
ዜጎች ሕጋዊ በሆነ መንገድ ወደተለያዩ ሀገራት በመሔድ መሥራት እንዲችሉ በኢትዮጵያ መንግሥት በኩል የተለያዩ ጥረቶች እየተደረጉ ቢሆንም ዛሬም ሕጋዊ ባልሆነ መንገድ የሚደረገው ፍልሰት ቀጥሏል:: የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት የምርመራ ቡድን በትናንትናው ክፍል ሁለት ዕትሙ ዜጎች፣ ሕጋዊ ባልሆነ መንገድ ሲሰደዱ የሚደርስባቸው ጉዳት ምን ያህል እንደሆነ በምርመራ ያገኘውን ዘገባ ለንባብ አብቅቷል:: በዛሬው ዕለት ደግሞ ሕጋዊ ያልሆነው መንገድ ላቅ ያለ ጉዳት የሚስተናገድበት ከሆነ ማስቆም አሊያም መቀነስ ያልተቻለው ለምንድን ነው? ከዚህ አኳያስ የሀገራት ተሞክሮ ምን ይመስላል? ሲል ያጠናቀረውን የምርመራ ዘገባ እነሆ ብሏል::
ክፍል ሶስት
ማስቆም ወይም መቀነስ ለምን አልተቻለም?
መደበኛ ያልሆነ ፍልሰት ጉዳት ተደጋግሞ ቢነገርም፤ ችግሩን ለመቅረፍ የተለያየ ግብረኃይል ቢቋቋምም፤ ሚዲያዎች ስለጉዳዩ በተደጋጋሚ ቢዘግቡም ችግሩ ከመቀነስ ይልቅ እየጨመረ ስለመሄዱ የተለያዩ መረጃዎች ያመላክታሉ:: ታዲያ ይህን ችግር ቢቻል ማስቆም ካልሆነም ለመቀነስ ለምን አዳጋች ሆነ? የምጣኔ ሀብት ባለሙያ እና በአውሮፓ ኅብረት ፕሮጀክት ለኢትዮጵያ መንግሥት ለሚሰጡት ድጋፍ ቡድን መሪ ጉቱ ቴሶ (ዶ/ር) እንደሚሉት፤ ኢ-መደበኛ ፍልሰት በኢትዮጵያ ዛሬ የተጀመረ ሳይሆን ረጅም ታሪክና ሰንሰለት ያለው ብዙ አካላት የሚሳተፉበት ነው::
እንደ እርሳቸው ገለጻ፤ መደበኛ ያልሆነ ፍልሰት እንዳይቆም ወይም እንዳይቀንስ ከሚያደርጉ ነገሮች ዋነኛው በሀገር ውስጥ በቂ የሥራ ዕድል አለመፈጠር ነው:: የሥራ ዕድል ፈጠራ ላይ ብዙ ችግሮች አሉ:: ኢ-መደበኛ ፍልሰትን ለመከላከል ዜጋው ከሀገር ሳይወጣ እንዲሠራ ከማድረግ አንጻር እንደ ሀገር መሠራት ያለባቸው ነገሮች በበቂ ሁኔታ አልተሠሩም:: ስለሆነም ብዙ ወጣት በሥራ አጥነት ምክንያት ሀገር ጥሎ ይወጣል::
በአቋራጭ እና በፍጥነት ለመክበር መፈለግና የሥራ ባሕል አለማዳበር ሌላው ተጠቃሽ ጉዳይ ነው የሚሉት ጉቱ (ዶ/ር)፣ በአካባቢ ያሉ ምቹ ሁኔታዎችን ዐይን ገልጦ አለማየት፤ በቤተሰቦቹ እጅ ያሉትን ሀብቶች እንደ ቡና፣ እርሻ እና ከብቶች ያሉ አማራጮችን አለማስተዋል ሌላው የችግሩ ምክንያት ነው ይላሉ::
በኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ አመራር እና አስተዳደር ኮሌጅ ምክትል ዲን፣ በሥራ እና ክህሎት ሚኒስቴር የሥራ እድል ፈጠራ አማካሪ የቦርድ አባል እና የፍልሰትና ልማት ትምህርት ክፍል መምህር ረዳት ፕሮፌሰር መሐመድ አሊ እንደሚሉትም፤ የሕዝብ ቁጥር ዕድገት ባለመመጠኑ እንደ ሀገር ያለን የወጣት ቁጥር በጣም ከፍተኛ ነው:: ካለው የሕዝብ ቁጥር ውስጥ 70 በመቶ የሚሆነው ወጣት ነው:: ስለሆነም በመንግሥት ብቻ ለዚህ ሁሉ ወጣት የሥራ እድል መፍጠር ከባድ ነው:: ይህም ሁኔታ ኢ-መደበኛ ፍልሰቱ እንዳይቆም ያደርጋል።
አንደ ሀገር የሚወጡ ሕጎች እና አዋጆች በሚገባ በተግባር ላይ አለማዋላቸውም እንደ መንስዔ ያነሱታል:: በኢትዮጵያ ኢ-መደበኛ ፍልሰትን ለመከላከል የሚያስችል አዋጅ ወጥቷል። አዋጁን ሥራ ላይ ማዋል ግን ብዙ ክፍተቶች አለው። ኢ-መደበኛ ፍልሰትን ለመቀነስ በሚደረገው እንቅስቃሴ ላይ የተቋማት ቅንጅታዊ ሥራ ላይ ክፍተት ይታያል።
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አርትስ ኤንድ ሂዩማኒቲስ መምህር እና አጥኚ ጉዲና በሹዳ (ዶ/ር) እንደገለጹት፤ ሕጋዊ ባልሆነ መንገድ ከሀገር የሚወጡ ዜጎች በሚፈለገው ደረጃ መቀነስ ከባድ የሆነበት ምክንያት የሥራ አጥነትን ቁጥር በሚፈለገው ደረጃ መቀነስ ባለመቻሉና የሀገራችን ኢኮኖሚ ለዜጎቹ በሚፈለገው ልክ የሥራ እድል ለመፍጠር በቂ ባለመሆኑ ነው ይላሉ:: ሕጋዊ ባልሆነ መንገድ ዜጎችን ድንበር የሚያሻግሩ ደላሎች ላይ የሚወሰደው ርምጃም በቂ እና ተመጣጣኝ አለመሆኑንም አክለውም በምክንያትንት ያነሳሉ:: የደላሎቹ አሠራር ውስብስብና ድብቅ ስለሆነም ፈልጎ በሕግ ተጠያቂ ማድረግ ስለሚከብድ ችግሩ እንዳይቀረፍ አድርጓል ይላሉ::
ጠቅለል አድርገው ሲያስረዱም ለወጣቶች በቂ የሥራ ዕድል አለመፈጠር፣ ሕጋዊ ባልሆነ መንገድ ዜጎችን ድንበር የሚያሻግሩ ደላላዎች ላይ በቂ ርምጃ አለመወሰዱ፣ በቂ የብድር አገልግሎት አለመኖር፣ ተመላሾችን መልሶ የማቋቋም ሥራው ላይ የሚታዩ ክፍተቶች ለኢ-መደበኛ ፍልሰት አለመቀነስ ምክንያቶች መሆናቸውን ይናገራሉ።
በኢ-መደበኛ ፍልሰት ላይ ሰፊ የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርት ቢሰጥም ችግሩን ማስቆም አልተቻለም የሚሉት ደግሞ የኦሮሚያ ሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ ምክትል ኃላፊና የስምሪት ዘርፍ ኃላፊ አቶ አበቲ ሃጂ ናቸው:: እርሳቸው እንደሚሉት፤ ኢ-መደበኛ ፍልሰትን በሚፈለገው ደረጃ መቀነስ ያልተቻለበት ሦስት ምክንያቶች አሉ። አንደኛ በቅንጅት መሥራት ያለባቸው ሥራዎች በሁሉም ደረጃ ባለመሠራቱ ሲሆን፣ ሁለተኛው የሥራ አጥነት ችግርን በሚፈለገው ደረጃ መቀነስ አለመቻል ነው፤ ሦስተኛው ምክንያት ደግሞ ወጣቶች በሕገወጥ ደላሎች እና በጓደኞቻቸው በቀላሉ መታለል መቻላቸው ነው። በሕገወጥ ደላሎች ላይ የሚወሰደው ርምጃና በመውጫ በሮች በኩል የሚደረግ ቁጥጥርም በቂ አለመሆኑም ይህን ችግር ለመቅረፍ እንዳይቻል አድርጓል።
አቶ ደረጀ ተግይበሉ፣ በሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የሕገወጥ የሰዎች ዝውውር መከላከልና የተመላሽ ዜጎች ክትትልና ድጋፍ መሪ ሥራ አስፈፃሚ ናቸው:: ይህንን ችግር ማስቆም ወይ መቀነስ ለምን አልተቻለም? ለሚለው ጥያቄ መንግሥት ኢ-መደበኛ ፍልሰትን ለመከላከል ከሚሰጠው መረጃ ይልቅ የሕገወጥ ደላሎችን ማታለያ ወጣቶች መስማታቸው አንዱ ምክንያት ነው ይላሉ:: አያይዘውም ኅብረተሰቡ የመፍትሄ አካል ሆኖ ሕገወጥ ደላሎችን አጋልጦ አለመስጠቱም ችግሩ እንዳይቀረፍ አድርጓል። ሕገወጥ ደላሎችን በሕግ ተጠያቂ ማድረግ ላይ ክፍተት መኖር፣ መውጫ በሮች ላይ የቁጥጥር አለመጠናከር፣ የአመለካከት ችግርና የፍልሰት ፖሊሲ ቶሎ አለመጽደቅ ኢ-መደበኛ ፍልሰትን የሚያባብሱ ምክንያቶች ናቸው ሲሉም አክለው ያስረዳሉ።
ከእነዚህም በተጨማሪ የሃይማኖት አባቶች እና በየአካባቢው ተቀባይነት ያላቸው ትልልቅ ሰዎችና ቤተሰብ ጭምር ዜጎችን ሕጋዊ ባልሆነ መንገድ ወደ ውጭ ሀገር በመላኩ ሂደት ላይ መሳተፋቸውንም እንደተጨማሪ ምክንያት ይጠቅሳሉ::
በዋቻሞ ዩኒቨርሲቲ መምህርና በፍልሰት ጉዳዮች ለይ ለረዥም ዓመታት ምርምር ያካሄዱና መጽሐፍም ለንባብ ያበቁት ጸደቀ ላምቦሬ (ዶ/ር) እንዳሉት፤ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ሀድያ ዞን፣ ከምባታ ጠንባሮ ልዩ ወረዳ እና በከፊል ሀላባ ዞን ላይ አተኩረው በሠሩት ጥናት በአካባቢው ካለው ማኅበረሰብ 40 በመቶ የሚሆኑት ቤተሰባቸውን ወደ ውጪ ልከዋል። ይህ ከፍተኛ ፍልሰት በአካባበቢው መኖሩን የሚያመላክት ነው። የፍልሰቱ ዋነኛ ምክንያት ደግሞ የኢኮኖሚ ችግር እና የመሬት ጥበት መሆኑ በጥናቱ ታይቷል።
ከዚያ ባለፈም በጥናቱ የተለየው ሌላ ነገር በተወሰነ መልኩም ቢሆን የአመለካከት ችግር መኖሩን ማየት ችለናል። በአካባቢው ፍልሰትን ባሕል የማድረግ ነገር በስፋት የሚስተዋል ሆኗል። ልጁን ወደ ውጭ ሀገር የላከ ቤተሰብና ያልላከ ቤተሰብ ተብሎ በማኅበረሰቡ መካከል ልዩነት መፈጠሩ ችግሩን ለመቀነስ እንቅፋት መሆኑን ለመረዳትም ችለናል።
በአካባቢው ለወጣቶች ሰፊ የሥራ እድል የሚፈጥሩ ፋብሪካዎች አለመኖር ለፍልሰቱ ሌላኛው ምክንያት ነው። ኢ-መደበኛ ፍልሰት በአካባቢው በከፍተኛ ደረጃ የሰው ሕይወት እያጠፋ ቢሆንም ወጣቱ ዛሬም “ዕድሌን ልሞክር” እያለ ሕጋዊ ባልሆነ መንገድ ከሀገር እየወጣ ነው። በሕገወጥ መንገድ ከሀገር እየወጡ ካሉት ወጣቶች ውስጥ አብዛኛዎቹ በአግባቡ ስምንተኛ ክፍል እንኳን ያልደረሱ ናቸው።
በሕገወጥ ደላሎች ላይ ክስ ሲመሰረት ማኅበረሰቡ “በሽምግልና እንፈታለን” ይልና በተከሳሽና ከሳሽ መካከል በመግባት እያስማማ የሕግ ጉዳይ እንዲንዛዛ የማድረግ ክፍተትም በስፋት ይታያል። በደላሎች ላይ ክስ ከተመሠረተ በኋላ በቂ ማስረጃ አልቀረበም በማለት ጉዳዩ እንዲቀር የሚደረግበት አጋጣሚ በፍትህ አካላት ዘንድ የሚታይ ክፍተት ነው። ዋናዎቹ ሕገወጥ ደላሎች ከኢትዮጵያ ውጪ ኬንያ፣ ታንዛኒያ፣ ደቡብ አፍሪካና አረብ ሀገራት ስለሚኖሩም በሕግ ተጠያቂ ማድረግ ከባድ ነው። በሀገር ውስጥ ያሉ ሕገወጥ ደላሎችን አጋልጦ መስጠት ደግሞ በኅብረተሰቡ ዘንድ የሚታይ ክፍተት ነው።
ከዚህ በፊት በነበረው አካሄድ ወጣቱ በሀገር ሽማግሌዎችና በሀይማኖት አባቶች ተመርቆ ሕጋዊ ባልሆነ መንገድ ድንበር በመሻገር እሳት ውስጥ የሚገባው ብዙ ነበር። አሁን ይህ አካሄድ በመወገዙና በሕግም የሚያስጠይቅ በመሆኑ እየቀረ መጥቷል የሚሉት ጸደቀ (ዶ/ር)፣ በዚህ ረገድም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ኅብረተሰቡ እየነቃ ቢሆንም ደፍሮ ለማቆም ግን አልቻለም ሲሉ ይናገራሉ። እነዚህ ሁሉ ተደምረው ኢ-መደበኛ ፍልሰት ስር እንዲሰደድ አድርገዋል። የሀይማኖት ተቋማትም በቀጣይ ስለሚሞተው ሰው ማሰብ እና ምዕመኑ በዚህ ተግባር እዳይሳተፍ ከማስተማር ይልቅ ሞቶ የመጣውን ብቻ መቅበራቸው ችግሩ በሚፈለገው መጠን እንዳይቀንስ አድርጓል:: ማኅበረሰቡም ከፍተኛ ትኩረት የሚሰጠው ለኢኮኖሚ ጉዳይ እንጂ ስለሚሞተው ዜጋ አይደለም ይላሉ።
በአሁኑ ወቅት በዓለም ላይ መደበኛ ያልሆነ ፍልሰት በወንጀል ገንዘብ ከሚገኝባቸው እንቅስቃሴዎች ከአደንዥ እጽ ማዘዋወር ቀጥሎ በሁለተኛ ደረጃ ላይ ለመቀመጥ በቅቷል። ዜጎች የውስን ሰዎች የፍልሰት ጉዞ መሳካትን ብቻ በመመልከትና ሌሎች እነሱን ሊገጥሙ የሚችሉ ክፉ ነገሮችን አለማየትም በስፋት ይታያል።
በእኛ ጥናት የመዳረሻ ሀገራት ምርጫን በተመለከተ ወንድሙ ወይም እህቱ የሄዱባቸውን ሀገራት የመከተል አካሄድ 67 በመቶ ይደርሳል’። ስለሆነም በአብዛኛው ገንዘቡንም የሚከፍሉት እዚያው በመዳረሻ ሀገራት ያሉ ቤተሰቦች ናቸው። ድርድሩም ክፍያውም የሚፈጸመው እዚያው ነው። አከፋፈሉም በየደረጃው የሚፈጸም ነው።
በአሁኑ ወቅት ባለው ዋጋ ሴት ከሆነችና ለትዳር የምትፈልግ ከሆነ እስከ አንድ ነጥብ ስምንት ሚሊዮን ብር ይደርሳል። ለወንድ ከ760 ሺህ እስከ አንድ ሚሊዮን ብር ይገመታል።
በፍትህ ሚኒስቴር ብሔራዊ የፍልሰት ትብብር ጥምረት ሴክሬቴሪያት ኃላፊ አቶ አብርሃም አያሌው እንደሚሉት፤ ለችግሩ አንዱ መንስዔ በቂ ቅንጅታዊ አሠራር አለመኖር ነው፤ ቅንጅታችንም በሕግ በተቀመጠው እና በሚፈለገው ልክ አይደለም:: በተቀመጠው ልክና የሕጉን ዓላማ ሊያሳካ በሚያስችል መልኩ ተቀናጅተን እየሠራን አለመሆናችን ግልጽ ነው::
እንደ አቶ አብርሃም ገለጻ፤ ለችግሩ አለመቀረፍ ሌላው ምክንያት በኢትዮጵያ የፍልሰት ፖሊሲ አለመኖሩ ነው:: ከተረቀቀ ዓመታት ቢያስቆጥርም፤ እስካሁን ግን በሚኒስትሮች ምክር ቤት ጸድቆ ወደ ተግባር አልገባም::
ለምሳሌ ኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ አላት:: ይህ ማለት መንግሥት የውጭውን ጉዳይ በተመለከተ ምን አይነት ስትራቴጂ ይከተላል? የሚለውን የሚያሳይ ነው:: ለፍልሰቱ ግን ፖሊሲ የላትም፤ ፖሊሲ ሳይኖር ሕግ መኖሩ ደግሞ ከፈረሱ ጋሪው ቀደመ አንደማለት ነው:: የፍልሰት ፖሊሲ ባለመኖሩ ምክንያት አንደኛ ዓለም አቀፍ ድጋፍም እየቀነሰ ነው:: ተቋማትም በኃላፊነት የሚሠሩት እና የተቋማት ሕጎች የሚሻሻሉትም ፖሊሲ ሲወጣ ነው:: ፖሊሲ ባለመውጣቱ ምክንያት ብዙ ችግሮች እንዲኖሩ አድርጓል::
አቶ አብርሃም እንደሚናገሩት፤ እንደ ሀገር በሕገወጥ ፍልሰት እያደረሰብን ያለው ችግር ከሌሎቹም ሀገሮች በላይ ስለሆነ እየሠራን ያለነው ሥራ ከጉዳቱ አኳያ ሲጤን በጣም አነስተኛ ነው:: በቅጣት ረገድ እስከ 25 ዓመት ማስቀጣት፣ ንብረቶችን አግዶ ምርመራ የማድረግ ጅምሮቹ መልካም ናቸው:: ወደውጭ ሀገር ከሚሄዱ ዜጎቻችን ዘንድሮ በዘጠኝ ወር መረጃ ብቻ ከ370 ሺ በላይ በሕጋዊ መንገድ መሄዳቸውም ይበል የሚያሰኝ ነው:: ይህ ሊበረታታ የሚገባው ነገር ነው:: ነገር ግን እየደረሰ ካለው ጉዳት እና እየተፈጸመ ካለው ወንጀል አንጻር ይህ በቂ አይደለም::
ግንዛቤ መፍጠሪያ ሥራችን ምን ይመስላል? ምን ዓይነት ለውጥ አመጣ? የሚለው መሠራት አለበት:: ከደላሎቹ በላይ በወጣቱ ዙሪያ ግንዛቤ በመፍጠር ደረጃ ላቅ ብለን መታየት አለብን:: ግንዛቤ ፈጠራ ላይ እየሠራን ነው ከተባለም፤ እኛ የምናደርገው የግንዛቤ ፈጠራ፣ ወጣቶቹ ሀገራቸውን ጥለው እንዳይሄዱና ከሔዱም በሕጋዊ መንገድ እንዲሔዱ ለምን አላደረገም? የሚለውን ማጤንና በአግባቡ ማየት ይኖርብናል:: ለምሳሌ ድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር በምክትል ከንቲባው የሚመራ ምክር ቤት አቋቁመው በሕግ እየሠሩ ነው:: ነገር ግን ድሬዳዋ መሸጋገሪያ ከመሆኗ አንጻር አሁንም ችግሩ በጣም ከፍተኛ ነው ብለዋል::
እንደ ሴክሬቴሪያት ኃላፊው አባባል፤ በኢትዮጵያ ሕገወጥ ፍልሰት አሁንም ትልቅ ችግር ነው:: ለምሳሌ ኬንያ በዓመት የሚኖራት የተመላሾች ቁጥር በመቶዎች የሚቆጠሩ ብቻ ናቸው:: አንዳንዶቹ ሀገራት እንዲያውም ተመላሽ የላቸውም:: የኢትዮጵያ ግን የሚሄደውም ሆነ ተመላሽ ሆኖ የሚመጣው በተመሳሳይ በመቶ ሺዎች የሚቆጠር ነው::
የእኛ ችግር ከሌሎቹም ሀገራት በተለየ ውስብስብ ነው:: መሄድ ብቻ ሳይሆን መምጣትም ጭምር ነው:: የሚመጣው ደግሞ ባዶ ኪሱን ነው:: ሕሊናው ተጎድቶ ልቦናው ተሰብሮ፣ እግሩ ተቆርጦና በጥቅሉ አካል ጉዳተኛ ሆኖ ነው:: ይሁንና የተሰጠው ትኩረት በሚፈለገው ልክ አይደለም ይላሉ::
በፌዴራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ቢሮ የተደራጁ ወንጀሎች ምርመራ ክፍል ኃላፊ ኢንስፔክተር ጌቱ ሙሉጌታ እንዳሉት፤ በሕገወጥ መንገድ ዜጐችን ወደ ውጭ ሀገር የሚልኩ ደላላዎች ከሰዎቹ የሚቀበሉት ገንዘብ በራሳቸው የባንክ ሒሳብ ቁጥር እንዳይዘዋወር በማድረግ ራሳቸውን ለመደበቅ መሞከራቸውም የሕግ ማስከበር ሥራውን ላይ ፈተና ሆኗል ሲሉ ያስረዳሉ። ደላሎች ዘመናዊ ቴክኖሎጂ የሚጠቀሙ መሆናቸው፣ በጣም ከፍተኛ ገንዘብ የሚያንቀሳቅሱና ሰዎችን በገንዘብ የሚለውጡ መሆናቸውን ተከትሎ ለመያዝና ለሕግ ለማቅረብም አስቸጋሪ ነው።
ኢንስፔክተር ጌቱ፣ ደላሎችን የሚደግፉ፣ የሚተባበሩና መረጃ የሚሰጧቸው እንዲሁም መንገድ የሚያሳዩ ግለሰቦች አሉ። በየአካባቢው ከደላላ ጋር የሚሠሩ የወንጀሉ ቡድን መሪዎችና ሙሰኞች አሉ። ከዚህም አልፎ ደላላዎችን የሚደግፉ ግለሰቦች በመንግሥት መሥሪያ ቤት ውስጥም መኖራቸው በችግሩን አባባሽ ተጨማሪ ነዳጅ ሆነዋል ሲሉ ያስረዳሉ።
በጥቆማና በምርመራ ተይዘው ክስ ከተመሠረተባቸው በኋላ ምስክሮችን በማስፈራራት ፍርድ ቤት ቀርበው እንዳይመሰክሩ የሚያደርጉበት ሁኔታ እንዳለ ይገልጻሉ:: ለአንዳንዶቹ ደግሞ ገንዘብ በመስጠት ፍርድ ቤት ቀርበው እንዳይመሰክሩ እስከማድረግ ይኬዳል። አንዳንድ ደላሎች ደግሞ ተከሰው ፍርድ ቤት ከቀረቡ በኋላ እንደ ታመመ ሰው በተደጋጋሚ በችሎት ላይ ዝልፍልፍ ብለው በመውደቅ ችሎቱ ብይን እንዳይሰጥበትና በቀጠሮ ብዛት ምስክሮቹ እንዲሰላቹ፤ የፍርድ ሂደቱም እንዲራዘም የሚያደርጉ አሉ ሲሉ ችግሩን ለመፍታት ያልተቻለባቸውን ምክንያቶች ያስረዳሉ።
ኢ-መደበኛ ፍልሰትን ማስቆም ወይም መቀነስ ያልተቻለው ለምን ይሆን ስንል የተለያዩ ክልሎችንም ጠይቀናል:: በጅማ ዞን ሰራተኛና ማሕበራዊ ጉዳይ ጽህፈት ቤት የሥራ ስምሪት ቡድን መሪ አቶ ገመቹ በየነ እንዳሉት፤ በዞኑ ልጃገረዶች ስምንተኛ ክፍል ካጠናቀቁ ወደ ዱባይ መሄድ የተለመደ ነው:: አባጅፋር በሳዑዲ አረቢያ የሰሩት ዲፕሎማሲ በፍልሰቱ ላይ ተጽዕኖ ፈጥሯል ማለት ይቻላል:: ይህ ማለት ዲፕሎማሲው መጥፎ ነው ማለት ሳይሆን ሳዑዲ አረቢያን እንደ ጅማ አድርጎ የማየት አመላከከት እንዲፈጠር አድርጓል::
እርሳቸው እንደሚሉት፤ ሌላው የሕገወጥ ፍልሰቱ ምክንያት የደላላ ሚና ከፍተኛ መሆኑ ነው:: ይህም በደላላ ላይ እየተወሰደ ያለው ርምጃ በጣም ቀላል መሆኑን ያሳያል:: ሕጋዊ ያልሆነ ፍልሰቱን ማስቆም ያልተቻለበት ዋናው ምክንያት ሕጋዊ የውጭ ሀገር የሥራ ስምሪት ቀልጣፋና ከቢሮክራሲ ነጻ አለመሆን ሌላኛው ነው፤ ደላሎች ከሕጋዊ ኤጀንሲዎች ጋር እየሠሩ መሆናቸውና ኢ-መደበኛ ፍልሰት ከፍተኛ ገንዘብ የሚገኝበት ወንጀል በመሆኑ በጣም ውስብስብና መረቡም ከሀገር ውስጥ እስከ ውጭ መዘርጋቱና ቁጥጥሩ አዳጋች መሆኑ ነው::
ቅንጅታዊ አሰራር ጠንካራ አለመሆን፤ ለሴክተሮች ተገቢ ትኩረት አለመስጠት፤ ጠንካራ የሥራ ባሕል አለመኖር፤ በአቋራጭ ሀብት የማፍራት ዝንባሌ፤ በውጭ ሀገር ለቤት ሰራተኛ የሚከፈው ደመወዝ ሳቢ መሆኑ፤ በኢ-መደበኛ ፍልሰት የሚያስከትለው ጉዳት ላይ ከሚሰጠው ግንዛቤ ይልቅ ደላሎችን መስማት፤ ፍች መበራከት፤ ሀገር ውስጥ በቂ የሥራ እድል አለመፈጠር፤ መለወጥ የሚቻለው በውጭ ሀገር ብቻ አድርጎ ማሰብም ከዋናዎቹ ፍልሰት ምክንቶች የሚጠቀሱ ናቸው::
በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ፍትህ ቢሮ የልዩ ልዩ ወንጀል ጉዳዮች ዳይሬክተር አቶ ሰይፉ ኬኒሶ እንደሚሉት፤ አንዳንድ ተጎጂዎች ከደላሎች ጋር ማበር፤ ምስክሮች በፍርድ ቤት ቀጠሮ ምስክር ሆነው ለመመስከር ፈቃደኛ አለመሆን፤ ደላሎች ምስክሮችን በማባበልና ለምስክርነት እንዳይቀርቡ ማስደረግ፤ ወንጀሉ በጣም እየረቀቀ በመምጣቱ መረጃን በቀላሉ ማግኘት አስቸጋሪ መሆኑ፤ ደላሎች በዋስትና ሲለቀቁ ከሀገር መውጣትና ሕገወጥ ኤጀንሲዎች በመበራከት ኢ-መደበኛ ፍልሰቱ እንዳይገታ ምክንያት ሆኗል::
ሌላው በሀድያ ዞን ፍትህ ጽህፈት ቤት የልዩ ልዩ ጉዳዮች አስተባባሪ አቶ አክሊሉ ቸርነት፣ ለፍልሰት ላለመቀነሱ ሰፊ የሥራ እድል በአካባቢው አለመኖር ነው ይላሉ:: ውጭ ሆነው ከትምህርት ቤት ጭምር ሕጻናትን የሚመለምሉ መኖራቸውና ደላሎች የምንላቸው ሰዎች አንዳንዴ አጎት ወይም አባት ሆነው መገኘታቸው ደግሞ ጉዳዩን አወሳስቦታል ሲል ይገልጻሉ::
ተጠርጣሪዎች ጉዳዩ በሽማግሌ እንዲታይ በማድረግ ለተጎጂ ወይም ለተጎጂ ቤተሰቦች ገንዘብ በመስጠት መፍታትና ምስክር ከማግኘት አኳያ የባሕል ተጽእኖ በስፋት መኖር ችግሩ መፍትሔ እንዳያገኝ ካደረገው ውስጥ የሚጠቀስ ምክንያት ነው ይላሉ:: የበጀት፣ የተሽከርካሪና የሎጀስቲክ ችግርም ሌላኛው ተግዳሮት ነው ሲሉ ያስረዳሉ::
በወጣቱ በኩል ወደ ውጪ ለመሄድ ያለው ፍላጎት ከፍተኛ መሆኑ፤ ደላሎች ጉዳዩ ወንጀል መሆኑን ስለሚያወቁ ሁሉንም ነገር የሚያከናውኑት በስውር መሆኑና በክትትሉ ላይ ሰፊ ክፍተት መኖሩ ፍልሰትን ለማስቆም የሚደረገውን ጥረት ውጤታማ እንዳይሆን አድርጎታል በማለት ይገልጻሉ::
ሕገ-ወጥ ስደትን በመከላከል የሀገራት ተሞክሮ
የአውሮፓ የደህንነት እና ትብብር ድርጅት በቅጽ 3 ላይ “መደበኛ ያልሆነ የጉልበት ፍልሰትን ለመከላከል ወይም ለመቀነስ የሚወሰዱ ርምጃዎች” በሚለው ርዕሰ ጉዳይ ላይ እንዳሰፈረው፤ “እኤአ በ1970ዎቹ ውስጥ ሕገወጥ የሰዎች ዝውውርን የሚመለከቱ አንዳንድ ዘግናኝ ክስተቶች ከደረሱ በኋላ መደበኛ ያልሆነ የስደት ክስተት የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ትኩረት እየሳበ መጣ። በተለይ አንድ ክስተት የዜና ዘገባዎችን የሳበ ሁነት ሆነ። ይህም ከማሊ የመጡ 50 የሚያህሉ አፍሪካውያን በአስፈሪ ሁኔታ ውስጥ በማውንት ብላንክ ዋሻ/መተላለፊያ ቱቦ ውስጥ በከባድ መኪና ተደርገው መገኘቱ የዓለም አቀፉን ማኅበረሰብ ትኩረት ሳበ።
ቀስ በቀስ እንደነዚህ ያሉ ክስተቶች አሳሳቢነታቸው እየጨመረ መምጣቱ ከጊዜ በኋላ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ እና የኢኮኖሚ እና ማሕበራዊ ምክር ቤት መደበኛ ያልሆነ ስደት ጋር በተያያዙ በርካታ ውሳኔዎችን ማሳለፍ ብቻ ሳይሆን የዓለም አቀፍ የሠራተኞች ድርጅት ቁጥር 143 ኮንፈረንስ ስምምነትን ተቀብሎ አፅድቋል። የዚህ ስምምነት የመጀመሪያ ክፍል ከስደት ሂደት ጋር ተያይዘው የሚደርሱ በደሎችን ለመከላከል የተዘጋጀ ሲሆን፣ ሕገወጥ የሰዎች ዝውውርን ጨምሮ የስደተኞችን ድብቅ እንቅስቃሴ ለማወቅ፣ ለማስወገድ እና ተግባራዊ ለማድረግ ርምጃዎችን እንዲወስዱ ሀገራት እንዲያፀድቁ ይጠይቃል። እንዲሁም (አንቀጽ 1 እና 9(1) መደበኛ ያልሆኑ ስደተኞችን በተለይም መሰረታዊ ሰብአዊ መብቶቻቸውን እንዲሁም ያለፉትን የሥራ ስምሪት (ያልተከፈለ ደመወዝ ወ.ዘ.ተ.) መብቶቻቸውን የሚጠብቁ በርካታ ድንጋጌዎችን ይዟል።
ነገር ግን እነዚህ ድንጋጌዎች ሰዎች ሕጋዊ ሆነው ከሀገር እንዲወጡ የሚያበረታቱ እንጂ መደበኛ ያልሆነ ስደትን የሚያስቀሩ አልሆኑም። በመሆኑም በአሁኑ ወቅት ሰዎች ከሀገር ለመውጣት የተለያየ አይነት ምክንያት ያቀርባሉ። አንዳንድ ሰዎች ሥራ ወይም ኢኮኖሚያዊ ዕድል ፍለጋ፣ ቤተሰብ ለመቀላቀል ወይም ለመማር ይንቀሳቀሳሉ። ሌሎች ደግሞ ከግጭት ወይም መጠነ ሰፊ ከሆነ የሰብአዊ መብት ጥሰት ለማምለጥ ይንቀሳቀሳሉ። በአሁኑ ወቅት ደግሞ አሳሳቢ ከሆነው የአየር ንብረት ለውጥ፣ የተፈጥሮ አደጋዎች ወይም ሌሎች የአካባቢ ሁኔታዎች ከሚያደርሱት አሉታዊ ተጽእኖ ለማምለጥ ወይም ምላሽ ለመስጠት ይንቀሳቀሳሉ።
ምክንያቱ ምንም ይሁን ምንም ግን መደበኛ ያልሆነ ስደት በአሁኑ ወቅት በሀገራችንም ይሁን በዓለም አቀፍ ደረጀ አሳሳቢ ሁኔታ ላይ ይገኛል። የተባበሩት መንግሥታት የኢኮኖሚ እና ማሕበራዊ ጉዳይ ዲፓርትመንት የሕዝብ ክፍል (UNDESA) የ2024 ሪፖርት እንደሚያመለክትው፤ ከተወለዱበት ቦታ ወይም ሀገር ወጥተው የሚኖሩ ሰዎች ከመቼውም ጊዜ በላይ በዝተዋል።
ለማሳያም ያህል የዓለም አቀፍ ስደተኞች ቁጥር በ1990 ከነበረው 154 ሚሊዮን በአሁኑ ወቅት ወደ 304 ሚሊዮን ደርሷል። ይህ አኃዝ በመቶኛ ሲሰላ በ1990 ሁለት ነጥብ ዘጠኝ በመቶ የነበረው የስደተኛ ቁጥር በአሁኑ ወቅት ወደ ሶስት ነጥብ ሰባት በመቶ ከፍ ብሏል። ከእነዚህ ውስጥ ደግሞ የሴት ስደተኞች ቁጥር 48 በመቶ የሚሆነውን ድርሻ ይይዛል ሲል ሪፖርቱ ይጠቅሳል። ይህም የስደተኛ ቁጥር በእጥፍ መጨመሩን አመላክቷል።
ዓለም አቀፉ የስደተኞች ድርጅት (አይ.ኦ.ኤም) የዓለም አቀፍ የፍልሰት ዳታ ትንተና ማዕከል መረጃ እንደሚያሳየው፤ በሕገወጥ መልኩ የሚደረግ ፍልሰት እየጨመረ መጥቷል። የተቋሙ የ2024 የጠፉ ስደተኞች ፕሮጀክት ሪፖርት እንደሚገልጸው፤ “ከ2014 ጀምሮ፣ በዓለም ላይ 72 ሺህ 932 የስደተኞች ሞት የተመዘገበ ሲሆን፣ ከእነዚህ ውስጥ ደግሞ 50 በመቶ በላይ የሚሆኑት ሕይወታቸው ያለፈው በውሃ ውስጥ ሰጥመው ነው:: እንደ ሪፖርቱ ገለፃ፤ በዓለም አቀፍ ደረጃ ካሉት የሕገወጥ ስደተኛ መፍለሻ መስመሮች መካካል መካከለኛው ሜዴትራኒያን ሲሆን፣ በትንሹ 24 ሺህ 494 ሰዎች ሕይወታቸውን ያጡበት ነው።
ሕገወጥ የሰዎች ዝውውር ከሚላከውም ይሁን በተቀባዩ ሀገር ላይ የሚያስከትለውን ጫና በመረዳት ሀገራት የተለያዩ አይነት የሕግ-ማሕቀፎች፣ ፖሊሲዎችን፣ የአሠራር ማንዋሎችን፣ መከላከያ መንገዶችን እና ለሕገወጥ ስደት የተጋለጡ ዜጎችን ወደ ሀገር የሚመለሱበትን አተገባባር ያዘጋጃሉ። በዚህ ጽሁፍ ላይ ሕገወጥ ስደትን ለመከላከል ሀገራት ምን ምን ተግባራትን ያከናውናሉ? የሚለውን የኢትዮጵያን ጨምሮ ለመዳሰስ እንሞክራለን።
ኬንያ
ምስራቅ አፍሪካዊቷ ሀገር ኬንያ፣ ሕገወጥ የሰዎች ስደትን እና ዝውውርን ለመግታት የተለያዩ ጥረቶችን ታደርጋለች። ኬንያ፣ የዜጎችን ደህንነት ለመጠበቅ የሚወጣውን ብቻ ሳይሆን ወደ ሀገሯ የሚገባውን ለመቆጣጠር ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር እየሠራች ትገኛለች። በዚህም ሙሉ ለሙሉ ሕገወጥ የሰዎች ዝውውርን ማስቆም ባትችልም በከፍተኛ ደረጃ ግን መቀነስ ችላለች። በተለይም የድንበር አስተዳደር ተግባራት ተልዕኮውን ከኬንያ ሕገ መንግሥት፣ የኬንያ ዜግነት እና ኢሚግሬሽን ሕግ 2011፣ የኬንያ ዜግነት እና ኢሚግሬሽን ደንቦች 2012፣ የምስራቅ አፍሪካ ማኅበረሰብ የሕግ ማሕቀፍ 2016 እና አጋር ሕጎች አንፃር እየሠራች ትገኛለች።
የኬንያ የሀገር ውስጥ እና የብሄራዊ መንግሥት የስደተኛ ማስተባበሪያ ሚኒስቴር የ2020 “የኬንያ የበጎ ፈቃድ ሀገር ግምገማ የግሎባል ኮምፓክት ኦን ማይግሬሽን (ጂ.ሲ.ኤም) መርሆዎች እና ዓላማዎች አፈፃፀም ሪፖርት እንደሚለው፤ በዋናነትም የኬንያ መንግሥት የሀገሪቱን ድንበር አቋርጠው ለሚሰደዱ ዜጎችን ለመከላከል የተለያዩ ተግባራትን እያከከናወነ ይገኛል።
ከኬንያ ወደ መካከለኛው ምስራቅ በሕገወጥ ምክንያት የሚሰደዱት በአብዛኛው ሴቶች ሲሆኑ፣ እነዚህን ዜጎቿን ከሕገ ወጦች ወይም አስኮብላዮች ለመጠበቅ የኬንያ ብሄራዊ ሥራ ስምሪት ባለስልጣን የቤት ሠራተኞችን ለመቅጠር የሚያስችል የኦንላይን/የኤሌክትሮኒካዊ መንገዶች ፈጥሯል። በተለይም ይህ መንገድ ከኬንያ እስከ ሳዑዲ አረቢያ ለቤት ሠራተኝነት የሚሄዱ ዜጎችን ለመጠበቅ ታስቦ የተዘጋጀ ነው።
ሌላው ሌሎች ኢንዱስትሪዎችን ጨምሮ የኬንያ ዜጎች የሀገር ውስጥ የጉልበት ሥራ ወደሚያገኙበት ሌሎች ሀገሮች ለማስፋት ስትሠራ ቆይታለች። በዚህም ባለስልጣኑ በመዳረሻ ሀገራት ለሥራ በዝግጅቶች ላይ ለሚሆኑ ኬንያውያን ስደተኞች፤ የሥራ የቅድመ መነሻ ስልጠና መርሃ ግብር አዘጋጅቶ ይሰጣል።
ሌላው በኳታር፣ በሳዑዲ አረቢያ እና በተባበሩት አረብ ኤምሬትስ ወደ ውጭ ሀገር ለሥራ የሚሄዱ ዜጎች ችግር እንዳይገጥማቸው የሚሲዮኖች ቁጥር ከፍ እንዲል ያደረገ ሲሆን፣ በተለይም በዮርዳኖስ፣ ሊባኖስ፣ የመን እና ኢራቅ የቆንስላ አገልግሎት ሰጪዎችን ቁጥር ጨምራል።
መንግሥት የሁለትዮሽ የሠራተኛ ስምምነቶችን የሚመለከት የሚኒስትሮች ኮሚቴ አቋቁሞ ከኬንያ ለመጡ የሰለጠኑ ይሁን ክህሎት የሌላቸው ዜጎች በተለይም የሴቶች ስደተኞችን ድርድር ለማሳደግ ዓላማ አድርጎ እየሠራ ነው። ኬንያ ድንበሯን ለመከላከል ደግሞ በተለያዩ ጊዜያት ሕጎቿን እያሻሻለች እና እየከለሰች ነው።
ናይጄሪያ
ሌላኛዋ በሕገወጥ ስደት ተጠቂ የሆነችው ሀገር ናይጄሪያ ናት። ናይጄሪያ፣ ሕገወጥ ስደት ዋነኛ መነሻ ከሆኑት ሀገሮች አንዷ ናት። ባለፈው ዓመት ብቻ ወደ 30 ሺህ የሚጠጉ ሰነድ የሌላቸው ናይጄሪያውያን የሜዲትራንያን ባሕርን አቋርጠው ወደ አውሮፓ ገብተዋል። ነገር ግን ወደ አሕጉሪቱ ለመድረስ ሲሞክሩ በየዓመቱ በመቶዎች የሚቆጠሩ ይሞታሉ። ይህ ሕገወጥ የሰዎች ዝውውር ናይጄሪያ በዓለም ዙሪያ ያላትን መልካም ስም አጉድፏል። አሁን ያለው ግምት በአውሮፓ ከ10 ሺህ የሚበልጡ የናይጄሪያ ሴቶች፤ ሴተኛ አዳሪነት ተግባር ውስጥ እንዲሠማሩ መገደዳቸውን ይጠቁማሉ።
ይህ ሁኔታ የናይጄሪያ መንግሥት በድብቅ የሚደረጉ ስደት እና አደጋዎች ስጋት ውስጥ የሚከቱ ናቸው ይላል። ናይጄሪያ በሕገወጥ መንገድ ሰዎች ወደ እርሷ የሚመጡ ሳይሆን፤ ናይጄሪያውያን ሀገሪቱን ለቀው የሚወጡ ናቸው። በመሆኑም የናይጄሪያ መንግሥት ችግሩን ለመፍታት የተለያዩ ሕጎች አውጥቷል።
የጀርመን ድምፅ ራዲዮ ዶ ቼ ቬሌ እኤአ በ2017 የናይጄሪያን የሀገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር አብዱልራህማን ዳምባዙን ጠቅሶ እንደዘገበው፤ በዘመናዊው ዓለም የስደት እውነታዎች ተለዋዋጭነት ያላቸው መሆናቸውን በመገንዘብ ዘመኑን የሚዋጅ የሕግ ማስተካከያ ያስፈልጋል። ሌላው በወቅቱ የናይጄሪያ ኢሚግሬሽን አገልግሎት ተቆጣጣሪ ጄኔራል መሀመድ ባባንዴዴ ደግሞ፤ “ናይጄሪያ በሕገወጥ መንገድ ስደተኞችን የሚያስኮበልሉትን ለመዋጋት ቁርጠኛ ነች። ምክንያቱም ብዙ ዜጎች በበረሃና በባሕር እየሞቱ ነው ብለዋል።
በዚህም የናይጄሪያ መንግሥት የዜጎችን ሞት ለማስቆም የሚያችል ጠንከር ያለ እርምጃ መወሰድ አለበት ብሎ ያምናል። በዚህ መሠረት የተሻሻለው ሕግ በሕገወጥ ስደት ላይ ከባድ ቅጣትን አካትቷል። ለምሳሌ እኤአ በ1963 የነበረው የድሮው የኢሚግሬሽን ሕግ ከአንድ ዩሮ (አንድ ነጥብ 08 ዶላር) በታች የሆነ መጠነኛ ቅጣቶችን ብቻ አስቀምጧል። በተቃራኒው ደግሞ የአሁኑ የናይጄሪያ ሕግ በሕገወጥ ስደት ላይ የተሳተፈ ሰው እስከ ሶስት ሺህ ዩሮ ወይም ሁለት ሺህ 800 ዶላር ድረስ ሲቀጣ፤ የኢሚግሬሽን ሕግን የጣሰ ደግሞ የእስር ቅጣት ካለፈው ጊዜ በጣም የረዘመ እንደሆነም ገልጸዋል።
በተጨማሪም ወደ አውሮፓ በሚያደርጉት ጉዞ ናይጄሪያውያን ስደተኞች የሚያቋርጡትን የኒጀር እና የሌሎች አጎራባች ግዛቶች ዘንድ ያለውን ትብብር የሚያሻሻል ሥራ የናይጄሪያ መንግሥት ሰርቷል። በዚህም ቅንጅታዊ አሠራር የናይጄሪያ ዜጎች ከሀገራቸው ብዙም እንዳያልፉ በማድረግ የሕገወጥ ስደተኞች ቁጥር መቀነስ ችሏል።
ሌላው የናጄሪያ ዜጎች በምዕራቡ የኢኮኖሚ ማኅበረሰብ ኤኮዋስ ክልል ውስጥ ዜጎቿ በነፃነት እንዲንቀሳቀሱ የሚያደርግ ስምምነት ፈፅማለች። ይህም የናይጄሪያ ዜጎች በስፋት የሥራ እድል ተጠቃሚ እየሆኑ ነው። በተጨማሪም ተመሳሳይ ሥራ የሚሠሩ በርካታ የሀገሪቱ ኤጀንሲዎች ተግባራቸውን ውጤታማነት እና ቅንጅት ለማረጋገጥ እያደረገች ነው።
በተጨማሪም ድንበር አካባቢ የሚሰማሩ ተቆጣጣሪ ግለሰቦች እና ባለስልጣናት ቅጣት ላይ ማተኮር ብቻ ሳይሆን ብዙ ስልጠና በመስጠት የግንዛቤ እና የአመለካከት ለውጥ እንዲኖር እያደረገች ነው። ለዚህም ሀገሪቱ በዋናነት አውሮፓ ሕብረት ኃላፊነቱን መወጣት አለበት ያለች ሲሆን፣ ለናይጄሪያውያን ሕጋዊ ስደትን የሚቆጣጠሩ የአውሮፓ ሕጎች በፍጥነት እንዲሻሻሉ እና የናይጄሪያ ዜጎች ተጠቃሚ እንዲሆኑ በማለት ጠይቃለች። ይህ ካልሆነ “ለመደበኛ ስደት እድሉ ካልተፈጠረ የወንጀል ቡድኖች ሕገወጥነትን እድሎች ይጠቃማሉ የሚል እምነት ይዛ እየሠራች ነው::
ሜክሲኮ
ሜክሲኮ መደበኛ ያልሆኑ ስደተኞች ከሀገሯ ወጥተው በተለይም ወደ አሜሪካ በስፋት የሚሰደዱባት ሀገር ነች። ሀገሪቷ እነዚህን ስደተኞች በመቀነስ ረገድ በቅርቡ ታወቂ እየሆነች መጥታለች። ለአብነትም የፈረንጆች የ2024 ሪፖርት እንደሚያመለክተው ከሆነ፤ ሜክሲኮ የአሜሪካንን ድንበር የሚያቋርጡ ዜጎቿን እንዲቀንስ በማድረግ በአሁኑ ጊዜ የሕገወጥ ስደተኞች ቁጥር በሶስት እጥፍ መቀነስ ችላለች።
ኤን.ቢ.ሲ እኤአ ግንቦት 15 ቀን 2024 ላይ ባስነበበው ጽሁፍ፤ የሜክሲኮ ደቡባዊ ድንበር አቋርጠው ከገቡት ስደተኞች ከአንድ ዓመት በፊት ከነበረው ቁጥር በአሁኑ ጊዜ በሶስት እጥፍ የሚበልጡ ስደተኞችን ማስቆም ችላለች። ይህ ሁኔታ ወደ አሜሪካ ድንበር ለመሻገር የሚደረገውን ለማስቀረት ረድቷል ብሏል።
በ2024 የፈረንጆች ዓመት መጀመሪያ ላይ ሜክሲኮ በየወሩ ወደ 100 ሺህ የሚጠጉ ስደተኞችን በደቡብ ድንበር በኩል እንዳይወጡ ስታደርግ፤ አሜሪካ ደግሞ በሁለቱ ሀገራት ድንበር አካባቢ ከ193 ሺህ በላይ ሕገወጥ ስደተኞችን በመያዝ ማስቆም ችላለች።
ሜክሲኮ የስደተኛ ምንጭ ብቻ ሳትሆን የሕገወጥ ስደተኞች መሸጋገሪያም ጭምር ነች። ይህን በመገንዘብ ባደረገችው መጠነ ሰፊ ሥራዎች የሕገወጥ ስደተኞችን ቁጥር ማጥፋት ባትችልም መቀነስ ግን ችላለች። የስደተኛ ቁጥሯን እንድትቀንስ ካስቻላት መካከል የውስጥ ቁጥጥር ማጠናከር፣ የድንበር ላይ ቁጥጥር ማጠናከር እና ከአሜሪካ ጋር ትብብር ፈጥራ መሥራት በመቻሏ ነው።
ኢትዮጵያም፣ የሕገወጥ የስደተኛ ማሸጋገሪያ ብቻ ሳትሆን ምንጭም ናት። በመሆኑም ይህን ችግር ከስር መሰረቱ ለማስቆም በርካታ ጥረቶች ቢደረጉም አሁንም ግን ችግሩ በስፋት ይስተዋላል። የሕገወጥ ስደትን ውስብስብ እና ብዙ ተዋንያን ያለው መሆኑ ደግሞ ነገሩን ለመቆጣጠር አዳጋች አድርጎታል።
በዚህም ዜጎች የሕገወጥ የሰዎች ዝውውር መስመሮችን እየተከተሉ እና ሕይወታቸውን አደጋ ላይ በመጣል ጭምር ሲጓዙ ይስተዋላል። ይህን ለመከላከል ሀገሪቱ “በሰው የመነገድ እና ሰውን በሕገወጥ መንገድ ድንበር የማሻገር ወንጀልን ለመከላከልና ለመቆጣጠር” የሚል አዋጅ 1178/2012 በ2012 ዓ.ም ላይ አውጥታለች።” አዋጁ ከእስራት እስከ ሞት ድረስ የሚያስቀጣ እንደሆነም እሙን ነው።
ብሔራዊ የፍልሰት ትብብር ጥምረት ሴክሬተሪያት ኃላፊ አቶ አብርሃም አያሌው እንዳሉት፤ ኢትዮጵያ አሁን እየተገለገለችበት ያለው አዋጅ 1178/2012 ብዙ ነገሮችን የያዘ እና የዳሰሰ ነው። መንግሥት አዋጅ ከማውጣት በተጨማሪ የውጭ ሀገር የሥራ ስምሪት በመጀመር ዜጎች በሕጋዊ መንገድ እንዲጓዙ እያደረገ ይገኛል። ይሁንና በሕገወጥ መንገድ የሚወጣው ቁጥር አሁንም ከፍተኛ ነው። ይህን ችግር ለመፍታት እና በሕገወጥ መንገድ የሚሰደዱ ዜጎችን ለማስቀረት በሀገር ውስጥ የተለያየ ሥራዎች መሥራት ያስፈልጋል።
በጅማ ዩኒቨርሲቲ፣ የሕብረተሰብ ሳይንስና ሂዩማኒቲ ኮሌጅ መምህርና ተመራማሪ ነጋ ጂባት (ዶ/ር) እንደሚሉት፤ በየትኛውም ሀገር ስደትን ሙሉ በሙሉ ማስቀረት ላይቻል ይችላል:: ነገር ግን አሁን በሚታየው ልክ እንዳይኖር ማድረግ ይቻላል:: ብዙ ሀገራትም እንደዚያ ማድረግ ችለዋል:: ይህ ደግሞ የሚቻለው መንስኤዎች ናቸው ተብለው የሚታመኑ ችግሮችን በመቅረፍ ነው:: በተለይ የትምህርት ጥራቱ መጠበቅ ከተቻለ፤ ሰፊ የሥራ ዕድል መፍጠር ከተቻለ፤ የሀገር ሰላም በሚፈለገው ደረጃ ከተረጋገጠ፤ በአጠቃላይ ብዙ ልማቶች በስፋት ከተሠሩ ብዙ ነገሩን መቀነስ ይቻላል::
ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ ሕገወጥነትን ለመቀነስ ሕጋዊውን እንደስሙ ሕጋዊ ማድረግ ግድ ይላል:: በሕጋዊ ሂደት ውስጥ ያሉ ቢሮክራሲዎችን፣ ሙስና፣ መልካም አስተዳደር ችግር ማስወገድ ከተቻለ መቀነስ ይችላል ይላሉ:: ምክንያቱም ሰው የሚፈልገው ሄዶ መሥራት እንጂ በሕገወጥ መንገድ መሄድ አይደለም:: ስለዚህ ሕጋዊ የተባለውን በአስተማማኝ ደረጃ መስፈርቱን አሟልተው እንዲሄዱ ቢደረግ ችግሩን ይቀንሰዋል:: ስደተኞች ደግሞ የተቀመጠውን መስፈርት (ለዚያ ብቁ የሚያደርገውን ክህሎት) አሟልተው እንዲሄዱ ማሳመን አስፈላጊ ነው:: ከዚህ ያለፈውን ደግሞ የቁጥጥር ሥርአቱን በማጠናከር ለመቀነስ መሥራት ይቻላል::
እንደተባለው፤ ሕገወጥ ስደትን ለማስቀረት ሀገራት የተለያዩ አይነት ተግባራትን ያከናውናሉ። ሕግ ያወጣሉ፤ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራ ይሠራሉ፤ የሥራ እድል ፈጠራን ያስፋፋሉ፤ በሕገወጥ የሰዎች ዝውውር ላይ ያሉ ሰዎችን የሚቀጣ አሠራር ይዘረጋሉ:: እናም ከሀገራት ጋር የሥራ ስምሪት ስምምነት ይፈጽማሉ። ይህም ኬንያን፣ ናይጄሪያን እና ሜክሲኮን ሕገወጥ ስደትን ከመከላከል አንፃር ለውጥ እንዲያመጡ እያስቻላቸው ይገኛል። ኢትዮጵያም ከእነዚህ ሀገሮች ተሞክሮ በመውሰድ የተጀመሩትን ሥራዎች የማጠናከር፣ የአሠራር ክፍተቶችን የማስተካካል፣ ከሀገራት ጋር የምታደርገውን የሁለትዮሽ የሥራ ስምምነት በስፋት ማከናወን ተገቢ ነው። ወድ አንባቢያን በነገው ዕለትም ክፍል አራት የሚቀጥል ይሆናል::
በኢፕድ የምርመራ ቡድን
አዲስ ዘመን ሰኞ ሐምሌ 7 ቀን 2017 ዓ.ም