በኢትዮጵያ የመገናኛ ብዙሀን አጀማመር ከህትመት ሚዲያው ጋር የሚገናኝ እንደሆነ በርካታ ፀሀፍት ይስማማሉ። በአፄ ምኒልክና በአፄ ኃይለስላሴ ዘመናት የህትመት ውጤቶች አጀንዳ በይዘት የየነገስታቱ ፍፁምነት የሚሰብኩ እንደነበሩ ይታወቃል።
በደርግ ዘመነ መንግስትም በአንፃሩ ቀደም ብለው ይታተሙ የነበሩ የህትመት ውጤቶችን በመዝጋትና በመውረስ ዘርፉን ጠቅልሎ በመያዝ የሶሻሊዝም ፕሮፖጋንዳ መሳሪያ አድርጓቸዋል። የህትመት ውጤቶቹም በሙሉ በቅድመ ምርመራ ማለፍ ግድ ነበረባቸው።
ከ1983 ዓ∙ም በፊት የነበሩት የሕትመት ውጤቶች የየስርዓቱ አመስጋኝና አወዳሽ፤ የታዘዙትን ብቻ የሚፅፉ የስርዓቱ ልሳኖች፣ የሐሳብ ልዩነት ማስተናገድ በፍፁም የማይችሉ፣ ጥብቅ የሆነ ቅድመ ምርመራ የሚደረግባቸው ፤ የግሉ ዘርፍ የማይሳተፍባቸውና የነፃ ሚዲያ ጉዳይ ሊታሰብ የማይቻልባቸው ዘመናት ነበሩ።
የደርግ ስርዓት በተገረሰሰበት ማግስት ግን ሐሳብን በነፃነት የመግለፅ መብት ለመተግበር የሚረዱ በርካታ የፕሬስ ውጤቶች ብቅ ብቅ ማለት ጀመሩ።ለፕሬስ ነፃነትም ሆነ አጠቃላይ ዘርፉን ለማሳደግ በርካታ አወንታዊ እርምጃዎች ተወስደዋል። የአመለካከትና ሃሳብን በነፃ የመያዝና የመግለፅ መብት በሕገመንግሰቱ አንቀፅ 29 ተደነገገ። ነፃ ፕሬስ መፈቀዱን ተከትሎ በይዘትና በአይነት ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው የግል ህትመት ውጤቶች ለገበያ ቀርበዋል።
የሃገራችን የፕሬስ ነጻነት የጅማሮውን ያህል ሳይሆን በሂደት የተለያዩ ህጎች ወጥተው ነፃነቱ አጣብቂኝ ውስጥ እየገባ መጥቷል። በመሆኑም ድንበር የለሹ የጋዜጠኞች ቡድን እአአ በ2017 ባወጣው የፕሬስ ነጻነት ደረጃ አገሪቱ 180ኛ ደረጃን መያዟን ይፋ አደረገ። በዚህ ወቅት የተለየ ነገር ባለመኖሩ በ2018 ሪፖርቱ 150ኛ ናት ሲል ያስቀመጣቸው ምክንያቶች ውስጥ የኢንተርኔት መዘጋት ተጠቃሽ ነው።
በተለየ ሁኔታ የወጣው የፀረ ሽብር ህጉ ጋዜጠኞችን ህግ ጥሳችኋል በሚል ለእስር ዳርጓቸዋል። አገሪቱ ባጋጠማት ችግር ምክንያት ያወጣችው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅን ተከትሎ የሰላ ሂስ የሰጡ ጋዜጠኞችን በማሳደድ ለእስር በመዳረግ ረጅም ዓመታት ቅጣት ተወስኖባቸው ነበር ሲልም ቡድኑ ለሪፖርቱ አስረጅ አድርጎ አቅርቦታል። ከዚህ ጋር ተያይዞ አንዳንድ የመገናኛ ብዙሀን በአገሪቱ እንዳይተላለፉ/ጃም/ ይደረጉ ነበር። ይህ ሁሉ ተግባር የአገሪቱን የፕሬስ ነጻነት አይሆኑ አደረገው።
ከላይ የተጠቀሱት ቁልፍ የፕሬስ ነፃነትን አፋኝ ተግባራት ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ ለውጡን ተከትሎ እንዲወገዱ ተደርገዋል። የታሰሩ ጋዜጠኞች ተፈትተዋል፤ አፋኝ ናቸው የተባሉ ህጎችም እየተሻሻሉ ነው፤ በውጭ ሃገር የነበሩ መገናኛ ብዙሀንም አገር ቤት ድረስ ገብተው ሀሳብን በነፃነት እንዲያስተላልፉ ተፈቀደ፤የተዘጉ ድረ ገጾች ተከፈቱ። የዚህ ሁሉ ለውጥ ድምር ውጤት የአገሪቱን የፕሬስ ነጻነት ደረጃ አሻሽሎታል።
ድንበር የለሹ የጋዜጠኞች ቡድን ኢትዮጵያ 40 ደረጃዎችን አሻሽላ 110ኛ ሆናለች ሲል ይፋ አድርጓል። በፕሬስ ነጻነት ለመጣው ለውጥ እውቅናም በመስጠት የዘንድሮ የዓለም የፕሬስ ነጻነት ቀን ኢትዮጵያ እንድታዘጋጅ ፈቀደ። ይሕ ለዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታችንም ትልቅ አቅም ሆኖ ይገኛል።
የአገራችን የፕሬስ ነጻነት አሁን የደረሰበት ለመብቃት ብዙ ፈተናዎችን እና ውጣ ውረዶችን ቢያልፍም ዛሬ ደግሞ ነፃነቱን ባየንበት ዓይን ከወገንተኝነት ርቀን፤የሀሳብ ብዝሀነትን በማስተናገድ፤ ራስን ተቆጣጥሮ ሙያዊ ስነምግባሮችን ተከትሎ፤ከመንግስት፣ ከተቋማትና ከግለሰብ ጣልቃ ገብነት ነፃ ሆኖ አለመስራት የወቅቱ አንኳር ፈተናዎች ናቸው። በመሆኑም በአሁኑ ወቅት ይህን ይህን ለምን አተምክ፤ለምንስ አስተላለፍሽ የሚል አለመኖሩ የፕሬስ ነጻነቱን ሙሉ ቢያደርገውም እንደ አንድ ሙያ ነፃነቱን በአግባቡ መጠቀም አለመቻል እየተስተዋለ ነው።
የመገናኛ ብዙሀን ሰብዓዊነትን ማጣት የለባቸውም። የአንድን ቡድን አሊያም ወገን ስሜት እና ጉዳይ በማራገብ ሰዎችን እርስ በእርስ ከማፋጀት ተግባር ሊሳተፉ አይገባም። የየዘገባዎቻችን ይዘት የሚፈጥሩትን ሰብዓዊ ቀውስ ኃላፊነት መውሰድ ግድ ይላል። በእርግጥ ይሕ አንዱ የጋዜጠኝነት መርህ በመሆኑ በሚገባ እንዲመለስ የሚዲያ ካውንስል በማቋቋም መፍታት ተገቢ ነው።
በአጠቃላይ አገራችን የፕሬስ ነጻነት በተለያዩ መንግስታዊ ስርዓቶች እየተፈተነ ዛሬ ላይ ደርሷል። አሁን ያለነው ሁሉም ባለድርሻ አካል ደግሞ በእጃችን ያለውን የፕሬስ ነጻነት ከወገንተኝነት ፀድቶ በህግና በስርዓት በመጠቀም ህዝብን እንዲያገለግልበት ማድረግ ከዚህም ሲያልፍ ለአገሪቱን የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ጉልበት እንዲሆን ማድረግ ይጠበቅብናል።
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 24/2011