ኢትዮጵያ በአፍሪካ እግር ኳስ ታሪክ ቀዳሚ ተሳትፎ ያላት ሃገር ብትሆንም፤ ከነበረችበት ወደ ተሻለ ደረጃ ማደግ ግን አልቻለችም፡፡ የአፍሪካ ዋንጫ መሥራች ሃገር ሆና ሳለ በመድረኩ ያላት ተሳትፎ ከረጅም ዓመታት እረፍት በኋላ የሚገኝ ከሆነም ሰነባብቷል። እግር ኳስ ንግድ በሆነበት በዚህ ዘመን ከተጫዋች ሽያጭ እስከ ቴሌቪዥን ሽፋን በርካታ ቢሊዮን ዶላሮች የሚገላበጡበት ቢሆንም ኢትዮጵያ ግን በዚህ ረገድም እዚህ ግባ የሚባል ተሳትፎ የላትም፡፡
በመሆኑም ይህን ሁኔታ ለመለወጥና ስፖርቱን ካለበት ችግር እንዲወጣ፤ ከዚያም አልፎ ንግድ ለማድረግ ወጥና እየሠራች ነው፡፡ ለዚህም ማሳያ የሚሆነውም የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በእግር ኳስ ላይ ከሚሠራው የጀርመኑ ተቋም ስሪ ፖይንትስ (3 points) ጋር በመተባበር በታዳጊዎች ያተኮረ ስልጠና ነው፡፡ ስሪ ፖይንትስ ለኢትዮጵያውያን ታዳጊዎችን በእግር ኳስ ተገቢውን ስልጠና በመስጠት ለአውሮፓ ገበያ ለማቅረብ አልሞ እየሠራ የሚገኝ ድርጅት ነው፡፡
የታዳጊዎቹ ሥልጠና ያለበትን ሁኔታ ለመመልከት ባለፈው ሳምንት የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ለመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች የጉብኝትና ጋዜጣዊ መግለጫ መርሐ ግብር አዘጋጅቶ ነበር፡፡ ስሪ ፖይንትስ ከኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ጋር በገባው ውል መሠረት መቀመጫውን በካፍ ልሕቀት ማዕከል በማድረግ ዕድሜያቸው ከ13- 16 ዓመት የሆኑ ታዳጊዎችን በማሰልጠን ላይ ይገኛል፡፡ ታዳጊዎቹ የኢትየጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ከሚመራው የፓይለት ፕሮጀክት የተመለመሉ ሲሆኑ፤ 30 ታዳጊዎችም እየሰለጠኑ ይገኛሉ፡፡ ሥልጠናውም የምግብ፣ የመኝታ፣ የትምህርትና የመዝናኛ አገልግሎት ተሟልቶላቸው የሚሰጥ ነው፡፡
ሥልጠናውን ከጀመረ ስምንት ወራት የተቆጠሩ ሲሆን፤ የሥልጠና ቡድኑ ከጀርመን የመጡ ባለሙያዎችንም እንዳካተተ በጉብኝቱ ወቅት ተጠቅሷል። እአአ በ2024 መጨረሻ ወይም በ2025 ኢትዮጵያውያን ተጫዋቾችን ለአውሮፓ ገበያ ለማቅረብም ተቋሙ ወጥኗል፡፡ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በበኩሉ እግር ኳስ ተጫዋቾችን ለአውሮፓ ገበያ ከማቅረብ ባለፈ የወደፊት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ተጫዋቾችን የማፍራት ሥራ ላይ መሆኑን አመልክቷል፡፡ አካዳሚው ብቃት ያላቸው ተጫዋቾችን ወደ ጀርመን አካዳሚና ሊጎች ለመላክ እዚያ ካሉ አካላት ጋር ስምምነት ገብቶ በመሥራት ላይም ይገኛል፡፡
‹‹የወደፊቶቹን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ተጫዋቾችን እያዘጋጀን እንደሆነ ነው የምናስበው›› ያሉት የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ዋና ጸሐፊ አቶ ባሕሩ ጥላሁን፤ ታዳጊዎችን በእግር ኳስ ሥልጠና በማብቃት ወደ አውሮፓ ገበያ ማቅረብና እና ጠንካራ ብሔራዊ ቡድን እንዲኖር እየተሠራ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ የእግር ኳስ ፌዴሬሽኑ ሚና የካፍ ልህቀት ማዕከልን ለሥልጠና እንዲውል እና ከአገልግሎት ጋር በተያያዘ ምንም አይነት ችግር እንዳይገጥመው ማድረግ ነው፡፡ ስሪ ፖይንትስ ደግሞ በእግር ኳሱ ያለውን የመዋዕለ ንዋይ ወጪዎችን በመሸፈን ይሠራል፡፡ የተጫዋቾቹ የዝውውር ክፍያ የሚመራው በፊፋ የክፍያ ሥርዓት ሲሆን፤ ፌዴሬሽኑ 40 ከመቶ ሲያገኝ ስሪ ፖይንትስ ደግሞ 60 ከመቶ የሚሆነውን እንደሚያገኝም ዋና ጸሐፊው አብራርተዋል፡፡
የካፍ አካዳሚ ሜዳ ጥራት የተጓደለ በመሆኑ እንዲሁም በስፍራው የውሃ ችግር በመኖሩ፤ እግር ኳስ ፌዴሬሽኑ እስከ 6 ሚሊዮን ብር የሚያወጣ የከርሰ ምድር ውሃ ለማውጣት እየሠራ ነው፡፡ መሰል አካዳሚዎች በየክልሉ መከፈት ቢቻል እንዲሁም ኢንቨስት የሚያደርጉ አካላት እየጋበዙ የሚሠሩበት እድል ቢመቻች እግር ኳሱን ከፍ ማድረግ የሚቻልበት እድል ይኖራል ሲሉም አቶ ባሕሩ ገልጸዋል፡፡ የዕድል ጉዳይ ካልሆነ በስተቀር ኢትዮጵያውያን ታዳጊዎች ስልጠናውን በትክክል የሚያገኙ ከሆነ የተሻለ ደረጃ መድረስ እንደሚችሉ ከሥልጠናው መረዳታቸውንም ጸሐፊው አያይዘው ጠቅሰዋል፡፡
የስሪ ፖይንትስ አካዳሚ ዳይሬክተር አቶ ሳሙኤል በለጠ በበኩላቸው ‹‹ፌዴሬሽኑ ከኛ ጋር ለመሥራት ፍቃደኛ መሆኑ ትልቅ እድል ነው›› ይላሉ፡፡ የኢትዮጵያን እግር ኳስ ታሪክ መለወጥ የሚቻልበትን መንገድ ማሳየት የተቋሙ ራዕይ ሲሆን፤ ብዛት ቢኖራቸው ጥሩ ውጤት ይመጣል ሲሉ እምነታቸው ነው፡፡ አካዳሚውን ለመክፈት የተካሄደው መንገድ ቀላል ባይሆንም ታዳጊዎቹ ያለቸው ችሎታ በማውጣት በስፖርቱ መለወጥ ይቻላል፡፡
ታዳጊዎቹ በእድሜ እርከን በመጫወት ብሔራዊ ቡድን የሚወክሉ ይሆናል፡፡ የውድድር እድልን እንዲያገኙ የተለያዩ ውድድሮች ላይ እንዲሳተፉ ከማድረግም ባሻገር አካዳሚው በኢትዮጵያ ከ17 ዓመት በታች ፕሪሚየር ሊግ ተሳታፊ እንዲሆን ለማመቻቸትም ታቅዷል፡፡
ዓለማየሁ ግዛው
አዲስ ዘመን ሰኞ ግንቦት 7 ቀን 2015 ዓ.ም