ለኢትዮጵያ የውጭ ምንዛሬ በማስገኘት ትልቅ ድርሻ ከሚያበረክቱት የግብርና ምርቶች መካከል ቡና ትልቁን ይጠቀሳል። በውጭ ምንዛሪ ግኝቱ በቀዳሚነት የሚጠቀሰው ቡና ካለፉት ጥቂት ዓመታት ወዲህ የውጭ ምንዛሬ በማስገኘት በኩል ከፍተኛ ውጤት እየታየበት ይገኛል።
በ2014 በጀት አመት ከዘርፉ የተገኘው የውጭ ምንዛሬ ለእዚህ ጥሩ ማሳያ ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል። በበጀት አመቱ አንድ ነጥብ አራት ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር በላይ ገቢ ማግኘት ችላለች። ይህን ያህል መጠን ያለው የውጭ ምንዛሬ የተገኘው 300 መቶ ሺ ቶን ቡና ለውጭ ገበያ በማቅረብ መሆኑን የቡናና ሻይ ባለስልጣን መረጃ ያመለክታል። ይህም ስኬት ኢትዮጵያ በቡና የወጪ ንግድ ታሪኳ ለመጀመሪያ ጊዜ የተመዘገበ ስኬት መሆኑም ታውቋል። ከቡና የሚገኘው የውጭ ምንዛሬ ቀደም ባሉት አመታትም ለውጥ አሳይቷል።
በ2013 በጀት አመትም እንዲሁ ቡና ባስገኘው የውጭ ምንዛሬ ተጠቃሽ መሆን ችሏል። በ2013 በጀት ዓመት ኢትዮጵያ በወጪ ንግድ ለዓመታት ሲታይ የነበረውን የቁልቁለት ጉዞ ከመግታት አልፋ አዲስ ታሪክ ማስመዝጓቧ በወቅቱ ተጠቁሞ እንደነበር መረጃዎች ያመለክታሉ። በበጀት ዓመቱ 248 ሺህ 311 ቶን ቡና ወደ ውጭ በመላክ 907 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ገቢ አግኝታለች።
ለዚህ ውጤትም መንግሥት ለዘርፉ የሰጠው ከፍተኛ ትኩረት የጎላ ድርሻ እንዳለው ሁሉ፤ ቡናን ከሚያለማው አርሶ አደር ጀምሮ ቡና አቅራቢና ላኪዎች እንዲሁም በአጠቃላይ የቡና ቤተሰቦች ሚና ከፍተኛ ግምት የሚሰጠው ነው።
የቡና ልማቱን በማጠናከር አዳዲስ የቡና ችግኞችን በመትከል፣ ነባሮቹን በመጎንደል ምርትና ምርታማነቱን ለማሳደግ ተሰርቷል፤ እየተሰራ ይገኛል። ቡና ለውጭ ገበያ በማቅረብ በኩል አርሶ አደሩ ጭምር የሚሰማራበት ሁኔታ በመፍጠር፣ በዚህም በአሴት ሰንሰለት ውስጥ ምን ፋይዳ የሌላቸውን ደላሎችን ከገበያ በማስወጣት፣ ዓለም አቀፍ ኢግዚቢሽኖችን በማካሄድ፣ የቡና ጣእም ውድድር በማካሄድ መዳረሻዎችን በማስፋት፣ በአጠቃላይ ለቡና ግብይት ደንቃራ የነበሩ አሰራሮችን በመቀየርና በመሳሰሉት በቡና ግብይት ላይ ትርጉም ያለው ለውጥ ማምጣት ተችሏል። ይህን ሁሉ ተከትሎ ነው በቡና የውጭ ምንዛሬ ግኘት ላይ ትርጉም ያለው ለውጥ ማምጣት የተቻለው።
ሀገሪቱ ይህን ስኬታማ ተሞክሮ በመያዝ በ2015 በጀት አመት አንድ ነጥብ ስምንት ቢሊየን ዶላር ከቡና የወጪ ንግድ ለማግኘት አቅዳ እየሰራች ትገኛለች። ይሁንና ዘንድሮ ቡና በዓለም ገበያ ያለው ዋጋ ቅናሽ እንደታየበት መረጃዎች ያመለክታሉ። የቡናና ሻይ ባለስልጣንም ይህኑ ነው የሚጠቁመው።
ይህን ተከትሎም የኢትዮጵያ ላኪዎች በአሁኑ ወቅት ቡና በሚፈለገው መጠን ለውጭ ገበያ እያቀረቡ አለመሆናቸውን ባለስልጣኑ ጠቁሟል። ይህም አገሪቷ ከዘርፉ ማግኘት የሚገባትን የውጭ ምንዛሪ እንዳታገኝ እያደረገ ይገኛል።
በወቅታዊ የቡና ዓለም አቀፍ ገበያ ዋጋና ኢትዮጵያ ይህን ተከትሎ እያከናወነች ስላለችው ተግባር ያነጋገርናቸው የቡናና ሻይ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አዱኛ ደበላ እንደሚሉት፤ ዘንድሮ በዓለም አቀፍ ደረጃ የቡና ዋጋ ካለፈው በጀት ዓመት ጋር ሲነጻጸር በ32 በመቶ ያህል ቀንሷል። ይህም ማለት የዛሬ ዓመት በአንድ ዶላር ሲሸጥ የነበረው ቡና ዛሬ ወደ 68 ሳንቲም ወርዷል ማለት ነው። በዓለም ገበያ የቡና ዋጋ መውረድ ኢትዮጵያ ለውጭ ገበያ የምታቀርበውን የቡና መጠን በእጅጉ ቀንሶታል። ወደ ውጭ ገበያ የሚላከው የቡና መጠን መቀነስ ደግሞ በአገሪቱ የውጭ ምንዛሪ ግኝት ላይ ጫና ይፈጥራል።
ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ችግሩን ማቃለል በሚቻልባቸው መንገዶች ላይ ትኩረት አድርጎ እየሠራ መሆኑን የገለጹት ዋና ዳይሬክተሩ፤ በተለይም ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ እንዲሁም የተንዛዛ የነበረውን የገበያ ሰንሰለት በማሳጠር የኢትዮጵያ ቡና በዓለም ገበያ ተወዳዳሪ መሆን እንዲችል በርካታ ሥራዎችን ሲሰራ መቆየቱን አስታውቀዋል።
በተለይም ባለፉት ሁለትና ሶስት ዓመታት የቡናን ጥራት ለማስጠበቅ ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን በርካታ ሥራዎችን ሲሠራ እንደነበረ ዋና ዳይሬክተሩ ጠቅሰዋል። የተሠሩት ሥራዎችም የኢትዮጵያ ቡና በዓለም አቀፍ ገበያ ተወዳዳሪ መሆን የሚያስችለው መሆናቸውን ገልጸው፣ ከእነዚህም መካከል አንዱ በየጊዜው የሚዋዥቀውን የዓለም የቡና ገበያ ዋጋ መቋቋም የሚችል የምርት አይነት ማምረት አንዱና ቁልፍ ጉዳይ እንደሆነ ጠቁመዋል።
እንደ ዋና ዳይሬክተሩ ገለጻ፤ በአሁኑ ወቅትም ዓለም አቀፍ ደረጃ የቡና ዋጋ መውረዱን ተከትሎ ቡና ላኪዎች ቡናውን በሚፈለገው መጠን ወደ ገበያ እያወጡ አይደለም። ለዚህም ዋናው ምክንያት ነጋዴው ቡናውን የገዛበት ዋጋ እና አሁን ያለው የዓለም የቡና ዋጋ ሰፊ ልዩነት በማምጣቱ ምክንያት ነው።
የተፈጠረውን የዋጋ ልዩነት ከግምት ውስጥ በማስገባት ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን ቡናው ወደ ውጭ ገበያ መውጣት የሚችልበትን መንገድ እያመቻቸ ይገኛል ሲሉም ዶክተር አዱኛ አስታውቀዋል።
ወደ ውጭ ገበያ የሚወጣው ቡና መጠን መቀነስ በአገሪቷ የውጭ ምንዛሪ ግኝት ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ እንደሚያሳድር አመልክተው፣ ቡናው ወደ ውጭ ገበያ መውጣት እንዳለበት አስገንዝበዋል። ለዚህም ባለስልጣን መሥሪያ ቤቱ ከፍተኛ ጥረት እያደረገ መሆኑን ገልጸዋል።
ዋና ዳይሬክተሩ እንዳሉት፤ በአሁኑ ወቅት ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ እያከናወናቸው ከሚገኙ በርካታ ሥራዎች መካከል ነጋዴው ቡናውን መሸጥ የሚችልባቸውን አዳዲስ ገበያዎች በማፈላለግ እየተንቀሳቀሰ ያለበት ሁኔታ ይጠቀሳል። ለዚህም በተለያዩ ዓለም አቀፍ ኤግዚብሽኖች ላይ ነጋዴዎች መሳተፍ የሚችሉበትን ምቹ ሁኔታ በመፍጠር ቡና ላኪዎች ተሳታፊ እንዲሆኑ ተደርጓል፤ ኤክስፖርተሮች ገበያ እንዲያፈላልጉ ተሰርቷል።
አዳዲስ ገበያ የማፈላለግ ሥራው ከኤምባሲዎች ጋርም መሰራቱን ዋና ዳይሬክተሩ ጠቅሰው፣ በቅርቡ ከአሜሪካ፣ ከጀርመን፣ ከቤልጂየምና ከሌሎች አገራት ጋር አዳዲስ የገበያ ኮንትራቶችን ለመፈራረም የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች እየተሠሩ እንደሆነ ዋና ዳይሬክተሩ ተናግረዋል። በቀጣይም ቡና ላኪዎች ከእነዚህ አገራት ጋር ተፈራርመው ቡናውን ወደ ለውጭ ገበያ ሊያቀርቡ እንደሚችሉ ጠቅሰው፣ ይህ አንዱ መፍትሔ መሆኑን አመላክተዋል።
በአሁኑ ወቅት መጠኑ ያነሰ የቡና ምርት ወደ ውጭ ገበያ መላኩን የጠቀሱት ዋና ዳይሬክተሩ፤ ለእዚህ ምክንያቱ በዓለም ገበያ የቡና ዋጋ ማሽቆልቆልን ተከትሎ ላኪዎች የሚጠበቀውን ያህል ቡና ባለመላካቸው ሳቢያ መሆኑን ገልጸዋል።
ዋና ዳይሬክተሩ በ2015 በጀት አመት አስር ወራት ውስጥ ለውጭ ገበያ የተላከው ቡና ምንም እንኳን በመጠን ያነሰ ቢሆንም፣ የተገኘው ገቢ ካለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር የተሻለ ነው›› ሲሉ ገልጸዋል። በበጀት ዓመቱ አጠቃላይ አንድ ነጥብ ስምንት ቢሊዮን ዶላር ለማግኘት ታቅዷል ያሉት ዶክተር አዱኛ፣ በአስር ወራት ውስጥ ለውጭ ገበያ ከተላከው ቡናም አንድ ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር መገኘቱን አስታውቀዋል። ይህን ዕቅድም በቀጣይ ሁለት ወራት ማሳካት ይቻላል ነው ያሉት።
ዓመታዊ እቅዱን ለማሳካት ከሚሠሩ ሥራዎች ጎን ለጎን የቡና ባለቤት የሆነው አርሶ አደር ተጠቃሚነቱን ማረጋገጥ የሚያስችሉ በርካታ ሥራዎች መሰራታቸውን የጠቀሱት ዋና ዳይሬክተሩ፤ ቡና አምራች የሆነው አርሶ አደር ከዚህ ቀደም ከዘርፉ የሚያገኘው ጥቅም ዝቅተኛ እንደነበረ አስታውሰዋል። በአሁኑ ወቅት ይህን ችግር በመፍታት መንግሥት የአሰራር ማሻሻያዎችን በማድረግ የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እየሠራ መሆኑን ተናግረዋል።
እንደ ዋና ዳይሬክተሩ ማብራሪያ፤ የኢትዮጵያ የቡና ንግድ ስርዓት የተንዛዛና ረጅም ሰንሰለት ያለው በመሆኑ በተለይም በግብይት ሂደቱ በርካታ ችግሮች ሲፈጠሩ ቆይተዋል። ቡናው ኤክስፖርተሩ እጅ እስኪደርስ እሴት የማይጨምሩ በርካታ ሂደቶች ነበሩበት፤ ይህም የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት ወደ ኋላ ሲጎትት ኖሯል።
ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት ከፍ ለማድረግ የተለያዩ ሥራዎችን መሥራት እንደቻለም ዶክተር አዱኛ ተናግረዋል። ከእነዚህም መካከል አርሶ አደሩ ያለማውን ቡና በቀጥታ ራሱ ኤክስፖርት ማድረግ የሚችልበትን የአሰራር ሥርዓት መዘርጋት አንዱ ነው ሲሉ ጠቅሰዋል።
ለአብነትም አርሶ አደሩ ያለማውን ቡና በራሱ ወደ ውጭ ገበያ ከመላክ በተጨማሪ በራሱ ወደ ውጭ ገበያ መላክ ካልቻለ ለቡና አቅራቢ እንዲያቀርብና አቅራቢው ደግሞ ለላኪው እንዲያደርስ በማድረግ ረጅም የነበረውን የግብይት ሰንሰለት በማሳጠር ግብይቱ በሶስት ደረጃ መጠናቀቅ እንዲችል ተደርጓል ብለዋል። ይህም በአርሶ አደሩ ተጠቃሚነት ላይ ትርጉም ያለው ለውጥ በማምጣት ውጤት እያስመዘገበ መሆኑን ነው ያብራሩት።
እሳቸው እንዳሉት፤ የቡናና ሻይ ባለስልጣን በቡና የግብይት ሂደት ውስጥ የነበረውን ረጅም ሰንሰለት በመቁረጥ ቡናው ሶስት ደረጃዎችን ብቻ አልፎ ለገበያ እንዲቀርብ ያደረገ ሲሆን፤ በዚህም ቀደም ሲል 40 በመቶ ብቻ የነበረውን የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት ዘንድሮ ወደ 80 እና 90 በመቶ ከፍ እንዲል ማድረግ ተችሏል።
ይህም ማለት ቡና በቀጥታ ለውጭ ገበያ የሚልኩ አርሶ አደሮች 100 በመቶ ተጠቃሚ መሆን የቻሉበት ሁኔታ እንዲፈጠር ማድረጉን ጠቅሰው፣ ሁለት ደረጃዎችን ማለትም ቡና አቅራቢውንና ላኪውን ብቻ ተጠቅመው ቡና ወደ ውጭ ገበያ የሚልኩ አምራቾች ደግሞ ከ80 እስከ 90 በመቶ ማግኘት መቻላቸውን አመልክተዋል። በመሆኑም የኢትዮጵያ መሰረታዊ ችግር የነበረውን የተንዛዛ የግብይት ሥርዓት ቆርጦ በመጣል ችግሩን መፍታት እንደተቻለ አስረድተዋል።
መረጃዎች እንደሚጠቁሙት፤ የኢትዮጵያ 60 በመቶ የሚሆነው የቡና ምርት ለውጭ ገበያ የሚቀርብ ሲሆን፣ 40 በመቶ ያህሉ ደግሞ ለአገር ውስጥ ፍጆታ ይውላል። የዓለም የቡና ዋጋ በመውረዱ ምክንያት በአሁኑ ወቅት ወደ ውጭ ገበያ እየቀረበ ያለው የኢትዮጵያ ቡና በመጠን ያነሰ ቢሆንም፣ በውጭ ምንዛሪ ግኝቱ ካለፈው በጀት ዓመት የተሻለ እንደሆነ ከባለስልጣን መስሪያ ቤቱ የተገኘው መረጃ ያመላክታል።
በቀጣይም የኢትዮጵያ ቡና በየጊዜው ከፍ ዝቅ በማለት የሚዋዥቀውን የዓለም የቡና ዋጋ መቋቋም እንዲችል ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ በርካታ ሥራዎችን እንደሚሠራ ጠቁመው፣ የሚገጥመውን የገበያ ችግር መሻገር የሚቻለው ውጤታማ በሆኑ ሥራዎች እንደሆነ ዋና ዳይሬክተሩ ጠቁመዋል። በተለይም በምርትና ምርታማነት፣ በጥራትና በግብይት ሂደት መሠራት ያለባቸው የቤት ሥራዎች ስለመኖራቸው አመልክተዋል።
ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ እንዲሁም ጥራት ያለው የቡና ምርት ለማምረት የተለያዩ ጥረቶች መደረጋቸውን የጠቀሱት ዋና ዳይሬክተሩ፤ በቅርቡ ዓለም አቀፍ የቡና መመሪያ መጽሐፍ ወደ አማርኛ መተርጎሙ ለዘርፉ ዕድገት ትልቅ ድርሻ እንዳለው ተናግረዋል። ዓለም አቀፍ የቡና ማህበር ከዩኤን ድርጅት ጋር በመተባበር በተለያዩ አገራት ያለውን የቡና አመራረትና የግብይት ስርዓት ቀምሮ በእንግሊዝኛ ያዘጋጀውን የቡና መመሪያ መጽሐፍ ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ አማርኛ በመተርጎም ወደ ሥራ ማስገባት መቻሉን አስታውቀዋል።
እሳቸው እንዳሉት፤ የቡና መመሪያ መጽሐፉ እንደ አዋጅና ደንብ ሳይሆን አጋዥ ሆኖ የሚያገለግል ነው፤ አምራቹ መጽሐፉን ተጠቅሞ ውጤታማ ሥራ መስራት ይችላል። ለአብነትም ዘር ለማባዛት የፈለገ አንድ ሰው እንዴት ማባዛት እንዳለበትና ሌሎች አጠቃላይ መረጃዎችን ከመጽሐፉ ማግኘት ይችላል።
ስለ ቡና አጠቃላይ መረጃዎችን የያዘው ይህ መጽሐፍ የዩኒቨርሲቲ መምህራን ተማሪዎቻቸውን ማስተማር የሚችሉባቸው መረጃዎች እንዲሁም የግብይት መረጃዎችን የያዘ ሲሆን፤ ኢትዮጵያ ባለፉት አስርና አስራ አምስት ዓመታት ውስጥ የነበራት የቡና ኤክስፖርት ልምድ ምን ይመስላል የሚለውንና የት ቦታ ላይ ሰፊ ሥራ መሥራት እንደሚገባ ይዳስሳል።
መጽሐፉ የተለያዩ አገራትን ተሞክሮ ቀምሮ የያዘ በመሆኑ ኢትዮጵያም በዘርፉ ከምትሠራቸው ሥራዎች መካከል ባለ ልዩ ጣዕም ቡና ዝግጅት ላይ ከኢትዮጵያ የተወሰዱ ልምዶች ተቀምረውበታል። ከዚህም ባለፈ መጽሐፉ አዳዲስ የገበያ አማራጮችንም ቀምሮ የያዘ በመሆኑ የትኛውን ስርዓት ብንከተል የተሻለ ገበያ ማግኘት ይቻላል የሚለውን ያመላክታል። መጽሐፉም በባለሙያዎች አማካኝነት እያንዳንዱ አምራች አርሶ አደር ጋር ተደራሽ በመሆን አገልግሎት የሚሰጥ ይሆናል።
ፍሬሕይወት አወቀ
አዲስ ዘመን ግንቦት 9/2015