ተኪ ምርቶች የሀገር ኢኮኖሚ የጀርባ አጥንት

የሀገሪቱ የወጪና የገቢ ንግድ ሚዛን ከፍተኛ ልዩነት ያለበት በመሆኑ ይህን ክፍተት ለማጥበብ የውጭ ምንዛሪ ለሚያስገኙና የውጭ ምንዛሪ ወጪን ለሚያስቀሩ ወይም ለሚቀንሱ ተኪ ምርቶች ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራ ነው። የግብርና ምርቶችና የኢንዱስትሪ ግብዓቶች ዋነኛ ትኩረት ከተቸራቸው መካከል ናቸው። ይህ ሥራ ለኢትዮጵያ የኢኮኖሚ እድገት ምን አስተዋጽኦ ይኖረዋል? በዘርፉ የሚሠሩ አካላት የሚሉት አላቸው።

አቶ መሳይነህ ውብሸት በኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የተኪ ምርቶች ተወዳዳሪነት መሪ ሥራ አስፈጻሚ ናቸው። በጉዳዩ ዙሪያ እንደሚሉት፤ እንደ ኢትዮጵያ ተኪ ምርቶች ፋይዳቸው ዘርፈ ብዙ ነው። ለአብነት በተኪ ምርት አማካኝነት በዓለም አቀፍ ገበያ ላይ ተወዳዳሪ ሆኖ መውጣት ይቻላል። ምርቶቻችንን ለመሸጥ ትልቅ እድል ይሰጠናል። የውጭ ምንዛሪ እጥረትን ለመቅረፍ፣ ሰፊ የሥራ እድል ለመፍጠርና ዜጎች ምርቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ እንዲያገኙ ለማስቻልም ይጠቅማል።

የአምራች ዘርፉን በመደገፍ ሚዛናዊና ቀጣይነት ያለው የኢኮኖሚ ዕድገት ለማስመዝገብ ያስችላል። የኢንዱስትሪ ተወዳዳሪነትን ለማጎልበት እና የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ ለማሻሻል ሁነኛ መፍትሔ ይሰጣል። በአጠቃላይ በሀገሪቱ ዘላቂ የኢኮኖሚ እድገት ለማስመዝገብ ጉልህ አስተዋጽኦ ይኖረዋል።

ከጎላው ጥቅሙ አንጻርም እንደ ሀገር ልዩ ትኩረት ተሰጥቶት እየተሠራበት ስለመሆኑ ያነሱት ሥራ አስፈጻሚው፤ አዲሱ የኢንዱስትሪ ፖሊሲ ከእዚህ በፊት ለወጪ ምርቶች ብቻ ይደረግ የነበረውን የትኩረት አቅጣጫ በመቀየር ተኪ ምርቶችንም የሚያበረታታ ሆኖ መዘጋጀቱ እንዲሁም በሀገሪቱ የተኪ ምርቶችን የማምረት አቅም ለማሳደግ የተኪ ምርት ስትራቴጂ ተግባራዊ መደረጉ አንዱ ማሳያ እንደሆነም ተናግረዋል።

በብሔራዊ ስትራቴጂው ውስጥ ሙሉ ለሙሉ በሀገር ውስጥ በሂደት መመረት ይችላሉ ተብለው የተለዩ ምግብና መጠጥ፣ ጨርቃ ጨርቅና አልባሳት፣ ቆዳና የቆዳ ውጤቶች፣ የኬሚካልና ኮንስትራክሽን ግብዓቶችና የብረትና ምሕንድስና ምርቶች እንደሆኑ የጠቆሙት አቶ መሳይነህ፤ በ2017 በጀት ዓመት ከአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፉ የሀገር ውስጥ ምርት በመተካት በመጀመሪያ ስድስት ወራት 1 ነጥብ 9 ቢሊዮን ዶላር የውጭ ምንዛሪ ማዳን የተቻለ ሲሆን፤ ከአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍ ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በሀገር ውስጥ በመተካት 2 ነጥብ 07 ቢሊዮን ዶላር ማዳን እንደተቻለና ከእዚህ ውስጥ እንደ ዘርፍ ትልቁን ድርሻ 843 ሚሊዮን ዶላር የያዙት ከምግብና መጠጥ ጋር የተያያዙት ምርቶች መሆናቸውን አመላክተዋል።

በዘጠኝ ወራቱ ደግሞ ከ3 ነጥብ 1 ቢሊዮን ዶላር በላይ ማዳን እንደተቻለና ለእዚህም ሀገራዊና ዓለም አቀፋዊ ሁኔታዎችን ያገናዘበ የኢንዱስትሪ ፖሊሲ ወደ ሥራ መግባት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደነበረው አብራርተው፤ አሁን ላይ 96 ስትራቴጂክ ተኪ ምርቶች ተለይተው በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ እንዲመሩ እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል። ይህ መሆኑም ከፍተኛ የምርት ዕድገት እንዲመጣ አስችሏልም ብለዋል።

የኢትዮጵያ ኢንተርፕራይዝ ልማት ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ አብዱልፈታ የሱፍ በበኩላቸው እንዳሉት፤ ተኪ ምርት ኢትዮጵያ ሁሉንም ነገር አምርታ በራሷ በመሸፈን የምግብ ዋስትናዋን እንድታረጋግጥም የሚያግዛት ነው። በተለይም ከፍተኛ የውጪ ምንዛሪን የሚጠይቁ እንደ ስንዴና ገብስ፣ መድኃኒት፣ የዘይት ምርቶችና የመሳሰሉ ስትራቴጂክ ምርቶች በተኪ ምርቶች መልስ የሚያገኙ ከሆነ መዋዕለ ንዋይን ሌሎች ላይ አድርጋ ኢኮኖሚዋን እንድታሳድግ እድል ይሰጣታል። በአጠቃላይ ተኪ ምርት ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በሀገር ውስጥ በማምረት ለአጭር ጊዜ ከሚቆዩ የፍጆታ እቃዎች ተነስቶ ደረጃ በደረጃ ወደ ወጪና ገቢ ንግድ ብዝሃነት ሀገር እንድትሸጋገር ያደርጋታል።

የተኪ ምርቱ ውጤታማ እንዲሆን ከሚያስችሉ አምራቾች መካከል አምራች ኢንተርፕራይዞች ከፍተኛውን ድርሻ እንደሚይዙ የገለጹት ዋና ዳይሬክተሩ፤ አምራቾቹ በዘጠኝ ወር ውስጥ ከውጭ የሚገባ ምርትን በሀገር ውስጥ በመተካት ከ1 ነጥብ 6 ቢሊዮን ዶላር በላይ የውጭ ምንዛሪ ማዳን እንዲቻል ማድረጋቸውን ተናግረዋል። እክለውም፤ አምራች ኢንተርፕራይዞቹ ለውጭ ገበያ ባቀረቡት ምርት 57 ሚሊዮን ዶላር የውጭ ምንዛሪ ማግኘት እንዲቻል ማድረጋቸውን አስረድተዋል።

መንግሥት በአሥር ዓመት መሪ የልማት ዕቅዱ ከለያቸው አምስት የኢኮኖሚ የትኩረት መስኮች መካከል የአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍ አንዱ ነው። በአሥር ዓመት የልማት ዕቅዱም የጸጥታ አካላትን የደንብ ልብስ ጨምሮ ከውጭ የሚገቡ የተለያዩ ምርቶችን በሀገር ውስጥ ምርት በመተካት በቢሊዮን የመቆጠሩ ዶላሮችን ማዳን ተችሏል። በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ብቻ በ2016 ዓ.ም ከ370 በላይ ኢንዱስትሪዎችን ወደ ሥራ በማስገባት የአምራች ኢንተርፕራይዞችን ምርትና ምርታማነት እንዲያድግ ተደርጓል። የኢንተርፕራይዞችን ቁጥር ከ26 ሺህ በላይ በማድረስ ከ570 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የሥራ ዕድል መፍጠር ተችሏል። ይህ ደግሞ በተኪ ምርቶች አማካኝነት ባለፉት ሦስት ዓመታት የ2017ን ጨምሮ ከውጭ ይገባ የነበረ 10 ነጥብ 34 ቢሊየን ዶላር የሚገመት ምርት ማስቀረት ተችሏል። ከእዚያም ባሻገር የአምራች አንዱስትረውን ዘርፍ አማካይ የማምረት አቅም ከነበረበት 46 በመቶ ወደ 61 ነጥብ 2 በመቶ ከፍ እንዲል አድርጎታል ሲሉም የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዴኤታ ተስፋሁን ጎበዛይ አስታውቀዋል።

በ2013 በጀት ዓመት በነበረው የተኪ ምርቶች ሥራ 345 ሚሊዮን ዶላር ማዳን የተቻለ ሲሆን፤ ይህ ምጣኔ በ2014 በጀት ዓመት ወደ 2 ነጥብ 98 ቢሊዮን ዶላር አድጓል። በ2017 በጀት ዓመት ዘጠን ወራት በሀገር ውስጥ ተኪ ምርቶችን በስፋት በማምረት 3 ነጥብ 1 ቢሊዮን ዶላር ማዳን እንደቻለ ተገልጿል። ስለዚህ ተኪ ምርትን በተመለከተ ሥራው ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ እድገት እያሳየ መምጣቱን የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል።

ሁለቱም ሰዎች እንደገለጹት፤ የሀገራት ኢኮኖሚያዊ እድገት የሚወሰነው በምርት እድገታቸው ልክ ነው። መንግሥትም ይህንን በመረዳት ምርትና ምርታማነትን ለመጨመር አንዱ የትኩረት አቅጣጫ አድርጎ የተኪ ምርቶች ላይ እየሠራ ይገኛል። ይህ ደግሞ በቀጣይ እንደ ሀገር በርካታ ለውጦችን ያመጣል። ለምሳሌ የሀገሪቱን ምርት በማሳደግና ገቢው እንዲጨምር በማድረግ አዳዲስ የሥራ እድል እንዲፈጠር፣ የዜጎችን ፍላጎት የሚያሟሉ ሸቀጦችና አገልግሎቶችን ማቅረብ እንዲቻል፣ የዜጎች ኑሮ እንዲሻሻል፣ ድህነት እየቀነሰ እንዲመጣ ያደርጋል።

እክለውም የተፈጥሮ ፀጋን ወደ ሀብት ለመቀየርም ያስችላል። የሰለጠነ የሰው ኃይል፣ ገበያና ፈጠራ እንዲሁም ሀገራዊ ፍላጎትና ዓለም አቀፋዊ ሁኔታን አመዛዝኖ መሥራት እንዲቻልም ያደርጋል። በየዓመቱ በቢሊዮን ዶላር በማውጣት ከውጭ የምታስገባቸውን ምርቶች በሀገር ውስጥ መተካት እንድትችልና በቀጣይም የንግድ ጉድለቱን እንድታመጣጥን በማድረግ በኩል የማይተካ ሚናን ይጫወታል ብለዋል።

ጽጌረዳ ጫንያለው

አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሰኔ 7 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You