የፋሽኑ ዘርፍ የተሰጠው አበረታች ትኩረት

የፋሽን ኢንዱስትሪ ጥቅምን ለማወቅ ያደጉ ሀገሮችን ማየት ብቻ በቂ ነው፡፡ ለምሳሌ ወደ ኢትዮጵያ የሚገቡ ምርቶችን ብንመለከትና ያንን እንዳይገባ በሀገር ምርት መተካት ቢቻል የሚያስገኘው ጥቅም ብዙ መሆኑን መገመት ይቻላል። በሌላ በኩል ፋሽን እያደገ ሲመጣ የተለያዩ የዓለም ዲዛይነሮች፣ ሞዴሎች፣ ፋሽን ተከታዮች ወደ ሀገራችን ይዘው የሚመጡት የውጭ ምንዛሪ በቀላሉ የሚታይ አይደለም።

በተጨማሪም እነዚህ ዓለም አቀፍ የፋሽን ባለሙያዎች ወደ ኢትዮጵያ ሲመጡ ሆቴል ይጠቀማሉ፣ ይዝናናሉ፣ የተለያዩ ዕቃዎችን ይሸምታሉ፣ ከፍ ሲልም እዚሁ የመሥራት ፍላጎት ሊኖራቸው ይችላል፡፡ ስለዚህ የፋሽን ኢንዱስትሪ ሀገሪቷን በተወሰነ መልኩ ሊደግፍና ሊያቀና የሚችል መሆኑ አያከራክርም። ይህም የቱሪዝም ፍሰቱ አሁን ካለበት በበለጠ እንዲጨምር ማድረጉ ሊሰመርበት ይገባል። አክሱም፣ ላሊበላና ሌሎች ታሪካዊ ቦታዎችን ሊጎበኙ የመጡ የውጭ ሀገሮች ዜጎች ወደ ፋሽኑ ጎራ ብለው ቆይታቸው ሲራዘም የሚያስገኙት ገቢ ከፍ ይላል፡፡

የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች አልባሳትን ለዓለም ማስተዋወቅ ለዘርፉ እድገት ቁልፍ ሚና እንዳለው ተደጋግሞ ተነግሯል፡፡ በዚህም ኢትዮጵያዊ የሆነውን ዕምቅ የባሕል አልባሳታችንን ለዓለም ማሳወቅና በሀገሪቱ ኢኮኖሚ ፋሽን የራሱን አስተዋጽኦ እንዲኖረው ለማድረግ ቀላል እንደሚሆን ይታመናል።

ፋሽን የሚያድገው በግለሰብ ብቻ አይደለም፡፡ ለዚህም ዕምቅ ችሎታ ያላቸው ወጣት ዲዛይነሮች አሉ፡፡ ለእነርሱ ደግሞ ዕድል መስጠትና መድረክ መፍጠር ኢንዱስትሪውን ከሚያሳድጉት መካከል አንዱና ዋነኛ ነው፡፡ በሌላ በኩል እነዚህ ዲዛይነሮች በየአካባቢው እየዞሩ የሀገራቸውን የባሕል አልባሳት ምቹ አድርገው ለገበያ በማቅረብና ራሳቸውን ኢንተርናሽናል ዲዛይነር ለማድረግ ነው ጥረት የሚደረገው፡፡

የሀገራችን አልባሳት በአብዛኛው የሚሠሩት በጥጥ በመሆኑ ለበጋም ሆነ ለክረምት ምቹና ጤናማ በመሆኑ ቀልብ የሚስብ ነው፡፡ ለዚህም ነው አብዛኛዎቹ የዓለም ሀገሮች ዲዛይነሮች ጥሬ ዕቃ ከኢትዮጵያ ወስደው መልሰው የሚሸጡልን፡፡ ታዲያ እንደዚህ ዓይነት መድረኮችን በመፍጠር ዲዛይነሮችን በማበረታታት ከሀገራቸው አልፈው አኅጉራቸው፣ ከዚያም ዓለም አቀፍ ብራንድ እንዲኖራቸው ማድረግ ይገባል።

ለዚህም የኢትዮጵያ የፋሽን ዲዛይን ማኅበር እንዲሁም ዘርፉን የሚመራው መንግሥታዊ አካል በጋራ መሥራት እንዳለባቸው ይታመናል። ያም ሆኖ ባለፉት ዓመታት ሁለቱ አካላት ተቀራርበው በመሥራት ረገድ ብዙ ርቀት ሲጓዙ አልታየም። እንደመንግሥትም ለዘርፉ ተገቢው ትኩረት ተሰጥቷል ለማለት አያስደፍርም።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን ይህን የሚቀይሩ እንቅስቃሴዎች እየታዩና መንግሥትም ለዘርፉ ትኩረት እየሰጠ መጥቷል። ለዚህም የኢትዮጵያ የፋሽን ዲዛይን ማኅበር የባሕልና ስፖርት ሚኒስቴር የጥባበት ዘርፍ ከሚከታተላቸው ማኅበራት መካከል አንዱ መሆኑ ማሳያ ነው።

ጥበባት ለሀገር ማንነት እና እድገት ቁልፍ ጉዳዮች መሆናቸውን የኪነጥበብ ፖሊሲው ላይ በግልፅ ተቀምጦ ይገኛል። ኢትዮጵያ በጥበባት ዘርፍ የቆየ ታሪካዊ ዳራ ያላት ሀገር እንደመሆኗ ዘርፉም የሀገራችን ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ገፅታ በመገንባታ ደረጃ የላቀ ድርሻ እያሳየ ይገኛል። ይህንንም ተከትሎ የባሕልና ስፖርት ሚኒስቴር የኪነጥበብ ሥነጥበብ ፈጠራ ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ነብዩ ባዬ (ረ/ፕ) ዘርፉን ለማጠናከር ከኢትዮጵያ የፋሽን ድዛይን ማሕበር ጋር ሰሞኑን ውይይት አድርገዋል።

ኢትዮጵያ በእደ ጥበብ ዘርፍ በተለይም በፋሽን እና በሞዴሊንግ ዘርፍ ከፍተኛ ሀብት ያላት ሀገር በመሆኗ ሀገሪቱ ከዘርፉ የምታገኘውን ጠቀሜታ ከፍ ለማድረገ ከዘርፉ ማሕበራት ጋር መሥራት እንደሚገባ በሁለቱ አካላት ውይይት ወቅት ተነስቷል።

የጥበብ ዘርፉ የማኅበረሰቡን የአብሮነት ተምሳሌት አልቀው የሚሳዩ ከመሆናቸውም ባሻገር የሥራ እድል በመፍጠር እንዲሁም ባሕላዊ እሴቶችን በዓለም መድረክ ጭምር የሚያስተዋውቁ መሆናቸው በውይይቱ ወቅት ተጠቅሷል።

የኢትዮጵያ የፋሽን ድዛይን ማሕበር ከዚህ አንፃር ከሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ጋር በቀጣይ አብሮ ለመሥራት በሚያስችለው ጉዳዮች ላይም ውይይት አድርጓል። ማሕበሩ የማሕበረሰቡን ባሕል ጠብቆ ባሕላዊ እሴቶችን ከማስተዋወቅ ባሻገር፣ የኪነጥበብ ዘርፍን አበርክቶ ለማስፋትም እንደሚሠራም አስታውቋል።

እያደገ የመጣው የፋሽን ኢንዱስትሪ ያለውን እምቅ አቅም አሟጦ ለመጠቀም የግሉ ዘርፍ ሚና የማይተካ ነው፡፡ በመሆኑም ሀገር በቀል እውቀቶችን ከፋሽን ኢንዱስትሪው ጋር አሰናስሎ የዜጎችን ተጠቃሚነት ለማላቅ ሥነ-ምህዳሩን ምቹ ለማድረግ የተጀመሩ ሥራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉም ተጠቁሟል።

በጋዜጣው ሪፖርተር

አዲስ ዘመን ሰኞ ሐምሌ 7 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You