ኢትዮጵያ ወቅቱ የሚጠይቀውን ዲጂታል ቴክኖሎጂ በተለያዩ ዘርፎች መተግብሩን አጠናክራለች። ክፍያዎች ከጥሬ ገንዘብ ውጪ በኤሌክትሮኒክስ መንገድ እንዲፈጸሙ እየተደረገ ነው። ዲጂታል ግብይቱ በቅርቡ ደግሞ በነዳጅ ግብይት ላይ ተግባራዊ ተደርጓል።
በሀገሪቱ በጥሬ ገንዘብ የሚደረገው የነዳጅ ግብይት ካለፈው ሚያዚያ አጋማሽ አንስቶ በአዲስ አበባ፣ ከያዝነው ግንቦት መጀመሪያ አንስቶ ደግሞ በክልሎች በኤሌክትሮኒክስ የነዳጅ ግብይት ተተክቷል። ቴክኖሎጂው ተገልጋዮች የሚፈልጉትን አገልግሎት ያለ ጥሬ ገንዘብ መፈጸም እንዲችሉ እያስቻለ ነው፤ ጊዜንና ድካምን እየቀነሰም ይገኛል። ለስርቆት የመጋለጥ እድልን እንደሚቀንስ፣ በነዳጅ ላይ የሚፈጸም ሕገወጥ ድርጊትን ለመከላከል እንደሚጠቅም እየተገለጸ ይገኛል።
ዲጂታል ቴክኖሎጂን ለመተግበር ሲታሰብ ግን በቂ ዝግጅት ማድረግ ያስፈልጋል፤ ወደ ስራ የገባው አዲስ አገልግሎት ፈጣንና ህብረተሰቡ በቀላሉ ሊጠቀምበት የሚችል መሆን ይኖርበታል።
አዲስ ነገርን ቶሎ ተቀብሎ ወደ ተግባር መግባት፣ እኩል የሆነ አረዳድ አለመኖር፣ በሌላ በኩልም የህብረተሰቡን የቴክሎጂ አጠቃቀም ማዕከል ባደረገ ቀድሞ የግንዛቤ ሥራ አለመሥራት የሚጠበቁ ተግዳሮቶች ናቸው። አዲስ ቴክኖሎጂን ከመተግበር ጎን ለጎን እነዚህን ታሳቢ ያደረገ ስራ መስራት፣ ችግሮች ሲያጋጥሙም እየፈቱ መሄድ ይገባል።
አሰራሮችን ወደ ዲጂታል ለመቀየር ወደ ስራ በተገባባቸው አንዳንድ ዘርፎች ላይ ይህን አይነት ችግሮች ሲያጋጥሙ ታይቷል። ለእነዚህም በቅርቡ ተግባራዊ በሆነው የኤሌክትሮኒስ የነዳጅ ግብይት ላይ የተስተዋለውን ችግር ለአብነት መጥቀስ ይቻላል። በአዲስ አበባ ከተማ የነዳጅ ግብይቱ በኤሌክትሮኒክስ አሰራር እንደተጀመረ ነዳጅ ለመቅዳት በየማደያው ረጃጅም ሰልፎች ሲታዩ ሰንብቷል። ይህም ተገልጋዮችን በእጅጉ አማሮም ነበር። በሂደት ወረፋው እየቀነሰ ቢሄድም፣ አገልግሎቱ አሁንም የተቀላጠፈ ነው ለማለት አያስደፍርም።
ስራ ላይ የዋለውን የኤሌክትሮኒክስ የነዳጅ ግብይት ሥርዓት ትግበራን አስመልክቶ የንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር፣ የነዳጅና ኢነርጂ ባለሥልጣን፣ ኢትዮ ቴሌኮምና የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ባለፈው ሳምንት በጋራ መግለጫ ሰጥተዋል። በመግለጫው ላይ እንደተጠቆመው፤ በኤሌክትሮኒክስ የነዳጅ ግብይት የክፍያ ሥርዓቱ ላይ ካጋጠሙ ችግሮች መካከል ነዳጅ ለመቅዳት የሚመጡ ተጠቃሚዎች ዝግጁ አለመሆን፣ እንደ ቴሌብር ያሉ ለኤሌክትሮኒክስ ክፍያ አገልግሎቱ የተቀመጡትን አማራጮች በእጅ ስልካቸው ላይ አለመጫን፣ በመክፈያ ዘዴው ውስጥ በቂ ገንዘብ አለመያዝ የሚሉት ጥቂቶቹ ናቸው።
በአዲስ አበባ ከተማ ላይ ከተስተዋለው ተሞክሮ በመውሰድ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎችን በመሥራት እንደ ሀገር የኤሌክትሮኒክስ የክፍያ አገልግሎቶችን መተግበር ውስጥ መገባቱ በመግለጫው ተመልክቷል።
የነዳጅና ኢነርጂ ቁጥጥር ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ሳህረላ አብዱላሂ፤ የዲጅታል ኤሌክትሮኒክስ ግብይት ሥርዓቱ የተጀመረው ከታለመለት የነዳጅ ድጎማ አተገባበሩ ጀምሮ መሆኑን አስታውሰው፤ ተጠቃሚው የዲጅታል ኤሌክትሮኒክስ ግብይት ሥርዓትን ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተላመደው መምጣቱን ተናግረዋል። በአሁኑ ጊዜም ግብይቱ በኢትዮ ቴሌኮም በኩል በለማው በቴሌ ብር ፣ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በኩል ደግሞ በሲቢኢ ብር እና የነዳጅ መተግበሪያዎች አማካኝነት እየተፈጸመ መሆኑን ገልጸዋል።
እንደ ዋና ዳይሬክተሯ ገለጻ፤ ወደ ሥራ ከተገባ በኋላ ሌላው ያጋጠመው ችግር ተጠቃሚዎች ለአገልግሎቱ የሚገለገሉበትን የሚስጥር ቁጥር (ፒን ኮድ) እየዘነጉ ያሉበት ሁኔታ ነበር። በአዲስ አበባ ከተማ ሚያዚያ 16 እና 17 ቀን 2005ዓ.ም ብቻ በነበረው የዲጅታል የኤሌክትሮኒክስ የነዳጅ ግብይት ከ56ሺ በላይ ተጠቃሚዎች ለአገልግሎቱ የሚጠቀሙበትን የሚስጥር ቁጥር (ፒን ኮድ) በመርሳታቸው ምክንያት ረጃጅም ሰልፎች ሊፈጠሩ ችለዋል። አገልግሎት የሚሰጡ ነዳጅ ማደያዎችም ሁሉም በአንድ አይነት ፍጥነት የመሄድ ችግሮች ነበሩባቸው።
በአንዳንድ አካባቢዎች የኢንተርኔት (በይነመረብ) መቋረጥም ተጽእኖ ፈጥሮ እንደነበር አስታውሰው፣ ይህም ችግር በኢትዮቴሌኮም በኩል መፍትሔ ማግኘቱን ገልጸዋል። አዲስ አበባ ላይ ከማደያዎች ጋር ተያይዞ ችግሮች ተከሰተው እንደነበርም ጠቅሰው፣ በዚህም በሁለት ማደያዎች ላይ እርምጃዎች ተወስደዋል ብለዋል። አዲስ አበባ ላይ የታዩ ችግሮች በተደጋጋሚ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎች መስራት እንዳለባቸው የሚጠቆሙ ናቸው ብለዋል።
ከንግድ መዋቅሩ ሥራዎች ጎን ለጎን አንዳንድ አካባቢዎች ላይ የዲጅታል ኤሌክትሮኒክስ የነዳጅ ግብይት ከመጀመሩ ጋር ተያይዞ የነዳጅ እጥረት ባለባቸው ማደያዎች የነዳጅ አቅርቦትና ስርጭቱንም ለማፋጠን የሚያስችሉ ሥራዎች እየተሰሩ መሆናቸውን አስታውቀዋል።
የግብርና ሥራ በስፋት በሚከናወንባቸው የሀገሪቱ አካባቢዎች በኤሌክትሮኒክስ ዘዴ ነዳጅ ለመቅዳት የሚያስችል የዲጅታል ነዳጅ ግብይት ሥርዓት አብሮ መልማቱንም ተናግረዋል። በእነዚህ አካባቢዎች በጀሪካንና በሃይላንድ የሚደረጉ የነዳጅ ግብይቶችን ስርዓት በማስያዝ በኢትዮ ቴሌኮም በኩል የሚሰራው ሲስተም አልቆ በቀጣይ ቀናት ውስጥ ሙሉ በሙሉ ወደ ሥራ ማስገባት የሚቻልበት ሁኔታ መመቻቸቱንም ገልጸዋል።
ዲጅታል የነዳጅ ኤሌክትሮኒክስ ግብይቱ ከግንቦት 1 ቀን 2015 ጀምሮ በሁሉም ክልሎች በአንድ አይነት ከጠዋቱ አስራ ሁለት ሰዓት ላይ መጀመሩን ያስታወሱት ዋና ዳይሬክተሯ፣ የክልል ሚዲያዎች በራሳቸው ቋንቋ የተለያዩ የግንዛቤ ማስጨበጥ ሥራዎች እየሰሩ እንደሆነም ተናግረዋል። አንዳንድ ክልሎች ሊፈጠር የሚችለውን መጨናነቅ ሊቀንሱ የሚያስችሉ የራሳቸውን የአሠራር ሥርዓት ዘርግተው እየሰሩ እንደሆነም ጠቅሰው፣ እስካሁን የነዳጅ ግብይት ሥርዓቱ በሚፈለገው መልኩ እየሄደ መሆኑን አመልክተዋል።
እንደ ዋና ዳይሬተሯ ማብራሪያ ፤ ኢትዮ ቴሌኮምና የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሠራተኞች በነዳጅ መቅጃ ማደያዎች በመገኘት ሕብረተሰቡን ግንዛቤ የማስጨበጥና ተገልጋዮች አጠቃቀም ላይ የሚያጋጥማቸውን ችግር በመፍታት እያገዙ ይገኛሉ። የተቋማቱ እገዛ የዲጅታል ነዳጅ ግብይቱን ይበልጥ ያሳልጠዋል። በክልሎች ከነዳጅና ከሌሎች አቅርቦት ጋር የሚገጥሙ ችግሮችን ለመፍታት ቡድን ተቋቋሞ በተለያዩ የኮሙኒኬሽን ዘዴዎች (ፕላትፎርም) ሥራዎች እየተሰሩ መሆኑን ነው ዋና ዳይሬክተሯ የጠቆሙት።
የዲጅታል ግብይቱ ተስፋ ሰጪ ነው ያሉት ዋና ዳይሬክተሯ፤ የዲጂታል ኤሌክትሮኒክ ግብይት ሥርዓቱ እየተሻሻለ እንደሚሄድ ገልጸዋል። ኢትዮጵያ ከውጭ ሀገር ገዝታ የምታመጣውንም ነዳጅ ጭምር በኤሌክትሮኒክ የነዳጅ ግብይት ሥርዓት ውስጥ የሚያልፍበትን ሥርዓት ለመፍጠርም እየተሰራ መሆኑ ጠቁመዋል።
በቀጣይ የነዳጅ የግብይት ሥርዓቱ ከመነሻ እስከ መዳረሻው የነዳጅ ማደያዎች ትዕዛዝ ሰጥተው ነዳጅ ከጂቡቲ ተጭኖ ሲመጣላቸው ጭምር ያለውን እንቅስቃሴ በቅርበት ለመከታተል የሚያግዝ ‹‹ፊውል ኦርደር ማኔጅመንት ሲስተም ›› የተሰኘ ቴክኖሎጂ ተግባራዊ እንደሚደረግ ነው የጠቆሙት። የመተግበሪያ ሥራው አልቆ ከጂቡቲ መንግሥት ጋር ንግግር ተደርጎ በቅርቡ ወደ ትግበራ እንደሚገባ አስረድተዋል።
‹‹ፊውል ኦርደር ማኔጅመንት ሲስተም›› ቴክኖሎጂ የሚቀረው ወደ አንድ ዳሽ ቦርድ ማምጣት ነው ። እነዚህ ኩባንያዎች ከዘጠኝ በላይ የሶፍት ዌር ኩባንያዎች ጋር የሚሰሩ ሲሆን፤ የተለያየ ሶፍትዌር የሚጠቀሙ በመሆናቸው ወደ አንድ ዳሽ ቦርድና ፕላፕፎርም ለማምጣት ከኢንፎርሜሽን መረጃ ደህንነት አስተዳደር ጋር ስራዎች መጀመራቸውን ተናግረዋል። አሁን ባለው አሠራር ከ3ሺ500 የነዳጅ ቦቴዎች መካከል ለ3ሺ416 ያህሉ ጂፒኤስ እንደተገጠመላቸው ጠቅሰው፣ በዚህ መሠረት ተጠያቂነት እንዲሰፍን የቦቴዎች ቁጥጥር እየተደረገ መሆኑን አብራርተዋል።
የሌሎች አገሮችን ልምድ በመቅሰም አስገዳጅ የሆነ ስታንዳርድ መዘጋጀቱን ዋና ዳይሬክተሯ ጠቅሰው፣ እንደኛ ሀገር የነዳጅ ማደያዎች ከ 1930 እስከ 1940ዎቹ የተቋቋሙ በመሆናቸው ስታንዳርድ አያሟሉም ሲሉም ይጠቁማሉ። በዚህ መሠረት አንዳንድ ኩባንያዎች ማደያዎቻቸውን ማዘመንና ምቹ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል ሲሉም አስገንዝበዋል።
የኢትዮ ቴሌኮም ቺፍ የሞባይል መኒ ኦፊሰር አቶ ብሩክ አድሀና እንዳሉት፤ ዲጅታላይዜሽንን በማምጣት የህብረተሰቡን የአኗኗር ዘይቤ በማቅለል በተለይ በውድ ሀብት እየተገዛ ያለውን ነዳጅ በአግባቡ ከመጠቀምና ለታለመለት አላማ እንዲውል ከማድረግ አንጻር ኢትዮቴሌኮም ሲስተም በማልማት ዲጅታል የነዳጅ ግብይት ሥርዓትን ለማሳለጥ የሚያስችል ስራ እየሰራ ይገኛል።
በአዲስ አበባ የኤሌክትሮኒክስ የነዳጅ ግብይት ከተጀመረ በኋላ ያጋጠሙ ክፍተቶችን በመፍታት እንዲሁም በክልሎች አስፈላጊውን የሰው ኃይል በመመደብ ከመገናኛ ብዙሃን /ሬዲዮና ቴሌቪዥን/ በመጠቀም በሁሉም ቋንቋዎች የማስተዋወቅና የማስተማር ሥራዎች በመሥራት ላይ መሆኑንም አቶ ብሩክ ጠቅሰዋል።
ከ31 ሚሊዮን በላይ የሆኑት የቴሌብር ደንበኞታችን በቴሌብር ሱፐር አፕ ተመዝግበው አገልግሎቱን እየተጠቀሙ መሆናቸውን ጠቅሰው፣ አሁን የሚስጥር ቁጥር (ፒን) የሚረሱ ደንበኞች ቁጥር እየቀነሰ መጥቷል ይላሉ። ችግሩን ለማቃለል ክልሎች ላይ በቂ የሰው ኃይል በመመደብ ሚስጥር ቁጥራቸውን የረሱትን በማስተካከል ፣ ጥሬ ገንዘብ የያዙትን ወደ ኤሌክትሮኒክ መኒ በመቀየር በአጭር ጊዜ ግብይት እንዲፈጸሙ እየተደረገ መሆኑን ጠቁመዋል።
አቶ ብሩክ እንዳብራሩት፤ የዲጅታል የነዳጅ ግብይቱ ከተጀመረ አንስቶ አስፈላጊው ክትትልና ቁጥጥር እየተደረገ ሲሆን፣ ብልሸት ሲገጥምም አፋጣኝ ምላሽ እየተሰጠ ይገኛል። ከዚህ አኳያ አዲስ አበባ ላይ የጎላ ችግር አልገጠመም።
በርካታ ደንበኞች ቪፒኤን (VPN) በመክፈት አገልግሎቶች ለማግኘት በሚሞኩሩበት ወቅት የተፈጠሩ የኔትወርክ መቋረጥ ችግሮች እንደነበሩ አቶ ብሩክ ጠቁመዋል። ደንበኞች የቪፒኤን (VPN/ አጥፍቶ መጠቀም ለኔትወርክ ጥራት አስተዋፅኦ እንዳለው ይናገራሉ ያሉት አቶ ብሩክ፣ ጉግል ያለ የቪፒኤን (VPN/ የሚጠቀሙ ደንበኞች በፍጥነት አገልግሎቱን ማግኘት እንደሚችሉ ገልጸዋል። ቪፒኤን(VPN) የሚጠቀሙ ከሆነ ግን ከውጭ ሀገራት የተለያዩ ሀገራት ላይ ገብተው ስለሆነ የሚጠቀሙት በዚህ የተነሳ የአገልግሎት የጥራት ችግር አለው ብለዋል።
እንደሀገር የተያዘውን የዲጂታል ግብ እውን ለማድረግ ሁሉም በጋራ ተቀናጅቶ መሥራት እንደሚጠበቅበት አቶ ብሩክ ጠቁመው፤ በቀጣይ ኢትዮቴሌኮም የሚነሱ ክፍተቶችን ከመንግሥት መዋቅር ጋር በተናበበ መልኩ ለመፍታት በቅርበት እንደሚሰራ ገልጸዋል።
የዲጂታል ኤሌክትሮኒክ ግብይትን እውን ለማድረግ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሁለት አማራጮች በማቅረብ አገልግሎት እየሰጠ መሆኑን የባንኩ የሲቢኢ ብር ዳይሬክተር አቶ መንግሥቱ እንዳለሙ ይጠቅሳሉ። ባንኩ ሲቢኢ ብር እና ነዳጅ የሚሉ አማራጮች እንዳሉትም ይናገራሉ። ሲቢኢ ብር ደንበኞች የሲቢኢ ብር አካውንታቸውን በመጠቀም ክፍያ መፈጸም የሚያስችላቸውን የዋሌት ሂሳብ መሠረት ያደረገ አማራጭ መሆኑን ገልጸዋል። የነዳጅ አማራጭ ደግሞ ደንበኞች ከመደበኛ ሂሳባቸው ተጠቅመው ነዳጅ በኤሌክትሮኒክስ ግብይት ለመፈጸም የሚጠቀሙበት ዘዴ መሆኑን ጠቁመዋል።
አቶ መንግሥቱ እንዳሉት፤ ሲቢኢ ብር እና ነዳጅ መተግበሪያ በመጠቀም የነዳጅ ደንበኛ ከሆኑ፣ በቂ ገንዘብ ካላቸውና የሚስጥር ቁጥራቸውን ማስታወስ ከቻሉ ግብይቱን መፈጸም የሚችሉባቸው አማራጮች አሉት። በቂ ገንዝብ ካልያዙና የሚስጥር ቁጥራቸውን ማስታወስ ካልቻሉ በአቅራቢያው ወዳሉ የባንኩ ቅርንጫፎች፣ ኤጀንቶች ሞባይል ባንኪንግ በመጠቀም ከመደበኛ ሂሳባቸው ወደ ሲቢኢ ገንዘብ በማስተላለፍ ነዳጃቸውን በቀላሉ መቅዳት የሚችሉበት አማራጭ ቀርቦላቸዋል።
እነዚህ አማራጮች የማደያ ሠራተኞች በየቀኑ የሚሸጡትን የሽያጭ መጠንና የገንዘብ ትራንዛክሽን መጠን በቀላሉ ማየት የሚችልባቸውም ናቸው የሚሉት አቶ መንግሥቱ፤ የነዳጅ ማደያ ባለቤቶችም በቀላሉ በስራቸው ያሉ ሠራተኞች ምንያህል እንደሰሩ ለማየትና ለመቆጣጠር የሚችሉባቸው አማራጮች ተሰጥቷቸው እየተጠቀሙበት ይገኛሉ ብለዋል።
የዲጂታል ነዳጅ ግብይቱን ለማሳለጥ የንግድ ባንክ ሠራተኞች በእያንዳንዱ ማደያ ተገኝተው አገልግሎት እየሰጡ መሆናቸውን ጠቁመው፤ ችግሮች ሲያጋጥሙም ደንበኞች በነጻ የስልክ መስመር 951 በመደወል ማማከር የሚችሉበት ሁኔታ ተመቻችቷል ሲሉ አስታውቀዋል።
ወርቅነሽ ደምሰው
አዲስ ዘመን ግንቦት 8/2015