ከአዳራሹ ውጪ ፊትለፊት በተንጣለለው መስክ ላይ የእርሻ ትራክተር፣ የደረሰ ሰብል ማጨጃና መውቂያ/ ኮምባይነር/ና ሌሎችም በርካታ ለግብርና ሥራ የሚውሉ ማሽኖችም ለእይታ ቀርበዋል፤ በአዳራሹ ውስጥም በርካታ የግብርና ቴክኖሎጂዎች ይታያሉ። ቴክኖሎጂዎቹን በመጠቀም እየመጣ ያለውን ለውጥ የሚያመለክቱ የተለያዩ ማሳያዎችም ቀርበዋል፡፡ ጎብኚዎች ይጎበኛሉ፤ አስጎብኚዎች ያብራራሉ፡፡
በስፍራው የሚታዩት ቴክኖሎጂዎችና የሚሰጡት ማብራሪያዎች ሞፈር፣ ቀንበርና በሬ በመጠቀም የእርሻ ሥራው ሲካሄድ እያየ ላደገና በግብርና ሥራ ውስጥ ለሚገኝ ትውልድ በግብርናው ዘርፍ አዲስ ታሪክ መጻፍ መጀመሩን እንዲገነዘብ ያደርጋሉ፡፡ ድካምን የሚቀንሱ፣ ጊዜንም የሚቆጥቡ የግብርና ቴክኖሎጂዎች በኢትዮጵያ ሥራ ላይ ሳይውሉ ዘመናት በመቆጠራቸው ገበሬው የግብርና ሥራውን ሲያከናውን የኖረው በብዙ ድካም ውስጥ በማለፍ ነው። ዛሬ አርሶ አደሩን ከኋላቀር የግብርና ሥራ ማውጣት የሚያስችሉ ተስፋ ሰጭ የግብርና ሜካናይዜሽን ሥራዎች ተጀምረዋል፡፡ ዛሬ ቀድሞ ቴክኖሎጂ ወይም የግብርና ሜካናይዜሽን የተተገበረባቸው የሀገሪቱ አካባቢዎችም በአርዓያነት እየተጠቀሱ ነው፡፡
በሳይንስ ሙዚየም ‹‹ከቤተ ሙከራ ወደ አዝመራ›› በሚል መሪ ሀሳብ እየተካሄደ ባለው የግብርና ቴክኖሎጂ ኤግዚቢሽን፣ በአዳራሹ መግቢያ በር ላይ ለእይታ የቀረቡት የግብርና ሜካናይዜሽን መሣሪያዎችም ኢትዮጵያ ግብርናን ለማዘመን እያደረገች ላለችው ጥረት ማሳያ ተደርገው የሚወሰዱ ናቸው፡፡ እኔም ከደጃፉ ለእይታ የቀረቡትን የተለያዩ የግብርና መሣሪያዎች በመመልከት ሁነቱ ከቀደመው የግብርና ሥራ ዘዴ አሁን ላይ በዘርፉ እየተስተዋለ ያለውን ለውጥ በዓይነ ሕሊና ለማነፃፀር ቀላል ነው፡፡
መድረኩ የግብርናው ዘርፍ የቴክኖሎጂ ማዕድ ልባል የሚችል ነው ለእይታ ምቹ በሆነው የሳይንስ ሙዚየም አዳራሽ ውስጥ ለእይታ የቀረቡት ሌሎች የግብርና ቴክኖሎጂዎችም፣ በሀገሪቱ በግብርናው ዘርፍ የተመዘገቡ ውጤቶችን የሚያስቃኙ የፈጠራና የግብርና ውጤቶች ሲሆኑ፣ ባለሙያዎችም ገለጻ በማድረግ ጎብኝውን በዘርፉ የተሻለ ግንዛቤ እንዲይዙ እያደረጉ ይገኛሉ፡፡ እንደ ሽንኩርት፣ ጎመን፣ ቃሪያ፣ ሰላጣ የመሳሰሉ በጓሮ የሚለሙ የአትክልት ዓይነቶችም በጓሮ መሬት ላይ ብቻ መወሰን እንደሌለባቸው በኤግዚቢሽኑ ላይ ከቀረበው ቴክኖሎጂ መረዳት ይቻላል፡፡
ውሃ በሚተላለፍባቸው ቱቦዎች ላይ በተዘጋጁ የአትክልት መትከያዎች አትክልት ማልማት የሚያስችል ዘዴ ነው በፈጠራ ባለሙያዎች የቀረበው፡፡ ውሃው ውስጥ ለውስጥ እየሄደ አትክልቱን የሚያጠጣ በመሆኑ ውሃ ለማጠጣት መድከምም አያስፈልግም፡፡ ሰዎች በዚህ ዘዴ ለእለት የሚጠቀሙበትን አትክልት በትንሽ ቦታ አልምተው መጠቀም ይችላሉ። በዚህ የቦታ ቁጠባ ዘዴ የቤት ግድግዳንም ለአትክልት ልማቱ መዋል እንደሚቻልም በኤግዚቢሽኑ ከቀረበው የግብርና ቴክኖሎጂ መረዳት ይቻላል፡፡
ሌላው የቀረበው በመሥኖ ግብርናን ለማከናወን የሚያስችለው ቴክኖሎጂ ነው፡፡ ተክሉ ወይንም ሰብሉ የሚያስፈልገው ውሃ በእኩል በሁሉም አቅጣጫ እንዲዳረስ በመቆጣጠሪያ ዘዴ እንዴት መጠቀም እንደሚያስችል የሚያሳይ ሲሆን፣ ይህም ዘዴ ጊዜን፣ ጉልበትንና ብክነት የሚያስቀር ነው፡፡ ቴክኖሎጂውን በቀላሉ መተግበርም ይቻላል፡፡ ቴክኖሎጂው በውሃ አለመመጣጠን ሳቢያ በሰብል ላይ ሊደርስ የሚችለውን ጉዳት ወይንም የሰብል መጥፋት ችግር በማስወገድ ረገድ ሳይንሳዊ የሆነ የመሥኖ አጠቃቀም ያለውን የጎላ ፋይዳ የሚያሳይ፣ ይህም ፍትሐዊ የውሃ አጠቃቀምን ለማስፈን እንደሚያግዝ ጭምር ነው፡፡ የግብርና ሥራው እየተስፋፋ በመጣበት በዚህ ወቅት በተለይ ለበጋ መሥኖ ልማት ሥራው እንደ አንድ ግብዓት ከሚነሳው ውስጥ ለልማቱ የሚውል የውሃ አቅርቦት በመሆኑ የመስኖ አጠቃቀሙ ሳይንሳዊ መሆኑ በዚህ ረገድ ያለውን ክፍተትም ለመቀነስ ያግዛል፡፡
በኤግዚቢሽኑ ያልቀረበ የግብርና ቴክኖሎጂ የለም ማለት ይቻላል፤ በእንስሳትና ዓሣ እርባታ፣ በንብ ማነብም በቴክኖሎጂ በመታገዝ ከኋላቀር ልማት መላቀቅ የሚቻልበት ዘዴም ለእይታ ቀርቧል፡፡ ኤግዚቢሽኑ የግብርና ውጤት የሆነውን ሰብል፣ አትክልትና ፍራፍሬ፣ የእንስሳት ውጤት፣ ማርና ሌሎችንም እሴት በመጨመር ከዘርፉ የሚገኘውን ገቢ እንዴት ከፍ ማድረግ እንደሚቻል ትምህርት የሚሰጥ ነው፡፡ ኢትዮጵያ በዲጂታል አብዮት እያደረገች ያለችው እንቅስቃሴ በግብርናው ዘርፍ የሚከናወኑ የተለያዩ ሥራዎችን በአንድ ስፍራ ላይ ለማሳየት የሚያስችል ዕድል መፈጠሩም ሌላው መጠቀስ ያለበት ጉዳይ ነው፡፡
80 በመቶ የሚሆነው የኢትዮጵያ ሕዝብ ኑሮው የተመሠረተው በግብርና ላይ እንደሆነ ይታወቃል። ከቀሪው ከተሜ አብዛኛው ስለግብርናው ዘርፍ የአመራረት ሂደት በቂ ግንዛቤ የሌለው፣ በተለይም በከተማ ተወልዶ ያደገው፣ በተለያዩ ምክንያቶች ወደ ገጠሪቱ ኢትዮጵያ ብቅ ያላለው ከተሜ ምንም ግንዛቤ እንደሌለው በአጭር ጊዜ የኤግዚቢሽኑ ቆይታ መረዳት እንደተቻለም በኤግዚቢሽኑ የተለያዩ ቴክኖሎጂዎችን ይዘው ከቀረቡት ተሳታፊዎች መረዳት ተችሏል፡፡ በተለይም የአንደኛና የሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች ጥያቄዎችን በማንሳት ስለግብርና ሥራ ለማወቅ የነበራቸውን ፍላጎት ከፍተኛ ሆኖ ታይቷል፡፡ አስጎብኚዎቹ ስለቴክኖሎጂው አተገባበር ሙያዊ ድጋፍ የሚፈልጉ ጎብኝዎችም እንዳጋጠሟቸው ገልፀዋል። በዚህ ረገድም ኤግዚቢሽኑ የተዋጣ ነው ለማለት ያስችላል፡፡
በኤግዚቢሽኑ መክፈቻ ላይ የኢፌዲሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ አሁን በግብርናው ዘርፍ እየታየ ያለው ለውጥ ተስፋ ሰጭ እንደሆነ ገልጸዋል። ‹‹ባለን ሀብት ላይ እሴት በመጨመር ሀገር እንድትጠቀም በየጊዜው ሥራችንን ማጎልበትና ማዘመን አለብን›› ሲሉም ተናግረዋል። ኤግዚቢሽኑ ለኢትዮጵያ የልማት ስኬት ጥሩ ልምድ የሚወሰድበት፣ የግብርና ሜካናይዜሽን ማስፋፋት፣ የግብርና ምርቶችን በብዛትና በጥራት በማምረት የሀገር ልማትንና እድገትን ማፋጠን እንደሚገባም ነው ያስገነዘቡት።
የግብርናውን ዘርፍ ከፍ ወዳለ ደረጃ ለማሸጋገር ከተለመደው አሠራር መውጣት፣ የምርት ስብጥሩን ማስፋትና ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችን በስፋት መጠቀም፣ በተለይም የአፈር አሲዳማነትን መከላከል ላይ ትኩረት ሰጥቶ በመሥራት የምርት መጠንን ማሳደግ ይገባልም ብለዋል፡፡ ባለፉት ጥቂት ዓመታት በስንዴ ልማቱ የተመዘገበውን ስኬት በሌሎች ምርቶች ላይም በተመሳሳይ ለማሳካት በትብብር መሥራት ይገባል ሲሉም ተናግረዋል፡፡
የግብርና ሥራው ዘምኖ ምርትና ምርታማነት እንዲያድግ በመንግሥት በኩል ቁርጠኛ አቋም ተይዞ ሥራ እየተሠራ ነው፡፡ ሥራው ግን በአርሶ አደሩ ኑሮ መሻሻል ላይም ለውጥ ማምጣት ይኖርበታል፡፡ ዛሬ አርሶ አደሩ ልጆቹን ወደ ትምህርት ቤት መላክ በመጀመሩ በልጆቹ ይጠቀም የነበረው ጉልበት እየቀነሰበት መምጣቱን በተለያዩ መድረኮች ላይ እየተጠቆመ ነው፡፡ የልጆቹን ጉልበት የሚተካ የሰው ኃይል ቀጥሮ ለማሠራትም አርሶ አደሩ የገንዘብ አቅም የለውም፡፡ ግብርናው ባለመዘመኑም ወደዘርፉ ለመግባት ፍላጎት ያለው የሰው ኃይል እያገኘ አይደለም፡፡
የግብርና ሚኒስትሩ ዶክተር ግርማ አመንቴ በኢትዮጵያ እንዲህ ያለ ኤግዚቢሽን ሲዘጋጅ ይህ የመጀመሪያ እንደሆነ ይገልፃሉ፡፡ እርሳቸው እንደሚሉት፣ በኢትዮጵያ የግብርና ሥራ የሚታወቀው በኋላቀር የአስተራረስ ዘይቤው ነው። ኤግዚቢሽኑ መንግሥት ግብርናውን በማዘመን ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ ባለፉት ዓመታት ያከናወናቸውን ተግባራት ሕዝቡ እንዲያውቀው ታልሞ የተዘጋጀ ነው።
‹‹በኢትዮጵያ ሳይደረስበት የቆየውን ግን ደግሞ ዓለም የሚጠቀምበትን ቴክኖሎጂ ሕዝቡ እንዲያይና እንዲገነዘብም ጭምር ነው ኤግዚቢሽኑ የተዘጋጀው። ማኅበረሰቡ በግብርናው ዘርፍ ስላለው ሁኔታ አርቆ እንዲመለከትና አስፍቶ እንዲያይ ይጠቅማል፡፡ በተለይ ደግሞ ወጣቱ ትውልድ ሀገሪቱ ስትጠቅምበት የቆየችው ኋላ ቀር የግብርና ዘዴ እንዲቀጥል የሚጠበቅ ባለመሆኑ፣ ወደፊት ግብርናው እንዴት መከናወን እንዳለበት ከአሁኑ እንዲያውቀውና ፍላጎት እንዲያድርበት ለማስቻልም የኤግዚቢሽኑ ፋይዳ ከፍተኛ ነው›› ይላሉ፡፡
በኤግዚቢሽኑ መክፈቻ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ኤግዚቢሽኑን ሁሉም ማኅበረሰብ እንዲጎበኘው ጥሪ ማድረጋቸውን ያስታወሱት ዶክተር ግርማ፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ኤግዚቢሽን በተከፈተ ማግሥት የተለያዩ እንግዶችን ይዘው ሲያስጎበኙ እንደነበርም ገልጸዋል፡፡ የውጭ ሀገር ዲፕሎማቶችም እንዲጎበኙ ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ጋር ምቹ ሁኔታ መፈጠሩን አመልክተዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባደረጉት ጥሪ መሠረትም ኢግዚቢሽኑ በተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች በብዛት እየተጎበኘ ነው። ተማሪዎች ተሰባስበው የጎበኙበት ሁኔታ የተለየ ስሜት እንዳሳደረባቸውም ነው የግብርና ሚኒስትሩ የተናገሩት። የተለያዩ ተቋማት ሠራተኞችም በተመሳሳይ እየጎበኙ መሆናቸውንና ካለፈው ዓርብ ጀምሮ ክልሎች እንዲጎበኙ መርሐግብር መውጣቱንና በዚሁ መሠረትም አርሶ አደሮች እና የልማት ሠራተኞች እንደሚጎበኙ ገልጸዋል። ይህ ደግሞ የግብርናውን ዘርፍ ብቻ ሳይሆን፣ በአጠቃላይ ማኅበረሰቡ ስለግብርና ያለውን ግንዛቤ ከማሳደግ አንጻር ከፍተኛ ድርሻ ይኖረዋል ሲሉ አብራርተዋል፡፡
ግብርናውን በማዘመን ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ መንግሥት በዘርፉ የተለያዩ ተግባራትን አከናውኗል፤ እያከናወነም ይገኛል፡፡ ነገር ግን የአርሶአደሩ ኑሮ አሁንም ከእጅ ወደ አፍ ነው፡፡ አርሶአደሩ በደከመው እየተጠቀመ ያለው በመካከል ላይ ያለው ደላላ እንደሆነ በተደጋጋሚ የሚነሳ ጉዳይ ነው፡፡ በሌላ በኩል የልጁን ጉልበት የሚጠቀመው አርሶ አደር አሁን ላይ እንደቀድሞው አይደለም፡፡
ዶክተር ግርማ እነዚህ ችግሮች መንግሥት ከያዘው ግብርናን ከማዘመንና ምርትና ምርታማነትን ከመጨመር ጋር እንዴት እንደሚታዩ ሲያስረዱ ‹‹በሰለጠነው ዓለም አርሶ አደሩ ሸጦ ነው የሚያመርተው፡፡ የኢትዮጵያ ግብርና ደግሞ ከእጅ ወደ አፍ ነው፡፡ የቀደሙት አባቶች የሚያመርቱት ለገበያ ሳይሆን ለቤት ፍጆታና ለልጆቻቸው የሚያስፈልጋቸውን ለማሟላት ነው፡፡ ይሄ ከእጅ ወደአፍ ግብርና ይባላል፡፡ አሁን በግብርናው ዘርፍ እየተሠራ ያለው ግብርናውን ከተለምዷዊ
አሠራር ለመውጣትና ወደ ኮሜርሻል ግብርና ለማሸጋገር ነው፡፡ በኮሜርሻል ግብርና የእርሻ ሥራው ከመከናወኑ በፊት ነው ምርቱ ለሽያጭ ወይንም ለገበያ የሚቀርበው፡፡ አርሶ አደሩ በቅድሚያ ገበያውን አውቆ ነው የሚያመርተው፤ ገዥውን አውቆ ማምረት ማለት ነው፡፡ ይህ ደግሞ በሕግ ወይንም በውል መታሰር አለበት፡፡ ቅድሚያ ውል ከሌለ ከተመረተ በኋላ ድርድር ማድረግ ኪሳራን ያስከትላል፡፡
ባለፉት ዓመታት ግብርናው ‹‹አሥመራችና አምራችን›› የሚያገናኝ የግብርና ምርት ውል (ኮንትራክችዋል ፋርሚንግ) የሚል አዋጅ ሲዘጋጅ ቆይቷል፡፡ ይህም የግብርና ውል አዋጅ ሰሞኑን በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ፀድቋል፡፡ በዚህ ውል መሠረት አርሶ አደሩ የቅባት እህል እንዲመረትለት ከሚጠይቀው ፋብሪካ ጋር በውል መሥራት ያስችላል፡፡ አሠራሩ በሰለጠነው ዓለም የተለመደ ነው፡፡
እንዲህ ያለው ዘዴ በመካከል ያለውን ደላላ በማስቀረት አርሶአደሩ ተጠቃሚ እንዲሆን ያደርጋል። ቀደም ሲል የነበሩ ክፍተቶችን ለመቀየር አንዱ ዘዴ ነው። በሚቀጥለው ዓመት ለመተግበር ዝግጅት ተደርጓል፡፡ የኢትዮጵያ የግብይት ሥርዓት ገና ያልዘመነ በመሆኑ ትግበራው ጊዜ ሊወስድ ይችላል፡፡ ግን በሂደት ውጤት እንደሚያስገኝ ተስፋ ተጥሏል፡፡ ሌላው በዘርፉ የታሰበው፤የኅብረት ሥራ ማኅበራት ለግብርና ሚኒስቴር ተጠሪ በመሆናቸው እነርሱን በማጠናከር አርሶአደሩ በቀጥታ ለማኅበራቱ እንዲያቀርቡ በማድረግ ለገበያ የሚያቀርቡበትን ሁኔታ አጠናክሮ መቀጠል ይጠበቃል፡፡ እንደተባለው አርሶአደሩ አምርቶ ከምርቱ ተጠቃሚ መሆን ካልቻለ መልሶ የሚያመርትበትን ማበረታቻ ያጣል፡፡
ለገበያ ማምረትና ሳያርስ በፊት መሸጥ፣ በማኅበራቱ በኩል ገበያ የማስተሳሰር ሥራ ይጠበቃል። ክፍተቶቹ በሚቀጥሉት ዓመታት በሚከናወኑ ተግባራት ይሞላሉ በሚል ተስፋ እየተሠራ መሆኑን ነው ዶክተር ግርማ ያብራሩት፡፡ ከግብርናው ላይ እየቀነሰ ስላለው የሰው ኃይል በተመለከተም ዶክተር ግርማ ችግሩ ግብርና ሲዘምን የሚፈታ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ እንደ እሳቸው ገለጻ፤ ግብርናው በሜካናይዜሽን ሲከናወን ወጣቶች እየተሳቡ ዘርፉን ይቀላቀላሉ፡፡ እንደቀደሙት አባቶች በሬ ጠምደው እንዲያርሱም አይጠበቅም፡፡
ግብርና የያዘው የሰው ኃይል ወደ ኢንዱስትሪ መሸጋገር አለበት፡፡ በግብርና ፖሊሲው ላይም የተቀመጠው ይኸው አቅጣጫ ነው፡፡ ‹‹ኢትዮጵያ ትበለጽጋለች የሚባለው ከ50 በመቶ በላይ ሕዝቧ ወደ ከተማ ሲገባ ነው›› ሲሉም ገልጸዋል፡፡ ይህ ሲባል ግብርና ይቀራል ማለት እንዳልሆነና ግብርና በዘመነ መልኩ በጥቂት የሰው ኃይል ይሠራል ማለት እንደሆነም አስረድተዋል፡፡ በአንዳንድ የኢትዮጵያ ክፍሎች በተለይም መቂ ላይ በሜካናይዜሽን በተጀመረው ሥራ ወጣቶች በስፋት መሳተፋቸውን ለአብነት ጠቅሰዋል፡፡
ለምለም መንግሥቱ
አዲስ ዘመን ሰኞ ግንቦት 7 ቀን 2015 ዓ.ም