አገልግሎት ሰጪ ተቋማት በሥራ ቅልጥፍና እና በሠራተኞች ሥነ ምግባርና ትህትና በተደጋጋሚ ሲታሙ ይሰማል። ተገልጋዩን የበለጠ የሚያማርረው ደግሞ የሰልፍ ብዛት ነው። በሁሉም ቦታ ወረፋ አለ፤ በተለይም እንደ ባንክ እና ገቢዎች ያሉ ገንዘብ የሚንቀሳቀስባቸው መገልገያዎች ደግሞ ከፍተኛ ጥንቃቄ ስለሚጠይቁ ወረፋ ይበዛባቸዋል፡፡
የአገልግሎት ሰጪ ተቋማቱ ችግር እንዳለ ሆኖ (በተደጋጋሚ ስንወቅሳቸው ስለኖርን) እስኪ ራሱ ተገልጋዩ ጋ ያለውን ችግር እንታዘብ። ልብ ብላችሁ አስተውላችሁ ከሆነ ከተገልጋዩም ብዙ ችግር አለ። የሚሞላ ቅጽ በትክክል አለመሙላት፣ የሚያስፈልጉ መረጃዎችን ሳያጣሩ መምጣት፣ የአገልግሎት ሰጪ ተቋሙን ሕግና ደንብ አለማወቅ፣ ከሕግና ደንብ ውጭ አገልግሎት ለማግኘት መጨቃጨቅ…. የመሳሰሉት አገልግሎቱን ያጓትታሉ፡፡
21ኛው ክፍለ ዘመን ሥራዎችን ሁሉ ቀላል አድርጓል። ከዓመት ወደ ዓመት በተሸጋገርን ቁጥር አዳዲስ የቴክኖሎጂ ዓይነቶች ብቅ እያሉ ነው። በብዙ ተቋማት ውስጥ የወረቀት አገልግሎት እየቀረ ነው።
እንግዲህ በሀገራችንም ይህን ቴክኖሎጂ በመጠቀም ብዙ ተቋማት አገልግሎታቸውን ወረቀት አልባ ካደረጉ ዋል አደር ያሉ ብዙ ናቸው። ወረቀት ሙሉ በሙሉ ባይቀር እንኳን የቴክኖሎጂ አማራጮች እየተሰጡ ነው። ለምሳሌ ባንኮች ወረፋን ለማስቀረት ብዙ የቴክኖሎጂ አማራጭ ሰጥተዋል፡፡
እዚህ ላይ ነው እንግዲህ ተገልጋዩን ማህበረሰብ የምንታዘበው። ብዙዎቻችን ለቴክኖሎጂ ነክ ነገሮች ሩቅ ነን። አንዳንዱ እንዲያውም ጭራሽ ‹‹አልወድም›› በማለት ራሱን እንደ ኩሩ የሚያይም አለ። ሌላው ደግሞ ቴክኖሎጂው አስማት ሆኖበት የሚከብደው አለ። እነዚህን ነገሮች የምንታዘበው የትምህርት ደረጃ በሌላቸው ሰዎች አይደለም። ቢያንስ ቢያንስ የመጀመሪያ ዲግሪ ካላቸው ሰዎች ነው፡፡
በትምህርት ብዙም ያልገፉ ወይም ጭራሹንም ትምህርት ቤት ያልገቡ ሰዎች ቴክኖሎጂ እንደማይጠቀሙ ግልጽ ነው። አማራጩ የመጣው መጠቀም ለሚችሉት ነበር። እነዚህ ቴክኖሎጂውን መጠቀም የሚችሉ ሰዎች ቢጠቀሙ፤ ለወረፋ የሚሰለፉት መጠቀም የማይችሉት ብቻ ይሆናሉ ማለት ነው። መጠቀም የማይችሉት ብቻ ቢሰለፉ ደግሞ የተጋነነ ሰልፍ አይሆንም። አሁን ግን አስቸጋሪ የሆነው የተማረ የሚባለውም ያልተማረውም አብረው የወረቀት አገልግሎት እየተጠቀሙ ነው።
የሕዝብ ቁጥር በየጊዜው እየጨመረ በሄደ ቁጥር ሁሉም የወረቀት አገልግሎት ከተጠቀመ ወረፋው እየባሰው እንጂ እየተሻለው አይሄድም።
የቴሌቭዥን ማስታወቂያዎች ላይ ብዙ የቴክኖሎጂ አገልግሎቶች ሲተዋወቁ እናያለን። የውሃ፣ የመብራት፣ የትራፊክ ቅጣት… የመሳሰሉ ክፍያዎች በሞባይል ባንኪንግ፣ በሲ ቢ ብር፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ በቴሌ ብር መክፈል እንዳለባቸውና ይሄውም ጊዜና የሰው ጉልበትን ድካም እንደሚቀንስ በተደጋጋሚ ይተዋወቃል። ተጠቃሚው ግን ትንሽ ነው። ባንክ ቤቶች ውስጥም ሆነ ሌላ የክፍያ አገልግሎት ያለባቸው ቦታዎች ላይ አሁንም ረጃጅም ወረፋ ነው ያለው።
የሞባይል ባንኪንግ አገልግሎት ከተጀመረ ብዙ ጊዜ ሆኖታል፤ ዳሩ ግን አሁንም የማይጠቀመው ሰው ብዙ ነው። እንኳን የሞባይል ባንኪንግ ኤ ቲ ኤም ካርድ የማይጠቀም ብዙ የተማረ የሚባል ሰው አለ። በነገራችን ላይ አንዳንድ ሰዎች ለምን የኤ ቲ ኤም ካርድ እንደማይጠቀሙ ሲጠየቁ፤ ብር ለመቆጠብ አይመችም የሚል ምክንያት የሚያቀርቡ አሉ። ይሄ በራስ አለመተማመን ነው። ኤ ቲ ኤም ማሽን ባገኘ ቁጥር ያለ አስፈላጊ ጉዳይ ብዙ የሚያወጣ ሰው በሒሳብ ደብተርም ቢሆን ያወጣዋል። ወረፋው ከአቅም በላይ ሲሆንበት እተወዋለሁ ብሎ ከሆነ ደግሞ ሌላ ጉዳት ነው። አስገዳጅ የሆነ ጉዳይ ቢያጋጥም ብሩን ማግኘት ባለበት ሰዓት ላያገኝ ነው ማለት ነው።
ብዙዎቻችን ለቴክኖሎጂ ነገሮች ራቅ ያልን ነን። ይሄ ማለት ግን በአገልግሎት ሰጪው ተቋም በኩልም ችግር የለም ማለት አይደለም። በተለይም ከኮኔክሽን ጋር በተያያዘ ችግር አለ። በተለይም ባንኮች የወሩ መጨረሻ ሰሞን የሠራተኞች ደመወዝ መግቢያ ስለሆነ ሞባይል ባንኪንግ ሥራ ያቆማል። ተፈላጊነቱ በሚጎላ ጊዜ ጭራሽ ሥራ ያቆማል። የዚያን ሰሞን በሒሳብ ደብተር እንኳን ለማውጣት ‹‹ሲስተም የለም›› በሚል ወረፋው በጣም ይበዛል። የኤ ቲ ኤም ማሽኖች ይበላሻሉ። አሁን አሁን የኤ ቲ ኤም ሰልፍ ራሱ የታክሲ ሰልፍ ያህል እየረዘመ ነው። ስለዚህ ባንኮች ደንበኞቻቸው የቴክኖሎጂ ተጠቃሚ እንዲሆኑ የሚወተውቱትን ያህል አገልግሎት አሰጣጣቸውንም እንደዚያው ቀልጣፋ ማድረግ አለባቸው። በተለይም ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የደንበኛ ብዛት ስላለው ነው መሰለኝ ማሽኖቹ የወር መጨረሻ አካባቢ አይሠሩም።
ሌላው የሚያጋጥመው ችግር ደግሞ ማሽኑ ያልሰጠውን ብር ‹‹ወጪ አድርጋችኋል›› የሚል መልዕክት በመላክ ብሩ ተቀናሽ መሆኑ ነው። በርግጥ ከቀናት በኋላ (ብዙ ጊዜም ወዲያውኑ) ብዙ ተመላሽ ይሆናል። በበኩሌ አጋጥሞኝ ባያውቁም አልተመለሰልኝም የሚሉ ሰዎችም ሰምቼ አውቃለሁ።
በነገራችን ላይ የትዝብት ትኩረቴን ባንኮች ላይ ረዝም ያደረኩት ከሌሎች አገልግሎት ሰጪ ተቋማት የተሻለ የቴክኖሎጂ ተጠቃሚ ስለሆኑ ነው። የሚደነቅ ብቻ ሳይሆን የሚወቀስም የሚሠራ ነው። ትችት የሚያጋጥመው የሚሠራ አካል ነው። አየር መንገድ እና ባንኮች ናቸው በኦንላይን መገልገልን ያስለመዱን። በዚህ በኩል በጣም ይመሰገናሉ፡፡
ወደ ሌሎች ተቋማት ስንሄድ እንኳን በመተግበሪያ አገልግሎትን ማፋጠን የማህበራዊ ትስስር ገጾቻቸው እንኳን የማይታደሱ ናቸው። ለእንቁጣጣሽ ‹‹መልካም አዲስ ዓመት›› ብለው ከአደይ አበባ ጋር የለጠፉት ጽሑፍ ዓመቱን ሙሉ ምንም የማይጨመርበት አሉ። የእነዚህ ተቋማት ሠራተኞች ቴክኖሎጂን እያስተዋወቁና እየተጠቀሙበት አይደለም ማለት ነው።
እዚህ ላይ ግን አንዳንድ ተቋማት አስቂኝ ነገሮች እንደሚለጥፉም ታዝበናል። በተለይም የወረዳ ኮሚኒኬሽን ገጾች ብዙ ጊዜ ማህበራዊ ገጾች እየተቀባበሉ ሲቀልዱባቸው ይታያል። ገጾቻቸው በግለሰብ ስለሚከፈቱ ‹‹Got Married፣ In Relationship›› የሚሉ ግለሰባዊ ጉዳዮችን ይለጥፋሉ። የማህበራዊ ገጾች ተጠቃሚዎች ደግሞ በብዛት ወጣቶች ስለሆኑ ትንሽ ነገር ሲገኝ መሳቂያ መሆኑ አይቀሬ ነው። ኦንላይን በባሕሪው ፈጣን ስለሆነ ስህተት እንደሚያጋጥም ቢታወቅም አንዳንዶቹ ደግሞ አስቂኝ ከመሆኑ የተነሳ ለምን አዘዋወሩት ብሎ ለመውቀስም አይመችም።
ቴክኖሎጂ ሲባል እንግዲህ የግድ ከኦንላይን ጋር የተያያዙ ነገሮችን ብቻ አይደለም። በአጠቃላይ ሥራን የሚያቀላጥፉ እና መረጃን የሚያፋጥኑ ነገሮችን መጠቀም ማለት ነው። ሠራተኞች በሚሠሩበት የሥራ ዘርፍ ሁሉ መሻሻል ማለት ነው። በ90ዎቹ የነበረ መገልገያ አሁን ላይ ብዙ ነገሩ ስለሚቀየር ከዚያ ጋር አብሮ መሄድ ማለት ነው። ለምሳሌ በየትኛውም ቢሮ ኮምፒዩተር አለ። የኮምፒዩተር ሶፍትዌሮች እንኳን ይቀየራሉ። ቀደም ሲል የነበረው አሁን ላይ የመጡ መተግበሪያዎችን ላይቀበል ይችላል፤ ስለዚህ ያንን አውቆ መቀየር ማለት ነው፡፡
ስለዚህ ተቋማትም ጠንክረው ይሥሩ፤ እኛ ተገልጋዮችም ተቋማትን መውቀስ ብቻ ሳይሆን እኛም ከቴክኖሎጂ ፍጥነት ጋር ራሳችንን በማሻሻል ተጠቃሚ እንሁን!
ዋለልኝ አየለ
አዲስ ዘመን ሰኞ ግንቦት 18 ቀን 2017 ዓ.ም