
አዲስ አበባ፦ በ2017 በጀት ዓመት አስር ወራት ውስጥ ከውጭ የሚገባ የደን ምርት ውጤቶችን በሀገር ውስጥ ምርት በመተካት 32 ነጥብ 86 ሚሊዮን ዶላር የውጭ ምንዛሪ ወጪ ማዳን መቻሉን የኢትዮጵያ ደን ልማት አስታወቀ።
በኢትዮጵያ ደን ልማት መሥሪያ ቤት የደን ውጤቶች አጠቃቀም ዴስክ ኃላፊ አቶ ፀጋ መንገሻ በተለይ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለጹት፤በ2017 በጀት ዓመት አስር ወራት ውስጥ እንደ ሀገር ከውጭ የሚገባ የደን ውጤትን በሀገር ውስጥ ለመተካት በተሠራው ሥራ ከውጭ የሚገባ 3 ነጥብ 75 ሚሊዮን ቶን የደን ውጤቶችን በሀገር ውስጥ ምርት በመተካት 32 ነጥብ 86 ሚሊዮን ዶላር የውጭ ምንዛሪ ወጪ ማዳን ተችሏል።
ሀገሪቱ ከውጭ ለምታስገባቸው የደን ውጤቶች በዓመት ከ110 ሚሊዮን ዶላር በላይ ወጪ እንደምታደርግ መረጃዎች ያሳያሉ የሚሉት ዴስክ ኃላፊው፤ ሀገሪቱ ያላትን የደን ሀብት እሴት ጨምሮ በማምረት ከውጭ የሚገባውን ምርት በሀገር ውስጥ መተካት እና የውጭ ምንዛሪ አቅምን ማዳበር የሚያስችል ተፈጥሮ ሀብትና ለደን ልማቱ ምቹ ሁኔታዎች እንዳሏት ተናግረዋል።
ዴስክ ኃላፊው አቶ ፀጋ፤ ሀገሪቱ ለደን ልማት ምቹ ሁኔታዎችና ተፈጥሮ ሀብት ቢኖሯትም በኋላቀር የደን ሀብት ጥበቃ፣ ልማትና አጠቃቀም የተነሳ ከንዑስ ዘርፉ የሚጠበቀውን ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊ፣ ሥርዓተ-ምህዳራዊ እና ተፈጥሯዊ ጥቅም ሳታገኝ መቆየቷን አመልክተዋል።
ሀገሪቱ ምቹ ሁኔታና የተፈጥሮ ሀብት እያላት የደን ውጤቶችን ከውጭ ማስገባቷ እንደ ሀገር የሚያስቆጭ ነው ያሉት ዴስክ ኃላፊው፤ የደን ሀብትን በዘላቂነት በማልማትና በመጠበቅ ለሀገሪቱ ኢኮኖሚያዊ እድገት የላቀ አስተዋጽኦ ለማበርከት፣ እንዲሁም ኅብረተሰቡን ያሳተፈ ዘላቂ የደን ልማትና እድገት ለማምጣት የደን ልማት፣ ጥበቃና አጠቃቀም አዋጅ ቁጥር 1065/2010 መውጣቱን ጠቁመዋል።
የእዚህ አዋጅ ማስፈጸሚያ ደንብ ማለትም የደን ልማት፣ ጥበቃና አጠቃቀም ቁጥጥር ደንብ ቁጥር 544/2016 ተረቅቆ በሕዝብ እንደራሴ ምክር ቤት ፀድቆ ወደ ሥራ መግባቱንም አመላክተው፤ አዋጅና ደንቡ ውስን የሆነውን የደን ሀብት በዘላቂነት ለመጠቀም መሠረት ከመሆኑ ባሻገር የግሉ ሴክተሩ በደን ልማትና ጥበቃ ዘርፉ እንዲሰማራ ምቹ ሁኔታ እንደፈጠረ ገልጸዋል።
ይህንን ተከትሎ የደን ውጤቶች ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪዎች በሀገር ውስጥ ተስፋፍተዋል የሚሉት ዴስክ ኃላፊው አቶ ፀጋ፤ የደን ውጤቶችን በማምረት ዘርፍ የተሰማሩ አምራች ኢንዱስትሪዎች እሴት የተጨመረባቸው ጥራት ያላቸው ምርቶችን አምርተውና የተወዳዳሪነት አቅማቸው ጎልብቶ በሀገር ውስጥም ሆነ በውጭ ባሉ የገበያ ዕድሎች ተጠቃሚ እንዲሆኑ ለማስቻል ከዘርፉ ባለድርሻ አካላትና ድጋፍ ሰጪ ተቋማት ጋር በቅንጅት እየተሠራ እንደሚገኝ አመላክተዋል።
በእዚህም በተያዘው በጀት ዓመት አስር ወራት ውስጥ ቀደም ሲል ከውጭ ሀገር ይገቡ የነበሩ 3 ነጥብ 75 ሚሊዮን ቶን የደን ውጤቶችን (ኮምፖርሳቶ፣ ኤም ዲ ኤፍ፣ ሀርድ ቦረድ፣ ፓርቲክል ቦርድ እና የተለያዩ የፈርኒቸር ምርቶችን) በሀገር ውስጥ ምርት በመተካት 32 ነጥብ 86 ሚሊዮን ዶላር የውጭ ምንዛሪ ወጪ ማዳን መቻሉን ዴስክ ኃላፊው ተናግረዋል።
በተመሳሳይ በ2017 ዓ.ም ዘጠኝ ወራት ደግሞ 7 ሺህ 842 ቶን የተለያዩ የደን ውጤቶች (ከባሕርዛፍ የተዘጋጁ የግንባታ እንጨቶች፣ ጣውላና ሞራሌ፣ ኮምፖርሳቶ፣ ኤምድኤፍ እና የተለያዩ የፈርኒቸር ምርቶች) ለወጭ ገበያ መቅረቡን ጠቁመው፤ ለውጭ ገበያ ከቀረበው ምርት በድምሩ 1 ነጥብ 42 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ገቢ ተገኝቷል ብለዋል።
ሶሎሞን በየነ
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሰኔ 7 ቀን 2017 ዓ.ም