙ ኢንዱስትሪዎች አሉ፤ የክልሉ መንግሥት ለአምራች ዘርፉ በሰጠው ትኩረት እና ይህን ችግር ለመፍታት በሚል በበጀት ዓመቱ ከ464 ሚሊዮን ብር በላይ ለመሰረተ ልማት ግንባታ መድቦ እየሰራ ነው። በስራ እድል ፈጠራ ረገድ ከ68ሺ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች ቋሚ የሥራ እድሎች ተፈጥረዋል። ኢንዱስትሪዎች ከስራ እድል መፍጠር አበረታች ለውጦች እየታየባቸው ነው። ‹ኢትዮጵያ ታምርት› ንቅናቄ የክልሉ መንግሥት የአምራች ዘርፉን ችግሮች ለመፍታት ቁርጠኛነቱን ያሳየበት ተግባራዊ እንቅስቃሴ ነው›› ይላሉ።
አዲስ አበባም የ‹‹ኢትዮጵያ ታምርት›› አገራዊ ንቅናቄ በረከቶች ደርሰዋታል። የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የሥራ ኢንተርፕራይዝና ኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ የአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍ ኃላፊ አቶ ኢዘዲን ሙስባህ ፤ ንቅናቄው በአዲስ አበባ ከተማ በአንድ ዓመት ውስጥ 677 አዲስ አነስተኛና መካከለኛ አምራች ኢንዱስትሪዎች ወደ ሥራ እንዲገቡ ማድረጉን አስታውቀዋል።
እንደ እሳቸው ገለጻ፤ በዘርፉ የሚስተዋሉ ችግሮችን በመለየት ደረጃ በደረጃ በመፍታት በኩልም ውጤታማ ሥራ ተሠርቷል። በዚህም በተለያዩ ምክንያቶች ሥራ አቁመው ከነበሩ 49 ኢንዱስትሪዎች ውስጥ 43 ያህሉን ወደ ሥራ ማስገባት ተችሏል። በንቅናቄው በተደረገው የድጋፍና ክትትል ስራ 210 አምራች ኢንዱስትሪዎች ምርታቸውን ወደ ውጭ መላክ ጀምረዋል፤ ተኪ ምርትን የሚያመርቱ አንድ ሺ 926 ኢንዱስትሪዎችንም ማፍራት ተችሏል።
በዘርፉ በማነቆነት የሚነሱትን የማምረቻ ቦታ፣ የፋይናንስ፣ የኃይል አቅርቦት፣ የገበያ ትስስር፣ የጥሬ እቃ አቅርቦት እንዲሁም የውጭ ምንዛሪ እጥረት ችግሮችን ደረጃ በደረጃ ለመፍታት ጥረት እየተደረገ መሆኑንም ነው አቶ ኢዘዲን የተናገሩት። ከቦታ ጋር ተያይዞ የሚነሱ ችግሮችን ለመቅረፍም ሰባት ነጥብ ሰባት ቢሊዮን ብር በከተማ አስተዳደሩ ተመድቦ በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ በ93 ሄክታር መሬት ላይ የሼድ ግንባታ እየተካሄደ መሆኑን ጠቅሰው፤ ይህም የ800 አነስተኛና መካከለኛ ኢንዱስትሪዎችን የቦታ እጥረት ችግር ይፈታል ተብሎ እንደሚጠበቅ ተናግረዋል።
ባለፉት አራት ዓመታት መንግሥት ተግባራዊ ካደረጋቸው ዘርፈ ብዙ የምጣኔ ሀብት ማሻሻያ መርሃ ግብሮች መካከል አንዱ የሆነውና ዓላማው አምራች የሆነውን የሠው ኃይል የሚሸከም የሥራ እድል እና የተረጋጋ የማክሮ-ኢኮኖሚ ከባቢ መፍጠር እንዲሁም የግል ዘርፍ መር (Private Sector-Led) የሆነ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ በመገንባት ዘላቂና ፈጣን የምጣኔ ሀብት እድገት ማስመዝገብ ያደረገው የ‹‹አገር በቀል የምጣኔ ሀብት ማሻሻያ መርሃ ግብር›› (Homegrown Economic Reform Program) አካል የሆነው ‹‹ኢትዮጵያ ታምርት›› አገራዊ ንቅናቄ፤ በክልሎች እያስገኛቸው ያሉ ውጤቶችን በማስፋት ለአምራች ዘርፉ ችግሮች ዘላቂ መፍትሄ መስጠት ይገባል።
በአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ አስቻይ ሁኔታዎችን በመፍጠር የዘርፉን የማምረት አቅም ማሳደግ፣ ለዜጎች ተጨማሪ የስራ ዕድል መፍጠር፣ የውጭ ምንዛሬ ግኝትን ማሳደግ እና ገቢ ምርቶችን በአገር ውስጥ በመተካት የውጭ ምንዛሬን ማዳን ከ‹‹ኢትዮጵያ ታምርት›› መርሃ ግብር የሚጠበቁ ውጤቶች ናቸው።
ክልሎች በኢንቨስትመንት አቅሞቻቸውና ሌሎች ነባራዊ ሁኔታዎቻቸው ላይ ተመስርተው የ‹‹ኢትዮጵያ ታምርት›› አገራዊ ንቅናቄን ተግብረዋል፤ ንቅናቄው በኢንዱስትሪው ዘርፍ ያጋጠሙ ችግሮችን በቅንጅት በመፍታት ውጤታማ ስራ መስራት እንዳስቻላቸውና በንቅናቄው ትግበራም አበረታች ውጤቶችን እያገኙ መሆናቸውን አስታውቀዋል
አንተነህ ቸሬ
አዲስ ዘመን ግንቦት 10/2015