በዚሁ በትዝብት ዓምድ ደጋግሜ እንዳልኩት በሰለጠኑ አገሮች መኖርን የምመኘው በመሰረተ ልማቱ ወይም ባላቸው የረቀቀ ቴክኖሎጂ አይደለም፤ በሰዎች ጭንቅላት ነው። በሰዎች የሰከነ፣ የተረጋጋና የሰለጠነ አመለካከት ነው። ትልቁ ሥልጣኔያቸው ለህግና ደንብ ተገዢ መሆን ነው።
አንድ የአገራችን ታዋቂ ሰው ከአንድ ዓመት በፊት በጃፓን ያጋጠመውን በማህበራዊ ገጹ ጽፎ አይቼ ታክሲ ውስጥ በገባሁ ቁጥር እሱን እያስታወስኩ እቀናለሁ። ነገሩ እንዲህ ነው። ለካ በሀገረ ጃፓን ባቡር ውስጥ ስልክ ማውራት አይቻልም። ይህ ኢትዮጵያዊ ይህን አያውቅም፤ እንደ አገሩ መስሎት በስልክ እያወራ ነው። ባቡሩ ውስጥ ያሉ ሰዎች ሁሉ በግርምት ያዩታል። በመጨረሻም ማውራት እንደማይቻል ተነገረውና አወቀ። በብዙ አገራት እንዲህ አይነት ህጎች አሉ። ስልክ ማውራት የማይቻልባቸው የሕዝብ አገልግሎት ሰጪ ተቋማትና ዘርፎች አሉ።
ይህን ያስታወሰኝ ባለፈው ቅዳሜ ከሽሮ ሜዳ ወደ መገናኛ ስሄድ ያገጠመኝ የስልክ ወሬ ነው። ይህን መነሻ አደረኩት እንጂ ይሄ ነገር በየዕለቱ በየታክሲው ውስጥ የምንሰማው አሰልቺ ነገር ነው። ሴትዮዋ ከሽሮ ሜዳ የጀመረች እዚያው መገናኛ እስከምንደርስ ድረስ በጣም እየጮኸች ነው የምታወራው። ወሬው የቤት ውስጥ ጣጣ ነው፤ ታክሲ ውስጥ መወራት ያለበት አልነበረም። በዚያ ላይ አንገብጋቢ ጉዳይ አይደለም፤ ከታክሲ ሲወርዱ ማውራት የሚቻል ነው። በዚያ ልክ የቤት ውስጥ ጣጣ ለዚያውም በጣም በመጮህ ሰው እየረበሹ ማውራት ምን ይሉታል? የታክሲ ውስጥ ህግ ይውጣ ማለቴ ሳይሆን ይሉኝታ ቢኖራት ግን ሰው እየረበሸች መሆኑን ማሰብ ቀላል ነበር።
ባልሠለጠነ አገር መብት የሚባለው የራስን ስሜት ብቻ በማዳመጥ ሌሎችን መረበሽ ነው። በሠለጠነው ዓለም ግን ሰዎችን መረበሽ ክልክል ነው። በእርግጠኝነት ያቺ ሴትዮ ‹‹ምነው ድምጽ ብትቀንሽ?›› ብትባል በቁጣ ያዙኝ ልቀቁኝ ነው የምትለው። በራሴ ስልክ፣ በራሴ ሳንቲም ማን ምን አገባው እንደምትል የታወቀ ነው። ለእርሷ የመናገር መብት ማለት ይሉኝታ ቢስ ሆኖ ማውራት ነው።
በዚያው ታክሲ ውስጥ ደግሞ አንዱ እንግሊዝ ኤምባሲ አካባቢ ስንደርስ የስልክ ወሬ ጀመረ። እሱም እየጮኸ ነው የሚያወራው። የእርሱ ደግሞ የሚያስቀው ወደ መገናኛ በሚሄድ ታክሲ ውስጥ ሆኖ ተቃራኒ ቦታ ጠቅሶ ነበር ‹‹…ነኝ›› ያለ። ይህ በተደጋጋሚ በየታክሲው ውስጥ የምንሰማው ሆኗል። የውሸቱን ነገር የራሱ ጉዳይ እንበል፤ ግን የሚያወራው እየጮኸ ነው። የሁለታቸው ድምጽ ተደምሮ ታክሲው የጋዝ ወፍጮ ቤት(ከፍተኛ ድምጽ ያለው) መሰለ። እንግዲህ ለእነዚህ ሰዎች መብትና ነፃነት ማለት ይሉኝታ ቢስና ሀፍረተ ቢስ ሆኖ ሰዎችን መረበሽ ነው።
በነገራችን ላይ ነፃነት ማለት ለሌሎችም ነፃነት መስጠት ነው። ይሉኝታና ስነ ምግባር ማለት ‹‹ምን ይሉኛል›› ሲኖረው ነው። ቴክኖሎጂ ስንጠቀም ሙሉ አገልግሎቱን በሙሉ ጊዜ መጠቀም ግዴታ ይመስለናል። የእጅ ስልክ(ሞባይል) ተንቀሳቃሽ ነው፤ በየትኛውም ቦታና ጊዜ ልናወራበት የምንችል ነው። የቴክኖሎጂው ባህሪ ይህ ስለሆነ ብቻ ግን ምቾት በማይሰጡ ሁኔታዎች ውስጥ ሁሉ ማውራት ግዴታ አይደለም። ስልኩን የሰሩት አገሮች ራሱ በዚህ ልክ ልቅ አይሆኑበትም።
‹‹መብቴ ነው!›› የሚባል ነገር ለሁሉ ነገር ግዴታ ይመስለናል። ብዙ ጊዜ ካፌ ውስጥ፣ ሆቴል ውስጥ የምታዘበው የብዙዎች ሰዎች ባህሪ ደግሞ ‹‹መብቴ ነው!›› በሚል ምክንያት መጨቃጨቅ ነው። ካፌ ውስጥ ማኪያቶ ነጣ ጠቆረ በሚል ከአስተናጋጅ ጋር የሚጨቃጨቁ፣ አለፍ ሲልም የሚሳደቡ ሰዎች አሉ። እነዚህ ሰዎች የተማሩና ትልቅ ደረጃ ላይ ያሉ ናቸው። ለእነርሱ የትልቅነት መገለጫ መስሎ ነው የሚታያቸው። አስተያየት መስጠት ለተጠቃሚውም ለባለቤቱም ገንቢ ነው። ማመናጨቅና መሳደብ ግን ትዝብት ውስጥ መግባት እንጂ ገንቢ ሊሆን አይችልም። የምር ግን እነዚያ ሰዎች በቤታቸው ውስጥ በትልቅ ምቾት የሚኖሩ ሆነው ይሆን?
የመስክ ሥራ በሄድኩባቸው አጋጣሚዎች ብዙ ነገር ታዝቤ አውቃለሁ። ከእኔ የኑሮ ደረጃ የተሻሉ እንዳልሆኑ የማውቃቸው ሰዎች ትልቅ ዓለም አቀፍ ሆቴል ውስጥ ገብተው ‹‹ይሄ ጎደለ›› በሚል ከእንግዳ ተቀባይ ጋር የሚጣሉ አሉ። በአልጋው ደረጃ የሚነጫነጩና የሚጣሉ አሉ። እርግጥ ነው ሆቴሉ እስከተከፈለበት ድረስ ደንበኛው ተገቢውን አገልግሎት ማግኘት አለበት። ዳሩ ግን ከቤቱ ተጠቅሞበት በማያውቀው ነገር መጣላት ልክ ነው? በቤቱ ውስጥ እየተጠቀመ የዚያን ቀን ብቻ የጎደለበት ቢሆን ስለማይችል ነው ይባላል፤ ከቤቱ ውስጥ አድርጎት በማያውቀው ነገር መደንፋት ግን ቅጥ ያጣ የመብት አጠቃቀም ነው።
መብቶቻችንን መጠቀም የለብንም እያልኩ አይደለም፤ ዳሩ ግን የግል መብታችን የሌሎችን ምቾት የሚነሳ መሆን የለበትም። አንድ ሰው ቤተ መጻሕፍት ውስጥ መጮህ ‹‹መብቴ ነው!›› ሊል ይችላል። እንደ ነፃነት ካየነው ቤተ መጻሕፍት ውስጥ መጮህ ለእርሱ የሚሰጠው ደስታ ይኖር ይሆናል። ዳሩ ግን በእርሱ መጮህ የሚረበሽ ሰው ስላለ ነው የሚከለክል ህግና ደንብ የወጣው።
ለብዙ ነገሮች የግድ ህግ ሊኖር አይገባም። የህሊና ህግ ነው ዋናው የሥልጣኔ መለያ። ይሄ ሰዎችን ይረብሻል ብሎ አሳቢ መሆን ነው አዋቂነት። ራስን የሚጎዳ ይሉኝታ ጥሩ ቢሆንም ለሌሎች ምቾት ማሰብ ግን በስነ ምግባር ከታነጹ ሰዎች የሚገኝ ነው።
ይሉኝታ ቢስና ሀፍረተ ቢስ የሆኑ ሰዎችን ልቅ የሆነ የመብት አጠቃቀም እንደምንታዘበው ሁሉ ራሳቸውን የሚጎዳ ይሉኝታ ያላቸው ሰዎችም አሉ። ለምሳሌ፤ ታክሲ ውስጥ ድጋሜ ‹‹ወራጅ አለ›› ላለማለት ሌላ ሰው በወረደበት ፌርማታ ወርደው ቀሪዋን በእግራቸው የሚሄዱ አሉ። ከእዚህ እዚህ ድጋሜ ወራጅ አለ አልልም ብለው ነው። በተቃራኒው ደግሞ ሁለት ደቂቃ እንኳን በእግር ላለመሄድ ብለው የማይቆምበት ቦታ ላይ በመድረስ የአንድ ፌርማታ ኪሳራ የሚሄዱ አሉ። ስለዚህ መብት ስንጠቀም ራሳችንንም ሌሎችንም በማይጎዳ መንገድ ትንሽ ይሉኝታ የታከለበት ቢሆን ጥሩ ነው።
ይሉኝታ ቢስ የሆነ የመብት አጠቃቀም የሚጠቀሙ ሰዎችን ሳይ በቤታቸውም እንዲህ ነው የሚኖሩ? የሚል ጥያቄ ነው የሚመጣብኝ። በቤቱ ውስጥ በምቾት የሚኖር ሰው በጉዞ አጋጣሚ ለአንድ ቀን ትንሽ ነገር ቢጎልበት ምን ችግር አለው? ወይስ በቤቱ ውስጥ አግኝቶት ስለማያውቅ በዝች አጋጣሚ ብቻ ለመጠቀም ይሆን?
ሥልጣኔ ከቁስ አካል ይልቅ ጭንቅላት ላይ ነው። የሠለጠኑ በምንላቸው አገሮች ውስጥ የምንቀናበትን ነገር ራሳችን ማድረግ እንችላለን። የቁስ አካሉ ሥልጣኔ የሚመጣው መጀመሪያ በአስተሳሰብ ስንሰለጥን ነው። ጥሎብን ግን የእኛ ሥልጣኔ አነጋገርና አለባበስ ላይ ያተኩራል። ለህግና ደንብ ተገዢ እንሁን፣ መብቶቻችንን ስንጠቀም ሌሎችን የማይረብሽ ይሁን!
ዋለልኝ አየለ
አዲስ ዘመን ግንቦት 9/2015